
ከዓመታት በፊት “ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ ነው” የሚለውን ጨምሮ ብዙ እንግዳ የሆኑ ነገሮችን የሚናገሩ ሦስት “አባቶችን” አውቅ ነበር አንደኛው ከሀገር ውጭ ናቸው፡፡ እነኝህ “አባቶች” ተከታዮች እያፈሩ መጡና ዛሬ ላይ እነሱ የሚሉትን የሚያምኑ ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባሉ ሰዎችን እያየን ነው፡፡ እነዚህን እንግዳ አስተምህሮዎቻቸውንም በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (social media) በከፍተኛ ደረጃ እየናኙት ይገኛሉ፡፡ እውን ግን የናዝሬቱ ኢየሱስ መሲሑ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ ነው?
ይሄንን ብለው እየሰበኩ ያሉ “አባቶች” ይሄንን ትምህርታቸውን በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ወይም ትውፊታዊ መረጃ በመስጠት አያረጋግጡም፡፡ የሆነ የራሳቸውን ነገር ይቀበጣጠሩና ክርስቶስንና ሌሎች ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ አባቶችን ሁሉ ኢትዮጵያዊያን ያደርጓቸዋል፡፡ እነኝህ አባቶች ሲያዩዋቸው የአእምሮ እክል ያለባቸው አይመስሉም፡፡ የሚናገሩትን ሲናገሩ እንደማንኛውም ጤነኛ ሰው ተረጋግተውና በቁምነገር ነው፡፡ ነገር ግን የሚሉት ነገር ሁሉ በቁም ያለ ሰው አይደለም የተኛ ሰው እንኳን በቅዠቱ የማይቃዠው የማይቀባጥረው ነገር ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ እኔ በግሌ የሚሉትን ነገር ብቻ ሳይሆን ጤናቸውንም ጭምር ለመጠራጠር ተገድጃለሁ፡፡
በተለይ አንደኛው እቤታቸው ጠርተውኝ ሄጀ ስንጫወት ስናወጋ ስለ ታቦተ ጽዮን አነሣንና “ታቦተ ጽዮን ማለት አሉና ከአልጋቸው እራስጌ በኩል ያለችውን የኪሊዮፓትራን ጉርድ የተቀለመ የሐውልቷን ፎቶግራፍ (ምስለ አካል) እያሳዩኝ ይህች ናት” ካሉኝ በኋላ ምንም እንኳን በቁም ከሚያቃዣቸው ከሚያስቀበጣጥራቸው ውጭ “ልብስ እንደመጣልና የመሳሰሉትን” የአእምሮ እክል ያለበት ሰው የሚያደርጋቸውን ድርጊቶች የሚያደርጉ ባይሆኑም ጤነኛ አለመሆናቸውንና መነኩሴ ነኝ ቢሉም፤ ሰውም ምንኩስናቸውን ቢያምንም፤ ኢአማኒ መሆናቸውን ጭምር ለራሴ አረጋግጫለሁ፡፡ እጅግ የሚገርመኝ ነገር ቢኖር እነኝህን “አባቶች” የሚያምናቸውና የሚከተላቸው ሰው መገኘቱ ነው፡፡
ሲመስለኝ እነኝህን ሰዎች እንዲህ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ያላቸው ፍቅር እጅግ መብዛቱ ከልኩ አልፎባቸው ተለክፈው ነው የቁም ቅዠት ውስጥ የገቡት፡፡ ብቻ ግን ይገርመኛል የሀገር ፍቅር ለአንዱ እንዲህ በዝቶበት የቁም ቅዠት ውስጥ ድረስ ሲጥለው ለሌላው ደግሞ እንጥፍጣፊ እንኳን አጥቶ ጉርቦዋን ፈጥርቆ አንቆ ሊገላት ያንፈራግጣታል፡፡ የሚያሳዝነው ሁሉም ግን በአንድ አፈር ላይ ተወልደው ያደጉ ከአንድ ውኃዋ የጠጡ ናቸው፡፡ በግል ጥረቱ ካልሆነ በስተቀር ሀገሪቱ እራሷ አንደኛውን ከሌላኛው ለይታ ያደረገችለት ምንም ነገር የለም፡፡ እንዲያውም የሚገርመው ነገር ብዙ ጊዜ ሀገር ፍቅር ስሜቱ እንደነገሩ ሆኖ የሚታየው በለም ጎኗ ያሳረፈችው ዜጋዋ ነው፡፡ በተጎዳው ጎኗ ያሳረፈችው ደግሞ በፍቅሯ ሲዋትት ይታያል፡፡ እንዲህ ብሎ መደምደም ግን አይቻልም፡፡ በተለይ መዚህ ዘመን በተጎዳው ጎኗ ያረፈው ነው ለጥፋቷ እጅግ ሲኳትን እያየን ያለነውና፡፡
እናም ይሄ ከልክ ያለፈው የሀገር ፍቅራቸው በዓለም መድረክ ላይ ትልልቅ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ኢትዮጵያዊ አንዲያደርጉ ያስገድዳቸዋል ይጫናቸዋል፡፡ አሁን አሁንማ ጭራሽ ለይቶላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ የማይሰብክ የማይናገር የማይገልጥ የማይመሰክር መጽሐፍ ሁሉ የሰይጣን ነው በማለት መጽሐፍ ቅዱስን ጨምሮ ሁሉንም የቤተክርስቲያን መጻሕፍ አራክሰዋል አጣጥለዋል አስተሀቅረዋል ክደዋል፡፡ መቸም ሰይጣን ሲፈትን ጠልፎ ለመጣል ሲፈልግ በምንወደው በሚገንብን ነገር ነውና የሚመጣው እነኝህንም አባቶች ለመጣል ሲፈልግ በሚወዱት ነገር መጣባቸው፡፡ ሰይጣን በምንወደው ነገር የሚመጣብን በቀላሉ ለመጣል ስለሚያስችለው ነው፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፉ “ሰው በወደደው በዚያ ይጠፋል” ማለቱ፡፡ እነኝህን የካዷቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ከጣሉ በኋላ እንዴት ብለው ምን ይዘው ክርስቲያኖች (ሃይማኖተኛ) ነን ሊሉ እንደሚችሉ አላውቅም፡፡
እነዚህ ሰዎች ከዚህ የለየለት የክህደት አቋም ላይ ከመድረሳቸው በፊት የት እንደነበሩና እንደቀልድ እንደዘበት በጀመሯት እብለት ሰይጣን እንዴት አድርጎ በትንሽ በትንሹ ቀስ በቀስ እየሳበ ወስዶ ዛሬ ካሉበት የክህደት ማጥ ውስጥ እንደከተታቸው መለስ ብለው ቢያዩት ለራሳቸውም ቢሆን ሳይገርማቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ጭራሽኑ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አውግዘው በመለየት “ኢትዮጵያይ ዐምሐራይ” የሚባል ሃይማኖት ያሉትን ድርጅት መሥርተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምን ይደረግ? እንግዲህ ክርስቶስ በቃሉ በማቴ. 24፤1-28 ላይ የዘመኑ መጨረሻ (የጌታ መምጫ) ሲቃረብ ሐሰተኖች መምህራን ሐሰተኞች ነቢያት ይመጣሉ በየእልፍኙ (አዳራሹ) ሐሰተኞችን ክርስቶሶች ይሰብካሉ ብሏልና ይህ ይፈጸም ዘንድ ግድ ነው፡፡
ከቅዠቱ ወጥተን ወደ እውነታው ስንመጣ ወደዱም ጠሉም ኢየሱስ ክርስቶስ በደም ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ እራሱን በማታለል የራሱን ውሸት የሚያምንና የሚሰብክ ሰው በእርግጠኝነት በኢየሱስ ክርስቶስ አያምንም አያውቀውምም፤ እውነትም በውስጡ የለም፡፡ ምን እየሠሩ እንደሆነ የማያውቁ እነኝህ ቃዣታሞች ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ ነው ብለው ሲደርቁ ምን ማለታቸው እንደሆነ እንኳን አያውቁም፡፡ ኢትዮጵያዊ ካልሆንክ በስተቀር ልናምንህ እንቸገራለን እያሉ ነው፡፡ ይሄ የዘረኝነት በሽታ ነው፡፡
ሲጀመር የሀገርና የዘር ልዩነት አጥር የሚሠራውና የሚያሳስበው ለእኛ ለሥጋዊያኑ እንጅ ለእግዚአብሔርና ለመንፈሳዊያኑ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርና ሥራዎቹ በዘርና በሀገር ከተወሰኑ ወይም የአንድ ሀገርና ሕዝብ ብቻ እንደሆኑ ከተቆጠሩ የመላው ዓለም መሆን አይችሉም፡፡ ይሄ ደካማ አስተሳሰብ ነው፡፡ ዘረኝነት የእኩያን ሰዎች ችግር እንጂ የፈጣሪ አለመሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ለምን ነጭ ሆነ ስለሆነም እኛ አፍሪካዊያኑ ጥቁሮች፣ ሩቅ ምሥራቃዊያኑ ቢጫዎችና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉቱ ቀዮች እሱን ልናመልክ አይገባም አይባልም፡፡
እስኪ አንድ ጥያቄ ልጠይቃቹህ ክርስቶስ በሁሉም የሰው ዘርሮች ሁሉ የዘረኝነት ጥያቄ ሳይነሣበት ያለልዩነት እንዲመለክ ከነማን መወለድ ነበረበት? ከጥቁሮቹ? ከቢጫዎቹ? ወይስ ከቀዮቹ? ወይስ እንደ ውኃ ቀለም አልባ ሆኖ መምጣት ነበረበት? የግድ ደግሞ ከሰው መወለድ እንደነበረበት አትርሱ፡፡ ከነጭ ሳይሆን ከሌሎቹ ቢወለድ ኖሮ በእኩያን ሰዎች አሁን እየተነሣ ያለው ቅሬታ (የዘረኝነት ጥያቄ) ሳይነሣበት መመለክ ይችል ነበር ወይ?
