ኢ.ቢ.ሲ. በሰበር ያስተናግደውን የኃይለማርያም ደሳለኝ መግለጫ፤ ዞምቢዎቹ ተሯሩጠው ለማጽደቅ ግዜ አልወሰደባቸውም። እሳቸውም ልክ ስልጣን እንደነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር “ስልጣን አስረክቢያለሁ” ሲሉ እፍረት የሚባል ነገር ፊታቸው ላይ አይታይባቸውም ነበር። ሹመት እንጂ ሕገ-መንግስቱ የሚፈቅደው ስልጣን እጃቸው ላይ እንዳልነበር ሕጻናትም ያውቁታል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መልቀቅያቸውን በብርሃን ፍጥነት ሲያጸድቀው፤ ድርጊትዋን ከደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ ክስተት ጋር ለማመሳሰል የተተወነች ድራማም አስመስሏታል። ስልጣን ሳይኖር “ሰላማዊ ሽግግር” የሚሏት ፌዝ …
ኃይለማርያም ደሳለኝ ተሸክመውት የነበረው ሹመት ይሁን ስልጣን ሲለቅቁ፤ “ከደሙ ነጻ ነኝ” ብለው ለተሰራው ወንጀል ሁሉ እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ሊታጠቡ እንደማይችሉ ግን እርግጥ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን የእሳቸው መውረድ በሃገሪቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ከቅርብም ይሁን ከሩቅ አይታይም። እንደማንኛውም የድል አጥቢያ ካድሬ፤ ቆሻሻውን እና የሸክሙን ስራ ሲሰሩ የሰነበቱ ሰው ነበሩ።
ሰውየው ለጥፋቱ ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርገው ሃላፊነት ቦታ ላይ ይቀመጡ እንጂ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ እሳቸው መሳለቅያ የሆነ መሪ አልነበረም። ተጠያቂነቱ እንዳለ ሆኖ ግና የራሳቸው ራዕይ እና አንዲት ቀን እንኳ የራሳቸው አቋም ያልነበራቸው አሻንጉሊት ነበሩ። “የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይለቀቃሉ!” ብለው በገዛ ገጻቸው የጻፏት መግለጫ እንኳን በዞምቢዎቹ ስምንት ግዜ ተሰርዛ – ስምንት ግዜ ተደልዛለች። ኃይለማርያም በዚህ ደረጃ ለመዋረድ ራሳቸውን ስላዘጋጁ፤ ይህ ድርጊት ለሳቸው አዲስ ነገር አይደለም። “መረጃ አይሰጡኝም። ስራዬን የማከናውነው ያለመረጃ ነው” እያሉ አንዳንዴ ጣል የሚያደርጓቸው እውነታዎች “ጉድ ነው” ቢያስብሉም፤ አጃኢብ የሚያሰኙ ንግግሮችንም በአደባባይ ይለቅቃሉ። ኢትዮጵያ፤ አንድ በመንገደኛ ፌደራል ፖሊስን በጥፊ የሚመታበት ሃገር እንደሆነች በቴሌቭዥን ቀርበው የሚናገሩ ሰው ናቸው። ለንግድ የሚነሳ ማንም ሰው ሰፌድ ብቻ ይዞ ትግራይ እና ደቡብ በመሄድ ወርቅ ማፈስ እንደሚችልም በብሄራዊ ቴሌቭዥን ተናግረዋል። “ኮብልስቶን” ድንጋይ ማንጠፍ እጅግ የሚያዋጣ ስራ እንደሆነ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሲመክሩም ተደምጠዋል።
ስልጣን የለቀቁበት ምክንያት ግን ግራ ሳያጋባ አልቀረም። “ሃገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው። ከፍተኛ የሆነ ያለመረጋጋት እና ችግር አለ። በርካታ ህይወት ጠፍቷል። በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል…” ብለውናል ኃይሌ። ችግሩ ይህ ሆኖ ሳለ ለችግሩ መፍትሄ ለመሆን እንዲያስችላቸው እሳቸው መውረድ እንዳለባቸው ነው የገለጹት። ከፍተኛው የመንግስት ስልጣን ላይ እያሉ ያልፈቱትን ችግር – ከዚያ በመውረድ የሚፈቱበትን ፎርሙላም በመግለጫቸው ጀባ ቢሉ ጥሩ ነበር። ሕዝቡ ለሚያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች የጥይት ምላሽ ሲሰጡ እንዳልነበረ። ሕዝብ ላይ ሲተኩሱ ለነበሩ ወታደሮች ማዕረግ ሲያንበሻብሹ እንዳልነበር – ይህንን ደፍረው ተናገሩ። ሹመቱ ወር እንኳ መች ሞላው?
ከምህንድስና ስራቸው አንስቶ የተዋጣለት ካድሬ ያደረጋቸውው የስልጣን ፍቅር ይሁን የበታችነት ስሜት – ብቻ አሁን ላይ ደርሰው በራስ መተማመንን ሳይቀር እንዳሳጣቸው ከንግግራቸው መገንዘብ አይከብድም። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን ይልቁንም እንደ ተላላኪ ሆነው ለማገልገል ሙሉ ፈቃዳቸውን ባይሰጡ እነሱም እንደ ጅሉ ሞሮን አይቀልዱባቸውም ነበር። ከተራው ሕዝብ ርቀው ጫፍ ላይ በመቀመጥ ሀገራዊ መርዶ ሲጋቱ ከከረሙ በኋላ ማልቀስ እና ማላዘን ምንም ትርጉም አይሰጥም።
በቅርቡ አሜሪካ የገባው የሳቸው ፕሮቶኮል ኃይሌ በግዞት ውስጥ ያሉ እስረኛ እንደሆኑ ቢናገርም እሳቸው ግን አንዲት ቃል እንኳ አልተነፈሱም ነበር። እንዲያውም በቅርቡ ሰጥጠውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የሃገሪቱ እድገት “የሚያስጎመጅ” በመሆኑ ሁሉም እንደሚመኙት በመናገር ትንሽ ፈገግ አድርገውናል። ይህንን ፈገግታችንን ሳንጨርስ ትላንት በኢ.ቢ.ሲ. ቀርበው ኢትዮጵያ በገባችበት አስከፊ ችግር ሳብያ ኢንቨስተሮች ሳይቀሩ ሃገሪቷን እየለቀቁ እንደወጡ አፈረጡት።
“በደርግ ዘመን ማሰቃያ የነበረው ማእከላዊ እንዲዘጋ እና ሙዚየም እንዲሆን” መወሰኑን ቢነግሩንም ይህንን ሙዚየም ሳያስመርቁ መሰናበታቸው ግን ቅር ያሰኛል። ይህንን መናገራቸው ባልከፋ ነበር ግና “ጽድቁ ቀርቶ …” እንዲሉ መንግስት የጀመራቸውን እቅዶች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለባቸው በስንብታቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም። የእስካሁኞቹ የመንግስት እቅዶችም ያየናቸው ናቸው። መብቱን ያወቀ እና መብቱን የጠየቀ ዜጋን ማሰር – ማፈናቀል – መግደል…. ናቸው።
ባለሙሉ ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለ ምህላ ሲያደርጉ፤ “እዚህ ያለሁት የመለስን ራዕይ ለማስፈጸም ነው” ብለው ነበር። ያን ለማድረግ ደግሞ የበላዮቼ እና የበታቾቼ የሚያዙኝን ሁሉ አደርጋለሁ ሲሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል። የበላዮቼ ያሉት ምክትል ሆነው የተሾሙ እነ ደብረጽዮንን መሆናቸው ነው። አድፍጠው ይህችን ወቅት ይጠብቁ የነበሩ እነ አቦይ ስብሃት ዛሬ አደባባይ ወጥተው፣ “የመለስ ራዕይ የሚባል ነገር የለም” ማለት ሲጀምሩ “ታላቁ መሪ”ን የተኩት “ታዛዡ መሪ” አይናቸው ፈጠጠ። መለስ የጀመረውን ለመጨረስ ቢፍጨረጨሩም ዳር አላደረሱትም። የመለስ “ዜጎችን በዘር ከፋፍሎ 100 አመት የመግዛት” ስትራቴጂ በነቄው ትውልድ ሲከሽፍ – እጅ መስጠት ግድ ይላል። እኚህ ሰው ነጸ አልነበሩም። ነጻ ሆነው ሲናገሩ የምንሰማቸው ተቃዋሚ ሃይሎችን እና ጋዜጠኞችን ሲሳደቡ ብቻ ነው።
ዛሬ ኳሷ ሕዝብ እጅ ላይ ስትወድቅ እሳቸውም ባነኑ። ከመለስ ወርሰው የተሸከሙት ነገር ራዕይ ሳይሆን – ቅዠት እንደሆነ የተረዱት በዚህ ሰዓት ይመስላል። ይህንን እስኪረዱት ግን ሕዝብ ማለቅ ነበረበት። መለስ የጀመረው ለእልቂት የተጠነሰሰ የፌዝ ፌደራሊዝም እጨርሳለሁ እንዳሉት ከግብ ባያደርሱትም፣ ብዙ ገፍተውታል።
