
የምርጫ ነገር ሲታሰብ ሲነሣ በሁላችንም ልቡና የሚታሰበን ከፊታችን ድንቅ የሚልብን ምርጫ 97ዓ.ም. ነው፡፡ በምርጫ 97ቱ ወቅት መቸም የማይረሱን ጉልህ ጉልህ ጉዳዮች አሉ፡- ያ ምርጫ የወያኔ “ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ አላደለንም” የሚለው የምጸት ጸሎቱ ተሰምቶለት ተአምር ሊባል በሚችል መልኩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከወያኔ የመቋቋም አቅም በላይ መልስ ያገኘበት፣ በዓለም ውስጥ ከታዩት ጥቂት ታላላቅ የሕዝብ ማዕበል ከታየባቸው ሰላማዊ ሰልፎች አንዱ የተደረገበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከየትኛውም ሀገር ሕዝብ በላቀ መልኩ (ይሄንን ስል በድፍረት ነው) ያለውን የበሰለ ፖለቲካዊ (እምነተ-አሥተዳደራዊ) አስተሳሰብና አስደናቂ ሥነ-ሥርዓት (ዲሲፒሊን) ያሳየበት፣ የወያኔን ሲጀመር ጀምሮ ይዞት የነበረውን የውሸት የማስመሰል ዲሞክራሲ (በይነ ሕዝብ) ካባ አስወልቆ እርቃሉን በማስቀረት ትክክለኛ አንባገነናዊ ማንነቱት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያጋለጠበት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሁሉ ያለውን ጠንካራ አንድነት ያሳየበት፣ ተጨባጭ የኢትዮጵያ ተስፋ ለአፍታም ቢሆን የታየበት፣ በሕዝቡ ልቡና ውስጥ ሀገርን ከወደቀችበት ለማንሣት ያለውን የጋለ የተነቃቃ ስሜትና ቁርጠኛ ፍላጎት ያየንበት፣ ወዲያው ተመትቶ ወደቀ እንጅ የንባብ ባሕል የተቀጣጠለበት (እናቶች ሳይቀሩ ጋዜጣ ገዝተው “እባካቹህ አንብቡልኝ?” እስከማሰኘት የደረሰ)፣ ከረጅም ጊዜ ጨፍጋጋና ኃዘን የተሞላ ገጽታ በኋላ በሕዝቡ ገጽታ ላይ ተስፋን የሰነቀ የሞቀ ስሜትና ፈገግታ ደምቆ የታየበት ወዘተ.

እኔ ደግሞ በግሌ አንድ ልዩ ትዝታ አለኝ በዚያ አይረሴ የምርጫ ሂደት ውስጥ ጎልቶ ይታይ የነበረው በየ የምረጡኝ የምርጫ ቅስቀሳና የክርክር መድረኮች ላይ ይገለጽ የነበረው የየፓርቲው መሪ ቃል (slogan) ነበር፡፡ ከእነዚህ መሪ ቃሎች ውስጥ የቅንጅትና የኢሕአዴግ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎች ሳይቀር ልዩነታቸውን በማንሣትም ጭምር ተደጋጋሚ ሽፋን ተሰጥቶት ነበር፡፡ እነዚህ መሪ ቃሎች የየፓርቲውን የብስለት፣ የአስተሳሰብ፣ የንቃተ ሕሊና ልዩነቶች አጉልተው ያሳዩ ነበሩ፡፡ የቅንጅትንና የኢሕአዴግን ብናይ የነበራቸው ልዩነት የኋላ ቀርና የዘመናዊ (የአናሎግና የዲጂታል) የዛሬና የነገ፣ የገጠርና የከተማ ያልሠለጠነና የሠለጠነ ያህል ዓይነት ነበር፡፡ የኢሕአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ መሪቃል “ ንብን ይምረጡ! ንብ ታታሪ ሠራተኛ ናት፤ ንብ ማር ትሰጣለች ንብን ይምረጡ!” የሚል ነበር የቅንጅት ደግሞ “ ቅንጅትን አለመምረጥ መብት ነው፤ ግን የሀገርን የስቃይ የመከራ የችጋር የፈተና ዘመንን ማራዘም ነው ” የሚል ነበር፡፡ ይሄንን በሚገባ የተረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብም በምርጫ ካርዱ ንቃቱን፣ ብስለቱን፣ ፍላጎቱን፣ ምኞቱን፣ ማንነቱን፣ አቋሙን ባረጋገጠ መልኩ ተናገረ ጮኸ አሰማ አስደመጠ፡፡ በሚያሳዝን መልኩ ወያኔም ይሁን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በእሱ የንቃተ ሕሊናና የብስለት ደረጃ ያሉ ስላልነበሩ ምላሻቸው የሚያሳዝን ሆነ፡፡
“ቅንጅትን አለመምረጥ መብት ነው፤ ግን የሀገርን የስቃይ፣ የመከራ፣ የችጋር፣ የፈተና ዘመንን ማራዘም ነው” ይህ መሪ ቃል የእኔ ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Leave a Reply