ስለዚህ ይህ ችግር ሰይጣን ያሳሳታቸው የእኩያን እንጂ የፈጣሪ አይደለም፡፡ ፈጣሪ የሚያውቀው አንድ አዳምን መፍጠሩንና ሁላችንም የሱ ልጆች መሆናችንን ነው፡፡ የቆዳ ቀለም ልዩነቱን የፈጠረው የአየር ንብረት ነውና ጥቁሩም፣ ነጩም፣ ቢጫውም፣ ቀዩም እንዲያ በመሆኑ ሊያፍር ወይም ሊኮራ ሊወቀስ ወይም ሊመሰገን አይችልም አይገባምም፡፡ ራሱን የፈጠረ የለምና፡፡ የእግዚአብሔር ወገንም ጠላትም መሆን የሚቻለው በሥራችን እንጅ በደም አይደለም ከአዳም ያልሆነ የለምና፡፡ ለዚህም ነው ክርስቶስ በወንጌሉ “የአብርሃም ልጆች ከሆናቹህ የአብርሃምን ሥራ ሥሩ፡፡ የአብርሃም ልጆች ነን በማለት የምትድኑ አይምሰላቹህ” ያለው፡፡
እነዚህ በቁማቸው የሚያቃዣቸው ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በደም ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ ከአብርሃም እስከ ዮሴፍ ያሉትን በክርስቶስ የዘር ኃረግ ወይም ትውልድ ያሉ 41 አባቶችን ሁሉ ኢትዮጵያዊያን ናቸው እያሉ እንደሆነ ልብ አላሉትም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ደግሞ ዕብራዊያን (እስራኤላዊያን) እንደሆኑ በግልጽ ያትታሉ፡፡ ሁሉንም ነገር በጭፍን ኢትዮጵያዊ የማድረግ አባዜ የከፋ የኢአማኒ አስተሳሰብ ነው፡፡ በውስጡ የመንፈስ ቅዱስ ሳይሆን የሰይጣን የሆነ ስግብግብነት ስስትና ለእኔ ብቻ የሚል ክፉ ስሜት የታጨቀበት ነውና፡፡ ይሄንን እንዲሉ የሚያስገድድ ምንም ነገር የለም፡፡ ከማንም የቀደመ አምልኮ እግዚአብሔር አለንና፡፡
ለዚህም ነው የእስራኤል ልጆች እንዳይረክሱ ከአሕዛብ ማለትም ከፍልስጥኤማዊያን፣ ከኢሎፍላዊያን፣ ከእስማኤላዊያን፣ ከኬልቄዶናዊያን፣ ከከለዳዊያን፣ ከሳምራዊያን፣ ከሰርቂሳዊያን፤ ከኬጢያዊያን፣ ከሮማዊያን፣ ከሰጢቃዊያን፣ ከሰርቂሳዊያን፣ ከተንባላታዊያን፣ ከዮናናዊያን፣ ከግብጻዊያን፣ ከአማሌቃዊያን፣ ከሰርቡሳዊያን ባጠቃላይ ከራሳቸው ዘር ውጪ እንዲያገቡ እግዚአብሔር በከለከላቸው ወቅት ሊቀ ነቢያት ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን ሊያገባ የቻለው፡፡ የእኛን ሕዝበ እግዚአብሔርነት አያውቁ የነበሩት ወንድሙ አሮንና እኅቱ ማርያምም ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን በማግባቱ ‹‹እግዚአብሔር በእኛ ብቻ ተናግሯልን በእሱም የተናገረ አይደለምን?›› ብለው አጉረመረሙ፡፡ ነገር ግን እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደሌላው ሕዝብ ከአሕዛብ ወገን ሳንሆን ከሕዝብ ወገን ነበርንና ነንምና የሙሴና የሲፓራ ጋብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ አልተጠላም አልተነቀፈም ተባረከ እንጂ፡፡ ሳይገባቸው አጉረምርመው የነበሩት እኅቱ ማርያምና ወንድሙ አሮንም በማጉረምረማቸው በእግዚአብሔር ተቀጡ ዘኁ. 12 ፤1-15 / ዘጸ. 2፣16-22 ፡፡
በእርግጥ ወደ ኋላ ላይ ግን ይህ ጉዳይ ማለትም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕዝበ እግዚአብሔር መሆኑ በደንብ ግልጽ ሆኖ ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ በትንቢተ አሞድ 9-7 ላይ እግዚአብሔር የተናገረውን ብናይ ጭራሽ እንዲያውም እኛ የኢትዮጵያ ልጆች በኩር ነን ከሚሉት ከእስራኤል ልጆች ይልቅ በእግዚአብሔር የተወደድንና የከበርን ሆነን እናገኘዋለን፡፡ ቃሉ እንደሚለው “የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር” በማለት እግዚአብሔር በኩራት ናቸው የሚባሉትን የእስራኤል ልጆችን ልክ እንደ እኛ አድርጎ እንደሚያያቸው ከእኛ አሳንሶ እንደማያያቸው እነሱን በማጽናናት መናገሩ ተጽፏል፡፡ እንግዲህ የእኛ ማንነት በእግዚአብሔር ፊት የተገለጸውን ያህል ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኢትዮጵያ ከመቼ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔርን ማምለክ እንጀመረች የተገለጸ ነገር የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ስንመረምር ልንረዳ የምንችለው ነገር ቢኖር ከቀደሙት የቀደምን መሆናችንን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ የከበረ ምንም ነገር የለም፡፡
አንዳንድ ቅናተኞችና ምቀኞች በመጽሐፍ ቅዱስ “በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያለ የሚጠራት ይህች አይደለችም ሌላ ናት” የሚለው ክርክር ሙሴ በዘፍ. 2፤13 ላይ ከዐባይ (ግዮን) ወንዝ ጋር በማያያዝ ዐባይ ከእሷ መንጭቶ ፈልቆ ምድሯንም የሚከባት በማለት አሁን ትናንትና ቅኝ ገዥዎች ቱርክና እንግሊዝ መጥተው ድንበራችንን በጣም ወደ ውስጥ እስከገፉብን ጊዜ ድረስ የነበረችውን፤ ኢትዮጵያ እያለ የሚጠራት ብርቅየ ሀገር ዐባይ የደጋን ቅርጽ ሠርቶ ምድሯን እንደከበባት በማሳየት ያለችበት ቦታ የት እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷልና የቅናተኞች የማስተባበያ ወሬ አልሠራም፡፡
እንደ የእግዚአብሔር ሕዝብነታችን ይህ እንዳትረክሱ ከማያምኑ ከአሕዛብ ጋር አትጋቡ የሚለው ክልከላ በእኛም ላይ ይሠራ ነበር አሁንም ይሠራል፡፡ የእኛ ከአይሁዶቹ የሚለየው ክርስቶስ ተወልዶ እነሱ ሳይቀበሉት ሰቅለው ከገደሉት በኋላ እራሳቸው አይሁዶቹ በእኛ ዘንድ ብንጋባቸው ከሚያረክሱን እንዳንጋባቸው ከተከለከልናቸው ወገኖች ቁጥር መጨመራቸው ነው፡፡ ልክ አይሁድ በመጻሕፍት የማይጋቧቸውን ዘሮች ዝርዝር እንደዘረዘሩ ሁሉ አንዳንድ የእኛ የቤተክርስቲያን መጻሕፍትም እንዲሁ በሀገራችን ያሉ ዛሬ ሳይሆን ቀድሞ ከሃይማኖት የራቁ በባዕድ አምልኮ የተተበተቡ ብሔረሰቦችን ወይም ጎሳዎችን ስም እየዘረዘሩ ከነሱ ጋር መጋባት ክልክል መሆኑን ያትታሉ፡፡ ነገር ግን ከነዚያ ብሔረሰቦች ወይም ጎሳዎች ያመነ የተጠመቀ ቢኖርና ጋብቻ ቢፈጸም ችግር እንደሌለበት ይገልጻሉ፡፡ ይሄንን በተሳሳተ አረዳድ በመተርጎም ለተሳሳተ የፖለቲካ (የእምነተ-አስተዳደር) ፍጆታ ለመጠቀም የሚሞክሩ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ለማንቋሸሽ የሚሞክሩ የማያስተውሉ ወገኖች እንዳሉም ይታወቃል፡፡
ከቤተክርስቲያን ውጭ የሆኑ የተለያየ እምነት ያላቸው ወገኖችም እነዚያን መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ናቸውና አንቀበልም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ይሔንን አይልም፡፡ ቃሉ የሚለው “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው መንገድ ደግሞ ይጠቅማል” ጢሞ. 3፤16-17 ነው የሚለው ቃሉ፡፡
በመሆኑም የቤተክርስቲያን መጻሕፍት 81 ናቸው የለም 66 ናቸው ማለት አይቻልም አይገባም ማለት ነው፡፡ ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌሉ 21፤25 ላይ እንደገለጸው “ኢየሱስ ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ይላልና ቅዱሳት መጻሕፍት እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ በሌሎች ሐዋርያት፣ ቅዱሳንና ሊቃውንትም የተጻፉትን መጻሕፍትም እግዚአብሔር በመረጣቸው ቅዱሳንና ሊቃውንት እንደመጻፋቸው ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ አለባቸውና የተቻለንን ያህል የመሰብሰብ ግዴታ አለብን፡፡
