ልዩነትን አድንቅ
አንድነትን አድምቅ
እንቆቅልሽ ፍታ
ጥላቻ ይረታ
ሁሉም ብሔረሰብ
ነውና ቤተሰብ
“እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለት ተውክ አማራ
ምንም እንኳን በአገር መንፈስህ ቢኮራ
“እኔ ኦሮሞ ነኝ” ማለት ተውክ ኦሮሞ
ምንም እንኳን ጥሪህ ሁሎ ቢያድር ከርሞ
“ኢትዮጵያዊ አማራ” ሆነህ ስትሄድ
“ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ” አገኘህ መንገድ
የልብ ትርታ ሲወጣ ገሃድ
ብለው ሲጠብቁ እሳትና ጭድ
ፍቅር ጣልቃ ገብቶ አደረገ ጉድ
የፍቅር ብልሃቱ
ግርም ማሰኘቱ
አንቺዬ ድንቅ አገር ኢትዮጵያ የሚሉሽ
ትግሬና ሶማሌ ደቡብን የያዝሽ
ጉራጌ ጋምቤላ አፋርን ያቀፍሽ
ስንቱን ልጠራ ነው በዙ ልጆችሽ
ነግሩ ሲጠራ
እንዲሁም ሲጣራ
እኩልነት ሰፍኖ
ፍቅርም ልቆ ገኖ
ኦሮሞ አማራ ማለቱ ይረሳና
ኢትዮጵያዊ ነኝም ማለት ይቀርና
ከአሁን ማንነትህ አድገህ ተመንድገህ
አፍሪካዊነትን ከሁሉ አብልጠህ
ለጥቁሩ ሕዝብህ ፋና ወጊ ሆነህ
እውነቱን እወቀው ታሪክ ትሰራለህ
እምዬ ኢትዮጵያ ፍቅር ሳያንስሽ
ልዩነት መርገምሽ ግራ አጋብቶሽ
የማታ የማታ መላው ቢጠፋሽ
ልጆቼ አድኑኝ ብለሽ ተማፀንሽ
መርገሙ ልዩነት ሞቶ ተቀበረ
ፍቅር ነፍስ ዘርቶበት ታሪክ ተቀየረ
ልዩነት በረከት ሆነና ከበረ
ልዮነት በጎ ነው ህብረ ብሔር ያብብ
ማህተቡ ሆኖ አንድ ሕዝብ በአንድ ልብ
መቸ መሽቶ ቀረ ነጋልሽ ለሊቱ
የሚገርም ነገር ነው የፍቅር ብልሃቱ
(ግጥሙን በድምጽ ለመስማት እዚህ ላይ ይጫኑ)
Leave a Reply