• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ወያኔ፣ ሽብር እና እኛ

September 13, 2014 12:02 am by Editor Leave a Comment

በአለም አቀፍ ደረጃ ስለ ሽብርተኝነት ያለው አረዳድ እና ወያኔ ሽብርተኝነትን የሚተረጉምበት መንገድ ለየቅል ናቸው። በአለም አቀፍ ደረጃ የሽብርተኝነት ጉዳይ እንደ ዋና አጀንዳ ተይዞ ለመጀመሪያ ጊዜ መነጋገሪያ የሆነው በ1934 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ነው። በዛሬው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተተካው የሊግ ኦፍ ኔሽን በሽብርተኝነት ዙሪያ ሲመክር ቆይቶ በ1937  ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ሽብርተኝነትን ለመከላከል እና ለመቅጣት የሚያስችል አንድ ድንጋጌ (Convention for the prevention and punishment of terrorism) አጽድቋል። ከዚህ ድንጋጌም በኋላ ከ14 የሚበልጡ አለም አቀፍ ድንጋጌዎችና ስምምነቶች በተባበሩት መንግስታት ጸድቀዋል። የእነዚህ ሕጎች ዋነኛ አላማም መንግሥታት ሽብርተኝነትን በተናጠልም ሆነ በጋራ እንዲዋጉ ለማስተባበር ብቻ ሳይሆን  ሽብርተኝነትን እንዋጋለን በሚል ሽፋን በዜጎቻቸውም ሆነ በተቀረው የሰው ዘር ላይ መድልዎን፣ ግፍና በደሎችን በመፈጸም ሰብአዊ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር የተጣለባቸውን አለም አቀፋዊ ግዴታ እንዳይዘነጉም ለማሳሰብ ነው። ምንም እንኳን ኃያላኖቹ አገራት ሳይቀሩ የጸረ-ሽብር ዘመቻን ለፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቻቸው ማስገኛ ሲያውሉትና ሲመነዝሩት በግልጽ ቢስተዋልም በሽብርተኝነት ላይ ያላቸው ምልከታና አቋም ግን በአለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡት መመዘኛዎች የራቁ አይደሉም።

በወያኔ መንደር ሽብርተኝነት ለየት ያለ መልክ ነው ያለው። የወያኔ የሽብርተኝነት መስፈርትም ሆነ ትርጓሜ ብዙ ሃገሮች፤ አንባገነን የተባሉት ሳይቀሩ ስለሽብርተኝነት ካላቸው ግንዛቤም ሆነ ከአለም አቀፉ መመዘኛዎች የተለየ ነው። የሽብርተኝነት ተግባር እየተተረጎመ ያለው በወያኔ ባልሥልጣናት የመሸበር መንፈስና ሰለራሳቸው ሥልጣን ብቻ በማሰብ ከጭንቀት በመነጨ የፍርሃት ስሜት ላይ የተመሰረተ ነው:: ባለሥልጣናቱን ጭንቅት ወስጥ የሚጥል፣ የሚያስደነብር፣ የሚያስቀይም፣ የሚያስቆጣ ወይም የሚያሰፈራራና እንቅልፍ አጥተው እንዲያድሩ የሚያደርግ ተግባራትን የፈጸመ ሁሉ በሽብርተኛነት ይፈረጃል:: ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀይ መስመር አስምረውና አዋቅረውት የሄዱትን የወያኔን አጥር የሚነቀንቅ ብቻ ሳይሆን ጠጋ የሚልም ሁሉ በአሸባሪነተ ሊፈረጅ፣ ሊታሰርና ሊከሰስ እንዲሁም ሊፈረድበት እንደሚችል እየታየ ነው:: ለአገዛዝ ሥርዓቱ የሥልጣን ዘመን መራዘም ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉዋቸውን አካላትና ግልሰቦች ሁሉ አሸባሪ አያሉ መክሰስ የተለመደ ሆኗል። ብዕራቸውን አንስተው በመንግሥት ላይ የሰሉ ትችቶችን በመጻፍ ተቃውሟቸውን የገለጹ፣ የሃይማኖትና የተለያዩ ማህበራዊ ተቋማትን በመወከል የመብት ጥያቄዎችን አንስተው የተሟገቱ የሕዝብ ወኪሎች፣ በወያኔ በባለሥልጣናት የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ሙስናዎችን፣ አገርና ሕዝብን ያዋረዱ ተግባራትን ያጋለጡና ባደባባይ ሥርዓቱን የሞገቱ ጋዜጠኞች፣ የማህብራዊ ድረ-ገጽ ተሳታፊዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ጭምር የሽብርተኝነት ካባ እያከናነቡ ማጎርና መወንጀል የሥርዓቱ ዋና ስልት ሆኗል። ይህም ወያኔ አለም በሚሸበርበት ጉዳይ ሳይሆን ራሱ በፍርሃት በፈጠረው የሽብር ዓለም ወሰጥ መሆኑን ያሳያል::

