በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ አካባቢ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በአገራችን ውስጥ ስላለው ችግር መፍትሔ ለማምጣት ይጠቅማል በሚል በጠራው ውይይት ላይ ኢትዮጵያውያን ከአውሮጳ፣ ከአሜሪካና ከካናዳ ተጠራርተው በመምጣት በዓይነቱ ለየት ያለ ውይይት አድርገዋል፡፡ “ሰላም፣ ፍትሕ፣ ዕርቅና መከባበር የሰፈነበት ማኅበረሰብ ለመመሥረት” አንዳችን ስለሌላችን በመናገር ሳይሆን እርስበርስ ስለችግራችን መወያየት አለብን በሚል መሪ ሃሳብ ኢትዮጵያውያኑ ግልጽና በቅንነት ላይ የተመሰረተ ውይይት አካሂደዋል፡፡ “ከዘረኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ” የመስጠት አስፈላጊነትም በስፋት ውይይት የተደረገበት ጉዳይ ነበር፡፡
በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው ኤምባሲ የስብሰባው አካል እንዲሆን ለአምባሳደር ግርማ ብሩ የንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ የላኩ ቢሆንም ከኤምባሲው በኩል የተሰጠ ምላሽም ሆነ በውክልና በስብሰባው ላይ የተገኘ አለመኖሩ በጋዜጣዊው መግለጫ ተወስቷል፡፡ የመግለጫው ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡
አዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ጋዜጣዊ መግለጫ
ኅዳር 17፤2006፤ዋሽንግቶን ዲሲ፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ኅዳር6፤2006/ኖቬምበር15፤2014 በአሜሪካ ዋሽንግቶን ዲሲ ባደረገው ስብሰባ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት ዕውቀት፣ ችሎታ፣ ስነምግባር፣ ብቃትና ልዩ ተሰጥዖ ያላቸው በርካታ ወገኖችን በተመለከተ አገራችን አሁንም የሰው ደሃ አለመሆኗን ያስመሰከረ ነበር።
በስብሰባው ወቅት ከበርካታ የአላማ ጽናት ካላቸው ደፋር፣ አርቆ አስተዋይ እና ብልህ ኢትዮጵያውያን እጅግ የሚመስጡ ንግግሮች ተካሂደዋል። የአስተሳሰብ ልዩነት በነበረበት ጊዜ እንኳን ቢሆን የነበረው መከባበርና የማስተዋል መንፈስ ለበርካታዎች ትምህርት የሰጠ ነበር። እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ የሰለጠነ ውይይት ለበርካታ በደል ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በመደማመጥ እንዴት መወያየት እንዳለባቸው መሠረት የጣለ ስብሰባ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ የመጡት በመጀመሪያ ራሳቸውን ወክለው ነው። ጉባዔተኛው በህብረት በሚጋራው እሴቶች ላይ በመቀራረብ እውነት፣ ነጻነት፣ ፍትህና መግባባት ለሁሉም መፍጠር በሚቻልበት የጋራ አጀንዳ ላይ ውይይት ለማካሄድ ተችሏል።