ነገር ግን “መጽሐፍ ቅዱስ” ተብለው በአንድ የመጠረዝ ዕድል ካገኙትና መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ ከሚታወቀው መጽሐፍ ላይ፤ ልክ አሁን አሁን “በቀላል አማርኛ፣ አዲስ ትርጉም” እየተባሉ ቀድሞ ከነበረው ላይ የነበረ ለማስመሰል ሌላ ቃል መጨመር ወይም ቀድሞ ያልነበረ ለማስመሰል ቃል መቀነስ ወይም መቆነጻጸል በዮሐ. ራእይ 22፤18-19 ላይ እንደተጻፈው ፈጽሞ የተከለከለና የገሐነም ፍርድ የሚያሰጥ ኃጢአት ነው፡፡ ከሌሎችም የቤተክርስቲያን መጻሕፍት ላይ ቢሆን ያው ነው፡፡ መተንተን መተርጎም ማብራራት ግን ይቻላል፡፡ ይህ ቃል ምንም እንኳን እዚያው ጥቅሱ ላይ በግልጽ እንደተገለጸው ግዝቱ የሚያገለግለው ለዚያ “የትንቢት መጽሐፍ” ለዮሐንስ ራእይ ቢሆንም ግዝቱ ወይም ማስጠንቀቂያው ለሌሎች የቤተክርስቲያን መጻሕፍትም ያገለግላል፡፡
እናም የሌለ ነገር መዘባረቅ ፈጽሞ አይገባም፡፡ እግዚአብሔር የእውነትና የፍቅር አምላክ ነው፡፡ ይህ የእውነትና የፍቅር አምላክ በዚህ ድርጊታቸው ቢያዝን ቢከፋ እንጅ አይደሰትም፡፡ በእጅጉም ይታዘበናል፡፡ እንደዚህ ባለ የሐሰት፣ የስግብግብነት፣ የስስትና የስርቆት መንፈስ በነገሰበት ልብ ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጽሞ አያድርም የክፉው መንፈስ እንጅ፡፡
ካቶሊኮች እግዚአብሔርን ያከበሩ ያስደሰቱ መስሏቸው እናቱን እመቤታችንን “ኃይለ አርያማዊት” (የሰው ልጅ ያልሆነች) ናት በማለት የሠሩትን ስሕተትና ክህደት እነኝህም ከጉያችን ያሉ የነበሩ “አባቶች” በሌላ መልኩ ደግመውታል፡፡ እግዚአብሔር በሐሰት ሥራ አይከብርም አይደሰትምም፡፡ እንዲህ ብለን ካሰብን ገና አለማመናችንን እንወቅ፡፡ ቅዠት ቅዠት እንጅ እምነት ሊሆን አይችልም፡፡ በሌላ በኩል ይሄ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ንቀትም ነው የሚያሳየው፡፡ ይህ እንቅስቃሴ በቸልታ ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡ እምነት እንዲህ ቀልድ አይደለም በእውነት እንጅ በስሜትም አይነዳም፡፡ እኔ ይሄንን ሁሉ ድርጊት በእግዚአብሔር እንደመቀለድ እንደማሾፍ አው የምቆጥረው፡፡
በሌላ በኩል ይህ እንቅስቃሴ የማይሆንና የማይመስሉ ነገሮችን እየተናገሩ በመጽሐፍ ቅዱስና በዓለም ታሪክ እንደነ ሔሮዱትስና ሆሜር ያሉ ከማንም ሀገር በላይ አልቀው በመጻሕፍቶቻቸው የመሰከሩላትን ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያንና ታላላቅ ሥራ እንደሠሩ የተነገረላቸውን በትክክልም ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ የሚታወቁትን የዋኖቻችንን ታሪክ ሁሉ ተረት ለማስመሰል የሚሠራ ሴራም ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታላላቅ አባቶች ዋነኛው የነበረውን አባት እንይ፡፡ ሕዝበ እስራኤልን ከእግዚአብሔር ጋር ያስተዋወቃቸው አብርሃም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አብርሃምን የባረከውና አብርሃምም ዐሥራትን ለእሱ ያወጣለትና አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋራ ከመተዋወቁ እግዚአብሐየርን አምላኪ ከመሆኑ በፊት የእግዚአብሔር ካህን የነበረው ግን መልከጸዴቅ ነው፡፡
ይህ ሰው ኢትዮጵያዊ ነበረ ወይም ነው፡፡ በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትውልዱ አልተገለጸም፡፡ ታዲያ በምን ታወቀ ቢሉ በስሙ፡፡ የመልከጼዴቅ ስም በየትኛውም የዓለማችን ቋንቋ በተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ብታዩ ተቸግረውም ቢሆን የሚያስቀምጡት ያው ራሱ “መልከጼዴቅ” የሚለውን ቃል ነው፡፡ ይህ ስም የግእዝ ስም ነው፡፡ ለሌሎች ቋንቋዎች በተለይም ሴማዊ ላልሆኑት ይህ ቃል ወይም ስም ባዕድ ነው፡፡ ሴማዊያኑ ግን ቃሉን ከግእዝ ወርሰው ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መልከጼዴቅ ሲናገር “የስሙ ትርጓሜ በመጀመሪያ የጽድቅ ንጉሥ ነው፡፡ በኋላ ደግሞ የሳሌም ንጉሥ ማለት የሰላም ንጉሥ ነው” ብሎ በቋንቋቸው ተርጉሞ ለወገኖቹ ለዕብራዊያን በመልእክቱ አስረድቷል፡፡
በተጨማሪም “እናትና አባት የትምልድም ቁጥር የሉትም” ብሎታል፡፡ ይህን ማለቱ ሰው አይደለም ለማለት ሳይሆን በአይሁድ መጽሐፍ ወይም የትውልድ ኃረግ ዝርዝር ስሙ የለም አልተጠቀሰም ማለቱ እንጅ፡፡ ያልተጠቀሰበትም ምክንያት አይሁድ ባለመሆኑ ነው ይህንንም እዚያው ላይ ገልጾታል፡፡ እንጅ ሥልጣነ ካህነቱና ክብሩማ የሱን የሚያህል ማን ነበር? እንዲያውም “የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ” ብሎም ይጠራዋል “ለዘመኑ ጥንት ለሕይዎቱም ፍጻሜ የለውም” ሲል ይሙትም አይሙትም አይታወቅም ማለቱ ነው፡፡ ዕብ. 7፣1-3
ሌላኛው መልከጼዴቅ ኢትዮጵያዊ መሆኑን የሚጠቁመው መላምት ከዘመነ ሐዲስ በፊት እግዚአብሔርን ያመልኩ እሱም ሕዝቤ ይላቸው የነበሩት ሕዝቦች የእስራኤልና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብቻ ነበሩ፡፡ እናም መልከጼዴቅ እስራኤላዊ ካልሆነ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔርን በማምለክ ከእስራኤላዊያንም እንቀድማለን ማለት ነው፡፡
እናም እኛ ኢትዮጵያዊያን ወይም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በቀጥታና በተዘዋዋሪም እስራኤላዊያንን ሕዝበ እግዚአብሔር እንዲሆኑ በማድረግ አኳያ ከፍተኛ ሚና መጫወታችንን መረዳት ይቻላል፡፡ እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ብቻም ሳይሆን የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓትንና ሕግንም ጭምር ለእስራኤላዊያን አስተምረናል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በእግዚአብሔር ተመርጦ ሕዝቡን ከግብጽ አውጥቶ እየመራ ወደ ምድረ ርሥት በሚወስድበት ወቅት ሕዝቡን ማስተዳደር መዳኘት ለሕዝቡና ለራሱም አስቸጋሪና አድካሚ ሆኖ ነበር፡፡
አማቱ ኢትዮጵያዊው ካህን ዮቶር ወይም ራጉኤል ይህ ሙሴ እያደረገ ያለው ነገር ትክክል ያልሆነና ለሕዝቡም ለራሱም አድካሚ ሥራ አስፈቺ መሆኑን አስረድቶ ከሕዝቡ የነቁ የጠነቀቁትን ሰዎች እንዲመርጥ ከእነሱም የሺ የመቶ የሃምሳ የዐሥር አለቆችን እንዲሾምላቸውና በሕዝቡ ላይ እንዲፈርዱ እንዲዳኙ፤ አውራውንና የሚከብዳቸውን ጉዳይ ብቻ ወደ አንተ ያምጡ ብሎ መክሮ በዚያ መሠረት በአንድ በሙሴ ብቻ ሙሉ ቀን ሥራ ፈተው ሲዋትቱ የነበሩበትን አሠራር ቀይሮ የተሳለጠና የተደራጀ ምቹ የአስተዳደር ሥርዓት እንደሠራላቸው ይህም አሠራር ዛሬ በመላው ዓለም ላለው ሁሉ ተዳርሶ እነሆ እየተጠቀመበት እንዳለና መሠረት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ዘጸ. 18፣13-27.