የፖለቲካ አክሮባቱን ተስተምረው – የሃይል ሚዛን እያዩ የመገለባባጥ አባዜ ካልሆነ በስተቀር ሃገሪቱ 27 አመት ሙሉ ችግር ላይ ናት። የሕዝብ ድምጽ ሲዘረፍ አብረው ዘርፈዋል፤ መቶ ሺህ የኦሮሞ ወገናችን ከሃረር ሲፈናቀል አብረው ነበሩ። ኮንሶ ላይ ወገኖች እንደ ባርያ አሳዳሪ በሰንሰለት ሲጠፈሩ አልሰማሁም አይሉንም። ጉራ ፈርዳ ላይ በአማራ ወገናችን የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸምበት አንዲት ነገር አልተነፈሱም። እሬቻ ለበዓል የወጣ ከሺህ በላይ ሰው ሲያልቅ ሰራዊታችን አንድም ጥይት አልተኮሰም ነበር ያሉት። የጎንደር እና የባህርዳር ወጣቶች እንደቅጠል ያረግፍ የነበረው እሳቸው የሚተዳደረው ሰራዊት ነበር። በወልድያ እና በቆቦ ግድያን ሲቃወሙት አልሰማንም። መግለጫቸውን እያነበቡ በነበሩበት ቅጽበት እንኳን በእሳቸው ጠቅላይ አዛዥነት የሚመራው ሰራዊት ሶስት ሰዎችን ገድሏል።
ልብ ያለው ሰው ሁሉ ወቅቱ የሚናገረውን ድምጽ ያደምጣል። የ”ታህሳሱ ግርግር” ለሃይለስላሴ መንግስት ምልክትን አሳይቶ ነበር። እሳቸው ግን አይተው እንዳላዩ አለፉት። የህዝብን ቁጣ በንቀት ከማለፍ ይልቅ በአግባቡ ቢያስተናግዱት ኖሮ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከመዋረድ ይድኑ ነበር። ደርግም ቢሆን የሕዝብ ጥያቄን በጥይት ለመፍታት ሲጥር የተሞከረበትን መፈንቅለ መንግስ በ”ጥቂት ጀነራሎች” ስም ከሚያጣጥለው ይልቅ ብሄራዊ እርቅ ቢያደርግ ኖሮ የሃገሪቱ ችግር መፍትሄ ያገኝ ነበር።
ዛሬም የመውረድ ወይንም የመዋረድ ደወል እያቃጨለ ነው። ገዢው ፓርቲ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ፈትቶ፤ ከእውነተኛ ተቃዋሚዎች ጋር ወደ ብሄራዊ እርቅ መጓዝ ሲችል ችግሩን ይፈታዋል። በአንድ ነገር እርግጠኛ እንሁን። ሕዝብን በጠመንጃ ያሸነፈ ሃይል በታሪክ ኖሮ አያውቅም።
ብሄራዊ ቀውስ – ችግር ብቻ አይደለም። ቀውስ እድልም ነው። ወያኔ ይህንን እድል ለእውነተኛ ብሄራዊ መግባባት ቢጠቀምባት ለራሱም ይበጀዋል። ይህ ዕድል ካመለጠው ግን ተዋርዶ፤ ይወርዳል።
ክንፉ አሰፋ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
aradw says
What a nice analysis. thank you
Mulugeta Andargie says
ጎልጉል!! ይህስ የምን ፅሁፍ ይሆን?? መቼም ጉድን ጉድ ያወጣዋል!!! ጠ/ም፣ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ግለሰብ ነው።ግን የሚያግዘውንቡድን መርጦ መሯሯጥን ተያያዘው ፣ጉዳዩ ተነባብሮ የመጣው ካለፈው ሟቹ መሪ ነበር። ሳያጠናቅቅ ሞተ። ሃይለ ማርያም ተተክቶ ሲሰራ፣ ብዙ የብሄር እኩልነትን መብት መስጠት ገጠመው። ኣከናውኗል!! ግሩም ስራ እንጂ ኣያስወቅሰውም!! ልማቱን በይደር ይሁን ኣላለም!! ይልቁንም ኣቆነጀው እንጂ!! ደቡብ ሂድ ወይም ኣማራ ወይም ኦሮሞ፣ሃረሪ ሂድ፣ወይም ኣፋር ብቻ ከልብ ተሯሩጧል!! ዋናው ዕቅዳችን ልማት ነው። ሃይለ ስላሴ ጥሎልን የሄደው ካዝና እኮ፣ ሲዊዝ ባንክ ነው የዋጠው።