በጋራ ውይይቱ ወቅት ከመድረኩም ሆነ ከተሰብሳቢው የተሰሙት ሃሳቦች እና ታሪኮች እንዲሁም አስተያየቶች ከዚህ በፊት በአብዛኛው ሲነገሩ ያልተደመጡ ናቸው። ለሕዝብ በተሰራጨው መጥሪያ ላይ በግልጽ እንደሰፈረው የውይይቱ ዋና ዓላማ “በኢትዮጵያውያን ተቋማት መካከል የተለመደውን አለመግባባት ለመስበር” ሲሆን ይህም “ስለ ሌላው መነጋገር ሳይሆን እርስበርሳችን መወያየት” አለብን በሚል መንፈስ የተጠራ ነበር። በመሆኑም ስብሰባው በሁለት ተከፍሎ ነበር ውይይቱ የተካሄደው።
የመጀመሪያው ስብሰባ ከታቀደለት ሰዓት ዘግይቶ የጀመረ ሲሆን ከጋራ ንቅናቄው በኩል ስብሰባውን የመሩት ነጋሽ አብዱራማን ናቸው። የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ የተለያዩ ተናጋሪዎች በልዩ ልዩ የሙያ ዘርፎች ንግግር አድርገዋል። በህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ሥርዓት ውስጥ በማገልገላቸው የሥርዓቱን ምንነት አብጠልጥለው ለመናገር ብቃት ያላቸው ተናጋሪዎች ትምህርታዊ የሆኑ ገለጻዎችን አድርገዋል። የዞን9 መስራች ሶሊያና ሽመልስ፣ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ፍርድቤት የቀድሞ ዳኛ ፈይሣ እስራኤል ኢታንሣ እንዲሁም በኢህአዴግ አገዛዝ የቀድሞው የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ድኤታ ኤርምያስ ለገሰ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉት ተቋማት እና እንዴት የአገዛዙ መጠቀሚያዎች እንደሆኑ ከልምዳቸው በዝርዝር አብራርተዋል።
በአገራቸው ቢሆን ከፍተኛ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉትና ለዘመናት ያጠራቀሙትን ዕውቀት ለወገናቸው ማካፈል ይችሉ የነበሩት የልማትና የፖለቲካ ኢኮኖሚክስ ከፍተኛ ምሁር ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ ከጀርመን በስካይፕ ሙያዊ ገለጻ አድርገዋል።
እነዚህንና መሰል ባለሙያዎች ከአገራቸው ወጥተው በከንቱ የውጭ አገራትን እየጠቀሙ መኖራቸው ሊያሳስብ የሚችል ጉዳይ ነው። እነዚህ በጣም ጥቂቱ ሲሆኑ አገራችን አሁንም የሰው ደሃ እንዳልሆነች በስደት የሚገኙ ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች በየተሰማሩበት ሞያ አብረዋቸው ያሉትን የሚያስደንቁና በስነምግባር የታነጹ መሆናቸው በየጊዜው የሚመሰከር ነው።
የመጀመሪያው ስብሰባ የተካሄደው በእንግሊዝኛ ሲሆን በዋሽንግቶን ዲሲና አካባቢው የሚገኙ የተለያዩ ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ የአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ውስጥ ኃላፊነት የነበራቸው አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ነበር።