ከግለሰብ (ከሟቹ ጠ/ሚ መለስ) አንባገነናዊነት ወደ ቡድን አንባገነናዊነት የተሸጋገረው የወያኔ-ኢሕአዴግ ሥርዓት ከመቼው ጊዜ በከፋ ሁኔታ በፍርሃት መዋጡን የሚያመላክቱ በርካታ ክስተቶችንም እያስተዋልን ነው። ፍጹም አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ የነበሩትን አቶ መለስ በብዙ ትናንሽ መለሶች ለመተካት ተጥሯል። ምንም እንኳን በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ ባይቻልም የሥርዓቱ ተዋናይ ከነበሩ እና አሁንም በሥልጣን ላይ ካሉ የአመራር አባላት እየሾለኩ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በድርጅቱ ውስጥ ባሉት ጎሣን መሰረት ያደረጉት ክፍልፋዮች መካከል ከሚስተዋለው ጤናማ ያልሆነ የፖለቲካ ፉክክር እና ሽኩቻ ባሻገር በግለሰቦች ዙሪያ የመቧደን ስሜት እየጎላ በመምጣቱም ድርጅቱ ውስጥ ፍርሃት እንዲነግስ አድርጓል። ይህንን ክፍተት በመጠቀም በሰላማዊም ሆነ በነፍጥ ኃይል የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎችና ቡድኖች መነቃቃትም በፍርሃት ውስጥ ያለውን የወያኔን ሥርዓት የበለጠ እንዲደነብር አድርጎታል።

በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰላማዊ ትግል አምነው ከተደራጁት የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የተወሰኑት በተከታታይ ያካሄዷቸው የተቃውሞ ሰልፎችና የሕዝብ ምላሽ፣ አፈና እና ስቃዩን ተቋቁሞ ለአመታት የዘለቀው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ፣ ልማትን ሽፋን አድርጎ ሥር እየሰደደ ያለው የኑሮ ዋስትና መታጣትና የከፋ ድህነት፣ በሃያ አመት ውስጥ የተዘራው የዘር ፖለቲካና በአዲሱ ትውልድ አእምሮ ውስጥ ፍሬውን አፍርቶ በሥርዓቱ ላይ ጭምር የዘር ጥላቸቻን ማሳየቱ እና ሌሎችም ውጫዊ ምክንያቶች ተደማምረው ገዢውን ኃይል እንዲፈራና የፈሪ ዱላውንም እንዲያነሳ አስገድደውታል። ዛሬ የወያኔ አመራሮች ሕዝብን ብቻ ሳይሆን የሚፈሩት እራሳቸውንም ጭምር ነው። ድርጅቱ አባላቱን ይፈራል፣ በአወራውና አጃቢ ድርጅቶች መካከል መፈራራት አለ፣ አባላቱ እርስ በርስ ይፈራራሉ፣ አባላቱ መሪዎቻቸውን ይፈራሉ፣ መሪዎች ተከታዮቻቸውን (ተራ ካድሬውን) ይፈራሉ፣ በአመራር ላይ ያሉት ሰዎችም እርስ በርስ ይፈራራሉ። የአንድ ላምስት የስለላ መዋቅር ምንጩም ይህ ነው። አንድ ሥርዓት ጭልጥ ወዳለ አንባገነናዊነት (totalitarianism) ሲገባ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን እራሱንም ይፈራል:: በደርግ ዘመንም የሆነው የሄው ነበር:: ለዚህም ነው በእንዲህ ያሉ ሥርዓቶች ውስጥ አባላቱና ደጋፊዎች ከሚሰሩበት ይልቅ እርስ በርስ የሚገማገሙበት ጊዜ ሳይበልጥ አይቀርም የሚባለው።  ሕዝብን እና ራስን መፍራት የሽብር መንፈስ ውስጥ ይከታል።