ደርግ ትቶልን የሄደው ባዶ ካዝና ነው። በመለስ ዜናዊ ያልተመለሱ ስራዎች ባሁኑ ጠ/ም እየተመለሰ ነው። እስቲ ውነት እናውራ!! ከሰላሳ ዓመት ጦርነት ተላቀናል!! በኢህኣድግ ጥረት!! ሻብያ ብሄራዊ የውትድርና ኣሰልፎ መጣብን። ልማታችንን ለማሰናከል ነበር፣ግን ኢህኣድግ ወጥሮ ይዞታል!! ማነው መሪው??? ሃይለ ማርያም እኮ ነው!!! ባሁኑ ሰዓት ጠ/ም፣መለስ ዜናዊ ያልመለሳቸውን የብሄር ዕኩልነት ጥያቄ፣ ተመልሷል ብንል ማጋነን ኣይደለም። የሃይለማርያም ስራ ለምን ጊዜም ህያው ነው!! እንኳን እሱ፣ ባለቤቱ ድንቅ ስራዋ ሲወሳ ይኖራል!!! ጮሌዎች፣ምላስ ኣስረዛሚዎች፣ብልጣብልጦች፣ ነገር ቀይዶች፣ተንኮልን ኣዘውታሪዎች፣ ኣጉል ፖለቲከኞች፣ምክንያት ፈላጊዎች፣ሽሙጥ ወዳዶች፣ የወረቀት ብርቅዬዎች፣ የካፌ ዕድምተኞች፣ማዕድ ኣራቋቾች፣ ጋለሞታ ኣነፍናፊዎች፣ በሰው ስህተት ተሳላቂዎች፣ ሌላም ሌላም ናቸው ሃይለ ማርያምን የሚጠሉ። ለፈለፍኩ????
በለው! says
ኢሕአዴግ ማለት የሾህ አጥር
ሰጠሁ ይለናል ሲቆነጥር
ኃይለመለስ በሙት መንፈስ ተዋከበና
ወዲህ ዞር ቢል ሰው የለምና
መጽሐፍ ቅዱስ ሳበ ሳመና
ለቀቅሁ ይለናል መች ያዘውና ?
**************
የኋላዊት እመቤት አዜብ መስፍን “ኢህአዴግ ቢለቀኝ ጉሊት ነግጄ ሀፍታም እሆናለሁ” አለችን እሺ አልን
ኅይሌ የወረዳ ጣፊስ ብሆን ሲል…አማራ ክልል ሰፌድ የገዛ ትግራይ..ኦሮሚያ.. ደቡብ ክልል ወርቅ ማፈስ ብቻ ነው …. አለ ማክሰኚት ገበያ ውሎ ዕረቡ ሥራውን ለቀቀ አሉ፤ ለነገሩ ታላቁ ጠቅላይ መሪም ተጠቅልሏል:
ኅይለመለስ ደስአለኝ….
“በአገራችን የተከሰተውን አለመረጋጋት ችግር፤ በዚህም ምክንያት በርካታ የሰው ህይወት መጥፋት፤ ከአካባቢያቸው የመፈናቀል… የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል በኢህአዴግ እና በመንግስት ደረጃ የተለያዩ ሪፎርሞች ለማሳካት እኔም በበኩሌ ለነዚህ ሪፎርሞች መሳካት የመፍትሄው አካል ለመሆን፤ የኢህአዴግ እና የመንግስት ሃላፊነቴን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርቤያለሁ።”
** እንዲያው ለመሆኑ ይህንን ጥሁፍ ማን ጥፎ ሰጠብኝ!?___________________________________________________
__ ሰውዬው ችግሩ ሁሉ እራሱ እንደፈጠረው አምኖ የፈጠረውን ችግር ሥራዬን ለቅቄ የመፍትሄው አካል ልሁን አለ?
** “ድርጅትና መንግስት ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አድርገው የቀድሞው ጠ/ሚ ለመባል ስለጓጓሁ…”
__ ሥልጣኑን ለማን ሊያሻሙት ነው? ለኦፌኮ እና ኦህዴድ ? …. ከእሥር ለተፈቱት እና ለዲያስፐሩ?
ወይንስ ለተቃዋሚውና ለመከላከያው…. ለእህት ፓርቲዎች እና ለአጋር ፓርቲዎች?
** የምንገኝበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ለመቅረፍና ኢትዮጵያዊ የቀድሞ ‘መቻቻልና መከባበር’ ባህል እንዲቀጥል!?
—ድሮ ታሪክ ያወረሰን ያልተገባ ግንኙነት አላሉንም!? እነሱስ እህት ድርጅቶች ያልተጣጣመ (መርህ አልባ) መላ ቢስ ግንኙነት ላይ ነን ሲሉ አሁን ሕዝብ እንኳን አብሮ ሊኖር አብሮ ኳስ መጫወት ባልተቻለበት ዘመን፡ቋንቋና ነገድ ተኮር ክልል(ጋጣ) አጉረው የእርስ በእርስ አንገት መቀላላትን: ንብረት ውድመት:እኛና እናንተ ዘርተው ሲያጭዱ ምን ተሰማቸው!? የሕዝብ ጥያቄ ሁላችሁም ከሥልጣን ውረዱ አንጂ እየመረጣችሁ አስወግዱ አላለም።
** የመድብለ ፓርቲ ቱማታ!?
___ እህት ፓርቲ: አጋር ፓርቲ: አላዋጣም፡ የመጨረሻው ካርታ የኢህአዴግን ግንባር ማፍረስ! ተቃዋሚውን ያቀፈ ድርጅት መመሥረት …ኢህአዴግን በአጋር ፓርቲን እግርና እጅ አድርጎ ኦሕዴድን ማሳነስና ማስበርገግ (!?) በአንዳንድ ክልል ተቃዋሚው አንዲያሸንፍ(ኦህዴድን በኦፌኮ) መቀየርና እርስ በእርሱ ማናከስ! በርካታ ሥልጣንን ለኦሮሞ ሰጥቶ በህወሓት ራዕይ እራሱን በዘሩ አመራር ሰጭነት ማስቀጥቀጥ!፡ ወይንም አባት ሀገር ሻቢያ ጉያ መሸጎጥ! … አለዚያም አመቻችቶ ለመከላከያው አስረክቦ ለፀብ:ሀገር መፍረስና የሕዝብ መመሰቃቀል ሰቆቃ እጃቸውን ያስገቡ ሁሉ: በባዶው እሥር ቤት በማጎር ሠራዊቱ ወገናዊነቱን አሳይቶ… በአዲሱ አንድ ኢታማዦር አማካኝነት: የሀገሪቱን ርዕሠ ብሔር (ፕሬዘዳንት) ይዞ ከተፎካካሪው ጎራ: ከምሁራን: የሃይማኖት አካላት፡ የታሪክ:የሕግና የፖለቲካ ጠበብቶችን አቀራርቦ: ያለማንም የውጭ ኅይል ጣልቃ ገብነት ሕዝባዊ መንግስት እንዲቋቋም በማድረግ ወገናዊነቱን ማሳየት: ሀገርና ሕዝብ ማረጋጋት ይጠበቅበታል:: አለዚያ መለስ ኖረ አልኖረ ኅይለመለስ ለቀቀ ተነጠቀ: ኦሮሞ ገባ ከንባታ ወጣ እንዲሁ መደናቆር እንጂ ለውጥ የለም። አራት ነጥብ። ነን ሶቤ?
Tedros Bogale says
ጸሓፊ ክንፉ አሰፋ፣
ለድርሰትህ በጣም አምሰግናለሁ። በፈገግታ ነበር ያነበብኳት ግን ድንገት አለቀችብኝ። ወርቅ በሰፌድ ይታፈሳል ብለው የተናገሩትን ቪድዮ አይቼ ነበርና አሁን ስትጠቅሰው አሳቀኝ። በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኞች እንደሌሉም ተናግረዋል ሰውየው ዳሩ ግን እስክሪፕቶ እንደክላሽ ካልተቆጠረ በስተቀር እነ እስክንድር ነጋና ሌሎች ጋዜጦች በየትኛውም መስፈርት አሸባሪዎች ሊሆኑ አይችሉም። እንደሳቸው ደነዝ መሪ በአፍሪካ ውስጥ ተፈልጎ አይገኝም። ህግና ፍትህ ሲሰፍን ከተጠያቂነት አያመልጡም። በድጋመ አመሰግናለሁ