• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት”

May 21, 2025 01:01 am by Editor Leave a Comment

የዛሬ አምስት ዓመት ግድም ነው። የሚያምሩ ሁለት ሸበቶ እናቶችን ጨምሮ ተገልጋዮች ይበላሉ። ይጠጣሉ። ያነሳቸውን ይጠይቃሉ። የወቅቱ የኢሳት ባልደረቦችም በአንድ ኮርነር ክብ ሰርተው የሚበላወንም የሚጠጣውንም በዓይነት ሤራ እያዋለዱ ይጠዘጥዛሉ። ቨርጂኒያ ዳማ ሆቴል!! 

በድንገት ሁለቱ ሸበቶ ሴቶች ይነሱና እንደ ብራቅ ይጮሃሉ። ክብ ሰርተው የሚመገቡትን የኢሳት የማታ ማታ ኮማንዶዎች እያመለከቱ እሳት ጎርሰው “አፈር ብሉ፣ እምዬ ማሪያም አፈር ታብላችሁ፤ ሕዝብ እያጫረሳችሁ እናንተ እዚህ ሥጋ ትቆርጣላችሁ። ደም ብሉ …. ” እናቶቹ ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው “ያዙኝ ልቀቁኝ” አሉ። ወርውረው ለመማታት ገላጋዮችን ታገሉ። ተለምነው። ተገዝተው …. የገባቸው እናቶች። እንደ እኔ ያልደነዘዙ።

“ሦስትን ወደ አራት” አስገራሚ ትርክት፣ አስገራሚ ሤራ ነው። ሤራው በርካቶችን የሰለበ የህሊና ቆንጨራ ነው፣ ትርክቱ ከአንድ ሰው በቀር የአማራ ምሑራን ማሕበር አባላት ሳይቀር “አሜን” ብለው የገዙት ነው። መግዛት ብቻ ሳይሆን እንደ ማተብ ያጠለቁትና ያለ አንዳች ሃፍረት በየመድረኩ እንደ ወንጌል የሚደጋግሙት ስብከታቸው  ጭምር ነው። ሤራው ባሪያ ስላደረጋቸው ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ባልደረባቸውን ዶክተር አንዱአለም የመሰለ የአገር ሃብት ደጃቸው ላይ ሲበላ እያዩ እንኳን ወደ ቀልባቸው እንዳይመለሱ አድርጓቸዋል። በከፊል የዳኑትን ሰለባዎች ሳይካተቱ ማለቴ ነው። 

“ሦስትን ወደ አራት” የማድረግ ጥበብ ተጸንሶ፣ የተወለደው “አዲስ ትርክት” በሚባለው የፈጠራ ድርሰት ነው። “ሦስትን ወደ አራት” የማድረጉ ትርክት ብዙዎችን እውነትን እንዳይሰሙ፣ ያዩትን እንዳያምኑ አድርጎ በልቷል።እየባላም ነው። ወደፊትም ይበላል። የ “ሦስትን ወደ አራት” የመለወጥና የማሳደግ ትርክት ደራሲና አዋላጆች በራሳቸው አንደበት ሤራቸው “ቅጥፈት ነው፣ ፈጠራ ነው” ብለው አደባባይ ቢመሰክሩም ትርክቱ እጅግ የሰረጸ በመሆኑ፣ የትርክቱ ሰለባዎች ሊቀበሉት ቀርቶ ሊሰሙት አይወዱም። በዚህ ላይ ደግሞ በፕሮፓጋንዳ አገርና ሕዝብን እንዲጠብቅ የተቋቋመው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎትና ዙሪያውን ያሰለፋቸው ሠራዊቶቹ ዱልዱም መሆናቸው ለቅጥፈት ትርክቱ ውሃና ማዳበሪያው ስለሆነለት አደጋው የሚጨምር እንጂ የሚቀዛቀዝ አይመስልም።

የ“ሦስትን ወደ አራት” ትርክት ውልደት ከቨርጂኒያው ዳማ ሆቴል በ360 ስቱዲዮ እስከ አራት ኪሎ 

የ”ሦስትን ወደ አራት” የማሳደግ ትርክት መነሻው ቨርጂኒያ በሚገኘው ዳማ ሆቴል ነው። “ሦስትን ወደ አራት” የማድረግ ትርክት የተወለደው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ሶስት ትልልቅ አመራሮችና በዙሪያቸው የነበሩ የጥበቃ ኃይሎች መገደላቸውን ተከትሎ ነው። በዋናነት አንድ ገዳይ፣ ሶስት ሟቾች ነበሩ። ገዳይ ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ፣ ሟቾች ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ አቶ እዘዝ ዋሴ ሲሆኑ ሶስቱም ከጎንደር ናቸው።

“ሚያዚያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድንገት ባጋጠማቸው ህመም ሆስፒታል ገብተው በህክምና ላይ እያሉ በተወለዱ በ52 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል” የተባለላቸው ኮሚሽነር አበረ አዳሙ “ይሄ ዕብድ ነው የገደላቸው። አሳምነው ዕብድ ነው” በማለት ወዲያውኑ ዝርዝር መረጃ ቢሰጡም ሰሚ አላገኙም። ይልቁኑም ተቀጠቀጡ። ተወገዙ። ተሰደቡ። ከራስ ዓይንና ጆሮ ይልቅ ፈጠራን የሚያምነውና ለሤራ የተማረከው ማህበረሰ የሟች ቤተሰቦችን ክብር፣ ማንነት፣ ሃዘንና ጉዳት ባራከሰ መልኩ ገዳይን አገነነ። “ጀጋዬ” ብሎ ገዳይን ከሟቾች አልቆ አወደሰ። ዛሬ ድረስ ቀጥለውበታል። “መክሬው ነበር። ገዳዩ እሱ ነው። የሚል ምስክርነት የሰጡት ምክትላቸው የነበሩት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞም በገዳይ ስም በተቋቋመ ብርጌድ ውስጥ የሚንቦጫረቁ ሃሳዊ ሆነዋል። 

ወቅቱ ሚዲያዎች የሚሰነጣጠቁበት ነበር። ኢሳት እንደ አሜባ መበጣጠስ ከጀመረ አንስቶ ውስጡ የነበሩት ኮማንዶዎች ተነጣጥለው ስንት ሚዲያ እንደተከፈተ አስሉት፣ በተሰነጠቀ ቁጥር ሌላ ስንጥቅ እየፈጠረ ኢትዮ360 ተወልዷል። በዚህ የመበጣጠስ ሂደት ከተወለዱት የወሬ ዓምዶች አንዱ ኢትዮ 360 “ሦስትን ወደ አራት” ትርክትን ያዋለደው ገና “ደግፉኝ” ብሎ ማስታወቂያ በለጠፈ ቀናት ውስጥ ነው። እኔም የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያቅሜን ጀብቻቸው ነበር። ሳይገባኝ። በዞረብኝ ዘመን!!