በዓለም ሥልጣኔና ሃይማኖት ላይ የእኛ ድርሻ ዋነኛውን ስፍራ ይይዛል፡፡ ከዚህ አኳያ ያለን ክብር ከበቂ በላይ ነው ይሄንንም አላምንላቹህም ብሎ ዓለም በሸፍጥ ፊቱን አዙሮብናል፡፡ ያለን ይበቃናል ለሌሎችም እናስብ፤ እግዚአብሔር እኛን ብቻ አልፈጠረም፡፡ ሁሉም የሰው ዘሮች የእግዚአብሔር የእጁ ሥራዎች ናቸው፡፡ ክርስቶስ የሞተው ለእኛ ብቻ አይደለም ለመላው ዓለም ሕዝብም እንጅ፡፡ ኢየሱስ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ እያወቅን በግድ ኢትዮጵያዊ ለማድረግ መሞከር ሀገርን የመውደድ መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ሐሰት ለምንም ነገር ቢሆን የጸና መሠረት ሊሆን አይችልምና፡፡ እንዲህ ብሎ በከንቱ ከመድረቅ ይልቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ልጅ በጠቢቡ ሰሎሞን እናት በቤርሳቤህ በኩል ኢትዮጵያዊ ደም አለበት ቢባል መልካምና ተአማኒም ነበር፡፡ የሰሎሞን እናት የኦርዮ ሚስት የነበረችው ቤርሳቤህ ኢትዮጵያዊት ናትና፡፡ ሰሎሞንም ራሱ በመኃልይው “እናንተ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ሆይ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፤ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞን መጋረጃዎች ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለሆንኩ አትዩኝ” ብሎ ተናግሯልና መኃልየ መኃልይ ዘሰ. 1፤5-6.

ወይ ደግሞ እንደ መጣቅ (ሳይንስ) አባባል ዘመናዊው የሰው ልጅ ዘር የዛሬ 100 ሽህ ዓመታት አካባቢ አዲስ አበባ አካባቢ ወጥቶ መላውን ዓለም አዳርሶታል ይላልና ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሰው ኢትዮጵያዊ ነው ማለትም አንድ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን መጣቅና ሃይማኖት የተለያዩ ብዙ ጊዜም የማይግባቡ ናቸውና የመጣቅን መረጃ ለሃይማኖት መጠቀም የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ስላሉ አስቸጋሪ ነው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!
ውድ አምሳሉ፣ ሠዓሊ መሆንህ በጀ። “የመልከጼዴቅ ስም በየትኛውም የዓለማችን ቋንቋ በተጻፈ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ብታዩ ተቸግረውም ቢሆን የሚያስቀምጡት ያው ራሱ “መልከጼዴቅ” የሚለውን ቃል ነው፡፡ ይህ ስም የግእዝ ስም ነው፡፡ ለሌሎች ቋንቋዎች በተለይም ሴማዊ ላልሆኑት ይህ ቃል ወይም ስም ባዕድ ነው፡፡ ሴማዊያኑ ግን ቃሉን ከግእዝ ወርሰው ይዘዋል” ማለትህ ስለ ቋንቋዎችና ስለ ስነ መለኮት ከግምት ያለፈ እውቀት እንደሌለህ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በግእዝ ሳይሆን በእብራይስጥና በግሪክ ቋንቋዎች ነው። በግእዝ ያልከው ትርጉሙን ነው። በቀላል አማርኛ ተብሎ ያነብበከው ትውልዱ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲረዳ ለማድረግ ነው። ማንም በፈቃዱ የጻፈው ሳይሆን ሊቃናት ከዋናው ቅጂ እንዳይፋለስ ተባብረው ያዘጋጁት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገሮች በሌሎችም ቋንቋዎች ተተርጉሞአል። ሁሉም ትርጉም ከዋናው እብራይስጥና ግሪክ ቅጂ ጋር መስማማት ይኖርበታል። ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ አይደለም ብለህ ያስረዳኸው ጥሩና ትክክል ነው። ሌሎቹ ነጥቦችህ ግን በስሜትና አገር ወዳድነት ብቻ የሚመከቱ አይደሉም።
አቶ መስፍን እባክዎን አስተውለው ያንብቡ እኔ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በዕብራይስጥና በጽርእ(በግሪክኛ) አይደለም በግእዝ ነው ብያለሁ እንዴ? የት ቦታ ነው ያልኩት? እኔ ያልኩት መልከጼዴቅ የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ነው ሴማዊያኑ ይሄንን ቃል ከግእዝ ወርሰው ወስደዋል አልኩኝ እንጅ መጽሐፍ ቅዱስ በግእዝ ነው የተጻፈው አላልኩም እሽ አቶ መስፍን፡፡ በነገራችን ላይ የሴም ቋንቋዎች በርካታ ቃላትን ከግእዝ ወስደዋል ግእዝ ከእነሱ እንደወሰደ ሁሉ፡፡
ወዴት ወዴት?መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራይስጥና በግሪክ ቋንቋዎች ተጻፈ ያልኩት እኔ ነኝ። አንተ አልክ አላልኩም። “መልከጼዴቅ” ቃሉ ግእዝ ነው ስላልክ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረቱ ግእዝ አይደለም ልልህ ነው። “መልከጼዴቅ” የግእዝ ስም ነው ካልክ፤ በዕብራይስጥ ምንድነው የሚባል? ይህን መልስ። ሌላውን ተወው። እስራኤልንና ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የሞከርከውንም ተወው። አገር መውደድህ ጥሩ ነው፤ ታሪክን ማዛባት ግን ምንም አይጠቅምም። “መልከጼዴቅ እስራኤላዊ ካልሆነ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔርን በማምለክ ከእስራኤላዊያንም እንቀድማለን ማለት ነው” አልክ። ያህዌ ነኝ ብሎ ራሱን የገለጠው ለሙሴ ነው። ሙሴ ኢትዮጵያዊ ነው ማለትህ ይሆን? ይኸ ደግሞ አዲስ ነገር ነው። ለማንኛውም ግምት ነው፤ ታሪካዊ መረጃ የለውም።
ውውው……ይይ አቶ መስፍን ልበ ግራ ሆኑብኝ እኮ፡፡ “መጽሐፍ ቅዱስ በዕብራይስጥና በግሪክ ቋንቋዎች ተጻፈ ያልኩት እኔ ነኝ። አንተ አልክ አላልኩም” አሉኝ፡፡ እኔን እንዲህ ብለው አሉኝ ብየ አልኩዎት? ወጣኝ? የተጻፈ ነገር አንብቦ መረዳት አይችሉም ልበል? ያልኩትን ደግሜ ለማንሣት ያህል “አቶ መስፍን እባክዎን አስተውለው ያንብቡ እኔ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በዕብራይስጥና በጽርእ(በግሪክኛ) አይደለም በግእዝ ነው ብያለሁ እንዴ?” ነበር ብየ የጠየኩዎት እሽ? አሁንስ ገብቶዎት ይሆን
“መልከጼዴቅ” ቃሉ ግእዝ ነው ስላልክ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረቱ ግእዝ አይደለም ልልህ ነው። “መልከጼዴቅ” የግእዝ ስም ነው ካልክ፤ በዕብራይስጥ ምንድነው የሚባል? ይህን መልስ። ብለውኛል እስኪ አንድ ጥያቄ ላንሣልዎ እርስዎ ውጪ የሚኖሩ ቢሆንና የዚያው ሀገር ሰዎች በቋንቋቸው ስለ እርስዎ ቢጽፉ ስምዎን “መስፍን” ብለው እየጠቀሱ ነው አይደል የሚጽፉት? ይሄኔ ታዲያ በራሳቸው ቋንቋ በተጻፈ መጽሐፍ ላይ መስፍን ተብሎ በመጻፉ መስፍን አማርኛ ሳይሆን የነሱ ቃል ነው ይባላል እንዴ? መልከጼዴቅ ላይ የሆነውም ነገር ይሄው ነው እያልኩ ነው እሽ?
