“…ከዚህ በኋላ ህዝብ ሰብስቦ ማውራት ላቆም ነው። ጊዜው ተቀይሯል። ትግል ለደካማ መንፈስ አይሆንም። ትግል መውደቅን ይጠይቃል። ሲወድቁ ግን ለመነሳት መሞከርን ይጠይቃል። ስንወድቅ ልታዩን ትችላላችሁ ስንነሳ ግን ታዩናላችሁ … ” ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ይህንን የተናገሩት የአስመራ ጉዟቸው ከመሰማቱ ጥቂት ቀናት በፊት ነበር። ንግግሩ ለብዙዎች ግርታ መፍጠሩ አልቀረም። ከቀናት በኋላ የኤርትራን ምድር ሲረግጡ “ስንነሳ ግን ታዩናላችሁ…” ማለታቸው ግልጽ ሆነ።
ከምርጫ 97 በፊት ዶ/ር ብርሃኑ በፖለቲካ ስብእናቸው የሚታወቁት ለሰላማዊ ትግል ባላቸው የከረረ አቋም ነበር። በእስር ቤት ሆነው በጻፉት “የነጻነት ጎሕ ሲቀድ፤ …” መጽሐፋቸው ሰላማዊ ትግል ያለውን የሞራል፣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ የበላይነት ምሳሌ እያስቀመጡ ዘርዝረዋል።
ለዚህም ነበር ከሰላማዊ ትግል ወጥተው “ሁለገብ ትግል” ለማካሄድ ማቀዳቸውን ሲገልጹ ለብዙዎች ድንገተኛ እና አስደንጋጭ የሆነው። የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ሲነግሩን የነበሩ እኝህ ምሁር በአንድ ግዜ ወደ ተቃራኒው የትግል ስልት ሲዞሩ ያቀርቡት የነበረው ምክንያት በወቅቱ ብዙዎችን ሊያሳምን አልቻለም። ምክንያቱም አመጽ ወይንም ጦርነት ከባድ ነገር ነው። ገንዘብ እና ግዜን ይበላል። ከሁሉም በላይ የህይወት መስዋእነትን ይጠይቃል። የሰላማዊ ትግሉ ስልቶች ገና በደንብ አልተፈተሹም የሚሉም ጥቂቶች አልነበሩም።
ከአምስት ግዜ ምርጫ በኋላም ህወሃት ሕዝብ ላይ መቀለዱን አላቆመም። በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትንም ጭራሽ ወደ ጫካ እንዲገቡ፣ አልያም እንዲሰደዱ አማራጭ መስጠት ያዙ። የትጥቁን መንገድ “ጨርቅ ያርግላችሁ” ሲሉም አሾፉ።
የ”ምርጫ 2007″ ውጤት በተሰማ ማዕግስት ከዴንቨር-ኰሎራዶ አንድ የቀድሞ ህወሃት ታጋይ ስልኬ ላይ ደውሎ እንዲህ አለኝ። “ግዜው የኛ ነው። ገና መቶ አመት እንገዛችኋለን። ታዲያ ስንገዘችሁ ዝም ብለን አይደለም። እየረገጥን እንገዛችኋለን…” ሰውየው እኔ እንድናገር እንኳን እድል አልሰጠኝም። ስለምርጫው ውጤት በድረ-ገጾች ላይ የሰጠሁት አስተያየት እንዳበሳጨው ገባኝ። በትግርኛ እና በአማርኛ እያቀላቀለ ተሳደበ። ዘር እና ሃይማኖትን ጭምር እየጠራ ተሳደበ። በትእቢት የተወጠረው ይህ ሰው ሙሉ ስሙን እና አድራሻውን ሳይቀር ይናገር ነበር። “ከፈለግክ ቅዳኝ። ማንንም አንፈራም!” ይል ነበር። እርግጥም ድምጹ በቴሌፎኔ መቅጃ ሳጥን ውስጥ ቀርቷል። ይህንን አጸያፊ ስድብ መልቀቁ ወገን ከወገን ማጋደል ይሆናል በሚል እሳቤም ለግዜው ይዤዋለሁ።
ማንነትን የሚፈታተን፣ ክብርን የሚነካ ንግግር ነው። ስድቡን ሁሉ በትእግስት ከሰማሁ በኋላ አንድ ቃል ብቻ ተናግሬ ስልኩን ዘጋሁት። “ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለች።”
የያዝኩትን ትንሽ መረጃ በመንተራስ ስለሰውየው ማንነት አንዳንድ ነገር ማወቅ ቻልኩ። ሰባት አመት የህወሃት ትግል ውስጥ የነበረ ሰው ነው። ይህ ግለሰብ ዴንቨር ኮሎራዶ ከአመታት በፊት ሲገባ ባዶ እጁን ነበር። አሁን ግን ሚሊየነር ሆኗል። የህወሃትን የተዘረፈ ገንዘብ በዶላር ለማጽዳት ወደ ዴንቨር የሚላኩ ሰዎች ቀጥር ቀላል አይደለም። እየረገጥን ገዝተን፣ እየረገጥን እንዘርፋለን፣ ይህንንም አሜን ብላችሁ ተቀበሉ ነው የሚሉን። ከባዶ ተነስተው መጠን የሌለው ስልጣን እና ገንዘብ ሲያካብቱ፤ በያዙት ነገር ይታወራሉ። ድንቁርና ሲታከልበት ደግሞ ስልጣናቸው ዘለአለማዊ፣ ሃብታቸውም የማያልቅ ይመስላቸዋል።
