የሰማያዊ ፓርቲ እሁድ መጋቢት 20 ቀን በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፍ አካሂዷል፡፡ በትዕይንቱ የወጣው ሕዝብ ነጻነት እንደሚፈልግ፤ ስቃይ፣ አፈናና ስደት እንደበቃው ባሰማው መፈክር አሰምቷል፡፡
ነገረ ኢትዮጵያ ከፎቶዎች ጋር በማጀብ ከሰልፉ ዝግጅት ጀምሮ በየሰዓቱ በፌስቡክ በለቀቀው መረጃ መሠረት አዲስ አበባን ጨምሮ በጅማ፣ በአዲስ አበባ፣ በሶዶ፣ በአርባ ምንጭ፣ በጭሮ፣ በደብረ ታቦር፣ በወልቂጤና ሌሎችም ከተሞች ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡
እንደተለመደው የኢህአዴግ ፖሊስ ሰልፉን በማጨናገፍ፣ ተሰላፊው ሰልፉን ጀምሮ ለማብቃት የወሰነበት ቦታ እንዳይደርስ በመከላከል ድርጅታዊና ወገናዊ ሥራውን አከናውኗል፡፡
በየከተማው በተካሄደው ትዕይንተ ሕዝብ ሰልፈኞቹ የሚከተሉትን መፈክሮች አሰምተው እንደ ነበር ከዜናው ዘገባ ለመረዳት ተችሏል፡
ነፃነት እንፈልጋለን፣ ነፃነት፣ ነፃነት!
መንግስት በእምነት ጣልቃ አይግባ!
ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነት ይፅዳ!
ህገ መንግስቱ ይከበር!
የፖለቲካ እስኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ!
ጋዜጠኞች ይፈቱ!
የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ይፈቱ!
አምባገነንነትን እንታገላለን!
ፖሊስ ለገዥው ፓርቲ መሳሪያ መሆን የለበትም!
ድል የህዝብ ነው!
ኢህአዴግ መንገድ ሊመርጥልን አይችልም!
ምርጫ ቦርድ ከኢህአዴግ ራሱን ነጻ ያውጣ!
በምርጫ ስም የሚደረግ ማጭበርበር ይቁም!
አምባገነናዊ ስርዓት ያብቃ!
የምርጫው ምህዳር ይስተካከል!
ስቃይ፣ አፈና፣ ስደት፣ ይብቃን!
በአዲስ አበባ የተካሄደው ትዕይንት መነሻውን ከስማያዊ ጽ/ቤት ካዛንቺስ አድርጎ በአምስት ኪሎና በግንፍሌ በኩል በቤልኤር ሜዳ ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ሰልፈኛው ቤተመንግሥት አካባቢ ሲደርስ በፌዴራል ስም የሚንቀሳቀሰው የኢህአዴግ ፖሊስ ሰልፈኛውን “በቤተ መንግስት ማለፍ ህገወጥነት ነው!” በማለት እንዳያልፍ አስመልሶታል፡፡ በቀጣይም ሰልፈኛውን እንዳስቆመው ነገረ ኢትዮጵያ በገጹ ላይ ዘግቧል፡፡ ከዚያው ገጽ ላይ ያገኘነውን አዲሰ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የተካሄደውን ሠልፍ የሚያሳይ ፎቶ ከዚሁ ጋር አያይዘን አቅርበናል፡፡ (ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ)
Leave a Reply