ይህ አደገኛ ትርክት ተመርቶ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲረጭ፣ “ትርክቱን ሳያታክቱ ደጋግመው በማቅረብ እውነት አስመስሎ ማስረጽ” በሚለው መርህ “ምሑራን” የሚባሉት ሳይቀሩ ሲሰለቡ የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ጽህፈት ቤት ለሽ ብሎ ነበር። እንቅልፉ ዛሬ ድረስ ያለቀቀው ይኸው ተቋም ” ውሸት ነው፣ ፈጠራ ነው፤ ትርክቱን የፈጠርነው በዚህ ቀን እዚህ ቦታ፣ በስልክ ዶልተን ነው ወዘተ” ተብሎ ሲነገረውም አልነቃም። ዐቢይ አሕመድን ገዳይ ያደረገውን አዲስ ትርክት ታቅፎ “የድሮ ትርክቶችን እናጥራ” በሚል መጽሐፍ ያስመርቃል። ሪባን ይቆርጣል። ማሳሰቢያ ይሰጣል። እንግዳ ይቀበላል። አንድም የልማትም ሆነ የተስፋ ዜና የሌላት ኤርትራ የወሬ ሚኒስትር ብልጫ የሚወስዱበት ተቋም፤ አይ ተቋም።

ከዳማ ሆቴል – የቀጥታ ስርጭት

የቨርጂንያ ዳማ ሆቴል ይታዘባል። እዚሁ ሆቴል ውስጥ አዲስ የተመሠረተው የኢትዮ 360 ሚዲያ አባላት ተሰባስበዋል። “አገልግሎታችንን የምትደግፉ በፔይፓል፣ በቀጥታ በባንክ፣ በዜል (Zelle)፣ በካሽአፕ (CashApp)፣ …ጣል፣ ጣል አድርጉ፣ … በሱፐር ቻት፣ በሱፐር ስቲከር፣ … ደግፉ” የሚለውን የዲጂታል መቀፈያ ለጥፈው፣ ጎፈንድሚ አውጀው ሚዲያው እንዴት እንደሚያዘግም እየመከሩ ነበር። ምን አይነት የሤራ ማከፋፈያ ዓምዶች እንደሚከፈቱ እየዶለቱ ነበር። እንዴት አድርገው ገባያውን እንደሚያደሩት እያቀዱ ነበር ….

ምናላቸው ስማቸው ማናጄር፣ ሃብታሙ አያሌው ኤዲቶሪያል ኃላፊ፣ ልዩ ጸጋዬ፣ ኢየሩሳሌም ተክለጻዲቅ (የምናላቸው ሚስት)፣ ኤርሚያስ ለገሠ፣ ርዕዮት ዓለሙና ተወልደ በየነ (የርዕዮት አካሏ) እና ሌሎች የቴክኒክ ሰዎች የኢትዮ 360 ስኳዶች ነበሩ። ዛሬ ላይ ተወልደ ከርዕዮት ጋር በመሆን፣ ምናላቸው ከጎጃም ባለፈረንካዎች ጋር ተሳስሞ፣ ኤርሚያስ በአካሄድ ችግር ተለይተው የየግል ሚዲያ ከፍተዋል። እንደው ለማስታወስ ያህል ነው። ስንት ቦታ እንደተበለቱ ለማመላከት ያህል…

ዳማ ሆቴል ምግብ ታዞ እስኪደርስ “ሚዲያውን እንዴት እናስኪደው? ኤዲቶሪያሉ ምን ይሁን? ምን ዓይነት ፕሮግራም ይዘጋጅ? ምኑን እንያዝ፣ ምኑን እንልቀቅ? ምን ዓይነት ሤራ እናዋቅር” ወዘተ እያሉ ገና ከተቋቋመ የአንድ ሳምንት ዕድሜ ለነበረው ሚዲያቸው እየመከሩ ነበር። ከአዲስ አበባው የስኳር አክሲዮን ፕሮጀክት ጀምሮ ባለሃብቶች ጥላ ሥር የማይጠፋው ምናላቸው ስማቸው ከባህር ዳር ስልክ ይደወልለትና በድንገት ተስፈንጥሮ ከሆቴሉ ይወጣል።

በትውልድ ጎጃሜ የሆነው ምናላቸው ከአፍታ በኋላ “አሳዛኝ ሰበር ዜና” እያለ ተመለሰ። ቁና ቋና እየተነፈሰ የአማራ ክልል መሪዎች መገደላቸውን ተናገረ። ከፍተኛ ድንጋጤ ተፈጠረ። ሁሉም ዘንድ የተለያየ ስሜት ተንጸባረቀ። በመጨረሻም በኢትዮ 360 የማህበራዊ ገጽ ላይ የመሪዎቹ መገደል “በሰበር ዜና” ተዘገበ። ይህ እስከሚያበቃ ድረስ ጸብም፣ ንትርክም፣ አለመግባባትም፣ ሤራም ሆነ የአሳብ ልዩነት አልነበረም። ይህን ሃቅ ሊክድ የሚችል አንድም አካል የለም። ሊኖርም አይችልም። ዳማ ሆቴል ምስክር ነው። እኔም ምስክር ነኝ። ሃብታሙ አያሌውም ሤራ እንደሆነ አረጋግጦልኛል። ይህቺን ምስክርነቴን ሲያነብ ማን እንደሆንኩ ይለየኛልና ደፍሮ ከደወለልኝ ክፍል ሁለትን ለመጻፍ ያነሳሳኛል። 

የአማራ ክልል ቁንጮ ባለሥልጣኖችንና በፕሬዚዳንቱ ቢሮ እየመከሩ ባሉበት ወቅት የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ያዘጋጁት ወጥመድ መርጦ በላቸው። ጄነራሉ የሚመሩት ልዩ ኃይል ለማመን የሚከብድ የጭካኔ ጥቃት ፈጸመ። በጥቃቱ ዶ/ር አምባቸው መኮንን፣ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ አቶ እዘዝ ዋሴ ተገደሉ። ሦስቱም ከጎንደር መሆናቸው ከግድያው ዜና ጋር አብሮ አየሩን ሞላው። 

