ለእኔ ፖሊቲካና የግለሰብ ጠባይ እንደውሃና ዘይት የማይደባለቁ ነገሮች ይመስሉኛል፤ አጼ ምኒልክ ‹‹አመልህን በጉያህ›› ያሉት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፤ ዘይትና ውሀ በባሕርያቸው የሚለዩትን ያህል ፖሊቲካና ግለሰብም የባሕርይ ልዩነት አላቸው ማለት ነው፤ የወያኔ መሪዎች ምንም ነገር የማይሰምርላቸው፣ ከመጀመሪያውኑ እነዚህን ሁለት የማይደባለቁ ባሕርዮች አደባልቀው በመንሣታቸው ነው፤ ፖሊቲካ ለማኅበረሰቡ መቆርቆር ነው፤ ለሕዝቡ መቆርቆር ነው፤ ለአገር መቆርቆር ነው፤ የፖሊቲካ መነሻም ይኸው መሆን አለበት፤ ዓላማውም የማኅበረሰቡ፣ የሕዝቡ ልማት እንጂ ጥፋት አይደለም፤ የነበረውንና ያለውን ማጥፋት የፖሊቲካ ዓላማ ሊሆን አይችልም።
የደርግ መንደር ምሥረታ የሕዝብ ዓላማ ነበረው፤ የዓላማው መሣሪያ ግን የሕዝብ ሳይሆን ወታደራዊ ጉልበት ነበር፤ በዚህም ምክንያት የሕዝብ ዓላማ ያለው ሥራ የሕዝብን ህልውና በሚፈታተን የጉልበት መንገድ መከተሉ ዓላማው እንዳይሳካ፣ ሕዝብና አገዛዙ ባላንጣዎች ሆኑ፤ ጥሩው ዓላማ በከሸፈ ጉልበተኛነት ሳይሳካ ቀረ፤ በመንደር ምሥረታው ዓላማ ደርግ ክፋት ወይም ቂም ቋጥሮ አልተነሣም፤ ስሕተቱ ከውትድርና ባሕርይ የመጣ ይመስለኛል።
ማጥፋት ዓላማ ሲሆንና ጉልበት የማጥፋት መሣሪያ ሲሆን ፍጹም የተለየ ነው፤ማጥፋት የሚመጣው ከግል ጠብና ከግል ቂም ነው፤ የራሱን ወይም የአባቱን፣ ወይም የእናቱን ቂም በልቡ ቋጥሮ ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባ ሰው ለጥፋት የተዘጋጀ ነው፤ ለጥፋት የተዘጋጀ ሰው ፖሊቲካ ውስጥ ሲገባ እሳት አደጋ መኪና ላይ ቆሞ ቤት እንደሚያቃጥል ሰው ነው፤ አታላይ ነው፤ ዓላማውንም የዓላማውንም መሣሪያ አያውቅም፤ የሚንቀሳቀሰው በጥላቻና በቂም ነው፤ ወይ የሕጻን ልጅ ወይም የተስፋ-ቢስ ደደብ ጠባይ ነው፤ እንዲህ ያለ ሰው ፖሊቲካ ውስጥ የሚገባውም በዚሁ በደደብነቱ ምክንያት ነው፤ የደደቡ ፖሊቲከኛ ሥራ የማያስወቅሰው ፖሊቲከኛውን ብቻ አይደለም፤ በዚያ ፖሊቲከኛ የሚመራው ሰው ሁሉ አብሮ የሚወቀስ ነው፤ እንዲያውም በፖሊቲከኛው እውቀትና ችሎታ ማጣት የተነሣ የሚደርሰው ስቃዩና መከራው፣ ችግሩና አበሳው በዚህ ዓይነቱ ፖሊቲከኛ ላይ አይደርስም፤ ሰቃዩንና መከራውን፣ ችጋሩንና አበሳውን የሚጋፈጠው በዚህ ዓይነቱ ፖሊቲከኛ የሚመራው ሕዝብ ነው፤ ሕዝብ መሪውን በትክክል መምረጥ ያለበትም ለዚህ ነው፤ ተንጋሎ የተፋ ለራሱ ከፋ የሚባለው ይደርሳል።
ዛሬ እያጎረሰ ምረጠኝ የሚለው ነገ ቆዳህን ልግፈፍ ይላል፤ እንደምንሰማው ወደቦሌ አካባቢ ‹መቀሌ› የሚባል የሰማይ-ጠቀስ ፎቆች መንደር አለ ይባላል፤ የዚህ መንደር ባለቤቶች የወያኔ ባለሥልጣኖች ለመጦሪያቸው የሠሩአቸው ናቸው ይባላል! በአንጻሩ እኔ የማውቀው አንድ ወያኔ አለ፤ በውጊያ ላይ በደረሰበት ጉዳት ይመስለኛል አንድ ዓይኑን ክፉኛ የታመመ ነው፤ ስለሚሸፍነው የጉዳቱን መጠን ባላውቅም ጉዳቱ ይሰማኛል፤ ሚስትና ሁለት ልጆች አሉት፤ ሚስቱ ጠዋት በጀርባዋ ከባድ ነገር አዝላ ልጆቿን ወደተማሪ ቤት ታደርሳለች፤ እንደምገምተው አንድ ቦታ ገበያ ዘርግታ የምትሸጠውን ትሸጣለች፤ ወደማታም እንደጠዋቱ ተጭና ወደቤትዋ ከልጆችዋ ጋር ትመለሳለች፤ የዚህ አንድ ጉዳተኛ ወያኔ ቤተሰብና የባለሰማይ-ጠቀስ ሕንጻ ባለቤቶች የሆኑት ወያኔዎች ኑሮ የሰማይና የመሬት ያህል የተራራቀ ነው፤ ለአንድ ዓላማ አብረው የተነሡ ሰዎች በሃያ ዓመታት ውስጥ ይህንን ያህል መራራቃቸው በጣም ያሳዝናል ብሎ ማለፉ አይበቃም፤ ደሀው ወያኔ ሕመሙንና ስቃዩን የምገነዘብበት መንገድ ባይኖረኝም አንድ ዓይኑን ማጣቱ ብቻ ጉዳቱን ያሳየኛል፤ እንግዲህ ባለሰማይ-ጠቀስ ወያኔዎችና ይህ ደሀ ወያኔ በጦርነት ላይ ያደረጉት አስተዋጽኦ በጉዳታቸው ቢመዘን የዚህ ደሀ ወያኔ እንደሚበልጥ አልጠራጠርም፤ ቢያንስ እንደአንዳንድ መሪዎቹ አልሸሸም፤ ታዲያ በምን ተበላልጠው እነሱ እዚያ ላይ እሱ እዚያ ታች ሆኑ? ይህንን አሳዛኝና አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ሁነት የሚያመጣው እሳት አደጋ መኪና ላይ ቆሞ ቤት እንደሚያቃጥለው ሰው ያሉ ፖሊቲከኞች-ነን-ባዮች የተዛባ ሚዛን ነው፤ በዚህ የተዛባ ሚዛን በየጦር ሜዳው አሞራ የበላቸው የታደሉ ናቸው፤ ተስፋቸው ትርጉም አጥቶ ሳያዩ፣ ውርደት ሳይሰማቸው፣ ችግርንና ግፍን ሳይቀምሱ ቀርተዋል፤ ለነገሩ ነው አንጂ እንኳን ወያኔ በሥልጣን ምኞት ከወገኑ ጋር የተዋጋውና ከኢጣልያ ወራሪ ጦር ጋርም የተዋጉት አርበኞችም ተመሳሳይ ዕድል ገጥሟቸው ነበር፤ ዛሬ ኢትዮጵያን ለክፉ ነገር የዳረጋት የእነዚህ ሰዎች ጡር ይመስለኛል።
የፖሊቲካ ተግባሮቻቸውን ከግል ጠባዮቻቸው እየለዩ የሚኖሩ ፖሊቲከኞች በአንዳንድ አገር አሉ ለማለት ይቻላል፤ ከአውሮፓ ስዊድንና ኖርዌይ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ከእስያ ዛሬን እንጃ እንጂ በነኔህሩ ዘመን ህንድ የሚጠቀስ ነበር፤ በአብዛኞቹ አገሮች ግን ፖሊቲከኞቹ እንደየደረጃቸው ለሀምሳ፣ ለሠላሳ፣ ለሀያ፣ ለአሥር ሰዎች የሚበቃ የተሟላ ቤት ውስጥ አምስት መቶ ሰዎችን የሚያስተዳድር ደመወዝ እያገኙ የሚኖሩ ሲሆኑ ምግባቸው ግን አብዛኛውን ጊዜ የአንድ ሰው ይመስለኛል፤ የዚህ ትርጉሙ ምንድን ነው? ለፖሊቲከኞቹ መቀማጠል በላባቸው የሚከፍሉት ደሀዎች ናቸው፤ ከተፎካካሪዎቻቸው ተንኮል የሚጠብቋቸው ደሀዎች ወታደሮች ናቸው፤ ምርጫ ሲደርስ በነቂስ ወጥተው ፖሊቲከኞቹን የሚመርጧቸው ጦማቸውን የሚያድሩት ደሀዎች ናቸው፤ እነዚህም ጊዜያዊና ትንሽ የግል ጥቅምን ከዘላቂው የአገርና የሕዝብ ጥቅም መለየት ያልቻሉ የሕዝብ ክፍሎች ከተበላሹት ግለኛ ፖሊቲከኞች የማይለዩ ናቸው።
ወደፍሬ ነገሩ ልምጣና፤- በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ፖሊቲከኞች የሚወጡትና የሚወርዱት ለየትኛው ዓላማ ነው?
- የበትረ መንግሥቱን ሥልጣን ከወያኔ ፈልቅቆ ለማውጣትና ለመያዝ?
- በምክር ቤት ገብቶ የወያኔ አጫፋሪ በመሆን ደህና ደመወዝና ነጻ ቤት ለማግኘት?
- ከውስጥ ሆኖ ወያኔን ለማጋለጥ?
የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖሊቲካ ቡድኖችን ሲደግፍ የፖሊቲካ ቡድኖቹን ዓላማዎች አጣርቶ በማወቅ መሆን አለበት፤ አለዚያ በሎሌነት እየኖሩ ጌታ መለወጥ ነው።
ግንቦት 2006
Leave a Reply