ዛሬ በስልጣን ላይ ያለው ጉደኛ ቡድን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በየጊዜው ቅርጹንም ሆነ ይዘቱን ሲቀያይር መኖሩን መስራቾቹ ነግረውናል። አንዳንዱን እያየንም ታዝበናል። ከመገለጫዎቹ ጥቂቶቹ አንባገነንነት፣ ገዳይነት፣ አፋኝነትና ጠባብነት ወይም ዘረኝነት እንዲሁም ጥላቻ ናቸው።
ከዚህ ጥቅል ተፈጥሮው ሌላ ስልጣን ከያዘም ጊዜ ጀምሮ የሚታዩበት ግልፅ ባህርያት አሉ። አንደኛው እውነታን መካድ ወይም አለመቀበል ነው። አይኑ ስር ያለውን ግልፅ እውነታ አይቀበለም። በተለይ ተቃውሞ ወይም ውድቀት ወይም የሃሳብ ልዩነት ከሆነ በጭራሽ አይደራደርም። አዘውትሮ የሚጠቀምበት አሰልች ስልት ለእውነታው ወይም ለችግሩ ሃሰተኛ ባለቤት መፈለግ ነው። ይህም ተቃዋሚ ፓርቲ፣ አክራሪ ቡድን፣ ፀረሰላም ሃይል፣ ፀረልማት፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል። እንዴት ያለ በሽታ ነው ጃል! ትክክለኛውን ህመም ለይቶ ትክክለኛ መድሃኒት ከመፈለግ ይልቅ ያለምክንያቱ ምክንያት መፈለግ።
ሁለተኛ መለያ ባህሪው ደግሞ እንቢተኝነት ነው። ኢህአዴግ ግትር ነው። እየተሸነፈ አሸናፊነቱን አያምንም። እየወደቀ አለሁ ይላል። እየጠፋ መልማቱን ይሰብካል።
ውድቀቱን እየጣለ ስኬቱን ብቻ ያወራል። የሚያሳዝነው ታዲያ የሚወድቀው ብቻውን ሳይሆን ከሃገር ጋር መሆኑ ነው። ብቻውን ቢወድቅ ኖሮ የእጁን አገኘ ማለት ብቻ ይበቃ ነበር።
ሌላው ጠባዩ ጥላቻና ቅራኔ ነው። ልዩነት የህልውናው መሰረት ነው። የሚፈልገው ልዩነት ብቻ ሳይሆን ጥላቻን የሚወልድ ልዩነት። የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነቱ ሳይሆን በልዩነቱ እንዲታወቅ ይፈልጋል። ብሄር ብሄረሰቦች የሚላቸው ቡድኖች እንዲስማሙ አይፈልግም። ፍቅራቸውን የሞት ያህል ይፈራዋል። እነርሱ ሲጣሉ ሽማግሌ ሆኖ በበላይነት መኖር ይፈልጋልና እነርሱ መስማማት የለባቸውም። ያሁኑ የአማራና ዖሮሞ በበለጠ መቀራረብ እንቅልፍ የነሳውም በዚህ ባህሪው ምክንያት ነው።
የመጨረሻውና እጅግ አደገኛው ባህሪው ሃገሪቱን በራሱ ያገዛዝ ዘይቤ ራሱ ነግሶ ለመኖር የሚያሳየው ቅዠት ነው። ለኢህአዴግ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊነት ውጭ ሃይማኖት የለም። ከልማታዊ መንግስት ውጪ አማራጭ ከንቱ ነው። ለኢትዮጵያ ከጎሳ ፌደራሊዝም በላይ ላሳር ነው። በጥቅሉ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ችግር መፍትሄው የኢህአዴግ አስተሳሰብና የኢህአዴግ ዘለአለማዊ አገዛዝ ነው። ታዲያ ከዚህ በላይ ጨርቅን ጥሎ ማበድ የት አለ ጎበዝ?
በመጨረሻም ለኢህአዴግና የሃገሬ ሰዎች ምክር ብጤ አለኝ።
በመጀመሪያ ለኢህአዴግ፣
ኢህአዴግ፣ እባክህ አስተሳሰብህም ሆነ አገዛዝህ ፎርሿልና ንቃ። የኢትዮጵያ ወቅታዊ ችግር ለዘለቄታዊ የሚፈታው በማን አለብኝነት፣ በትእቢት፣ በእብሪትና ፉከራ ሳይሆን ባስተዋይነት፣ በሆደሰፊነት፣ በምክክርና በፍቅር ነው። ይህን ሳትገነዘብ ቀርተህ በያዝከው የጥፋት ጎዳና ዘመቻህን እቀጥላለሁ የምትል ከሆነ ግን መጨረሻህ እንጦረጦስ ባይሆን ከምላሴ ጸጉር!
ያገሬ ሰዎች፣ ተቃዋሚ ሃይላትና ዳያስፖራ፣
ይህን የታሪክ አጋጣሚ የኢትዮጵያን ህዝብ ያንድነት ጎጆ እንደገና አሳምረን ለመስራት እንጠቀምበት። የህዝብን አንድነት የሚያውክና ለቡድናዊ ጥቅም ካልሆነ በቀር ለህዝብ የማይጠቅም ጥላቻን በመዝራት ለኢህአዴግ ላገርና ህዝብ መምቻ ዱላ አናቀብለው። አሁን የሚታየውን የመቀራረብ መንፈስ አበልፅጋችሁ ቀጥሉ። የችግራችን መፍትሄው ፍቅር ነው። ከተቀራረብንና በሰለጠነ መንገድ ከተወያየን የተበላሸውን ጠግነን የጎደለውን ሞልተን ህዝብ የሚኮራባት ሃገረ ኢትዮጵያን መፍጠር የማንችልበት ምንም ምክንያት የለም። እናም ተባበሩ! ልዩነትን ጤንነት እንጂ በሽታ አታድርጉት። ይህ ወቅት የፍትህና ዴሞክራሲ አንባ የሆነች ታላቋን ኢትዮጵያ የምንፈጥርበት አጋጣሚ ነውና ሁላችንም እናስተውል።
ቸር ይግጠመን
ህሩይ ደምሴ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
Leave a Reply