እሱም ለጉድ መትረፉን ጠቅሶ የነበረው አሰማኸኝ አስረስ በግል የፌስ ቡክ ገጹ “… ከጥቂት አመታት በፊት ሰኔ 15 የተከሰተው በሀሳብ ልዩነት ምክንያት ነው። ይህ ክስተት ብዙ የሤራ ትንታኔ ቢኖረውም በአማራ ብሔርተኝነት ውስጥ የሀሳብ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማስተናገድ ያለመቻል ውጤት ተደርጎ ሊወስድ ይችላል። የአማራ ብሔርተኝነት ማቆጥቆጥ የቆረቆራቸው ወይም ያሰጋቸው አካላት በሰኔ 15 አፈፃፀም ላይ ተሳትፎ ቢኖራቸውም በዋነኛነት ግን የሀሳብ ልዩነትን ተነጋግሮ የመፍታት ጉድለት ነው ሰኔ 15ን የፈጠረው። ቀጥሎም ግርማ የሺጥላን እና ደሳለኝ አስራደን የመሠሉ መሪዎች ተበልተውበታል። በአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ዉስጥ ጠላት ከምትለው ጋር ተዋጋተህ ብትሠዋ ክብር ነው። በወንድምህ፣ በአመንኸው ተክደህ ስትረሽን ግን ህመም ነው፤ ፀፀት ነዉ፤ መስዋትነቱንም የውሻ ነው” ሲል “ሦስትን ወደ አራት ” የማድረግ ሤራን መነሻና ውጤት መስክሯል። እዚህ ላይ የሟች ቤተሰቦች ያሉትን አክሉበት። ከዛ ዝቅ ብዬ የማጣቅሰውን የኤርሚያስ ለርገሰን ኑዛዜ አካታችሁ እንዴት በፈጠራ ትርክትና ሤራ ሰክረን፣ አቅላችንን ስተን፣ ተሸውደን፣ ዞሮብን እንደኖርን ይገባናል። ልክ እንደ እኔ።

ወደ ዋናው መነሻዮ ላምራ። ዜናው ሰበር ሆኖ በፌስ ቡክ በተለቀቀ ማግስት (በበነጋው) የ360 ስኳዶች የቀጥታ ስርጭት ገቡ። ስርጭቱ እንደተጀመረ ተወልደ ወይም ተቦርነ እሳት ጎርሶ፣ ራሱን መቆጣጠር አቅቶት እየተወራጨ አቶ ላቀ አያሌውንና “ባለሃብቱን” አቶ ወርቁ አይተነውን በስም በመጥራት “ወንድሞቼን ገደሉ፤ ወንድሞቻችንን ገደሉ” ሲል ደጋግሞ ጮኸ። በጎንደሬነቱ ጥቃት እንደገባው አምኖና ተቀብሎ ራሱን መቆጣጠር እያቃተው ግድያው ሆን ተብሎ ጎንደሮች ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገለጸ። ተቦርነ ዜናው ይፋ ከሆነ በኋላ እንደ ጣዖት ከሚያመልከው ወንድሙ ታማኝ በየነ ጋር ሲመክር ማደሩን የሚያውቁ ቁጣው በስሜት ሳይሆን በትክክለኛ የጉዳት ስሜት የተወለደ መሆኑን አመኑ። ተመክሮበት የተያዘ ዓቋም መሆኑን ሹክ ያሉኝም ነበሩ። በውቅቱ ሳልነቃ። እንደዛሬው ነጥቦችን የማገጣጠም አቅም ሳይኖረኝ። በድንዛዜው ዘመኔ።

ይህን ጊዜ ከእነ ኮሚሽነር አበረ አዳሙና ወርቁ አይተነው ጋር ግንኙነት እንዳለው በይፋ የሚታወቀው ምናላቸው ስማቸው ተቦርነን ቀበል አድርጎ “እነሱ አይደሉም። ይሆናል ብዬ አላስብም” ብሎ መከራከሪያ አነሳ። ሞገተ። ይህን ጊዜ ነገሩ ሁሉ መልኩን ቀየረ። የዜናው መልኩን መቀየር ገና ከተቋቋመ የሳምንት ዕድሜ ላለው የኢትዮ360ም ታላቅ አደጋ ይዞ መጣ። ይህኔ “የሦስትን ወደ አራትን” ሤራ ተረገዘ። ምናላቸው ኮሚሽነር አበረ ሁሉንም ጉዳይ እንደወረደ ስላስረዱት ገዳይን ለይቶ ያውቅና ሟቾችም ለምንና እንዴት ተመርጠው እንደተረሸኑ ይረዳ ነበር። በወቅቱ ስብሰባ ላይ ከነበሩት “እነማን ተረፉ” የሚል ጥያቄ ለሚያነሱ ሁሉ ነገሩ ግልጽ ሆኖ ሳለ ቀሸቡን። በሌላ አነጋገር ደፈሩን!! ይቆጫል። ያንገበግባል።

አዲስ ተመሥርቶ የጎፈንድሚ ዕርዳታ እየለቀመ ለነበረው ኢትዮ 360 ትልቅ ተግዳሮት የሆነው ይህ ዜና አማራን የሚከፋፍል፣ በተለይም ጎጃሜና ጎንደሬ መካከል እሳት የሚያስነሳ በመሆኑ የቀጥታ ስርጭቱ ካለቀ በኋላ መላ እንዲፈልግለት ግድ ሆነ። አለያ ገበያውም፣ ጎፈንዱም፣ ድጎማውም ሊቆም ሆነ። በሃብታሙ ቋንቋና አገላለጽ ለኢትዮ 360 ዋና የገቢ ምንጭ የሆነው አክራሪው አማራ ጎጃሜና ጎንደሬ መጋጨት 360ን ገና በሁለት እግሩ ሳይቆም ቁልቁል ይደፋዋል። ሳይታወቅ ያከስመዋል። 

