* ደርግ የረሸናቸው የንጉሡ ባለሥልጣናት 60 አይደርሱም ተብሏል
* መፈንቅለ መንግሥቱ ቢሳካ ኖሮ ኤርትራ ከመገንጠል ትድን ነበር?
* በዓሉ ግርማ መገደሉን ኮሎኔል ፍስሃ በመጽሐፋቸው ይፋ አድርገዋል
በደርግ ዘመን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉትና በመጨረሻም የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተናል ኮሎኔል ፍስሀ ደስታ፤ከ20 ዓመት እስር በኋላ የፃፉት “አብዮቱና ትዝታዬ” የተሰኘ መፅሐፋቸው፤ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሂልተን ሆቴል ሲመረቅ አብዛኛውን ታዳሚ ለክርክር ጋብዟል፡፡ ደግነቱ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ ከታደሙት አብዛኞቹ የ1960ዎቹ ትውልድ አባላት ነበሩ፡፡ የደርግ ባለሥልጣናት፣ ከፍተኛ የጦር አዛዦች እንዲሁም ከደርግ በተቃራኒ ቆመው ሲፋለሙ የነበሩ የኢህአፓ፣ መኢሶንና ሌሎች በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት በታደሙበት መድረክ የታሪክና የህግ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችም ተገኝተዋል፡፡
ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ካሣሁን ብርሃኑና ገጣሚና ፀሐፌ-ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በመፅሐፉ ላይ የዳሰሳ ፅሁፍ ያቀረቡ ሲሆኑ የታሪክ ተመራማሪውና ምሁሩ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ደግሞ ውይይቱን በአጋፋሪነት መርተዋል። አጋፋሪነታቸው ታዲያ በየመሃሉ የራሳቸውን አስተያየት ከመሰንዘር አላገዳቸውም፡፡ እንደውም ሳይመቻቸው አልቀረም፡፡
“ኮሎኔል መንግሥቱ ሀገር ወዳድ ናቸው አይደሉም?”
ኮ/ል ፍስሀ ደስታ በመፅሀፋቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን በተመለከተ ባሰፈሩት ጽሁፍ፤“በመጨረሻ አበላሸው እንጂ ወደ ዚምባቡዌ እስከ ሸሸበት ጊዜ ድረስ አገር ወዳድ መስሎኝ ነበር” የሚል ሀሳብ ያሰፈሩ ሲሆን የዳሰሳ ፅሁፍ አቅራቢው ዶ/ር ካሳሁን ግን ኮ/ል መንግሥቱ አገር ወዳድ መሆኑን በፍፁም እንደማይቀበሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ “ከራሳቸውና ከስልጣናቸው በኋላ አገራቸውን ይወዱ እንደሆነ አላውቅም” ያሉት ምሁሩ፤ “አገራቸው ጥሩ ነገር ብታገኝ ይጠላሉ ብዬ አልደመድምም፡፡ ከሁሉ በላይ ራሳቸውንና የግል ጉዳያቸውን አስቀድመው፣ ከዚያ በኋላ አገራቸውን ከወደዱ ደግሞ አብሮ የሚሄድ ነገር አይደለም” ብለዋል፡፡ “ለምሳሌ ትግራይ ለጠመኔ መግዣ አያዋጣም የሚል መሪ አገር ወዳድ ነው? የሰሜን ሸዋ ሰው ዘምቶ እንጂ ተዘምቶበት አያውቅም በማለት ህዝብን የሚቀሰቅስ መሪ አገሩን የሚወድ ነው ወይ?” ሲሉም ዶ/ር ካሳሁን ሞግተዋል።