በሁለተኛው ውይይት ወቅት “በልዩነታችን በመከባበር አዲሲቷን ኢትዮጵያ እንገንባ” በሚል ርዕስ ዙሪያ በርካታ የስብሰባውን ተካፋዮች ስሜት የነካ ዘለግ ያለ ውይይት ተካሂዷል። ይህኛው ውይይት በአማርኛ ቋንቋ የተካሄደ ሲሆን በወቅቱም ቄስ ተጋ ለንዳዶ (ከአሜሪካ)፣ ፊዮሬላ ሮማኖ (በትውልድ ጣልያንና ኤርትራ፤ ከስዊትዘርላንድ)፣ ፈይሣ እስራኤል ኢታንሣ (ከካናዳ)፣ ሼኽ ካሊድ ኦማር (ከአሜሪካ)፣ አካሉ ትርፌ (ከዩክሬን)፣ ሰዋሰው ዮሐንሰን (ከኖርዌይ)፣ ነጋሲ በየነ (ከአሜሪካ)፣ ዲባባ አመሌ (ዩኬ)፣ ዮሐንስ በርሔ (ካናዳ)፣ ሐምራዊት ተስፋ (ከአሜሪካ) እና መምሬ ፍሬሰንበት (ከአሜሪካ) ከመድረኩ ንግግር አድርገዋል። ከጋራ ንቅናቄው በኩል ዳዊት አጎናፍር ከዋና ዳይሬክተሩ ኦባንግ ሜቶ ጋር በመሆን ውይይቱን ሲመሩ አምሽተዋል። ሼኽ ካሊድ ኦማር እና ሰዋሰው ዮሐንሰን ባደረሱት የመግቢያ ጸሎተ ቡራኬ ስብሰባው ሲጀምር መምሬ ፍሬሰንበት የማሳረጊያውን ቡራኬ አቅርበዋል።
ተሳታፊዎቹ የየትኛውንም የፖለቲካ፣ የዘር፣ ጎሣ፣ … ቡድን ሳይወክሉ በቅድሚያ ሰው በመሆናቸው ሲቀጥልም በኢትዮጵያዊነታቸው “ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ ሊሆን አይችልም” በሚል መሪ ሃሳብ አዲሲቷን ኢትዮጵያ መገንባት የሚቻልበትን መንገድ እና ቅን ፍላጎታቸውን በግልጽ ከልብ አስረድተዋል። በተደጋጋሚ ሲነገር እንደሚሰማው በህወሃት/ኢህአዴግ ላይ ጣት ከመጠቆም ይልቅ በኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች ውስጥ የተዘራውን መርዝ እንዴት መንቀል እንደሚቻል፤ የእያንዳንዱን ሰው ልዩ መሆኑን እንዲያም ሲል ባህሉን በማክበር እንዴት ግንኙነትን ማበልጸግ እንደሚቻል፣ እርስበርስ በመከባበር ያለፉትን በደሎች በመወያየት እንዴት ለወደፊቱ ትውልድ አዲስ የዕርቅ ምዕራፍ በመክፈት ሁሉም ከፈጣሪውና ከጎረቤቱ ጋር መስማማት እንደሚችል፣ እርስበርስ ክፍፍልና ጥል ሳይኖር በልዩነት መስማማት እንዴት እንደሚቻል፣ ወደነበርንበት በመመለስና በመካከላችን የተከሰተውን በማረቅ እውነት፣ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ መከባበርና ፍቅር የሰፈነባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያ መመሥረት እንዴት እንደሚቻል፣ ወዘተ ስሜት መሳጭ፣ ዓይን ከፋችና ማራኪ ውይይት በመድረኩ ከነበሩትም ሆነ ከጉባዔተኛው በጥያቄና መልስ ቀርቧል።
የጋራ ንቅናቄው ስብሰባውን በሚያዘጋጅበት ወቅት የትኛውንም መለየት ስላልፈለገ በዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው ኤምባሲ አምባሳደር ግርማ ብሩ ከስብሰባው 11 ቀናት በፊት የጥሪ ደብዳቤ ቢልክም ከኤምባሲው ተወክሎ በመምጣት በስብሰባው የተገኘ ማንም ሰው አልነበረም። ዋና ዳይሬክተሩ ኦባንግ ሜቶ በአኢጋን ስም በላኩት በዚህ ደብዳቤ ላይ የስብሰባውን ሁኔታ ሲያስረዱ እንዲህ ብለው ነበር፡-