አስደንጋጩን ዜና ይዘው ላይቭ የወጡት የኢትዮ360 አባላት የተነሳው ጩኸትና እልህ የተላበሰ ዛቻ አዲስ እየተወለደ ያለውን ኢትዮ360 እንዳይበላው ስጋቱ በመጨመሩ ሃብታሙ አያሌው መላ ለመፈለግ ይባትት ጀመር። በተመሳሳይ ቀን ስርጭቱ እንዳለቀ ለኤርሚያስ ለገሰ ደውሎ ወተወተ። ኢትዮ360 አንድ መላ ካላዘጋጀና በጎንደርና በጎጃም መካከል የተነሳውን ልዩነት ማስቀየስ ካልተቻለ መክሰም ዕጣ ፈንታቸው እንደሚሆን ተነተኑ። ከብዙ ንግግርና የሤራ አማራጮች በኋላ ዐቢይ አህመድን ባዋለደው ሤራ ላይ ተስማሙ። 

ድርሰቱና ደራሲዎቹ የ360 ሚዲያ ተዋንያኖች ዜናውን በፌስቡክ ገጻቸው ካሰራጩ በኋላ “የገበያ ዋና ምንጫችን” የሚሉት አማራ መንጫጫቱ፣ ጎንደሮች ስልክ እየደወሉ ማበዳቸው፣ ቁጣው በሚዲያ ውስጥ ያሉትን ጎንደሮችና ጎጃሞችም ጭምር ማናከሱ ወዘተ …  ዐቢይን እንደ የመስዋዕት በግ ለማቅረብ በተወሰነው መሰረት፣ በቀጣይ ቀን ዐቢይ አሕመድን ገዳይ አድርገው ለማቅረብ ወሰኑ። “እረኛውን ምታ በጎቹ ይበተናሉ” በሚል ወያኔ አቅጣጫ እየሰጠ ስማቸው እንዲጠለሽ የተዘመተባቸው ዐቢይ በሌሉበት የአራት “ጀግኖች” ገዳይና አስገዳይ ሆኑ። ወገን እናስብ፣ አነተ፣ አንቺ በዚህ ደረጃ በትፈረጂ/ ጅና በገዳይነት ዕለት ዕለት ብትወነጀል ምን ይሰማሃል/ ይሰማሻል? ቤተሰብ፣ ልጆች፣ እናት አባት ምን ያህል ይጎዳሉ? ለዩቲዩብ ገበያ ሲባል በዚህ ደረጃ ድራማ መስራት፣ ሤራ ማምረት ዛሬ ሳይሆን ከ1966 ጀምሮ ብዙ የጎዳን ሆኖ ሳለ እንዴት መንቃት አቃተን? በሤራ “አንጃ” እየተባለ ስንቱ ተቆላ? ስንቱ ተፈጀ? የስንቱ ቤት ኦና ሆነ? ስንት እናቶች የወላድ መካን ሆኑ? ስንት ቤተሰብ እንዳለቀሰ በሰቀቀን … እናስብ!!

ዐቢይ አሕመድ ሤራው የወለደው “ነብሰ ገዳይ” ለማድረግ የኢትዮ 360 ስኳዶች ተቆነጃጅተው ወደ ምሽት ገበያቸው ብቅ አሉ። ጎራ ለይቶ ሲላተም ላደረው  ጎጃሜና ጎንደሬ፣ እንዲሁም ዜናውን ሲከታተሉ ለነበሩ ሁሉ “አዲስ ትርክት እንፍጠር” በሚል ስሌት የተወለደው ሤራ ከትነተና ጋር “ሰበር ዜና” ተብሎ አየር ላይ ዋለ። እዚህ ላይ ምናላቸውን አስቡት። ምናላቸው እውነቱን እያወቀ፣ እውነቱ ተነግሮት ሳለ ነብሰ ገዳይ ጀግና አስብሎ በኩራት በቀጥታ ስርችቱ ወቅት ሲወጣጠር። ልቡ ዳንኪራ ሲመታ። ወዳጆቹን የታደገው ሤራ የሃፍረት ሞገስ ሰጥቶት ህዝብ ላይ ሲተፋ። ሌሎች ዕቃ ስለሆኑ ስማቸውንም አጠራቸውም ግን ራሱ ኤርሚያስ ለገሰና ሃብታሙ አያሌው ሤራ አዋልደው፣ አዲስ ትርክት ፈጥረው ህዝብ ፊት ቆመው እየተቀባበሉ … ቃል የለኝም። እንዴት መሽቶ እንደሚነጋላቸው ሳስብ ያመኛል። በተለይ ሃብታሙ የታላቁን መጽሃፍ ውድ የሕይወት ጥቅሶች እያጣቀሰ ስለ ሞራልና የሞራል ፍሬዎች ሲያወራ … አቤት ስናሳዝን!! አቤት ውርደት። አቤት …..

በሤራ የተወለደው “ሦስትን ወደ አራት” የሚያደርገው አዲስ የቅጥፈት መረጃ አደባባይ እንዲቀርቡ ከተደረገ በሁኋላ ኢትዮ 360 ወስጥ ሰርግና ምላሽ ሆነ። “ከረበትነው፣ ገለበጥነው፣ ወንዳታ” በሚል ጀግንነት “ቺርስ” ተባብሉ። በተለይ ምናላቸው ስማቸው እና ሃብታሙ አያሌው ፈነደቁ። እኔን ጨምሮ ሳናላምጥ ለምንውጠው ዜናው በወዘን። “ይሄ ነብሰ ገዳይ” በማለት ዐቢይ አሕመድ ላይ ዛትን። ርግማን አወረድን። ዛሬ ድረስ የሚራገሙ ሳይሆን በዚሁ የስህተት ትርክት ሳቢያ ቃታ ይዘው ጫካ ያሉ ጥቂት አይደሉም። እንግዲህ የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ ኃይሎች የተኙት በዚህ ደረጃ አገሪቱን ዋጋ ያስከፈለው ትርክት ውሸት መሆኑ እየሰሙ ነው።