መልከጼዴቅ ቃሉ ግእዝ ከሆነ በዕብራይስጥ ምን ይባላል? ላሉኝ ጥያቄ ቅዱስ ጳውሎስ ለራሳቸው ለዕብራዊያን (ለእስራኤላዊያን) በጻፈላቸው መልእክቱ በምእራፍ 7 ላይ ስለሱ ሲያትት የመልከጼዴቅ የስሙ ትርጓሜ “የሰላም ንጉሥ፣ የጽድቅ ንጉሥ” ማለት ነው ብሎ ተርጉሞላቸዋልና “የሰላም ንጉሥ፣ የጽድቅ ንጉሥ” በእብራይስጥኛ ምን እንደሚባል እኔ የዕብራይስጥኛ መጽሐፉ ቅዱስ የለኝምና ዕብራይስጥኛ መጽሐፍ ቅዱስ ይፈልጉና እዚያ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ “መልከጼዴቅ” የሚለውን ስም ምን ብሎ በእብራይስጥኛ እንደተረጎመው እዚያው ላይ ተቀምጦልዎታልና ፈልገው ያንብቡት እሽ አቶ መስፍን?
መልከጼዴቅ እስራኤላዊ ካልሆነ ሊሆን የሚችለው ኢትዮጵያዊ ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔርን በማምለክ ከእስራኤላዊያንም እንቀድማለን ማለት ነው” አልክ አሉኝና “ያህዌ ነኝ ብሎ ራሱን የገለጠው ለሙሴ ነው። ሙሴ ኢትዮጵያዊ ነው ማለትህ ይሆን? ይኸ ደግሞ አዲስ ነገር ነው። ለማንኛውም ግምት ነው፤ ታሪካዊ መረጃ የለውም” አሉኝ በእርስዎ ቤት ሙሴ ከነ አብርሃምና መልከጼዴቅ ይቀድማል አይደል? አየ አቶ መስፍን ሰውን በግምት ታወራለህ ይላሉ እርስዎ ግን አብርሃምና መልከጼዴቅ ከሽህ ዓመታት በላይ የሚቀድሙትን ሙሴን አስቀድመው ይዘባርቃሉ፡፡
አጭር ላርግልን። 1/ “መልከጼዴቅ” ትርጉሙን አልጠየቅሁህም። ቃሉ ግን ግእዝ ሳይሆን ዕብራይስጥ ነው። 2/ እግዚአብሔር “ያህዌ ነኝ” ብሎ ራሱን የገለጠው ለሙሴ ነው። ከአብርሃም ይቀድማል አላልኩም። 3/ ሙሴ ኢትዮጵያዊ አይደለም። 4/ ኢትዮጵያ እግዚአብሔርን በማምለክ ከእስራኤል አትቀድምም። 4/ ልትለው ያሰብከውን እንዲደግፍ የጠቀስከው ትርጉሙ ተዛብቷል፤ ለምሳሌ፣ “ኢየሱስ ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” [ዮሐንስ 21፡25]። ኢየሱስ ያደረገው ብዙ ነው ማለቱ ነው እንጂ ሌሎች መጽሐፍት አሉ ማለቱ አይደለም። እዚያው ዮሐንስ ወንጌል 20፡30-31 ላይ እንዲህ ይላል፣ “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።” 5/ቀጥሎ እንዲህ ብለሃል፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ልጅ በጠቢቡ ሰሎሞን እናት በቤርሳቤህ በኩል ኢትዮጵያዊ ደም አለበት ቢባል መልካምና ተአማኒም ነበር፡፡ የሰሎሞን እናት የኦርዮ ሚስት የነበረችው ቤርሳቤህ ኢትዮጵያዊት ናትና፡፡ ሰሎሞንም ራሱ በመኃልይው “እናንተ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ሆይ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፤ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞን መጋረጃዎች ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለሆንኩ አትዩኝ” ብሎ ተናግሯልና መኃልየ መኃልይ ዘሰ. 1፤5-6”
ቤርሳቤህ ኢትዮጵያዊ ነች ላልከው ማስረጃ ማቅረብ ይኖርብሃል። 2ኛ ሳሙኤል 11፡3 ቤርሳቤህን “የኤልያብ ልጅ የኬጢያዊው የኦርዮ ሚስት” ይላታል፤ ኤልያብን ደግሞ “የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ” ይለዋል [2ኛ ሳሙ 23፡34]። መኃልየ መኃልይ ላይ “ጥቁር ነኝ” ያለችውን ኢትዮጵያዊት እንዴት ልትላት ቻልክ? እንዴትስ ከቤርሳቤህ ጋር አገናኘሃት? ይህን ለአንባቢው ማስረዳት ይኖርብሃል። ይህን ሁሉ የምልህ ለመማማር እንጂ አንተን ለመንቀፍ እንደ ሆነ አድርገህ አትውሰድ፤ የአገላለጼ ቀጥተኛነት ቅር አሰኝቶህ ይሆናልና ይቅርታ እጠይቃለሁ። ሁለታችንም የያዝነው ልኩን አውቀን ስህተቱን ለማረም ነው። ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ አይደለም ማለትህ ተገቢና ትክክለኛ እርምት የሚሰጥ በመሆኑ እስማማለሁ። ብዙው የኛ ሰው መጽሐፍ ቅዱሱን እንደ አንተ ለመርመር ጊዜውም ፍላጎቱም የለውም። የተባለውን ነው የሚቀበል፤ ወይም ሌላው እንዲነግረው ይሻል። ለስህተት ትምህርት ሰለባ የሆነውም ለዚሁ ነው። ለማንኛውም እግዚአብሔር ጥረትህንና አንተን ይባርክ።
አቶ መስፍን እኔ እያወራሁት የነበረውና የጽሑፉ ዋና ነጥብ ዕብራዊያኑ እግዚአብሔርን ያወቁበትን እሱን ወደ ማምለክ የመጡበትን ሁኔታና ቅጽበት ነው፡፡ ይሄንን የተረዱልኝ አልመሰለኝም ምክንያቱም በዚህ አውድ ውስጥ እግዚአብሔር ለሙሴ ስለነገረው ስሙ ሊያስነሣ የሚችል ጉዳይ አልነበረምና፡፡ ሙሴ የመጣው አምልኮተ እግዚአብሔር በእስራኤላዊያን ዘንድ ከተስፋፋ በኋላ ተስፋና ቃል ኪዳን ከተሰጣቸው በኋላ በመሆኑ፡፡
አቶ መስፍን አንድ ጥያቄ ልጠይቅዎት? ወንጌላዊው ዮሐንስ 20፤30-31“ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ….” ብሎ ሲል የትኛውን መጽሐፍ ማለቱ ነው የሚመስልዎት? አቶ መስፍን መጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ምሉእ እንዳልሆነ የሚያውቁ አልመሰለኝም፡፡ እስኪ ለምሳሌ ያህል አንድ ሦስት ጥያቄዎችን ላንሣና እርስዎ መጽሐፍ ቅዱስ ይሄ ብቻ ነው ብለው ከሚሉት መጽሐፍ ይመልሱልኝ፡፡
1. ማቴዎስ ወንጌላዊ በ1፤1-16 ላይ የጌታን የትውልድ መጽሐፍ ሲጽፍ ከአብርሃም ይጀምርና 42 ትውልዶቹን ዘርዝሮ ዮሴፍ ላይ ይጨርሳል፡፡ ነገር ግን ዮሴፍ የጌታ የሥጋ አባት ነው እንዴ? ይሄንን እንኳን ክርስትና እስልምና እንኳን አይጠራጠርም አያምንም፡፡ ታዲያ አባቱ ካልሆነ እንዴት በጌታ የዘር ሀረግ ውስጥ ሊቆጠር ቻለ?