“ይህ የፖለቲካ ስብሰባ አይደለም፤ ነገር ግን ይህ ስለ ኢትዮጵያ ግድ የሚላቸው ወገኖች ተሰባስበው ውይይት ስለሚያደርጉበት ሁኔታ መድረክ ለመፍጠር የታቀደ ነው፤ ይህንን በማመን ነው እርስዎም የዚህ ውይይት አካል እንዲሆኑ የጋበዝንዎት፤ ይህ “መንግሥትን ስለመቃወም ወይም ስለመደገፍ” የሚካሄድ ስብሰባ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዳይ ለመመካከር ነው፤ የስብሰባው ተሳታፊዎች በወገኖች መካከል የሚኖር የሃሳብ ልዩነቶችን ያከብራሉ ተብለው ይጠበቃሉ፤ ነገርግን የኢትዮጵያውንን ጨዋነትና የውይይት ስልጣኔ በማሳየት በኩል ምሳሌያዊ ሆኖ የሚካሄድ ስብሰባ በመሆኑ እርስዎም ሆነ የሚመጡት የኤምባሲው ተወካዮች በዚህ ረገድ ለመሳተፍ ደኅንነት ሊሰማቸው ይገባል፤ ይህንን ደግሞ እኔ ስብሰባው ሲጀመር በይፋ በመናገር የማስታውቀው ሲሆን ማንም ሰው ከማንም ጋር የሃሳብ ስምምነት ቢኖረውም ባይኖረውም አክብሮትና ትህትና ማሳየት እንደሚጠበቅበት ይህ ደግሞ ሌሎችን ስለማክበር የምንማርበት መድረክ እንደሚሆን በግልጽ በመክፈቻው የማስረዳው ጉዳይ ይሆናል፤ ይህ አስተሳሰብ ደግሞ አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመመሥረት የሚያስፈልግና የአኢጋን ዋና መመሪያ ነው፤ እንዲህ አይነቷ ኢትዮጵያ ለሁሉም ቦታ ይኖራታልና።” (የደብዳቤው ሙሉ ቅጂ እዚህ ላይ ይገኛል)
ስብሰባው በወቅቱ ከሚካሄድበት ቦታ በቀጥታ ስርጭት በዓለም ዙሪያ የተላለፈ በመሆኑ ውይይቱን በአካል ተገኝተው መከታተል ያልቻሉ ወገኖች ባሉበት ለመከታተል ችለዋል። የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ስለ ውይይቱ ዘገባዎችን ያቀረበ ሲሆን በተለይ ስለ ውይይቱ ጠቅለል ያለ ዘገባ የተጠናቀረበት የድምጽ ሪፖርት እዚህ ላይ ይገኛል። ኢሣትም በበኩሉ የቀረጸው ቪዲዮ እዚህ ላይ ይገኛል። ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ፣ ከኢሣት፣ እንዲሁም ከሌሎች ድረገጾች፣ የሬዲዮ ጣቢያዎችና የሚዲያ አካላት ላገኘነው ትብብር ምስጋናችንን እናቀርባለን። በአኢጋን የሚዲያ ሰዎች በዕለቱ የተካሄደው ሙሉ ውይይት እንዲሁም ከስብሰባው በፊት በተደረገው የራት ግብዣ ላይ ከወገኖቻችን የሰማነው እጅግ ስሜትን የሚነኩ፣ ትምህርታዊና ልባዊ የሆኑ ንግግሮች ተቀርጸዋል።
የጋራ ንቅናቄው እያንዳንዱ ሰው የሚናገረውና የሚያካፍለው ታሪክ እንዳለው ያምናል። ከዚህም እያንዳንዳችን መማር ስለምንችል ስለሌሎች ከመነጋገር ይልቅ እርስበርሳችን ስለራሳችን ታሪክና ልምምድ በመነጋገር ብዙዎችን ሊያስተምሩ የሚችሉ ጠቃሚ ትምህርቶችን መለዋወጥ አለብን። ይህ ደግሞ በአንድ ስብሰባ ብቻ ተጀምሮ መጠናቀቅ ያለበት ሳይሆን ኢትዮጵያውያን በሚገናኙበት ቦታ ሁሉ ለቡና ስንሰባሰብ፣ በቤ/ክን ወይም በመስጊድ፣ በኮሙኒቲ ማኅበረሰቦች፣ ወይም በቤታችን ውስጥ በምግብ ጠረጴዛችን ላይ፣ ወዘተ በተደጋጋሚ እየተነገሩና ልምምድ እየተካፈልንባቸው የምንሄድባቸው ሊሆን ይገባል። ስለሌሎች ከመነጋገር ይልቅ እርስበርሳችን መነጋገር፤ ልምምዳችንን መለዋወጥ፤ አንዳችን ከሌላው ትምህርት መውሰድ፤ ይህንን ትምህርት ደግሞ ለሌሎች ማስተላለፍ፤ ማስተጋባት፤ በክፉው ከመጠመድ ይልቅ መልካሙን ለራስ በማድረግ ይህንን ይበልጥ በማኅበረሰባችን ውስጥ ማስፋፋት፣ ማበልጸግ፣ ደግሞ ደጋግሞ ያለማቋረጥ ማስተጋባት!