የፖለቲካ ተቀናቃኞችንና የሰላ ትችት የሚሰነዝሩበትን ሁሉ አሸባሪ እያሉ የጥቃት ዒላማ ማድረጉም ዋነኛ አላማው አነሱን ከትግሉ ሜዳ ለማሸሽ ብቻ ሳይሆን የቀረውንም ሕዝብ ለማሸማቀቅና በፍርሃተ ውስጥ ሆኖ ጸጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛም ለማድረግ ነው::  ሥርዓቱ የሕዝብ ስላልሆነ ሕዝብን ይፈራል። ለነገሩ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ለጥቅም ሲሉ በዙሪያው የተኮለኮሉትን ሹማምንት፣ አባላቱን እና ‘የአባቴ ቤት ሲዘረፍ አብሬ ልዝረፍ’ በሚል ሕሊና ማጣት ወይም አይን ያወጣ ሌብነት የከበቡትን ‘መሁራን’ና ባለሃበቶች ጭምር ይፈራል:: በመሆኑም የሥርዓቱ ደጋፊዎችና አባላቱ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል በከፋ ሁኔታ የአፈና መዋቀሩ ዋነኛ ሰለቦች ናቸው:: አንድ የወያኔ-ኢህአዴግ አባል የሆነ ሰው በአባልነቱ የተለያዩ ቁሳዊ ጥቅሞችን በብቸኝነት ወይም በቅድሚያ ከሌላው ሰው ተለይቶ የማግኘት እድል ይኖረዋል:: ይሁን እንጂ ይህ እድል በነጻነት ማሰብን፣ ሃሳቡን በነጻነት መግለጽን፣ ያመነበትን የፖለቲካም ሆነ ሌሎች አስተሳሰቦቹን ባደባባይ ማንጸባረቅን ወይም ባመነበት ጉዳይ አቋም የመያዝን፣ በመንግሥት ፖሊሲዎችና አፈጻጸሞች ላይ የሰሉ ትችቶችን የመሰንዘር ባጠቃላይ የፖለቲካና የሲቪል መብቶቹንና ነጻነቶቹን አያጎናጽፈውም:: በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች የነጻነትን ጣእም አያቁትም።