2. የይሁ. ቁ. 9 ላይ “የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገስጽህ አለው እንጅ የስድብ ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም” የሚለውን ታሪክ እርስዎ መጽሐፍ ቅዱስ ይሄ ብቻ ነው ብለው ከሚሉት ሊያገኙት ይችላሉ?
3. ዘፍ. 4፤1 ላይ “አዳም ሔዋንን አወቀ ፀነሰችም ቃየንንም ወለደች ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች” ይላል ይሄም ማለት በምድር ላይ ያሉት ሰዎች አራት ብቻ ናቸው ማለት ነው፡፡ ወረድ ብሎ ግን ቁ. 17 ላይ ቃየንም ሚስቱን አወቀ ጸነሰችም ሄኖሕንም ወለደች ይላል፡፡ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች አራቱ ብቻ ነበሩ ይህች ሴት ከየት መጣች?
እነኝህን የመሳሰሉ እርስዎ መጻሕፍተ ቅዱሳት እነኝህ ብቻ ናቸው ብለው የሚሏቸው መጻሕፍት መልስ ሊሰጧቸው የማይችሏቸው በርካታ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ቤተክርስቲያን ግን እነኝህን ጎደሎዎች የሚሞሉ፣ እግዚአብሔርን በምልአት እንድናውቀው የሚያደርጉ፣ የተጣረሱና የተሳሳቱ የሚመስሉትን አንቀጾችን የሚያስማሙ በርካታ ተጨማሪ ቅዱሳት መጻሕፍት አሏት፡፡ ከላይ ለጠቀስኳቸው ጥያቄዎች መልስ የሌለዎት ሆኖ እያለ መልስ የያዙትን ቅዱሳት መጻሕፍት እንዴት ሊጥሏቸው አልቀበልም ሊሏቸው ይችላሉ? በዚህ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ በጢሞ. 3፤16-17 ላይ የተናገረውን አይርሱ፡፡
አቶ መስፍን “እኔ ጥቁር ነኝ” ብሎ ተናግሯል ያልኩት እኔ ጥቁር ነኝ ብሎ ያለውን የዳዊትን ልጅ ሰሎሞንን ነው፡፡ ሰሎሞን በእርግጥ ጥቁር የሆነው በእናቱ በቤርሳቤህ በኩል ነው ብያለሁ፡፡ ቤርሳቤህ የሰሎሞን እናት መሆኗን እኮ ገልጫለሁ፡፡ የቤርሳቤህና የወላጆቿ ስሞች ኢትዮጵያዊ ስላልሆኑ ነው አይደል ኢትዮጵያዊያን አይደሉም ያሉት? አቤሜሌክ ኢትዮጵያዊ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ኤር. 38፤7-13 ኤር. 39፤15-18 ላይ ተገልጧል ስሙ ግን ኢትዮጵያዊ ነው እንዴ? እንግዲህ የቤርሳቤህንና የቤተሰቦቿንም ጉዳይ እንደዚያው አድርገው ይመልከቱት እሽ? አሁንም ቢሆን በዚህ ዘመን ክርስቲያኖች ነን ከምንለው የምንበዛው በአይሁድ ስሞች እንደምንጠራ ልብ ብለውታል?
ቀጣዩን ሳልልዎት ብዘጋው ቅር ይለኛል፡፡ ምን ይገርመኛል መሰልዎት አቶ መስፍን ሰው ኢትዮጵያዊ ሆኖ እያለ ከኢትዮጵያ ጥቅሞች በተጻራሪ የሚቆመው ለምንድን ነው? እስኪ እባክዎች ከቻሉ ይሄንን ይመልሱልኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ከእስላም ወገኖቻችን ፌስ ቡክ ሼር በተደረገው ላይ በግጥም ሳይቀር ሊመለስላቸው የሚገቡ በሦስት ዋና ዋና ጥያቄዎች ዙሪያ ያተኮሩ በርካታ እስላሞች ደጋግመው አንሥተዋልና ምላሻቹህ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
1. አምላክ በሰዎች በፍጡሩ ተገርፎ፣ ተሰቃይቶ፣ ተሰቅሎ ከተገደለ እራሱን እንኳን ማዳን ያልቻለ ይሄ ምኑን አምላክ ሆነ? ስትሉ ጠይቃቹሀል፡፡
መልስ፡- እግዚአብሔር ወልድ (አምላክ) ከፈጠራቸው ከሰዎች መወለድና መከራ መቀበል ተሰቅሎ መሞትና መነሣት ያስፈለገው ምክንያቶች አምስት ናቸው፡-
ሀ. ሰይጣን አዳም አባታችንንና ሔዋን እናታችንን በገነት በነበሩበት ጊዜ በሥጋ ከይሲ (በእባብ አካል) ተሰውሮ ተሸሽጎ ክፉ ምክርን መክሮ አምላክ አታድርጉ ያላቸውን እንዲያደርጉ በማድረግ እግዚአብሔርን እንዲበድሉ ኃጢአት እንዲሠሩ ትዕዛዙን እንዲያፈርሱ አድርጓቸው ነበር፡፡ ይህ የአዳም በደል ኃጢአት ከባድ ስለነበር በደለኛው አዳም ባቀረበው ይቅርታና ልመና ሊሥተሰረይ ሊጠፋ ሊደመሰስ የሚችል አልነበረም፡፡ ይህ በደል ሊሥተሰረይ የሚችለው ፍጹም ንጽሕና ባለው አምላክ መሥዋዕትነት ብቻ ነበርና አዳም እግዚአብሔርን ይቅርታ ምሕረት በለመነው ጊዜ በአምስት ቀን ተኩል(5500 ዘመን በኋላ) ከልጅ ልጅህ ተወልጀ ተገርፌ ተሰቃይቸ ተሰቅየ ሞቸ ተነሥቸ አንተንና በአንተ ምክንያት የሚኮነኑ ልጆችህን አድናቹሀለሁ ብሎ ቃል ገብቶለት ስለነበር ያንን የገባውን ቃል ለመፈጸም በቀጠሮው መሠረት መጥቷል፡፡
ለ. እግዚአብሔር “ለኛ መስሎ ለሚታየን” ከራቀበት ለመቅረብ ከተሠወረበት ለመገለጥ፡- እግዚአብሔር መንፈስ ነው የሚታይና የሚዳሰስ አካል አልነበረውም ፍጥረቱ ደግሞ እሱን የማየት ፍላጎትና ጥያቄ ሲያነሣ ቆይቷልና ተወልዶ በመሀከላችን በመገኘት በዓይን ለመታየት በእጅ ለመዳሰስ፣ ስለ ማንነቱ ከራሱ ከባለቤቱ አንደበት ኃጢአተኛ ጻድቅ ብሎ ሳይለይ ለሁሉም ለመግለጥ፡፡
ሐ. ፍጹም ፍቅርን፣ ፍጹም ትሕትናን፣ ፍጹም ይቅር ባይነትን ለማስተማር፡- “ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳቹህም ዕረፍት ታገኛላቹህ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና” ማቴ. 11፤29-30 እንዳለው ሁሉ የተበደለ እሱ ሆኖ ሳለ እንደተበዳይነቱም በበዳይ ተክሶ ይቅርታ መጠየቅ ሲገባው የተገላቢጦሽ ተበዳይ በዳይን ክሶ ፍጹም የሆነን ቸርነቱን፣ ፍቅሩን፣ ትሕትናውን፣ ይቅር ባይነቱን እራሱ በእራሱ ላይ አድርጎ አሳይቶ ለማስተማር፡፡
መ. ጥበብን በጥበብ ለመሻር ፡- ከላይ ሰይጣን አዳምን ሲያስተው በእባብ አካል ላይ አድሮ ተሠውሮ ተደምቆ ነበር፡፡ በግልጽ ቢመጣባቸው ኖሮ አዳምና ሔዋን ሰይጣንነቱን ዐይተው አይስቱለትም ነበርና፡፡ ሰይጣን በዚህ አዳምንና ሔዋንን ባሳተበት ጥበቡ ይኮራ ይታበይ ነበር፡፡ እሾክን በሾክ እንዲሉ እግዚአብሔርም ደግሞ ሰይጣንን ያሳፍረው ዘንድ ፈጽሞ ባልገመተውና ባልጠበቀው መንገድ በሰው ሥጋ ተሰውሮ (ሰው ሆኖ ከሰው ተወልዶ) በመምጣትና ድል በመንሣት 5500 ዘመን ያህል ሥጋቸውን በመቃብር ነፍሳቸውን በሲዖል እየተቆራኘ ሲያሰቃያቸው የነበሩትን ነፍሳት ሁሉ ነጻ አውጥቷቸዋል፡፡ የሰይጣንን ጥበብም በጥበቡ ሽሮበታል፡፡
ሠ. የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ፡- ሰይጣን አዳምንና ሔዋንን ካሳተ በኋላ በእብነ ሩካብ (በድንጋይ ላይ) አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ (አዳም የዲያብሎስ ባርያ ነው ሔዋን የዲያብሎስ አገልጋይ ናት ) ብሎ ሁለት የዕዳ ደብዳቤ ጽፎ አስፈርሞ አንዱን በሲኦል አንዱን በዮርዳኖር ባሕር ላይ አስቀምጦባቸው ነበርና ጌታ ሰው ሆኖ በመምጣት ሁለቱንም እንደሰውነቱ እረግጦ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ ሊያጠፋላቸው ሊደመስስላቸው ሰው ሆኖ ተወልዷል፡፡
እንግዲህ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ከሰው ተወልዶ እንደሰው አድጎ ሰው እንደመሆኑም ከኃጢአት በስተቀር ሰው የሚደርገውንና ሰው የሚሆነውን ሁሉ ሆኖ በመጨረሻም የማዳን ሥራውን መራራ መከራን በመቀበል ተሰቅሎ እስከመሞት ድረስ ፍጹም ፍቅሩን ቸርነቱን አሳይቶን ሊያድነን ችሏል፡፡ እናም ጌታ ሰው የሆነበትና ሁሉን ማድረግ እየተቻለው አቅም እንደሌለው መከራን ሊቀበል የቻለባቸው ምክንያቶች እነኝህ ናቸው፡፡
2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሐዋርያት ናቸው እንጂ እራሱ ኢየሱስ በግልጽ እኔ “አምላክ ነኝ” ያለበት አንድም ቦታ የለም በማለጽ የሥላሴን (የእግዚአብሔርን) አንድነትና ሦስትነት ካለማወቅ የተነሣ የተጠየቀ ጥያቄ አለ፡፡
መልስ፡- “ለአብ ያለው ሁሉ የእኔ ነው ስለዚህም ለእኔ ካለኝ ወስዶ ይነግራቹሀል አልኩ” ዮሐ.16፤15 “እኔና አብ አንድ ነን” ዮሐ. 10፤30
3. ኢየሱስ ሞቶ መነሣቱን የሚገልጽ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የለም፡፡
መልስ፡- መቸም ዛኪር የተባለው የሚናገረውን የማያውቅ ወፈፌ እስላም ህንዳዊ ስንቱን አሳስቶታል መሰላቹህ፡፡ የተናገረው ሁሉ እውነት መስሏቸው ወገኖቻችን እሱ ያለውን እየጠቀሱ ይጠይቃሉ፡፡ ለማንኛውም መልሱ በዮሐ. ራእይ 1፤18፣ በሉቃ. 23፤47-48፣ ማቴ. 27፤62-66፣ 1ኛ ተሰ. 4፤14፣ 2ኛ ጢሞ. 1፤10 1ኛ ቆሮ. 15፤20 ወዘተ. ላይ ይገኛል፡፡
