የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ጸጋ ቅዳሜ ሐምሌ 5፤ 2012 ከፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጋር በሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ የሃጫሉ ሁንዴሣ ግድያን አስመልክቶ የተቀናበረውን ድራማ አስረድተዋል። የድራማውን ጸሐፍትና የድራማ ትወናቸውንም በዝርዝር ተናግረዋል።
ቃታ ሳቢው ጥላሁን (ተኳሽ)
“የአርቲስቱ ግድያ ግብ ነበረው” ያሉት አቶ ፍቃዱ ጸጋ “አርቲስቱ የግድያ ዛቻ ይደርስበት እንደነበር ለጓደኞቹ ተናግሯል” ብለዋል። ወደ ግድያው አፈጻጸም ዝርዝር ትንታኔ በመግባትም ገዳዩ ጥላሁን ያሚ በሚኖርበት የገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ሁለት የማያቃቸው ሰዎች ስሙን ጠርተው እንዳናገሩት ራሱ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል አስረድቷል። ይህንን የእምነት ክህደት ቃል የሰጠውም ሕገመንግሥታዊና የወንጀል ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መብትና ግዴታው ተነግሮት በራሱ ፈቃድ መሆኑን አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል።
ጥላሁንን ቀርበው ካናገሩት ሰዎች አንዱ ገመቹ እባላለሁ ያለው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የህወሓት ታጋይ መሆኑን ነግሮታል። ግለሰቦቹም የነገሩት ነገር አገሪቷ እየፈረሰች እንደሆነ፤ በዚህም ምክንያት የኦሮሞ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር እንደሚጋለጥ፤ ይህንን መታደግ እንደሚገባ፤ እርሱ ቆራጥና የተሰጠውን ተልዕኮ በመፈጸም ጎበዝ ልጅ መሆኑን አውቀው እንደመለመሉት፤ አሁን የሚሰጠውን ተልዕኮ ከፈጸመ ለኦሮሞ ሕዝብ ትልቅ ውለታ እንደሚፈጽም፤ ለራሱም ሕይወቱን የሚቀይርና ቤተሰቡን የሚጠቅም ነገር እንደሚያተርፍ፤ በጉዳዩ ላይ አስቦበት በሚቀጥለው ውሳኔውን እንዲያሳውቃቸው ተነጋግረው ተለያይተዋል።
ጥላሁን በወቅቱ ስልኩን ሊሰጣቸው ሲል እንዲህ ዓይነት ጉዳይ በስልክ ማለቅ እንደማይችል፤ ነገርግን እነርሱ ራሳቸው በድጋሚ መጥተው እንደሚያገኙት፤ እነርሱ የዚያ አካባቢ ኃላፊዎች መሆናቸውን መግለጻቸውን አቶ ፍቃዱ በጋዜጣዊ መግለጫቸው አስረድተዋል።
በሁለተኛው ግንኙነት ወቅት ጥላሁን ተልዕኮውን መፈጸም ለራሱና የሚጠቅም ከሆነና የኦሮሞን ሕዝብ የሚታደግ ከሆነ መስማማቱን ከገለጸ በኋላ ተልዕኮ እንደሚሰጠውና ለዚያም እንዲዘጋጅ እንደተነገረው፤ እርምጃ የሚወሰድበት ሰው እንዳለ፤ ይህ የመጀመሪያው ኦፐሬሽን እንደሚሆን፤ ሌሎችም ተልዕኮዎችን እንደሚሰጡት፤ ለዚህኛው እንዲዘጋጅ ተነገረው።