ዐቢይ አሕመድ የሶስቱ የአማራ ክልል ፈርጦች ዶ/ር አምባቸው፣ አቶ ምግባሩ ከበደ፣ አቶ እዘዝ ዋሴ ገዳይ፣ አስገዳይ ያደረጋቸው ትርክት መሬት ነክሶ። የጎጃሜና የጎንደሬ ጸብ አረገበ። እኔም ተወደ ጎንደሮቹ ነበርኩና በረደልኝ። አደጋ ተጋርጦበት የነበረው የኢትዮ360 ጎፈንድሚና እርጥባን ከመንጠፍ ዳነ። እያደር እንደ አሜባ ቢቆራርጥም አሁን ድረስ ሤራ ያመርታል። መከራ ያጭዳል። አሁን ላይ ባለኝ መረጃ እዛም እዚህም “በሰበር፣ በሰነድ ተገኘ” ስም የሚሰራጩ መረጃዎች ሚዲያዎቹ ጓሮ፣ አለያም በቅብብሎሽ አብረዋቸው ከሚሰሩት “ፖለቲከኞች” ወይም ከሚቀልቧቸው ጎረቤቶቻችን የሚላክላቸው የፈጠራ ድረሰት ነው። አሁን ተገልጦልኛል ወደፊት እመለስበታለሁ።

ከሰኔ 15 ቀን 2011 ዓም በኋላ በያዝነው ወር 2017 ኤርሚያስ ለገሰ ይፋ ያደረገው እውነት በሚገባውና ለጥፋቱ በሚመጥን ደረጃ ይቅርታ ባይጠይቅም የሚያስመሰግነው እንደሆነ እገምታለሁ። ባጭሩ “አዲስ ትርክት እንፍጠር፣ ሤራ እናምርት ተባባልንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ገዳይ አደረግን። ይህን ያደረግናው ሃብታሙ ደውሎልኝ ከተወያየን በኋላ ነው። የሰራነው ቅጥፈት ነው” ነው ያለው። ኤርሚያስ ይህን ማለቱን ተከትሎ ሃብታሙ አያሌው “አይ ሰው፣ አይ ኅሊና፣ ሰውን ማመን …” ከሚሉ የተለመዱ የትዝብት ማሳያ ቃላት ከመጠቀም ውጭ የረባ ማስተባበያ አላቀረበም። ኤርሚያስ ላይ ስድብ ከማዝነቡ በስተቀር አንድ ገዳይ ሶስት ሟቾችን በአንድ ላይ ደምሮ ገዳይ በመሰየም ከርስን ለመሙላት የተኬደበትን ርቀት በአመክንዮ አላስተባበለም። እንደገባኝ ከሆነና ዛሬ ላይ ባለኝ ዕውቀት ማስተባበልም አይችልም። ግን በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግሥት ሚዲያዎች ለምን ኤርሚያስ ለገሠን በገሃድ አይጠይቁትም? እነሱ ካልቻሉ ለምን የመንግሥት ወዳጆች፣ የዐቢይ አድናቂዎች ወይም ፍትህ ፈላጊና “የጋዜጠኝነት አድባር ነን” የሚሉት ክፍሎች ይህን ሃቅ አደባባይ አይሰቅሉትም? አልሰሙም እንዳልል የማይሰማውንም ይሰማሉና። 

ሃብታሙ ለማስተባበል በሚል ስለ ሕሊና ውበትና የሰውነት ሚዛን እያጣቀሰ ሲሳደብና ሲወራጭ ድንገት ዶክተር ዳኛቸው ብቅ አሉና የሃቅ ናዳ አወረዱበት። ዶክተር ዳኛቸው ሰሞኑን አንዳፍታ ላይ ኤርሚያስ ሃቁን ማፍረጡን የሚያሳይ መረጃ አቀረቡ። በማብራሪያቸው ያነሷት የ“አራት” ቁጥር ጉዳይ በድጋሚ ቀልቤን የሳበኝ ጉዳይ ነበር። ለወትሮው ጭፋ ላይ ደርሼ ነበርና “ሦስት አራት” የሚለው ትርክት በዶክተር ዳኛቸው ሲዝረከረክ በደንብ በራልኝ። 

ኤርሚያስ “ዐቢይ አህመድን ገዳይ አድርጎ ገዳይንና ሟቸን እኩል ማጀገን በሚል ሤራ ተማምነን አዲስ ትርክት ፈጠርን” ሲል የሰጠውን ምስክርነቱን የሚያረጋግጠው የዶክተር ዳኛቸው ገለጻ፣ ሤራውን የሚያሳጣ ከበረዶ የነጣ መረጃ ቢሆንም ሃብትሽ ባላየ አልፎታል። እንደ “ሚዲያ ሰው” ቢያስብ ኖሮ እሳቸውንም ሆነ የቀድሞ ባልደረባውን በዝርዝር በሞገተ ነበር። እንደ ሰማሁት ከሆነ ይህ ሤራ ሲጎነጎን ሃብትሽ የተነፈሳት ሁሉ በድምጽ ተይዛለች። እናም ከዚህ በላይ እላፊ አይሄድም።

አማራ ክልልን በድንጋጤ ከራደውና መላ አገሪቱን ካሳዘነው ግድያ በኋላ ባህር ዳር ተደርጎ በነበረ የአማራ ክልል ምሑራን ስብሰባ ላይ ሊቀመንበሩ “አራት ጀግኖች አጣን” ሲሉ በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩት ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ “ጓዶች እኔ የማውቀው ሦስት ጀግኖችን እንዳጣን ነው። ማስታወሻዬ ላይ ጽፌ የያዝኩት ሶስት ናቸው። ማን ነው አራተኛው? አራተኛውን አላውቀውም” ብለው መጠየቃቸውን ለአንዳፍታ ተናግረዋል። በዚሁ የመደነቅ ምስክርነታቸው፣ አንዱ /ፕሮፌሰር ነው መስለኝ/ እጁን አውጥቶ “ማን እንደሆኑ እኛ እናውቃቸዋለን አራት ናቸው” በሚል ምላሽ ሰጣቸው። ከዛን ቀን ጀምሮ “ገዳይና ሟቾችን አብሮ ጀግና ባደረገው ማኅበር ውስጥ አልቀጥልም” በማለት ማኅበሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መለየታቸውን ዶክተር ዳኛቸው በአንዳፍታ በኩል ነገሩን። ይህኔ ነው እኔም ሙሉ በሙሉ ነቅቼ ይህን ለመጻፍና ለማጋራት የወደድኩት።

ሃብታሙ አያሌው “ሰዎቹን መለያየት የለብንም። ሁሉንም ማጀገን አለብን። አለበለዚያ ሚዲያችን ላይ ችግር ይፈጠራል” በማለት ዐቢይ አሕመድን ገዳይ አድርጎ የማዋለዱ ሤራ ላይ ምን ያህል እንደዳከረ ለመሸሸግ ቢሞክርም የዶክተር ዳኛቸው ምስክርነትና የኤርሚያስ ንስሃ ጉዳዩን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ሆኗል። እናም “ይህ አደገኛ የወንጀል ትርክት በመንግሥት የፕሮፓጋንዳ ተቋማትና መሪዎቻቸው ዘንዳ እንዴት ለዶክመንታሪ አልመጥንም አላቸው?” ብዬ ብጠይቅ ይፈረድበኛል? ለሁሉም ጊዜ አለው!!