እንደ እኔ እምነት የወያኔ ጀሌዎች ከሌላው ሕዝብ በከፋ አፈና፣ ፍርሃትና ሽብር ውሰጥ ነው የሚኖሩት:: ልዩነቱ እነዚህ ሰዎች ወደውና ፈቅደው ነጻነታቸውን ከሥርዓቱ ለሚወረወርላቸው ቤሳና ጠናነሽ ጥቅማጥቅም አሳልፈው መስጠታቸው ብቻ ነው:: ሲያሰቡም፣ ሲናገሩም ሆነ ሲጽፉም እራሳቸውን ሆነው እንደ አንድ ነጻ ሰው ሳይሆን በቡድን እንደ ወያኔ ሆነው ነው:: በዚሀ ቡደን ወስጥ በነጻነት ማሰብም ሆነ ያሰቡትን የመግለጽ ነጻነት የተሰጠው የድርጅቱ አናት ላይ ለተቀመጡ ጥቂት አመራሮች ብቻ ነው:: ቀደም ሲል በመቶ ሺ ለሚቆጠሩት የድርጅቱ ጀሌዎች የማሰቡንም ሆነ እንደልብ የመናገሩን ድርሻ የያዙት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒሰትር ነበሩ:: ከሳቸው እልፈት በኋላ ከስራቸው የነበሩት ጠቂቶች የፈላጭ ቆራጭነት ቦታውን ይዘዋል:: አንድ ቀላል ምሳሌ ለመስጠት የወያኔ-ኢሕአዴግ አባላት የትኞቹን የጋዜጣ ህትመቶች ማንበብ እንደሚችሉና እንደማይችሉ እንኳን የሚወሰንላቸው በድርጅታቸው አንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ አድምጫለሁ:: ወያኔን የሚነቅፉ የጋዜጣ ህትመቶችን ስታነቡ ታይታችኋል ተብለው ለግምገማ የቀረቡም መኖራቸውን ይታወቃል:: ነጻነቱንና ከብሩን የወደደው ሌላው ሰው ግን ታግሎ ለውጥን ባያመጣም ከነክብሩ የግፍ እንቆቆውን ይጋታል:: የሥርዓቱ ደጋፊ ወይም አባል ባለመሆኑ ብቻ መከራን የቀበላል:: ገበሬው ከሆነ ከማዳበሪያና ሌሎቸ ጥቅማቅሞችን ከመክልከል አንስቶ ከመሬቱና ከቅዬው እንዲፈናቀል ይደረጋል፣ ሠራተኛውም ለተለያዩ አሰተዳደራዊ በደሎች ይጋለጣል፣ ተማሪና ነጋዴውም በትንሽ በትልቁ ይዋከባል፣ ወጣቶችም በሥራ እድል መድሎ ይፈጸምባቸዋል:: ባጭሩ ወያኔ በፍርሃተ ውስጥ ሆኖ እያስፈራራ፣ ተሸብሮ እያሸበረ፣ ታፍኖ እያፈነ ቀጣዩን ምርጫ ካለፉት ምርጫዎች በከፋ ሁኔታ ለማስተናገድ ሽርጉዱን ጀምሯል::

ጥልቅ በሆነ ፍርሃት ወስጥ ሆኖና ውሉ በማይታወቅ የሸብር ስጋት ተሸብሮ ሕዝብን ማሸበር፣ በጎሣ ፖለቲካ የሰበጣጠሩትን ሕዝብ የቡና ማህበር ድረስ ሥር የሰደደ የአፈና መዋቅር ዘርግቶ በመጠርነፍ የልቡን እንኳን ቡና እየጠጣ እንዳይተነፍስና በሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹም እንዳይተዛዘንና እንዳይረዳዳ ማድረግ ሥርዓቱ አገሪቱን እና ሕዝቡን ይዞ ሊገባ እየተንደረደረ ያለበትን ጥልቅ ገደል ያመላከታል:: በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ተማሪዎች ያነሱዋቸው ጥያቄዎች ባህሪያት እና የሥርዓቱ ምላሽ የዚህን አደጋ ቅርበት ጥሩ አድርጎ ያሳያል:: እንግዲህ የሁሉም ሰው ጥያቄ እንዲህ ፈርቶ እያስፈራራ፣ ተሸብሮ እያሸበረ፣ ሕዝብንም አገልጋዮቹንም አፍኖ አገሬውን ሁሉ የቁም እስረኛ፤ ቀሪውንም በየማጎሪያው ካምፑ ከርችሞ እያሰቃየ ያለውን ክፉና በአጉል ቀን የተጣባንን ሥርዓት በምን መላና ዘዴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትከሻችን ላይ አውርደን እንገላገለው የሚል ይመስለኛል:: ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት እንዲህ ቀላል ባይሆንም ወደ መልሱ የሚያመሩ መንገዶችን ግን መጠቆም ይቻል ይሆናል::

እኛስ?