ዕርምጃ የሚወሰድበትን ሰው ማንነት እንዳልተነገረው፤ ነገርግን በዕለቱ እርምጃውን እንዴትና በማን ላይ እንደሚወስድ እንደተነገረው አስረድቷል። አቶ ፍቃዱ እንደሚሉት ይህ ዓይነቱ አሠራር በኦነግ ሸኔ የተለመደ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በኦነግ ሸኔ ላይ በከፈታቸው የክስ ፋይሎች በተመሳሳይ እርምጃ የሚወሰድባቸው ሰዎች እንደማይገለጹ፤ ነገርግን የመለያ ምልክቶች እንደሚሰጡ፤ የመኪና ታርጋ፣ የቤት አድራሻ የመሳሰሉ ብቻ እንደሚነገሩ፤ ይህም የሚሆነው እርምጃ ወሳጁ እርምጃ የሚወሰድበትን ግለሰብ ካወቀ ሊከራከርና ሃሳቡን ሊቀይር ይችላል በሚል እንደሆነ አቶ ፈቃዱ ጸጋ ተናግረዋል።
ጥላሁን በሦስተኛው ግንኙነቱ ወቅት ለተልዕኮው እንዲዘጋጅ እንደተነገረው፤ ሰዎቹ በዚህ ሁሉ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ በኦሮምኛ እንደነበር፤ እርስበርሳቸው ሲነጋገሩ ግን በትግርኛ እንደሆነ፤ በሦስቱም ግንኙነቱ ወቅት ገንዘብ እንደተሰጠው፤ ዋናውና ጠቀም ያለው ብር ደግሞ ተልዕኮውን ከፈጸመ በኋላ እንደሚሰጠው አስረድቷል።
ጥላሁን ለዚህ ተልዕኮ የተመለመለው ዒላማውን በአግባቡ ሊመታ የሚችልና የማይስት በመሆኑ፤ በአንድ ጥይት ነገሮችን ሊያከናውን እንደሚችል፤ ይህንንም መሠረት በማድረግ ሃጫሉን በተነገረው ቦታ በሚያገኘው ጊዜ በአንድ ጥይት ብቻ ተኩሶ እንደገደለው፤ ሃጫሉ በወቅቱ ወዲያው የሕክምና ዕርዳታ ቢደረግለት እንኳን ሊድን እንደማይችል የህክምናው ማስረጃ እንደሚያረጋግጥ፤ ይህም ማለት በወቅቱ ሳምባው፣ ልቡና ጉበቱ እንደተጎዳ፤ የተገደለበት ጥይትና ቀለሃ እዚያው እንደተገኘ፤ ሃጫሉ ከመገደሉ በፊት ራሱን ለመከላከል በሚመስል መልኩ መኪናው ወንበር ሥር ጎንበስ ብሎ እንደነበር፤ ነገርግን ከዚያ በፊት እንደተቀደመ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል።
ከዚህ ወንጀል ጋር በመጠርጠር የተያዘችው ናርዶስ ለብዙ ክትትሎች የሚሆኑ መረጃዎችን እንደሰጠች፤ የተኮሰውንም ልጅ ብታየው እንደምታውቀው፤ ባየችውም ጊዜ በትክክል እንዳረጋገጠች፤ ሌሎችንም በርካታ መረጃዎችን እየሰጠች እንደሆነች፤ ከገዳዮቹ ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠና እንደሆነ፤ የእርሷም ጉዳይ ወደፊት በፍርድቤት የሚታይ እንደሆነ በመግለጫው ተነግሯል።
ኦኤምኤን እና ቃለምልልሱ
አርቲስት ሃጫሉ ከመገደሉ ጥቂት ቀናት በፊት ከኦኤምኤን ጋር ቃለምልልስ ማድረጉን፤ ዐቃቤ ሕግ ሙሉው ቃለምልልስ በእጁ እንደገባ፤ በኦኤምኤን ለሕዝብ የቀረበው 47 ደቂቃ ብቻ ሲሆን ሙሉው ግን 1 ሰዓት ከ11 ደቂቃ እንደሆነ፤ ሃጫሉ ከኦነግ ሸኔ ይደርስብኛል በማለት በተደጋጋሚ የተናገረው የግድያ ማስፈራሪያ ከቃለምልልሱ እንደተቆረጠ፤ በቃለ ምልልሱ ሃጫሉን ከአንድ ማኅበረሰብ ጋር እንዲጋጭ የሚያደርግ ጥያቄዎች ይጠየቅ እንደነበር፤ ለውጥ እንደመጣ፣ ለውጡን መደገፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን፣ አብሮ መቆም እንደሚያስፈልግ ደጋግሞ የተናገረው ለሕዝብ በተላለፈው ቃለምልልስ እንደተቆረጠ፤ ይህ የኦኤምኤን ዓላማ ጥያቄ እንደሚያጭር፤ ወሳኝ የሆኑት ሁለት ጉዳዮች በተለይ የግድያ ዛቻው መቆረጡ ኦኤምኤን ከኦነግ ሸኔ ጋር ስለሚሠራ ይሆን የሚል ጥያቄ እንዲጠየቅ የሚያደርግ መሆኑ፤ ቃለምልልሱ በዓላማ የተቀነባበረ ስለመሆኑ ብዙ ጥያቄዎችን ማስነሳቱን የመምሪያ ኃላፊው አብራርተዋል።