“ኮ/ል መንግሥቱ አገር ወዳድ ቢሆኑ ኖሮ እንደ አፄ ቴዎድሮስና እንደ አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን ለመስጠት ፍቃደኛ ይሆኑ ነበር” ያሉት ምሁሩ፤እሳቸው ግን ወሳኙ ጊዜ ሲመጣ አገራቸውን፣ ህዝባቸውንና ሰራዊታቸውን ጥለው ሸሽተዋል፤ሲሉ ተችተዋል፡፡ እሳቸውን ተከትሎ አስተያየቱን የሰነዘረ አንድ ታዳሚ በበኩሉ፤“ኮ/ል መንግሥቱ ምን ማድረግ ነበረባቸው ነው የሚሉት? ራሳቸውን ማጥፋት ወይስ ሌሎች እስኪያጠፏቸው መጠበቅ ነበረባቸው?” ሲሉ ጠንከር ብለው ጠይቀዋል። ጽሁፍ አቅራቢው ሲመልሱም፤“ምንም ይምጣ ምንም ራሱንም ያጥፋም ይትረፍም በወቅቱ አገር ጥሎ ባይወጣ፣ ታሪክ ሌላ መልክ ይኖረው ነበር” ብለዋል፡፡
ይሄኔ ከጎኔ የተቀመጡ ራሽያ የተማሩ አንድ ጠና ያሉ ሰው ወደ እኔ ጠጋ ብለው፤ “ኮ/ል መንግሥቱ በውጭ ሀይሎች በተለይ በአሜሪካና በCIA ግፊትና ጫና “አንተ ካልወጣህ ህዝብ ያልቃል” ተብለው መውጣታቸውን ኮ/ል ፍስሀ አያውቁም ማለት ነው ወይስ መናገር አልፈለጉም?” ሲሉ በጆሮዬ ሹክ አሉኝ፡፡
ክርክሩ እንደቀጠለ ነው፡፡ በንጉሱ ዘመን በትግራይና በወሎ ረሀብ ተቀስቅሶ፣ ከ200 ሺህ በላይ ህዝብ ሲረግፍ ባለስልጣናቱ አይተው እንዳላዩ በመሆን ወገን እንዳይደርስላቸው ደብቀው ከማቆየታቸው አንጻር፣ ፍርዳቸው በአግባቡ ታይቶ ቢሆን ኖሮ፣ በሞት መቀጣት ይገባቸው ነበር” ሲሉም ዶ/ር ካሳሁን በተደጋጋሚ ቁጭታቸውን ገልፀዋል፡፡ ይሄ ሃሳባቸው ግን ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል፤ያውም ከውይይቱ አጋፋሪ ከፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀኝ፡፡
በዶክተሩ ሀሳብ በአብዛኛው እንደሚስማሙ በመግለጽ ነበር ወደ ተቃውሟቸው ያለፉት፡፡ “ረሀቡን የደበቁትን ባለስልጣናት በሞት መቀጣት ነበረባቸው ብለህ ከአንዴም ሁለት ጊዜ በመናገርህ በጣም ደንግጫለሁ” ያሉት ፕ/ሩ፣ በ“21ኛው ክ/ዘመን የሰለጠኑት ሀገራት የሞት ቅጣት የሚባለውን ነገር ለማስቀረት በሚታገሉበት ወቅት እኛ በብዙ ችግሮች የተከበብን የታዳጊ አገር ህዝቦች ስንቱን ስንገድል ልንኖር ነው? ስንቱንስ ስንሰቅል ልንኖር ነው?” ብለዋል፡፡
ከትላንት ወዲያ በአንድ ጋዜጣ አንድ ወጣት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አዲሱ ሚኒስትር ይመስለኛል፣“ያጠፋ ሃላፊ ይሰቀል” ብሏል ያሉት ፕ/ሩ፤“ይህ የመንግሥት ፖሊሲ ነው ወይስ ባልበሰለ አንደበት የሚነገር ጉድ ነው? የመንግሥት ፖሊሲ ከሆነ እንደገና ታጥቦ ጭቃ ሊሆን ነው፤ ስለዚህ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል” ሲሉ ምክር ለግሰዋል፡፡
ሌላው የዳሰሳ ፅሁፍ አቅራቢ ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ አያልነህ ሙላቱ፤ በማርፈዳቸው ይቅርታ ከጠየቁ በኋላ ያረፈዱበትን ምክንያት በመግለጽ ታዳሚውን ፈገግ አሰኝተዋል፡፡ “አቅም የሌለው ወደ ገጠር ይውጣ በተባለው መሰረት ቤት ሰርቼ የምኖረው ሰበታ ነው፤ ከሰበታ እዚህ ለመምጣት ከቤት የወጣሁት ማለዳ 1 ሰዓት ላይ ነው፤ ግን እስካሁን በጉዞ ላይ ነበርኩ” ብለዋል፡፡ የመጽሐፍ ዳሰሳቸውን ሲጀምሩም፤ “ለወጣቱ ትውልድ ማገናዘቢያ፤ ለታሪክ ለፖለቲካ ማመሳከሪያ የሚሆን ሥራ በማበርከትህ የተሰማኝ ደስታ ከፍተኛ ነው፤ እኮራብሀለሁ” በማለት ለኮሎኔል ፍስሀ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
“እኔ ጸሀፊ እንጂ ሀያሲ አይደለሁም፣የዚህች አገር ስነ-ፅሁፍ ከቀጨጨበት ምክንያቶች አንዱ በቂ ሀያሲያን ባለመኖራቸው ነው” ያሉት አያልነህ፤ በእርግጥ ይህ ችግር የኪነ ጥበቡ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የአገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካውም ችግር ነው፤ብለዋል፡፡ ፖለቲካውንም ሆነ ኢኮኖሚውን የምንሰማው ከመንግሥት አካል እንጂ ራሱን ከቻለ ኤክስፐርት አለመሆኑ ትልቁ የአገራችን ፈተና ነው፤ በየቦታው የሚደነፋው እንደኔ አይነት ደፋር ነው ያሉት ጽሁፍ አቅራቢው፤“በዚህ ትልቅ መፅሀፍ ላይ ሂስ ለመስጠት የተነሳሁት በድፍረትና በአይናውጣነት ነውና ይቅር በሉኝ” በማለት ወደ መፅሀፉ ርእሰ ጉዳይ ገብተዋል፡፡
“መፅሀፉ መታሰቢያነቱ በአመራሩ ስህተት ለተሰው ይሁን፤ደርግ በወሰዳቸው በጎ እርምጃዎች እንደምደሰት ሁሉ ባጠፋቸውም ጥፋቶች ሙሉ ኃላፊነት ወስጄ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እጠይቃለሁ” የሚለው የመፅሀፉ መግቢያ ውስጣቸውን እንደነካው የጠቆሙት አያልነህ፤እስካሁን በወጡ ተመሳሳይ መፅሐፎች ጎልተው የማይታዩ በመሆናቸው ልዩ ክብር የሚታደሉ ሀረጎች ናቸው ብለዋል፡፡ ቀጥለውም የመፅሀፉ ምዕራፎችና ይዘቶች ላይ አጠር አጠር ያለ ምልከታ አቅርበዋል፡፡ የመፅሀፉን የአቀራረብ ስልትም አድንቀዋል፡፡ ከእሳቸው የዳሰሳ ፅሁፍ በኋላ በተካሄደው ውይይትም ብዙ ጉዳዮች አከራክረዋል።
60ዎቹ የንጉሱ ባለሥልጣናት መረሸን
60ዎቹ የንጉሱ ባለሥልጣናት የተረሸኑበት ቀን፣ ኮ/ል መንግሥቱ እንዲረሸኑ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው በደብዳቤ መረጋገጡን በማያሻማ መልኩ በመፃፋቸው እጅግ አድርጌ አመሰግናቸዋለሁ ብለዋል፤ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፡፡ በሌላ በኩል የ60ዎቹን አሟሟት ከኮ/ል ፍስሀ ይልቅ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ፣ በድራማዊ መልክና በውብ ቋንቋ እንዳቀረቡት የገለጹ አስተያየት ሰጪዎችም ነበሩ፡፡ ኮ/ል ፍስሀ ደስታ፤የተረሸኑት የንጉሡ ባለሥልጣናት 60 ሳይሆኑ 54 ናቸው በማለት በመጽሐፋቸው መግለጻቸው ከፍተኛ ክርክር ያስነሳ ጉዳይ ነበር፡፡ ከውይይቱ በኋላ በቁጥሩ ልዩነት ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮሎኔሉ ሲመልሱ፤ “እንደውም 54 ሳይሆኑ ትክክለኛ የንጉሡ ባለሥልጣናት 47 ብቻ ናቸው” በማለት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የደርግ ባለሥልጣናትን በፍርድ ቤት ከስሰው ያስፈረዱባቸው የህግ ባለሙያው አቶ ተሾመ ገ/ማርያም በበኩላቸው፤ስለ ቅርብ ወዳጃቸው ፍስሀ ደስታ የመናገር ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመው፣ ኮሎኔሉ በፀባያቸው ፎልፏላና ቁምነገርን በቀልድ እያዋዙ የሚናገሩ መሆናቸውን ገለጹ፡፡ “እርግጥ ክፉ እንዲነካቸው አልፈልግም፤ ወዳጅነታችን እንዳለ ሆኖ የአገር ጉዳይ በመሆኑ ለሰራችሁት ጥፋት ተከራክሬ እንድትታሰሩ አድርጌያለሁ” አሉ፤የህግ ባለሙያው፡፡ ሆኖም ፕ/ር ገብሩ ጣልቃ ገብተው፣አቶ ተሾመ መፅሀፉን አንብበው እንደሆነ በመጠየቅ አለማንበባቸውን ሲገልጹ፣ተጨማሪ አስተያየት እንዳይሰጡ አግደዋቸዋል- መፅሐፉ ላይ ብቻ እንወያይ በማለት፡፡