በተረፈ የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት የራሳቹህ መጽሐፍ ቁርአናቹህ ይነግራቹሀል፡፡ እስልምና ኢየሱስ ከሱም በፊት ከሱም በኋላ ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ ከድንግል ማርያም ያለ አባት እንደተወለደ አምኖ ይመሰክራል፡፡ ሲራህ. 3፤45-49፣ ሱራህ 4፤171 ቁርአናቹህ ኢየሱስን ነፍስን እንደፈጠረ ይናገራል፡፡ ታዲያ ያለ ፈጣሪ በስተቀር ነፍስን መፍጠር ለማን ይቻላል? ቁርአናቹህ ኦሪትንም ወንጌልንም ከእግዚአብሔር እንደወረዱ ይናገራልና መጽሐፍ ቅዱስን አምናቹህ ልታደርጉ የሚገባቹህን በማድረግ ዳኑ፡፡ ሱራህ 3፡3፣44-48
To Ato Mesfin, and Amsalu-
i apperciate the conversation between you two guys about the historicity of different personalities from the bible. i believe and historically verifiable that Jesus at least has “ethiopian” blood if not fully blooded. When we say ethiopia, i put it in qotation for good reasons as there are different ethnicities within that country. Even the name ethiopia is debateable as to which people group it referes for there is a concrete historical evidence that the center of ethiopia is in present day sudan than in present day ethiopia. But whether it includes presentday ethiopia is a different matter. My argument is that if we know the different tribal or ethnic groups orgin and historical trajectories of those ethnic group’s social development, we can certainly shed light that the bible’s historical narrative is shared by ethiopian people’s! There are many geez literatures that talks about israel or jewish people in ethiopia before and after the birth of christ. i belive that those litratures are true unless otherwise proved to be false! More than that the origin of semetic language and culture is in the continent of Africa than middle east-so if culture has to flow, it should be first from Africa than vias versa! Third you can find archeological evidence that tells the different ethnic groups of the present day ethiopia from the Aksumite and Da amat period-such as saba, habeshat, eber…etc Given the above evidences, we can be shure that there was some sort of assocation between the people of the book and the different tribal/ethnic people of ancient ethiopia/aksum. i do not like the way Mesfin was arguing in that he is certain that some of the personalities in the bible do not relate to ethiopia at all-he might also think that the Ark of the covenant’s presence is a fairy tale-for i smell from the way he argues. We need people like walelenge mekkonen to break the ice so that our countries history be examined throughly. Any ways-if you guys can make a blogspot to discuss such issues, i will be glad to participate! Anyways, i hope one day, a new generation will rise up to clear the dust from our countries and its people history-it already began by the work of walelinge mekonnen! Even yekno Amlak claims decent from solomon-so mesfin, was he making it up? how abot amsalu-do you have the answer?
Dear Sayint,
You come across as an arbiter of no consequence. First, you are commenting in English on an article written in Amharic thus excluding many whose history it is we are discussing. Second, your arguments are based on hearsay and wishful thinking. Nothing about the Ark was raised in Amsalu’s article but you still “smell” I take it to be a fairy tale. You “believe and historically verifiable that Jesus at least has “ethiopian” blood if not fully blooded.” No evidence for it other than that YOU say so. I suggest you get your facts together before you present your argument.
Haven’t you read the article at all @Sayint? or you lost your attention while you are reading ? because I mentioned clearly the geographical location of Ethiopia Biblically. I don’t understand why you are argue the geographical location of Ethiopia after you read. Read it again attentively.
What I want to say about your last question is that, off course history has the answer for all questions we have, evidences never perish or destroy at all in any cases. But viewers of the historical events have many different eyes with different interests. Most of them couldn’t believe what they see. they believe what they want to see or what they want it to be.
@Sayint because of that, it is so difficult to argue or discus about the issue you want we discus. The problem is as I mentioned above we already believe the history what we want to have, to hear. specially Know a day’s in our country there is no one worry about the veracity of the history. Everybody created his fictitious history. but that is what he would like to be, not the real nor his past.
That all problems are comes from ethnic politics created by your Hero Walelligne Mekonen and his sorts of persons. What Walelligne Mekonen and his disciples Woyyane couldn’t understand and realized is that, substantially there is no nations and nationalities or Ethnic groups on the ground. @Sayint I’m not saying his idea about equality in nations and nationalities or ethnic groups is wrong. It is blessed idea and must acceptable.
“እውን ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ ነውን?”