ሥርዓቱ ዕለት ተዕለት በአገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጽማቸውን ወንጀሎችና ደባዎች፤ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ረገጣዎች እየተከታተሉ በማጋለጥና ሕዝብ እንዲያውቀው በማደረግ ረገድ የግል ሚዲያውና የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ትልቁን ሚና ተጫውተዋል:: ይሁንና ጥረታቸውን የሚያግዝና ሥርዓቱን ሊያርቅ የሚችል ሌላ የተጠናከራና አገራዊ ዕራይ ያነገበ ኃይል ሊፈጠር ወይም ከተፈጠረም በዘላቂነት ሊቆይ ባለመቻሉ የተቆለሉት ወንጀሎችና ጥፋቶች የወያኔን ገጽታ ወደ አስፈሪ ጭራቅነት አግዝፈውታል:: በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ ያሉ ቡዙዎቹ የውይይት መድረኮችና ሚዲያዎች ወያኔን ለማዋረድ በማሰብ ብቻ በየቀኑ የሚያዥጎደጉዱት ፕሮፓጋንዳ ብዙዎች ወያኔን የማይደፈር ኃይል አድርገው እንዲያስቡት እስተዋጾ አድርጓል:: ከዚያም በላይ ከጥላቻ ያልዘለለው የአንዳንድ ሚዲያዎች ያላቋረጠ የጸረ-ወያኔ ፕሮፓጋንዳ ተደማምሮ ደርግ አላሸቆት የሄደውን የሕዝብ ወኔና የመንፈስ ጥንካሬ እንዳያገግምና የፖለቲካ ምህዳሩን እንደ ፈንጂ ቀጠና እንዲያየው አድርጎታል:: ወያኔ ባያወቀው ነው እንጂ እነዚህን ሚዲያዎች ለማፈንና ከሕዝብ ዘንድ እንዳይደርሱ ለማድረግ የሚጥረው እነዚህ ሚዲያዎች ባለውለተኞቹ ናቸው:: በግምት 95% በሚሆነው ዘገባቸው የወያኔን ወንጀል የመፈጸም ችሎታ፣ አቅምና የአፈጻጸም ሥልቱን፣ ስለ ተደራጀው የአፈና መዋቀሩ፣ ወደር ስለሌለው ጭካኔው፣ ከሕግ በላይ ሰለመሆኑ እና ያሻውን ቢያደርግ የሚመልሰው አንዳችም ኃይል አለመኖሩን ነው ነጋ ጠባ የሚዘከዝኩት:: ወያኔ እነኚህን መድረኮች ከሚያፍናቸው ይልቅ ሕዝብን የማስፈራራቱን ሥራ እየሰሩለት ስለሆነ በእጅ አዙርም ቢሆን ገንዘብ እየደጎመ ቢያጠናክራቸው አድሜውን ለማራዘም ይረዱታል::

በእነዚህ መድረኮች እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስላለው እምቅ ኃይል፣ በሰውነቱ ሰለተጎናጸፋቸው መበቶችና ነጻነቶች፣ ከሌሎች ጋር በጋራ አብሮ ሲቆም ሊፈጥር ስለሚችለው ኃያል ጉልበትና ተአምር፣ ሕዝብ እንዴት የሥልጣን ባለቤትነቱን ማረጋገጥ እንደሚችል፣ የሰላማዊ እመቢተኝነት ኃያልነትን ማወራትና ማሰተማር የተለመደ አይደለም:: ወያኔን ለመታገል በተቃራኒው ተደራጅቶ ሰለቆመውም የፖለቲካ ኃይል ከሚናገሩት ውስጥ አመዛኙ መርዶ ነው:: አንጃ ተፈጠረ፣ ኅብረት ፈረሰ፣ ውህደቱ መከነ፣ እገሌ ከዳ፣ እገሌ የተባለው ፓርቲ ‘እገሌ-ዲ’ የተባላ ደባል አፈራ የሚሉና አዳዲስ ግንባሮችና ውጥኖች መጠንሰሳቸውን ሰምቶ የሚቦርቀው ሰው ላቡን ሳያደርቅ ደም እንባ የሚያስለቅሱ የክሸፈት መርዶዎችን ያበስሩናል:: እንደ እኔ እምነት እነዚህ ሚዲያዎችም ሆኑ የሚዲያዎቹ ተሳታፊዎች የሳቱት ትልቁ ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዝምታ የወያኔን ደባና ወንጀል በደንብ ካለማወቅ ነው ከሚል መነሻ ላይ ሆነው ሥራቸውን መጀመራቸው ይመስለኛል:: ተደበደብክ፣ ታሰርክ፣ ታፈንክ፣ በላይህ ላይ ሞሰኑብህ እያሉ ለተደበዳቢው፣ ለታፋኙ፣ ለታሳሪው፣ ሌት ከቀን የግፍ እንቆቆውን ለሚጋተው ሰው ለራሱ ‘ሰበር’ ዜና እያሉ ማደንቆር ተበዳዩን አያጀግነውም፣ ለትግልም አያነሳሳውም፣ ብርታትም ሊሆነው አይችልም:: የማይካደው ቁምነገር ግን ቢያንስ በደሌን ሕዝብ አውቆልኛል ብሎ አንዲጽናና እና አሱም የሌሎችን በደል እያደመጠ በደልን እንዲላመድ ይረዳው ይሆናል::  ለዛም የምስለኛል ይህ ሁሉ መከራ ቢሚወርድበት አገር ከ90 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ብቻ ለራሳቸውና ለሕዝብ ነጻነትና ከብር ባደባባይ ወጥተው የሚታገሉት:: ለዚህም ይመስለኛል ሃዲዱን የሳተውን የአገሪቱን የፖለቲካ አቅጣጫ ለማስተካከልና መረን የለቀቀውን የወያኔን ባህሪ ለማረቅ ዕዳው በጣት በሚቆጠሩ ግለሰቦችና ደርጅቶች ላይ የተጫነው:: እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምወደው ሥርዓቱ የሚፈጽማቸው ወንጀሎችና ጠፋቶች አይነገሩ፣ ሕዝብ እንዳይሸበር ተሸፋፍነው ይቅሩ እያልኩ አይደለም::

ሕዝቡ የሚደርስበትን በደል ጠንቅቆ ሰለሚያወቅ እሱኑ ነጋ ጠባ አያወጡና እያወረዱ ማብጠልጠል መፍትሄ አይሆንም:: ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች የለውጥ ኃይሎች በሕዝቡ ውስጥ የሰረጸውን ጨለምተኝነት ለመግፈፍና ሕዝቡም የትግሉ አካል እንዲሆን፤ እንዲሁም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፣ ባለድርሻም ነኝ፣ ኃላፊነትም አለብኝ፣ ለውጥ ለማምጣትም የሚያስችል አቅም አለኝ በሎ ማሰብ እንዲጀምር ሊያስተምሩትና አቅሙን አጉልተው ሊያሳዩት ይገባል:: መልካም ዜጋን የመገንባት ሥራ ላይ ልናተኩር ይገባል:: የአገዛዝ ሥርዓቱን አያገዘፉ ሕዝብን ማኮሰስና ማስፈራራት ወያኔ እንደተፈራ ሌሎች አስርት ዓመታትን እንዲቆይ ይረዳዋል:: ሸነጥ ሲያደርገን በቻ እየተነሳን ሥርዓቱን የገለባ ክምር አድርጎ በማቅለል በስድስት ወር እንንደዋለን፣ የመሪዎቹን ጉሮሮ አንቀን ከምድረ ገጽ እናጠፋለን አያሉ መፎከርና ለአመታት ይህንኑ እየደጋገሙ መማልና መገዘት በጭንቅ ውስጥ ያለውን ሕዝብ በቀቢጸ ተሰፋ እንዲቆይና በአገር ላይ የተጋረጠውንም አደጋ በቅጡ እንዳያይ በማድረግ መዘናጋትን ይፈጥራል እንጂ ግዴታውን እንዲወጣ አያነሳሳውም:: ፉከራና ቀረርቶውም እየተስተዋለ ይሁን::

በቸር እንሰንብት!

ከያሬድ ኃይለማርያም

yhailema@gmail.com

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Opinions Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am
  • የብልፅግና ፓርቲ ሹመኛ ካድሬዎች February 3, 2025 11:07 am
  • ትግሉን የጎዳው የእስክንድር ነጋ አካሄድ February 3, 2025 10:29 am
  • ኤሊያስ መሠረት “ጭምብሉ ዛሬ ወለቀ”፤ ተከፋይ ነው! February 2, 2025 05:32 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule