በሱዳን የተለያዩ የሰደተኛ ካምፖች፣ እንዲሁም በከተሞችና በተለዩ ሥፍራዎች የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) ያደራጃቸውና “ሳምሪ” የሚባሉ ታጣቂዎች መስፈራቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል። በማስረጃና በመረጃ ወደ ሱዳን ማቅናታቸው ሲገለጽ ጎን ለጎን እነዚሁ ታጣቂዎች በማይካድራ ጭፍጨፋ፣ ከግብጽና ሱዳን ሰፊ ድጋፍ አግኝተው ራሳቸውን ለጦርነት እያዘጋጁ መሆኑ በተለያዩ አውዶች ሲገለጽ ነበር።
ትሕነግ “የትግራይን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ” ብሎ ሲነሳ ጀምሮ ከሱዳን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው እንደሆነ አባላቱና አመራሩ በኩራትና በውለታ ቆጣሪነት መስክረዋል። “ከአማራ ይልቅ የሱዳን ህዝብ ይሻለናል” በሚል በግልጽ ንግግርም ተደርጎ እንደነበር ይህ ትውልድ ያስታውሳል።
ግንቦት ሃያ መቀሌ ሲከበር የቀድሞው የሱዳን መሪ አልበሽር የትሕነግን መለያ ለብሰው በበዓሉ ላይ እንደ ቤተሰብ ይጋበዙ የነበረውም፣ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር በወልቃይት በኩል በመድፈር ትሕነግ መሳሪያ እንዲታጠቅ፣ የዕርዳታ ዕህል እንዲነግድ፣ ለትሕነግ አመራሮች ሽፋን በመስጠት ያበረከትችው ውለታ ለትሕነግ ተቆጥሮ ስለማያልቅ ነው። የዚያኑ ያህል “ኢትዮጵያን የሚወድ መሪ መቼ መጥቶ ሱዳንን በሯን ይከፍላታል” በሚል የሚቃጠሉ ወገኖችም ነበሩ።
ትሕነግ ከሥልጣን ከተወገደና የወልቃይት ጠገዴ ሲቲት ሁመራን ከተነጠቀ በኋላ የሱዳን የግንኙነት መስመሩ በመዘጋቱ አልቡርሃን የሚመሩት ጦር በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያን ሲወጋ መቆየቱ፣ የሳምሪ ታጣቂዎችም በጋራና በተናጠል የሱዳንና የትግራይን መገናኛ ኮሪዶር ለማስከፈት ሙከራ ሲያደርጉ ከርመው ባለመሳካቱ ኮሪዶሩ አሁን ድረስ እንደተጠረቀመ ነው።
አሁን ላይ ትሕነግ በወልቃይት በኩል ዳግም ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት ማድረጉና፣ ለዚህም ይረዳው ዘንዳ በሱዳን ያለውን ኃይል የማንቀሳቀስ ሥራ እየሠራ መሆኑ በመረጃ መንታፊዎች ይፋ አድርገዋል። ይህን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ካርቱምን ጨምሮ አብዛኛውን ሱዳንን የሚቆጣጠረው የጀነራል መሃመድ ዳጋሎ (ሀሚቲ) የሚመሩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) በመሆኑ ትሕነግ ለሚፈልገው ዕቅዱ አላመቸም።
ጉዳዩን የሚከታተሉ የመረጃ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ በግብጽ ሙሉ ድጋፍ የሚደረግላቸው ጀኔራል አልቡርሃን ሳምሪ የሚባለው የትሕነግ ኢመደበኛ ኃይል ከጎናቸው አሰልፈው የዳጋሎን ኃይል እየወጉ እንደሆነ ይፋ በሆነ በሳምንት ጊዜ ውስጥ የፈጣን ኃይሉ በሕጋዊ የድረገጽ አምዱ “ትሕነግ ከጀነራል አልብሩና ጋር ሆኖ በቅጥረኛነት እየወጋኝ ነው” ሲል መግለጫ አውጥቷል።
ይህን መግለጫ ተከትሎ ነው ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ ከ600 በላይ ንጹሃን በግፍ መጨፍጨፋቸው ዳግም እንደ አዲስ መዘከር የያዘው። “ሳምሪ” የሚባለው የትሕነግ ኢመደበኛ አደረጃጀት ወደ አደባባይ በማውጣት “አዲስ ፍቅር ከአማራ ፋኖ ጋር” የሚለው ትሕነግ አዲስ ቀመር ውስጥ የተሳተፉና ለመሳተፍ ያኮበኮቡ ራሳቸውን እንዲፈትሹ ጥሪ የቀረበው።
ከጭፍጨፋው ጋር ብቻ ሳይሆን ይህ ኃይል ወደ ሱዳን ማቅናቱና በሱዳን ካሉ የትሕነግ ሌሎች ኃይሎች ጋር ሆኖ ሰፊ አደረጃጀት መዘርጋቱን የሚገልጹ የምስልና የጽሁፍ ማስረጃዎች ሲሰራጩ እንደነበር በወቅቱ የተዘገቡ ዘገባዎችን በማጣቀስ ጉዳዩ አየሩን ሲይይዘው ትሕነግ ከመቀለ “ፍጹም ሃሰት ነው” ሲል ክሱን ለማስተባበል ተገዷል። በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት “ጥሪ አይቀበልም” ያለ ይመስላል።
የሦስተኛ አገራት እጅ ያለበት የሱዳን የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉት ተፋላሚ ቡድኖች በርካታ ናቸው። ከነዚሁ መካከል ጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ ወይም ሂመቲ የሚመራውን የፈጥኖ ደራሽ ጦር RSF (Rapid Support Forces) እየወጉ ካሉት መካከል የትሕነግ ኃይሎች መሆናቸው ተመልክቷል። “በሱዳን በጥገኝነት ይኖሩ የነበሩት የወያኔ ወታደሮች ከአልቡርሃን ሰራዊት ጋር ወግነው ወታደሮቼን እየወጉ ነው” ሲል በይፋ መግለጫ ያወጣው የጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ደጋሎ ኃይል ከበቂ በላይ ማስረጃ እንዳለው አመልክቷል። ከዚህ በፊት ቆስለው የተማረኩ የትሕነግ ወታደሮችን ወደ አገራቸው መሸኘቱንም በመግለጫው ጠቅሶ አስጠንቅቋል።
የሃምዳን ዳጋሎ መግለጫ በቀጥታ ትሕነግን ወይም ወያኔን የሚመለከት ቢሆንም መግለጫውን “ፍጹም ሀሰተኛ ነው” ሲል የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ነው ያስተባበለው። ማብራሪያም የሰጠው።
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል /Rapid Support Forces – RSF/ በሚባል የሚጠራው “የህወሓት ታጣቂዎች ከሱዳን ወታደራዊ ኃይል /SUDANESE ARMED FORCES SAF/ ጋር በማበር እየወጉኝ ነው” በማለት ያወጣውን መግለጫ ሲያጣጥል፣ “የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መግለጫ ለዘመናት የቆየውና በፅኑ መሰረት የቆመው የትግራይና የሱዳን ህዝቦች ወዳጅነት ከግምት ያላስገባ ነው ብሎታል” የሚል የቀድሞ ውለታን የሚዘክር ማስታወሻ አስቀድሞ ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በሱዳን የሺዎች ህይወት በመቅጠፍ ላይ ያለውን የአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ “የህወሓት ሃይሎች ተሳትፈዋል የሚል ክስ ማቅረቡ ሃሳባዊና መሬት ላይ መረጋገጥ የማይችል የለየለት ፈጠራ ነው” በማለት ራሱን የተከላከለው የትግራይ አስተዳደር፣ “በሱዳን ያለው የአርስበርስ ግጭት ዓለምአቀፍ መልክ ለማስያዝና እርዳታ ለማግኘ ያለመ ነው” በሚል ከክሱ ጋር ግንኙነት የሌለው ሐረግ አንስቷል።
በመግለጫው የትግራይ ህዝብ ነሳ አውጪ ግንባር “በመሠረቱ ህወሓት የፓለቲካ ድርጅት እንጂ የሚያዘውና የሚያስተዳድረው ታጣቂ ኃይል የለውም” ሲል በመግለጫው ውስጥ ማካተቱ ከማስተባበያው በላይ ሌላ ዜና ሆኗል። “ከሚሰጠኝ በጀት ላይ በማንሳት 250 ሺህ ጦር ካምፕ አስቀምጬ እየቀለብኩ ነው” ያለው ጌታቸው ረዳ በስሙ ከወጣው መግለጫና ማብራሪያቸው ጋር እንዴት ሊታረቅ ነው? በሚል እየተወረፈ ነው። “ያዳቆነ ሰይጣን” ሲሉም የተረቱ ብዙ ናቸው።
ትሕነግ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ በተደጋጋሚ ሰፊ ኃይል አሰልፎ፣ ያሰለፈውን ኃይል ሲያሰለጥንና ሲያስመርቅ፣ ከዚያም አልፎ ቲዲኤፍ ብሎ ሰይሞ ለዓለም ሚዲያ ነጋ ጠባ መግለጫ ሲሰጥ እንዳልነበር፣ አሁንም ይህን ኃይል እንደማይበትን በተደጋጋሚ እያስታወቀ “በመሠረቱ ህወሓት የፓለቲካ ድርጅት እንጂ የሚያዘውና የሚያስተዳድረው ታጣቂ ኃይል የለውም” ሲል በይፋ መናገሩ “አይቼሽ ነው ባይኔ …” የሚለውን ዘፈን አስታውሷል።
እስከ አፍንጫው ታጥቆ፣ የአገር መከላከያን ትጥቅ ዘርፎ ግዙፍ ኃይል የገነባውና አሁን ድረስ “ምዕራብ ትግራይ” እያለ ወቅት የሚጠብቀው ትሕነግ ኃይል እንዳለው የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ የተሳተፉ በቁጥር፣ በደረጃና በትጥቅ ብዛት ለይተውት እያወቁት በዚህ ደረጃ መግለጫ ማውጣቱ ውሸት በትሕነግ ዘንድ ባሕል ቢሆንም፣ አስደንግጧል። እነ ትኖንቮል “ቲዲኤፍ” የሚል ስያሜ የሰጡት ትሕነግ የሚቆጣጠረውና የሚመራው ኃይል በመሆኑ ነው ፕቶሪያ ላይ “ትጥቅ እፈታለሁ” ብሎ የፈረመው። ይህንን ኃይል የሚመራው የትሕነጉ ታደሰ ወረደ እንደሆነ ታምኖ እያለ ትሕነግ የእርሱ ያልሆነን ኃይል እንዴት “ትጥቅ እፈታለሁ” ብሎ ሊፈርም ቻለ ብሎ ብቻ መጠየቅ የትሕነግን ማንነት የሚያሳይ ይሆናል።
መግለጫው በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንዳ ያስነሳውን ቁጣ ለመከላከል ያለም ቢሆንም “የትግራይ መከላከያ ኃይል (ቲዲኤፍ)” የሚባለው ሠራዊት ለወረራ ሲተም የሚያሳዩ የፊልም መረጃዎችን በማንሸራሸር በርካቶች በማህበራዊ ገጾች አሽሙር እየተጫወቱ ነው።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በሱዳን የተፈጠረው አውዳሚ የአርስ በርስ ጦርነት የሚያስከትለው አደጋ በመረዳት የውጭ ኃይሎች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ ጥሪ ሲያቀርብ፣ ዋናው ተዋንያን ግብጽ ሆና ሳለ አልጠቀሳትም። ሻዕቢያንም አላነሳም። የሱዳን ጦርነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሆኖ ሳለ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ያለው ነገር የለም። ለአፉ እንኳን መንግሥት ሰላም እንዲወርድ እንዲተጋ ጥሪ አልቀረበም። ትሕነግ በኢመደበኛ አደረጃጀት ስላደራጃቸው ሳምሪዎች ምንም አላነሳም።
ሳምሪ – ምን ተብሎ ነበር? ሊካድ የማይችል ሃቅ!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌት፣ አብን፣ መንግሥት፣ የአሜሪካ ድምጽ ወዘተ መረጃ ጠቅሰው ሳምሪን በማይካድራ ለተፈጸመው ዘርን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ ተጠያቂ አድርገዋል።
“በማይካድራ የተፈጸመው ግድያ ‘የጦር ወንጀል’ ሊሆን እንደሚችል ተመድ” ሲገልጽ ኢሰማኮ ከሕዳር 5 እስከ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ፣ በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጎንደር ከተሞች ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝት ይፋ ባደረገበት ሪፖርቱ፣ “ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በወቅቱ በሥልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን ነው” ብሏል።
“ይህ ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በበንጹሃን ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል” ሲል ኮሚሽኑ በውቀቱ ገልጾታል። ኢሰመኮ አይይዞም “ጭፍጨፋውን የፈጸሙት ቡድኖች ‘አማሮችና ወልቃይቴዎች’ ያሏቸውን ከቤት ቤት እየዞሩ ነው የገደሉዋቸው” ብሏል። ደብቀው የተረፉዋቸው የትግራይ ተወላጆች እንደነበሩም ምስክሮችን ጠቅሶ ጠቁሟል።
አምነስቲ ስለ ጭፍጨፋው ባወጣው ሪፖርቱ “በየቦታው ወድቀው የሚታዩና በአልጋ ላይ የሚታዩ አስከሬኖችን አሰቃቂ ፎቶ ግራፎችና ቪዲዮዎችን የተረጋገጡ” በሚል ነው የገለጸው።
ሪፖርቱ እንደሚለው ከሆነ በህወሃት ቡድን አደራጅነት ማይካድራ ላይ የተፈፀመው የጅምላ ግድያ ቦኮሃራምና ሌሎች የሽብር ቡድኖች በተለዩ ሀገራት ከፈፀሟቸው አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች በመብለጥ በርካታ ንፁሃን ሰዎች ህይወታቸውን ያጡበት ኢሰብዓዊ ድርጊት ሆኗል።
የህወሃት ቡድን አስታጥቆ እንዳሰማራቸው በተገለጸው ሳምሪ የተሰኙ ኢመድበኛ የወጣቶች ቡድን በማይካድራ በፈፀሙት ማንነትን መሰረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋ በወቅቱ ከ600 በላይ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን በኢንተርፖል የሽብር ወንጀል መከላከል ዳይሬክቶሬት ያወጣው መረጃ አረጋግጧል።
ከሶስት ወራት በፊት በህዳር ወር ላይ ብቻ በተፈፀሙ የሽብር ወንጀሎች አፍሪካ ቀዳሚ ስፍራ ላይ መቀመጧን የጠቀሰው የኢንተርፖል መረጃ ንፁሃን ላይ ባነጣጠሩ የጅምላ ግድያ ወንጀሎች በርካታ ህይወት መቀጠፉን አስገንዝቧል።
የሽብር ቡድኖቹ ከሰብዓዊ ፍጡር በማይጠበቅ መልኩ ጭካኔ የተሞላባቸውን የጅምላ ጭፍጨፋዎች መፈፃማቸው የተገለፀ ሲሆን ከአፍሪካ በመቀጠል ደቡባዊ የእስያ አካባቢና ምስራቃዊ የሜዲትራኒያን ቀጠና የዚህ ሽብር ወንጀል ሰለባ መሆናቸው ተጠቁሟል።
ይህ ቡድን የትሕነግን ሽንፈት ተከትሎ ወደ ሱዳን ማምራቱ፣ የሚመራቸው መሪ እንዳላቸው፣ በህጋዊ የተመድ የስደት ጣቢያ ውስጥ ሆኖ ስልጠናና ሎጂስቲክ እንደሚሟላለት፣ ግብጽ በከፍተኛ ደረጃ በሱዳን መንግስት በኩል ድጋፉና እንደምትሰጠ፣ ቁጥራቸውም እስከ አስር ሺህ እንደሚደርስ፣ አንዳንዶች አምስት ሺህ ይላሉ፣ ራሳቸውን ትሕነግ በተለያዩ ጊዜያት በሞከራቸው መልሶ ማጥቃቶች ከሱዳን በኩል ሆነ የራሳቸውን የቤት ስራ የሰሩ ስለምሆናቸው ለተለያዩ መገናኛዎች ምስክርነት የሰጡ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። ተመድ በሱዳን የስደተኞች መጠለያ ወታደራዊ ምልመላ ይደረግ እንደነበረ መረጃው ጠቅሶ ይፋ ተናግሯል። ይህን ዜና ቢቢሲ ጭመሮ በርክታ በውጭ መንግስት የሚደገፉ የአማርኛ የዜና አውታሮች እያመማቸውም ቢሆን አስተላልፈውታል።
“የማይካድራ ጭፍጨፋ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ሰብዓዊ፣ ስነልቦናዊ ቀውስና ጥልቅ ሀዘን ያስከተለ ነው” ዶ/ር ዳንኤል የገለጹት የተለያዩ ኢሰብዓዊ ዓላማዎችን ይዘው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች በንፁሃን ላይ የሚፈፅሟቸው ግድያዎች አሳሳቢ መሆናቸው በመረጃ መረጋገጡን በማመልከት ነው።
ጎልጉል በሚል ኢንተርፖል ጠቅሶ እንዳለው በወቅቱ የንፁሃንን ህይወት የቀጠፉ የሽብር ወንጀሎች ከተፈፀሙባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን፣ ናይጄሪያን፣ ሞዛምቢክን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን፣ ሶማሊያን፣ ቡርኪናፋሶንና ቻድን የያዘችውን አፍሪካን በቀዳሚነት ጠቅሷል።
ከሌሎች የአለም ክፍሎች ደግሞ ከደቡብ እስያ አፍጋኒስታን፣ ከምስራቅ ሜዲትራኒያን ሶሪያን እንዲሁም ኢንዶኔዥያንና ኦስትሪያን አካቷል።
የሽብር ቡድኖ ቹ በእነዚህ ሀገራት በፈፀሟቸው አሰቃቂ የጅምላ ግድያዎች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በኅዳር ወር 2020 ዓ.ም ብቻ አንድ ሺ የሚጠጉ ንፁሃን ዜጎች መገደላቸውን ኢንተርፖል ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።
ኢንተርፖል ያሰባሰበው የመረጃው ግኝት እንደሚያሳየው መንግሥታዊ ባልሆኑ ታጣቂ ቡድኖች ከተፈፀሙ ጥቃቶች አራቱና በከፍተኛ ሁኔታ የንፁሃንን ህይወት የቀጠፉ የሽብርተኝነት ወንጀሎች በአፍሪካ፣ በደቡብ እስያ (በዋናነት በአፍጋኒስታን) በባህረ ሰላጤ አካባቢ ሀገራት በዋነኝነት በየመንና በምስራቅ ሚዲትራኒያን (በሶሪያ) የተፈፀሙ መሆናቸውንም አመላክቷል።
ይህ ሁሉ ማስረጃ ትሕነግና በሥሩ ባሉት የታጠቁ ኃይላት ታጅቦ እመራዋለሁ ለሚለው ክፍለ ሃገሩና ለአካባቢው ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን በግልጽ ተሰንዶ የተቀመጠ ቢሆንም ትሕነግ “አንድም ታጣቂ የለኝም” ቢል ማንን እንመን? ያየነውን፣ የሰማነውን፣ የዳሰስነውንና ኖረን የተለማመድነውን ክስተት ወይስ በማያቋርጥ ውሸት እና ማጭበርበር የተካነውን?
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Tesfa says
በቅርብ ቀን ለስፓርት ወጣ ብዬ አንዲት ኮረዳ ጡቶቿን ያለ ቅጥ ገላልጣ ትሮጣለች። መቸም አይን ከማየት ጀሮ ከመስማት አይከለከሉምና ልጅቷን ሳያት አንድ የእውቁ ኢትዮጵያዊ ተሰማ እሸቴ ቅኔ ወደ ልቤ መጣና ራሴን አሳቀኝ። እንዲህ ይላል።
ይኸው ደረትሽ ነው ያጣላው ሰውን
እስኪ ሸፈን አርጊው ያጡት እንደሆን።
ለነገሩ ዛሬ ላይ ጾታ የለኝም ከሚሉ እብዶች ጋር አብረን ስለምንተራመስ ቁሞ ይሽና ተቀምጣ የምናውቀው የለም። ወደ ፍሬ ሃሳቡ ስመለስ ወያኔ ጦር የለኝም ቢል ለዜና የሚበቃ አይደለም። በዘመናቸው እውነትን አያውቋትምና! ግን ወያኔ ለሶስት ሆነ ለአራት ተከፈለ እያሉ የሚያናፍሱ ሁሉ ወያኔ ተከፋፍሎ መኖር አያውቅም። የተለዬ ሃሳብ ይዞ አብሮ መዝለቅ ጭራሽ አይፈቅድም። ለዚህ ነው የፕሪቶሪያው ስምምነት እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ ያልሆነው። ገና ብዙ ጉድ እንሰማለን እንያለን። በተለይ በሱዳን ጦርነት በእውነትም እጃቸውን ከተው ከሆነ ለአሁኑና ለመጭው የሱዳን ኢትዮጵያ ግንኙነት አስከፊ ሁኔታን ይፈጥራል። ግራም ነፈሰ ቀኝ ወያኔ እንደ እሳት ራት እሳት ካለበት አይጠፋምና ጊዜ እውነቱን ይነግረናል። ሃበሻን የቸገረው የሰላም እጦት እንጂ ጦርኛ መቼ ከምድሪቱ ጠፍቶ ያውቃል። ሁሌ መናኮር ነው። ሁሌ ተንኮልና ሴራ ነው። ለሰላም እንስራ! ወያኔና የብሄር ሰካራሞችን እንርሳ!