ዶክተር ዳኛቸው “ገዳይም ተገዳይም እንዴት እኩል ጀግና ይሆናሉ” በማለታቸው ሳቢያ ዘር ማንዘራቸው ሳይቀር ተሰድቧል። ሕዝብ እንዲያስቆጣ ታስቦ የተጠመቀውን ሤራ በመግለጣቸው ሳቢያ በስድብ ተበልተዋል። እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ይህን ጉዳይ አንስተው “በማንኛውም ምድራዊ አመክንዮ ገዳይና ሟች እኩል ጀግና ሊሆኑ አይችሉም” በሚል መከራከሪያ ለሚያቀርቡ ሁሉ እነ ሃብታሙ ያዋለዱት “ሤራ” እየተጠቀሰ ለአብዛኞች የስህተት መንገድ መንሸራሸሪያ ሆኗል። አሁን ድረስም እየሆነ ነው። በዚሁ “ዕብድ” በተባለና ምርጥ የአማራ ልጆችን በበላ ገዳይ ስም “የአማራ ነጻ አውጪ ክፍለ ጦር” ተሰይሟል። 

የአሁን የፋኖ አዝማች ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ በይፋ የዚሁ የነፍሰ ገዳይ ምክትል ነበሩ። ለጉዳዩ አንደኛ ደረጃ ምስክር ለመሆን ከእሳቸው ፊት ሊቆም የሚችል አንድም ሰው ሊኖር አይችልም።  “መክሬዋለሁ። አልሰማም አለ” ሲሉ በሰጡት ምስክርነት ባልደረባቸው ብ/ጄነራል አሳምነው ጽጌ ግድያውን መፈጸማቸውን ሲመሰክሩ እንኳን እነ ሃብታሙ ወይም 360ዎች ይቅርታ አልጠየቁም። 

“… አሳምነው ፅጌ ችግር በሚገኝባቸው ቦታዎች አይገኝም። የፌስቡክ አርበኛ ነው። አንዲት ጠብ የሚል ስራ አይሰራም። እቅድ የለውም።የተማከለ ስራ አይሰራም። አያስተባብርም…የፌስቡክ አርበኛ ነው የፌስቡክ ጄነራል ነህ። የፌስ ቡክ ቡድን አደራጅተህ የክልሉን አመራር እያጥላላህ ነው። “እራስህን ንጉስ እያስባልክ አመራር ለመሆን ነው እየሄድክ ያለኸው። ፋኖ እያደራጀህ ገንዘብ እየሰጠህ ልታስመታን ነው ብለነዋል…” በማለት ከባህር ዳር እስከ አዲስ አበባ በተደረገ ግምገማ መወቀሱን የዛሬው ፋኖ መሪ ተፈራ ማሞ መስክረዋል። “እዚህ መነገር የማይችሉ ብዙ ጉዳዮች ተነስተው ነበር” ብለዋል።

ይህን የሰማው ሃብታሙ “አቁም” በማለት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞን ማስፈራራት ጀመረ። “አዲስ ሴት አግብተህ…” ወዘተ እያለ እንደሚያቆሽሸው እየዛተ ዝም እንዲል አስገደደው ። ሤራ መፍጠርና የፈለጉትን ማራከስ “ተው” የሚል የሌለበት ተሞክሮ በመሆኑ ሌሎች ላይ የደርሰውን ስም ማጥፋት ያጤነው ተፈራ ፈራ። ወዲያውም ድምጹን አጠፋ። ለመጨረሻ ጊዜ አዲስ አበባ የክልሉ ሚሊሻ፣ ፖሊስ፣ ልዩ ሃይል አዛዦች እንዲሁም አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አቶ ደመቀ መኮንንና የክልሉ አመራሮች ባደረጉት የአንድ ቀን ተኩል ስብሰባ ላይ ሰፊ ተግሳጽ የገጠወው ጄነራል አሳምነው ራሱን መከላከል እንዳቃተው ተፈራ ማሞ በበቃሉ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይፋ ተናግረዋል። 

“ከአክራሪው የአማራ ክፍል ገቢ ማግኘት አንችልም። ገቢያችን ይነጥፋል” በሚል ስሌት ዐቢይ አሕመድን ገዳይ አድርጎ “አራት ጀግኖች አጣን” የሚል ትርክት የተከለው ኢትዮ360 ውሎ አድሮ በርካታ ጉዳዮች ይፋ እንደሚወጡበት እምነቴ ነው። ጽሁፌን ሳልቋጭ አንዳንድ ጉዳዮችን ላነሳ ወደድኩ።

የሃሰት ትርክት “ባለፉት 50 ዓመታት የተከሰቱት ጦርነቶች የተጀመሩት ሚዲያው ባስተጋባው ውሸት መሆኑን ደርሼበታለሁ” ሲል ጁሊያን አሳንዥ የተባለው የዊኪሊክስ መሥራች መናገሩን ማስታወስ ልብ ይሏል።

የአገራችን ሚዲያ አውታሮች በተለይም የግል ሚዲያ የሚባሉት አክቲቪዝምንና ጋዜጠኛነትን ቀላቅለው የአገሪቱን ፖለቲካና የሕዝብ ሰላም እያናወጡት ነው። በ1997 ምርጫ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲቀጭጭ፣ የሃሳብ ልዩነት እንዳያድግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች ጉያ ሥር ገብተው የፈጸሙት ወንጀል የሚመረመረው ቢያገኝ የሚያስጠይቅ፣ አንገት የሚያስደፋና አሁን ላለው ትውልድ መማሪያ የሚሆን ታላቅ ግብዓት በሆነ ነበር።  በደንብ ተጠንቶ ለቀጣዩ ትውልድ መማሪያ ይሆን ዘንድ በወጉ ተሰንዶ ሊቀመጥ በተገባም ነበር። ይህ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ምን አልባትም ዛሬ ላይ ራሳቸውን ታጋይና አርበኛ አድርገው በህዝብ ደም፣ መፈናቀልና ሞት ለሚዛበቱት ሸቃዮች ልጓም ሊሆን በቻለ ነበር። 

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሚዲያዎች አንድም ፓርቲ ወይም የፓርቲ መሪ ጉያ ስር የሚለጠፉ ቁሶች ናቸው። ዛሬ ራሳቸውን ጻድቅ አድርገው የሚቀርቡና ለራሳቸው “የፖለቲካ መሪ ነኝ” የሚል ካባ የደረቡት ሳይቀሩ ከጀርባቸው ሚዲያ እያደራጁ አጀንዳ በማስያዝ ሲነዱዋቸው ይቆዩና በኋላ  ላይ እንደለመዱት የእርስበርስ ሽኩቻ ውስጥ ሲወድቁ የሚፈልጉትን ለማጥቃት ይጠቀሙባቸዋል። 

በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ባልደረቦቻቸውን ለመወንጀልና ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት ሲሉ ለሚዲያዎቹ ባለቤቶቹ በባርነት ያድራሉ። ተገዢ ሆነው ለሚዲያ ውሪዎች ይሰግዳሉ። ጀርባቸው ንጹህ ያልሆነ፣ የሤራ አባቶች ስለሆኑ እዚህ ግቡ የማይባሉ ውርጋጥ ሚዲያዎች ይነዷቸዋል። በ1997 የሆነው ይህ ነው።

“ፖለቲከኞች” ቀንድ ሆነው ሚዲያውን መምራት ሲገባቸው በሚዲያው በመመራትና የአሽከርና ባሪያ ግንኙነት ፈጥረው አገር በውርጋጦች አጀንዳ እንድትታመስ አድርገዋል። ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። በማሕበራዊ ሚዲያዎች ሳይቀር ሰፊ መንጋ ላላቸው መስገድና አዘቅዝቆ መገረድ ከቀድሞው ትምህርት የቀጠለ ነው። የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ ሃይል መድከምና ቸልተኛነት በፈጠረላቸው ዕድል ሳቢያ ሁሉም እየተነሱ በደም ቆጠራ፣ በአካባቢያዊነት፣ ራሳቸውን በመሸጥ ወዘተ አገርና የፖለቲካ ልዩነትን ሳይለዩ በፈጠራ ትርክት የትርምስ ፊት አውራሪዎች ሆነዋል። በዲጂታል ልመና በሚያገኙት እርጥባን ሸሚዝና መታነቂያቸውን እየቀያየሩ፣ ዘወትር ማታ ሳያሰልሱ ኢትዮጵያን ሕዝቧን ያለመታከት ያተራምሳሉ። ከአንዱ ትርምስ ወደ ሌላኛው ትርምስ እየዘለሉ ሕዝብን በመከራ ያዝላሉ። ሕዝብ መቼ እንደሚነቃ፣ እንዴትና ምን ሲሆን እንደሚባንን ለዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ግራ ነው። ከቅንጅት ጊዜ ጀምሮ በቁጥር በሚታወቁ ሰዎች መነዳት ምን የሚሉት ድንቁርና ይሆን? በቅርቡ ብቅ ካሉት የቀድሞዎቹ ተማሪዎች አያያዝ ከሆነ፣ የቅብብሎሽ የሃሰት ትርክት መውጫችን ለዚህ ጹሁፍ አቅራቢ ሩቅ ነው። ያስፈራዋል። ምክንያቱም እነዚህን ሤራ ጠማቂዎች “በቃችሁ” ለማለት የሚያበቁ ዕልፍ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ሆነዋል። እየሆኑ ነው። ገና ይሆናሉ። 

በኢትዮጵያ “እገሌ ተገደለ” ይባላል እንጂ ገዳዩ በደንብ ተጣርቶ አይቀርብም። ይህ ደግሞ ለአዳዲስ ትርክት በር ከፋች ሆኗል። ለምሳሌ “ትርክት እንፍጠር” ተባለው ኢትዮ360ዎች ዐቢይን ገዳይ ያደረጉበትና ሕዝብን ለማነሳሳት የተጠቀሙበትን ትርክት በፍርድ ቤት በግልጽ ሕዝብ እያየ እልባት መስጠት በተገባ ነበር። አሳምነው እነ ዶክተር አምባቸውን አስረሸነ። በሤራ ዐቢይ አህመድ አንገት ላይ የገዳይነት ሜዳሊያ እንዲጠልቅ ተደረገ። ትርክቱ ተደጋግሞ ለህዝብ በቅብብሎሽ እንዲነገር ሆነ። ከዛም ሃሰት እውነት መሆኑ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ “ገዳይና ሟቾችን ጀግና” የምትል አገር ሆነች። ለገዳይና ሟች እኩል ሐውልት አቁማ ታሪክ የሚጻፍባት ምድር ተደረገች። መጪው ትውልድ ይህን ታሪክ እየተጋተ ይኖራል። የእነ ዶክተር አምባቸው፣ አዘዝና ምግባሩ እንዲሁም አብረዋቸው የነበሩ ጥብቃ ቤተሰቦች ገዳያቸው ጀግና የሆነበትን ታሪክ እያዩ ይኖራሉ። ይህን ፍርድ ነው እነ ሃብታሙ ያዋለዱት። ጉዳዩ ለዐቢይ አሕመድ መከራከር ሳይሆን የሃቅና የፍትህ ጉዳይ ነው።


ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው እነ ዶክተር አምባቸውን ስለመግደሉ ምንም ጥርጥር እንደሌለው እኔ አሁን ላይ ያለ አንዳች ብዥታ አምኛለሁ። በግል ንስሃም ገብቻለሁ። ይህን እውነት በዶክመንታሪ ማቅረብ እንደ እኔ ብዙዎችን ያድናል። የፈጠራውን ትርክትም ያጸዳዋል። ሤራ ጠማቂዎች ልጆች ስላላቸው ቢያንስ እነሱን ለማዳንም ይጠቅማል። ከምንም በላይ የተጎዱ ሰዎች ልቡናን ለማከም ይረዳል። 