እንደዚህ አይነቶች ወንድነትን እና የሃገርን ክብር የሚፈታተኑ ነገሮች ተቆጥረው አያልቁም። ተሳፋሪዎችን ይዞ እየበረረ ያለ የአየር መንገድ አውሮፕላን በአንድ ካድሬ ትዕዛዝ እንዲመለስ የሚደረግባት ሃገር ሆናለች ኢትዮጵያ። ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ያገኘሁት አንድ መረጃ የሚያሳየን ይህንኑ ነው። ከአዲስ አበባ ናይሮቢ-ኬንያ ይጓዝ የነበረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራውን ከጀመረ በኋላ እንዲመለስ መደረጉ እና በዚህም ምክንያት አየር መንገዱ የሁለት መቶ ሺህ ዶላር ኪሳራ ደርሶበታል። ይህ የሆነው ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ አውሮፕላኑ ውስጥ ስለነበር ብቻ ነው። እነዚህ ሰዎች ሃገሪጥዋን የግል ንብረታቸው አድርገዋታል።
በፈለጉ ግዜ፣ የፈለጉትን ያስራሉ። በፈለጉ ግዜ የፈለጉትን ይለቅቃሉ። በእስር ላይ ከሉ 19 ጋዜጠኞች ይልቅ ለአንድ ባእድ መሪ ክብር የሚሰጡ፣ በአልሻባብ ከሚገደልው ሰራዊት ይልቅ ለአሜሪካ ብሄራው ጥቅም የሚጨነቁ የውስጥ ባዕዳን ናቸው ስልጣኑን በሃይል ያየዙት።
20 አመታት በአንድ ርእዮተ-ዓለም፣ በአንድ አገዛዝ፣ በአንድ ሰው አስተሳሰብ መዝለቅ እጅግ እጅግ ይከብዳል። በተለይ ደግሞ በምእራቡ አለም ውስጥ ለሚኖር ሰው ፍጹም የማይታሰብ ነገር ነው። በ97ቱ ግድያ እጅግ ተቆጥቶ የነበረው ሰር ቦብ ጌልዶፍ “መቼ ነው የምታድጉት? እስቲ እደጉ!” ብሏቸው ነበር። አሁንም አላደጉም። አሁንም ሰው እየገደሉ ነው። ለማደግ የምኒሊክ ቤተ-መንግስት ሃያ አመታት መቆየት አያስፈልግም። ለእድገት ለውጥ ያስፈልጋል። የስርዓት ለውጥ፣ የሰው ለውጥ፣ የአስተዳደር ለውጥ፣ የአቅጣጫ ለውጥ፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል።
በርካቶች በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት እጅግ ጣሩ። ጥረታቸው ግን እንደ ደካማነት ተቆጠረባቸው። በያዙት የጦር መሳርያ ብቻ የሚተማመኑ ጉልበተኞች ቀለዱባቸው። የህዝብን ድምጽ እየሰረቁ መቀመጣቸው ሳያንስ መራጩን ሕዝብ እያሳደዱ መበቀል ያዙ። ኢትዮጵያ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ማምጣት ምርጫ ለአምስተኛ ግዜ ተሞከረ። አምስቱም ተጭበረበረ። ከአሁን በኋላ በምርጫ ለውጥ እናመጣለን ብሎ ማሰብ የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንደሆነ የምርጫ 2007ቱ ትዕይንትን ብቻ ማጤኑ ይበቃል። በታሪክ 100% አሸነፍኩ ብሎ የተናገረ አንባገነን መንግስት በኛው ምድር ተፈጠረ። ይህ ሕዝብ ላይ ማፌዝ ነው። ትዕቢት፣ ድፍረት እና ንቀት የተሞላበት ፌዝ። “ምንም አታመጣም!” አይነት ንቀት!
በፖለቲካ አግባብ ጦርነት የዲፕሎማሲ ጣርያ፣ የሰላማዊ ትግል መጨረሻው አማራጭ ነው።
ከዚህ የአገዛዝ ንቀት በኋላ ህዝብ ለአመጽ ቢነሳ ተጠያቂው ያለህዝብ ይሁንታ ስልጣን ላይ ያለው ስርዓት ብቻ ነው። ህዝቡን ወደ ስደት እና ወደማይፈልገው አመጽ እየመሩት ያሉት እነዚያው የስልጣን እና የንዋይ ጥመኞች ናቸው። ይህ ንቀት ከትጥቅ ትግል ጋር ችግር አለብኝ የምንል ወገኖችን እንኳን የሚፈታተን ነገር ነው።
ዶ/ር ብርሃኑ ሲተቹበት የነበረው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ትግሉን ከርቀት መምራት ያለመቻሉ ነገር ነበር። በሻእቢያ ላይ ያለው ጥርጣሬ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ይህ ጉዞ በዶ/ር ብርሃኑ ላይ ይነሳ የነበረውን የሞራል እና የሃላፊነት ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። ለሰራዊቱ የመተማመን፣ ለህዝቡም የመነሳሳት ስሜት ይፈጥራል።
ከ21 ዓመት በላይ ያለ ለውጥ መቀመት በጣም ያሰለቻል። 21 አመት እየረገጡ እና እየዘረፉ መቀመጥ ይበዛል። ኢትዮጵያ ለውጥ ያስፈልጋታል። የኢትዮጵያ ህዝብ ፍትሃዊ ስርዓት ያስፈልገዋል። በሰላማዊው መንገድ ለለውጥ የተሰለፉ ሃይሎች እየታፈኑ፤ እየተሰቃዩ፣ እየተገደሉም ነው። እየተገደሉ የሚገድሉ ሲነሱ “ባንደግፋቸውም አንቃወማቸው” ያለው ማን ነበር?
ለነጻነት ሲባል ራሳቸውን ለመሰዋዕትነት የሚያቀርቡ ወገኖች የሚያምጹት ያለ ምክንያት አይደለም። በሁሉም ውስጥ ቁስል አለ!
Leave a Reply