ማጠቃለያ
በመካከላችን ስላሉት ችግሮች መነጋገር እንዳለብን ግልጽ ነው። ሆኖም ይህ ከመንግሥት ጋር ዕርቅ መፈጸም፤ ወይም በተለያዩ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች መካከል ዕርቅ መፈጸም ማለት አይደለም። ነገር ግን እርስበርሳችን በመነጋገር ወደ አንድ ዓላማ ለመምጣት አብረን መሥራት ማለት ነው። ይህንን ዓይነቱ ውይይት በቀጣይነት ፍሬያማ የሚያደርገው አስቸጋሪ ወይም ውስብስብ ናቸው በምንላቸው ጉዳዮች ላይ በመከባበር እና ስለሌላው በማሰብ መወያየት ስንችል ነው። ስለዚህ በስሜት እየተነዳን ከምንጠቀማቸው ቃላቶችና አነጋገሮች መቆጠብ ይገባናል። ምክንያቱን ጉዳት ያደርሳሉ፤ ግንኙነት ላይ ትልቅ ችግር ያመጣሉ፤ ለመግባባት እንቅፋት ይፈጥራሉ። የዚያኑ ያህልም የሚነገሩ ነገሮችን ሁሉ እኛን በግል ለመጉዳት የተነገሩ አድርገን በመውሰድ ችግሮችን ከማቀጣጠል ይልቅ አንዳንዴ ሆደ ሰፊ በመሆን ለምናልመው ታላቅ ሃሳብና ዕቅድ ቅድሚያ በመስጠት ቸል እያልን ማለፍን መማርም ያስፈልጋል። በዚህ ዓይነት ሁኔታ መተማመን የምንችልበት ሁኔታ ላይ ከደረስን እንደ አንድ ቡድን በመሆን ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የምንችልበትን ሥራ እንደ አንድ ቡድን ሆነን መሥራት እንጀምራለን። ይህ እየቀጠለ ሲሄድ ለችግሮቻችን፣ ለቅሬታዎቻችን፣ ለተግዳሮቶቻችን፣ ወዘተ በቀላሉ መፍትሔዎችን ማግኘት እንችላለን።
ስለዚህ ሰላምን የመፍጠር ባህል በውስጣችን ሊዳብር ይገባል። ይህ ሊሆን የሚችለው እውነትን በትህትና ስንናገር፣ ፍትህንና ከበሬታን ለጎረቤቶቻችን (ለሌሎች) ለመስጠት ስንመኝ፣ የሕግን የበላይነት በልባችን በመጠበቅ በስነምግባር የታነጽን ሐቀኛ ሰዎች ስንሆን ነው። የዘርን፣ የሃይማኖትን፣ የፖለቲካን እና የሌሎችን ግድግዳዎች በማፈራረስ ከፈጣሪ በተሰጠን ኃላፊነት በሐቅ ላይ ሳንመቻመች የሰላም መልዕክተኞችና ሰላም ፈጣሪዎች መሆን የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው። ይህ ቀላል አይደለም፤ ብዙ ጊዜ እንደሚባለው “የሚያስቸግር ነገር ማለት የማይቻል ማለት ሳይሆን ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ማለት ነው”።
የጋራ ንቅናቄያችን ከዚህ ውይይት የተማረው ነገር ቢኖር ይህንን መፈጸም የሚቻል መሆኑን ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች በተግባር አከናውነውታል። ከዚህ ጅማሬ በመነሳትም በሌሎች ቦታዎችም ይህንን መሰል ውይይቶች እንዲካሄዱ እናስባለን፤ እናቅዳለን። ስለዚህም በመጪው የአውሮጳውያን አዲስ አመት የጸደይ ወራት በአውሮጳ ሌላ የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ይቻላል የሚል ተስፋ አለን።
ፈጣሪ ለሁላችንም ለመስማት የፈጠነ ለቁጣ የዘገየ፤ ይቅርታን ለመጠየቅም ሆነ ለመስጠት የተዘጋጀ ትሁት ልብ ይስጠን። በመሆኑም ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ብቻውን ነጻ መውጣት ስለማይችል ከዘር ይልቅ ሰብዓዊነትን ከፍ አድርገን የምንሰብክበትን ማኅበረሰብ ለመገንባት እንድንችል ፈጣሪ ሁላችንንም ይርዳን፤ ቅን ልብ ይስጠን።
ለተጨማሪ መረጃ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶን በዚህ ኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡- Obang@solidaritymovement.org
Leave a Reply