አስተኳሾቹና የተውኔቱ ጸሐፍት
አርቲስት ሃጫሉ ለኦኤምኤን ቃለመጠይቅ ካደረገ በኋላ ግልጽ የሆነ ዛቻና ስድቦች ይደርሱት እንደነበር፤ በቴሌግራም በጽሁፍና በድምፅ ጭምር ዛቻው ይደርሰው እንደነበር፤ “በኦኤምኤን የሰጠኸውን ኢንተርቪው አይቻለሁ፤ ምላስህ ያንን ያህል የመርዘሙን ያህል የምንሠራልህ ይሆናል” የሚል መልዕክት እንደደረሰው፤ ይህንንም ለጓደኞቹ መናገሩን፤ የፎረንሲክ ምርመራው ከስልክ የተገኘው መረጃ ይህንኑ እንደሚረጋግጥ፤ በተለይ ኩምሣ ፖሴና ዕምሩ እባላለሁ በማለት ራሱን ያስተዋወቀው ልጅ በቴሌግራም ልታወራኝ የምትፈልግ ከሆነ ስልኬ ይኸው በማለት እንደሰጠው፤ የወቦ ማለትም “የወራን ቢሊሱማ ኡመተ ኦሮሞ” አባል መሆኑን እንደገለጸለት፤ ይህም የኦነግ ሸኔ የሚሊታሪ ክንፍ እንደሆነ፤ ኩምሣ የምዕራቡ ክፍል አስተባባሪ መሆኑን እንደገለጸለት፤ መረጃው በእርግጥ ከምዕራብ ወለጋ አካባቢ የተላከ መረጃ መሆኑንና ሌሎችንም ማስረጃዎች በጥናት መረጋገጣቸውን፤ ሙሉውን ቃለምልልስ ሳይሰማ ይህንን እንዴት ለማለት እንደቻለ እየተጠና እንደሆነ፤ ሌሎችም ዛቻዎች አብረው እንደተገኙ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ተናረዋል።
በቀለ ገርባ የአርቲስት ሃጫሉ አስከሬን ወደ አምቦ እየሄደ ባበለት ጊዜ ቡራዩ ለሚገኙ ስልክ በመደወል መመሪያ መስጠቱን፤ አስከሬኑን በፈለጉበት መቅበር የመጨረሻው ወሳኞች ቤተሰቡ መሆናቸው እየታወቀ በቀለ ግን አስከሬኑ ከቡራዩ እንዳያልፍ መመሪያ እንደሰጠ፤ አስከሬኑ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ፤ በአዲስ አበባ ለ10 ቀናት ለቅሶ እንደሚደረግ፤ ቀጥሎም እዚሁ አዲስ አበባ እንደሚቀበር ትዕዛዝ ማስተላለፉን፤ ጃዋር መሐመድ ደግሞ ወደ ቡራዩ ይዞት በሄደው መኪና የታጠቁ የጥበቃ ሰዎች አብረውት እንደነበሩ፤ ከመኪናው ውስጥ ጥበቃዎቹ ይተኩሱ እንደነበር፤ የአስከሬኑን መኪና ካስቆሙት በኋላ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስና “እኛ ተከተል” የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጠ፤ ቀጥሎም አስከሬኑን ይዘው የኦሮሚያ ብልጽግና ጽ/ቤት እንደመጡና በኃይል ጥሰው እንደገቡ ከዓይን ምስክሮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክት አቶ ፍቃዱ አብራርተዋል።
በቀለ ገርባ ቡራዩ ከሰጠው መመሪያ በተጨማሪ ሻሸመኔ በመደወል “ልንታሠር ነው፤ ቄሮ አመጹን ይቀጥል፤ አቀጣጥሉት” የሚል መረጃ መስጠቱን በፎረንሲክ መረጋገጡን፤ ሻሸመኔና ምዕራብ አርሲ የተፈጸሙት ግድያዎችና ወንጀሎች ከዚህ በኋላ መከሰታቸውን፤ አንዳንድ ቦታዎች ደግሞ የሃጫሉ መሞት ገና ሳይሰማ ዝርፊያ፣ ግድያ፣ ንብረት ማውደም እንደተፈጸመ፤ ይህም አስቀድሞ የታቀደ ተልዕኮ ይሆናል የሚል ፍንጭ እንደሰጠ በጋዜጣዊ መግለጫው ተወስቷል።
እስክንድር ነጋ እና የባልደራስ አባላት “ቄሮ እየመጣልህ ነው፤ ቤተክርስቲያንን ሊያቃጥል ነው” በማለት ገንዘብ በማደልና በማደራጀት ሰኔ 23 እና 24 ዓመጽ እየቀሰቀሱ እንደነበር፤ ይህንንም የቀረቡ የሰው ምስክሮች እንዳረጋገጡ፤ በተለይ ሰኔ 24 ቀን ምሽቱን ቤ/ክ የሚያቃጥሉ መጡ የሚለው የሽብር መረጃ ራስን ከመከላከል ባለፈ መልኩ ቅስቀሳ ሲካሄድ እንደነበር፤ መሃል ከተማ ጨምሮ የአካባቢው ኅብረተሰብ ሲራወጥ ማደሩን፤ ይህ ሁሉ ሥራ ገንዘብ በማከፋፈል ይካሄድ አንደነበር፤ ይህንንም እንዲያስፈጽሙ ተልዕኮ የተሰጣቸው ወጣቶች እንደነበሩ፤ በተለይ “ራስህን ተከላከል” የሚለውን የሰኔ 24ቱን ቅስቀሳ ተከትሎ በርካታ ሰዎች እንደሞቱ፤ ይህ ሃሰተኛ መረጃ ከዚህ ቡድን የመጣ ስለመሆኑ ምስክሮች ቀርበው መናገራቸውን የድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ፀጋ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት አስረድተዋል።
ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት የተመራና ገና የሚቀሩ በርካታ ምርምሮች የሚቀጥሉ በመሆናቸው ላሁኑ የሚበቃ መረጃ ለሕዝቡ ማሳወቅ ተገቢ መሆኑ በወቅቱ ተነግሯል። ከዚህ በተጨማሪም ሕዝቡ ያሳየው ትብብር አስደናቂ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን አንዳንድ ወላጆችም ልጆቻቸውን ለሕግ አሳልፈው መስጠታቸው በጋዜጣዊው መግለጫ ተወስቷል። አቶ ፍቃዱ እንዳሉት ይህ መረጃ የወጣው የፍርድ ሥርዓቱን በማያዛባ ሁኔታ አግባብ ባለው መልኩ መሆኑን አስታውቀዋል።
የመግለጫው ሙሉ ቪዲዮ ከዚህ በታች ቀርቧል
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ ንብረት ናቸው። ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን።
unwanted comment says
Who is in the main picture? And is implicitly accusing Eskender? Because the title implies he was an accomplice in the killing of Hchaloo. But he is charged with ‘exaggrated’ self defence – what ever that means. As for you this shows your mind set and the extent you go in the name of journalism. Grow up golgule.