ከምንም በላይ የአማራ ምሑራን ማሕበርም አሁን ላይ ቢጠየቅ ይቅርታ እንደሚጠይቅ አያመንኩ አንድ ጥቆማ አነሳለሁ። ማስረጃዎች ተሰባስበው ቢሞቱም ገዳይ ላይ ክስ መመስረት አለበት። በተውተፈተፈ መልኩ ሳይሆን በገሃድ የፍርድ ሂደቱ ለሕዝብ ግልጽ ሆኖ ገዳይ በሌሉበት በወንጀላቸው መጠን ሊፈርዳባቸው ይገባል። አንድ የሕግ ሰው እንዳለኝ ከሆነ በቀጥታ ፍርድ ጉዳዩ ታይቶ በሰነድ ቢቀመጥ በቁጭበሉ ትርክት ለሚወናበደው አዲሱ ትውልድ ጥሩ ማጣቀሻ ይሆናል። የሤራ ባለቤቶችም በቅጥፈት ሲታወሱ ይኖራሉ።

ይህ ብቻ ሳይሆን ተጋራቸው ምንም ይሁን ምን የጀነራል ሰዓረና ሜ/ጀነራል ገዛኢ፣ የኢንጅነር ስመኘው በቀለ፣ የሰኔ 16 ቦንብ ፍንዳታ ወዘተ ጉዳዮች የፍርድ ሂደት ጽድት ብሎ ሊቀርብ ይገባል። የፍትህ ሂደቱ በግልጽ ለህዝብ ሊነገር ይገባል። ሁሉም ጉዳይ እየተውተፈተፈ እስከመቼ ይገፋል። ኃላፊነቱ የተሰጣችሁ በእነዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ ግልጽነትንና የሕግ አግባብን የተከተለ ብይን ይፋ አድርጉልን። 

በዚህ አጋጣሚ ሰዎችን በሌሉበት ማንሳትና በዚህ ደረጃ በማያውቁት ወንጀል ፈርጆ ከርስና ኪስ መሙላት እጅግ ነውር በመሆኑ ኢትዮ 360ዎች በይፋ ይቅርታ ትጠይቁ ዘንድ እመክራችኋለሁ። ኤርሚያስ ለገሰም “ሶስትን ወደ አራት” በማድረግ ገዳይንና ሟቾችን እኩል ያጀገነውን የፈጠራ ትርክት አድምተህ በይፋ ደጋግመህ ይቅርታ ጠይቅ። ደጋግመህ ትርክቱን እንዳሰረጽክ፣ ደጋግመህ ንስሃ ግባ። ቢያንስ በልጆችህ በረከትን ትቀበላለህ። በተመሳሳይ የእነ ሃብታሙ ባለቤት ባለቤትሽን አርቂ። በማህበራዊ ሚዲያ እየለመነ በሚሰጥሽ ፈራንካ ታውረሽ ያ በችግር ጊዜ የረዳሽን ሕዝብ አታስቀይሚ። ልክ እንደዛሬው ሌሎችም ብዙ ሸፍጦችና ሤራዎች እያደር ይፋ መሆናቸው አይቀርም። በእርም በሚገኝ ሃብትና አትደነቂ። ባለቤትሽ ለብዙ እናቶች ጠንቅ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። በግፋ ባሎቻቸውን ባጡና አባቶቻቸውን በተነጠቁ እንዲሁም በሞቱና  በተፈናቀሉ ዜጎች እንባ እየንጸባረቀ ያለውን ባልሽን እባክሽን አርሚ። የእሳክሁኑ ተባባሪነትሽ ይብቃሽ። ይህ ለእነ መሳይ፣ ደረጀ፣ ፋሲልና ባልደረቦችህ እንዲሁም “አንቱ” ለሚባሉት አዛውንት ጭምር ነው። አለያ ወዮልኝ ንጉሱ መቅጫ መንገዱ ብዙ ነው!! ብናምንም ባናምንም!! (ኢትዮ ሪቪው)

መዐዛ ሃሰን ከሜሪላንድ 


“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Middle Column, Opinions Tagged With: Asamnew Tsigie, Dagnachew Assefa, Dr Ambachew, ethiopian terrorists, Ezez, Migbaru, operation dismantle tplf, tplf terrorist

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm
  • ሃይማኖትን ለተራ የፖለቲካ ሸቀጥ ማዋል ውርደት ነው April 24, 2025 12:43 am
  •  የኬሪያ ኢብራሒም ኑዛዜ “ብትንትናችን ወጥቷል” April 22, 2025 12:08 am
  • ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አመራሮች ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጠ April 16, 2025 11:44 pm
  • ዓቅም እንደሌለው የገመገመው ሻዕቢያ ፊቱን ከጦርነት ወደ ዲፕሎማሲ እያዞረ ነው   April 15, 2025 12:32 am
  • “አንድ የፋኖ ተቋም (የእስክንድር) ተመሥርቷል፤ ሌሎቹ ደግሞ እንዲሁ አንድ ተቋም መሥርተው ወደዚህ ይመጡ” አበበ ጢሞ April 11, 2025 12:07 am
  • መለስ (ለገሰ) ዜናዊ – ተዋርዶ ያዋረደን! April 9, 2025 10:28 pm
  • የተከዜ ዘብ: የሉዓላዊነት መጠበቂያ April 8, 2025 11:49 pm
  • አዲስ አበባ አስተዳደር የሪፖርተርን የተዛባ መረጃ ኮነነ፤ ሕጋዊ እርምጃ እወስዳለሁ አለ April 8, 2025 10:06 pm
  • ሀሰተኛውን የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በጽኑ ተቃወመ፤ እርማትም ጠየቀ April 8, 2025 09:48 pm
  • “ኦሮሚያ ላይ ወይም ሌላ ቦታ ላይ ስታደርገው ከነበረ ትግራይ ወስጥም የማታደርግበት ምንም ምክንያት አይኖርህም” ነው ጌታቸው ረዳ April 7, 2025 10:22 pm
  • “TPLF’s belief in a strong federal government was always tied to its own dominance in Addis Ababa” April 7, 2025 10:15 pm
  • Counter-Video by EBC Challenges EBS Broadcast, Sparks Public Outcry Over Alleged Misinformation March 31, 2025 02:36 am
  • የኤሊያስ መሠረትን ፌክ መረጃ ማን ያጋልጥ? February 19, 2025 06:00 pm
  • አዘርባጃን፡ የሻዕቢያን ሸምቀቆ ማጥበቂያ?! February 19, 2025 12:29 am
  • የአሜሪካ ድምፅ/ቪኦኤ ይዘጋ ተባለ  February 12, 2025 03:37 am

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule