የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ የቀድሞ የወላይታ ዞን አመራሮች የነበሩ ግለሰቦችን ጨምሮ 20 ተጠርጣሪዎች በወላይታ ሶዶ ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጠ። ፍርድ ቤቱ፤ ለተጠርጣሪዎች ተፈቅዶ በነበረው ዋስትና ላይ ፖሊስ የመልስ መልስ ይዞ እንዲቀርብ ለመጪው ሳምንት ማክሰኞ መስከረም 19 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ተመስገን ዋጃና ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ የተጠርጣሪዎችን አቆያየት በተመለከተ በትላንትናው ዕለት ከሰዓት ብይን ለመስጠት ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም በጠዋት ችሎት ቀርበው የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች አልተገኙም በሚል ብይኑን ለዛሬ ማሳደሩን ጠበቃው ገልጸዋል። እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ሲጠብቁ የቆዩ ሰባት ተጠርጣሪዎችም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በሐዋሳ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ መደረጋቸውንም አክለዋል።
ዛሬ ረፋዱን በነበረው ችሎት በህመም ምክንያት ትላንት ከሰዓት ያልተገኙት ሁለት ግለሰቦችን ጨምሮ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር ተብሏል። ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ተከትሎም ከዛሬ ችሎት መጠናቀቅ በኋላ ዘጠኙም ተጠርጣሪዎች በፖሊስ መኪና መወሰዳቸውን የስድስት ተጠርጣሪዎች ጠበቃ የሆኑት አቶ ተመስገን ለ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
በፖሊስ ከተወሰዱት ተጠርጣሪዎች መካከል የወላይታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉነህ ወልደጻዲቅ፣ የዞኑ የፍትህ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ምህረት ቡኬ እና የወላይታ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን አቶ ተከተል ላቤና ይገኙበታል።
“ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል በመናድ” ወንጀል በተጠረጠሩት 20 ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ባለፈው ነሐሴ ወር አጋማሽ ከስልጣናቸው የተነሱት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ እና የዞኑ ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ዮሃንስም ተካትተዋል። ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ጠይቆባቸው ነበር።
በወላይታ ግጭት በተቀሰቀሰበት ወቅት የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን እና የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ለደቡብ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ የወላይታ ዞን አመራሮች የተለያዩ ህገወጥ አደረጃጀቶችን ፈጥረው ግጭት የመቀስቀስ ፍላጎታቸውን እንዲያስፈጽሙ እያደረጉ ነበር ማለታቸው ይታወሳል።
አመራሮቹ በፓርቲ ደረጃ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ሀገር ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር ተቀናጅተው በመሥራት ላይ ይገኛሉ ያሉት አቶ አለማየሁ ሀገር ለማፍረስ የሚሰሩ በማለት ከገለጿቸው ህወኃትና ኦነግ ሸኔ አካላት ጋር በድብቅ ሰው እየላኩ ስብሰባ እንደሚያደርጉ እና ተልዕኮ እንደሚቀበሉ ተናግረዋል። ለዚህም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት መረጃዎች ተገኝተዋል ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
GI Haile says
ስልጣን መከታ አድርገው ሕገወጥ ስራ የሚሰሩ ባለስልጣናት በሕግ ከፍቸኛ ስፍራ የያዙ ኣይሎች ናቸው። እነዚህ ግሐሰቦች የአገሪቱን ሕግ በፍትህ ከፍተኛ ዕርከን ላይ ተቀምጠው ሕገወጥና ፀረ ሔገመንግስታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከሽብርና ከሕገመንግስቱ ኣላማና መሠሪያ ውጭ ነው። በተለይም ከኣሸባሪ ፀረ ሕዝብና ፀረ አገር ድርጅትች ጋር መስራቴ ሔገኸጥነትና በሴልጣን መባለግ ነው። መሠጃው ትከከለኛ ከሆነ ከፍተኛ ወኔጀል በመህኑ ከኣምሴት እሴከ ዔድሜ ልኬ የሚያሳሴር ነው።