በመቀጠል አንድ ጠና ያሉ ታዳሚ የመናገር እድል ተሰጣቸው፡፡ “ይህ ሰው” አሉ አቶ ተሾመን፤ “ይህ ሰው በጃንሆይ ጊዜ የማዕድን ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ነበር፤ የታላቅ ወንድሜ ጓደኛም ነበር፤ሁለታችንም የሲዳሞ ልጆች ስለነበርን እንቀራረብ ነበር፤ የኃይለሥላሴ ባለሥልጣናት እንዲገደሉ ሲያንቀሳቅሰን ነበር፤ የበላበትን ወጪት ሰባሪ ነው፡፡ አሁን ደግሞ እዚህ ቆሞ ሲከራከር የሚያሳዝን ነው —-..” እኚህም ሰው አስተያየታቸው ከመጽሐፉ ውጭ ነው በሚል ከንግግራቸው ተገተዋል። ምንም እንኳን ብዙውን ነገር ተናግረው ከጨረሱ በኋላ ቢሆንም፡፡
የግንቦት ስምንቱን መፈንቅለ መንግሥት በተመለከተ ጽሁፍ አቅራቢው ዶ/ር ካሳሁን በሰጡት አስተያየት፤“መፈንቅለ መንግስቱ ቢሳካ ኖሮ ኤርትራ አትገነጠልም ነበር፤ ሁኔታዎች ከዚህ የተሻለ ይሆኑ ነበር” ይባላል፤በጉዳዩ ላይ ከጓደኞቼም ጋር ብዙ ጊዜ ተከራክሬበታለሁ፤እኔ መፈንቅለ መንግስቱ ቢሳካም ኖሮ ኤርትራ ከመገንጠል ትድናለች፤ መልካም አስተዳደርም ይሰፍናል ብዬ አላምንም” ብለዋል፡፡
ዕውቁ የጦር አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ በበኩላቸው፤ በ17 ዓመት ውስጥ ኮ/ል ፍስሀን ሁለት ጊዜ ብቻ እንዳገኟቸው አስታውሰው፤በወቅቱ ያሳዩዋቸውን ትህትና ከገለፁ በኋላ ኮሎኔሉ በመፅሀፋቸው አንድ የሚቆረቁራቸውን ነገር በማንሳታቸው እንደተደሰቱ ተናገሩ፡፡ “ዩኒቨርሲቲ እያለን የጃንሆይ መንግስትን እንቃወም ነበር፤ ይህን የምናደርገው ፍትህና ዲሞክራሲ ፈልገን ነበር፤ ይህ ፍላጎት ቢኖረንም አንደማመጥም ነበር” ያሉት ብርጋዴር ጄነራሉ፤ ዛሬስ እንደማመጣለን ወይ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “ጠዋት የተነሳንበት ዓላማ ሌላ፣ መንገድ ላይ ስንደርስ የምናደርገው ሌላ” ያሉት ብ/ጄነራሉ፤“አሁን ስልጣን ላይ ላለውም ሆነ ወደፊት አገር ለሚረከበው ወጣት መደማመጥ ካላስተማርነው የምንፈልገውን ሳናይ ሁላችንም እንጠፋለን” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
“የኮ/ል ፍስሀን መጽሐፍ ሳነበው የተፈራረቁ ስሜቶች ነበሩኝ፤ አንደኛ በታሪክ ምሁርነቴ፣ ሁለተኛ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፉት 40 ዓመታት በመካፈሌ፣ 3ኛ በኢትዮጵያዊነቴ” ያሉት ፕ/ር ገብሩ ታረቀ፤“ኮ/ል ፍስሀ ደርግን እንደ አብዮተኛ፣ ኢህአፓን እንደ ፀረ አብዮተኛ ያዩበትን መንገድ በፍፁም አልስማማበትም” ብለዋል፡፡ ኮሎኔል ፍስሀና ኮሎኔል መንግሥቱ ኢህአፓን በቆራጥነቱ አድንቀውታል፤ምክንያቱ ደግሞ የኢህአፓ ዋና መሰረቱ የእምነትና የመንፈስ ፅናት፣አገር ወዳድነትና ህዝባዊ አፍቅሮት ስለነበር እንደሆነ አልጠራጠርም ብለዋል፡፡ ስለ አብዮቱ የኮሎኔል መንግስቱን፣“ትግላችን” እና የሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስን “እኛና አብዮቱ”ን ማንበባቸውን የጠቀሱት ፕ/ሩ፤ በሁለቱም መጻህፍት በኢህአፓ ላይ የተሰነዘረውን ትችት እንደማይቀበሉ ገልጸዋል፡፡ በአጻጻፍ ረገድ ግን የኮሎኔል ፍስሀን “አብዮቱና ትዝታዬ” አድንቀዋል፡፡
የኮ/ል ፍስሀ ደስታ ጋዜጣዊ መግለጫ
በምርቃት ስነስርዓቱ መጨረሻ ኮ/ል ፍስሀ ደስታ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ተጠይቀዋል፡፡ የበዓሉ ግርማ አገዳደል ጉዳይ? በህይወትዎ በጣም የሚቆጭዎትና በጣም የሚያስደስትዎት ምንድን ነው? በ60ዎቹ ባለስልጣናት የቁጥር ልዩነት ዙሪያ እንዲሁም የዛሬዋን ኢትዮጵያ እንዴት ያዩዋታል? — የሚሉ ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡
“በህይወቴ በጣም የሚያስደስተኝ የመሬት አዋጁ ነው” ያሉት ኮ/ል ፍስሀ፤ “ይህን አዋጅ የመሬት ለውጥ ብቻ አድርገው የሚወሰዱት አሉ፤ ነገር ግን በዚህች አገር ላይ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርነቀል ለውጥ ያመጣ አዋጅ ነው፡፡ ይሄ በጣም ያስደስተኛል፡፡ ብለዋል፡፡ በጣም የሚያሳዝነኝና የሚቆጨኝ በተለይ የኤርትራ ጉዳይን መፍትሄ ልናስገኝለት ስንችል ወቅቱ እያመለጠን ሳናደርገው በመቅረታችን፣ በመጨረሻም ኤርትራ በመገንጠሏ ነው ሲሉ መልሰዋል፡፡
ህይወት ለእርሶ ምንድናት ላላችሁኝ፤ ህይወት ለእኔ ውጣ ውረድ ናት፤ በህይወቴ ክፉና ደግ ነገሮች ተፈራርቀውብኛል፡፡ በደረሱብኝ ክፉ ነገሮች አላዘንኩም፤በጥሩዎቹም እስከ መጨረሻው አልተደሰትኩም፤ ህይወትን ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ለዚህም ነው 20 ዓመት በእስር ላይ ተስፋ ባለመቁረጥ በፅናት ቆይቼ እዚህ የደረስኩት፤ የሰው ልጅ የሚሞተው ተስፋ ያጣና ተስፋ የቆረጠ ዕለት ነው፤ያንን 20 ዓመት ረስቸዋለሁ፤እንደውም ከእድሜዬ ላይ ሁሉ እቀንሰዋለሁ ብለዋል፡፡
የበዓሉ ግርማን አሟሟት በተመለከተ ግፊቱ ምን ነበር የሚለውን አስቀምጫለሁ፡፡ በዓሉ መፅሀፉን ከፃፈ በኋላ ሻዕቢያ በሬዲዮ ጣቢያው በዝርዝር ለፕሮፓጋንዳ መቀስቀሻ አደረገው፡፡ በዚህ ጊዜ የጦሩ አባላት በተለይ ኤርትራ ውስጥ የነበረው ጦር፣ በደህንነቱ በፖለቲካው ሁሉ ከፍተኛ አቧራ አስነሳ፡፡ በተለይ ሻዕቢያ በጦሩ ላይ ያደረሰው ስነ-ልቦናዊ ተፅዕኖ ለበዓሉ መገደል ከፍተኛ ግፊት አድርጓል፡፡ ሁለተኛው የበዓሉን መገደል የደህንነት ሚኒስትሩ ናቸው የነገሩኝ፤ ሚኒስትሩ አዎ አልፈዋል፤ በህይወት ቢኖሩም የምደግመው እውነታ ነው፤ አሁን ለምንስ ለማንስ ብዬ እዋሻለሁ? ነገሩኝ ስል በቃ ነግረውኛል፤ ይህን መቀበል አለመቀበል የእያንዳንዱ ሰው ፋንታ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የዛሬይቱን ኢትዮጵያ እንዴት አዩዋት ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤“በእርግጥ ፎቆች ተገንብተዋል፤መንገዶች ተሰርተዋል፤ ሌላ ያየሁት ነገር የለም” ብለዋል፤ ኮሎኔል ፍስሀ ደስታ፡፡
“አብዮቱና ትዝታዬ” የተሰኘው መጽሐፍ በእለቱ በ250 ብር ሲሸጥ የነበረ ሲሆን ብዙዎችም ወረፋ ይዘው ኮሎኔል ፍስሀን በገዙት መጽሐፍ ላይ አስፈርመዋል፡፡ (ናፍቆት ዮሴፍ – አዲስ አድማስ)
Leave a Reply