በሚል ርእስ፡ ከሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው፡ ለቀረበው መጠይቃዊ ትችት፡
ከኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት አገልጋይ፡
ከእኔ፡ ከንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ-ኢየሱስ፡
የተሰጠ፡ የማብራሪያ መልስ።
መግቢያ
“እውን ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ ነውን?” በሚል ርእስ፡ ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
የተባሉ ሰው፡ በኅዋ አውታር ሰሌዳ ላይ፡ በይፋ ያወጡትን ጽሑፍ፡ እኔም ስላነበብሁት፡ የኅዋ
መድረኮቻችን ተከታታዮችና ተሳታፊዎች ለኾናችሁት ኹሉ፡ ይህን መግለጫ ማቅረብ አስፈላጊ ኾኖ ስለአገኘሁት፡ እነሆ፡ አቅርቤላችኋለሁ።
ይህን መግለጫ ማቅረብ አስፈላጊ ኾኖ ያገኘሁትም፡ እንዲያው ያለበቂ ምክንያት አይደለም።
ምንም እንኳ ጸሓፊው፡ በዚያ ድርሰታቸው ውስጥ፡ ስሜን፡ ለይተውና ግልጽ አድርገው
ባይጠቅሱም፡ ““ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ ነው” የሚለውን ጨምሮ ብዙ እንግዳ የሆኑ ነገሮችን የሚናገሩ ሦስት “አባቶችን” አውቅ ነበር፤ አንደኛው ከሀገር ውጭ ናቸው፡፡” ሲሉ ካሠፈሩትየመግቢያ ዐረፍተ ነገራቸው፡ “‘አንደኛው’፡ እኔ ሳልኾን አልቀርም!” ብዬ ስላሰብሁ ነው።
“‘አንደኛው’ እኔ ሳልኾን አልቀርም!” ብዬ ማሰቤም፡ እንዲያው ያለበቂ ምክንያት አይደለም።
“የእግዚአብሔር ልጆች” በኾኑት፡ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያት ዘንድ፡ በሕያውነት ተጠብቆ በቀጠለው፡ በኢትዮጵያ የህልውና ዜና መዋዕል ካልኾ ነ በቀር፡ “የሰው ልጆች” ተብለው፡ በምውትነት በተፈረጁት፡ በመላው ዓለም የአሕዛብ ታሪክ ዘንድ እስከዛሬና ዛሬም ቢኾን፡ “ወልደ አብ ወልደ ማርያም ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ኢትዮጵያዊ ነው!!!” ብዬ፡ በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኮ፡ ለመጀመሪያ ጊዜ፡ በቃልም፥ በመጽሓፍም ያወጅሁ፥ ከዚህም እውነታ ጋር፡ በአገር ውስጥ ግዞተኝነትና በፈቃድ ስደት፡ በውጭው አህጉር የምዘዋወር፡ እኔ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ኢትዮጵያ አገልጋይ በመኾኔ ነው።
በተጭማሪም፡”“ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊ ነው” የሚለውን ጨምሮ ብዙ እንግዳ የሆኑ
ነገሮችን ከሚናገሩ ሦስት “አባቶች” መካከል፡ ምናልባት፡ ያ አንዱ እኔ ሳልኾን ብቀር እንኳ፡
ይህ ጥያቄ፡ ለማንኛውም፡ ጽሑፋዊ መልእክት፡ አርእስት ኾኖ መቅረቡን የተመለከተ እውነተኛ
ኢትዮጵያዊ ኹሉ፡ ወንድ፡ ኾነ ሴት፥ ይልቁንም፡ ኪዳናዊው እና ኪዳናዊቷ፡ የነገሩን እውነታ
ሳያጣሩና ሳያስተካክሉ፡ በምንም መልኩና ይዘቱ፡ እንዲያው፡ ዝም ብለውና አግድመው ሊያልፉት ስለማይቻላቸው፡ እኔም፡ በኪዳናዊ ኢትዮጵያዊነቴ፡ ይኸው ግዳጅ ስለሚመለከተኝ ነው።
ለመግቢያ ያህል፡ ይህ ይበቃልና፡ አኹን፡ ወደዋናው ቍም ነገር እገባለሁ፦
አዩ! ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው! እውነተኛ፡ የእግዚአብሔር ሰው ቢኾኑ ኖሮ፡
“አባቶች” ያሏቸውን፡ የሦስቱንም ሰዎች ስሞች ዘርዝረው ባስታወቁ ነበር። እኔም፡ ስለራሴ፡ ይህን
ኹሉ ማተተት ባላስፈለገኝ ነበር። ስማችንን ለመግለጥ፡ ከቶ፡ ምን አስፈራዎ? ወይስ፡ ምን
አሳፈረዎ? እውነተኛ፡ የእግዚአብሔር ሰው፡ እንዲህ አያደርግም። ወይስ፡ ያ፡ ያሉት ሰው፡ እኔ
ሳልኾን፡ ሌላ ነውን? ሌላ ከኾነ፡ አኹንም፡ ማንነነቱን፡ ከነስሙ ሊገልጡት ይገባል። አለዚያ፡
ሊቃችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ “እስመ ኵሉ፡ ዘእኩይ ምግባሩ፡ ይጸልእ ብርሃነ፤ ወኢይመጽእ ኀበ
ብርሃን፡ ከመ ኢይትከሠቶ ምግባሩ፤ እስመ እኩይ ውእቱ። ወዘሰ፡ ጽድቀ ይገብር፡ ይመጽእ ኀበ
ብርሃን ከመ ያስተርኢ ምግባሩ፣ እስመ በእንተ እግዚአብሔር ይገብር።”
ማለትም፡ “ክፉ የሚያደርግ ኹሉ፡ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ፡
ወደብርሃን አይመጣም። እውነትን የሚያደርግ ግን፡ ሥራው፡ በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደኾነ ይገለጥ ዘንድ፡ ወደብርሃን ይመጣል።” ብሎ የተናገረው፡ መለኮታዊ ቃሉ ይጸናብዎትና ይኰነኑበታል። (ዮሓ. ፫፥ ፳-፳፩።)
የፈጣሪያችንና የአምላካችን፥ የጌታችንና የመድኃኒታችን፥ የንጉሠ ነገሥታችንና የሊቀ
ካህናታችን፡ የኢየሱስ ክርስቶስንና የቅድስት እናቱን፡ ኢትዮጵያዊነት የሚናገሩትን መጻሕፍቴን፡
እርስዎ እንዳነበቧቸው የሚያረጋግጠው፡ ይህ፡ የትችት ድርሰትዎ፡ የያዛቸው ቍም ነገሮች፡ በሙሉ፡ ከዚያ የተቀዱ መኾናቸውን፡ መጻሕፍቴን ያነበበ ኹሉ በቀላሉ ሊገነዘበው የሚችል ነው።
እንዲህ ከኾነ፡ ያው፡ ከጽሑፍዎ እንደሚታየው፡ በአንድ በኩል፡ የእርሱን፡ የጌታችን፡
የኢየሱስ ክርስቶስን ኢትዮጵያዊነት፡ ራስዎ እያሳዩ፡ በአንጻሩ ደግሞ፡ ኢትዮጵያዊ አለመኾኑን
ለማሳመን ይሞክራሉ። በዚህ ረገድ፡ ራስዎን፡ በራስዎ እያስተሓቀሩ፡ የእግዚአብሔርን እውነት
ለማምታታትና ሰዎችን ለማሳሳት፥ ለፀረ ኢትዮጵያ ወገኖችም መሣሪያ በመኾን ሊያገለግሉ፡ ዓላማዎ አድርገው የተነሡ መኾንዎን፡ በራስዎ ላይ፡ ራስዎ ይመሰክራሉ።
ለዚህም እውነታ፡ ሌላ ማስረጃ ፍለጋ መኼድ አያሻም፤ እንዲህ የሚለው፡ የራስዎ አባባል
ይበቃል፦ “ኢየሱስ ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ እያወቅን በግድ ኢትዮጵያዊ ለማድረግ መሞከር ሀገርን የመውደድ መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ሐሰት ለምንም ነገር ቢሆን የጸና መሠረት ሊሆን
አይችልምና፡፡ እንዲህ ብሎ በከንቱ ከመድረቅ ይልቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በዳዊት ልጅ በጠቢቡ
ሰሎሞን እናት በቤርሳቤህ በኩል ኢትዮጵያዊ ደም አለበት ቢባል መልካምና ተአማኒም ነበር፡፡
የሰሎሞን እናት የኦርዮ ሚስት የነበረችው ቤርሳቤህ ኢትዮጵያዊት ናትና፡፡ ሰሎሞንም ራሱ
በመኃልይው “እናንተ የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ሆይ እኔ ጥቁር ነኝ፤ ነገር ግን ውብ ነኝ፤ እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞን መጋረጃዎች ፀሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለሆንኩ አትዩኝ” ብሎ ተናግሯልና መኃልየ መኃልይ ዘሰ. 1፤5-6.”
በመሠረቱና በአጠቃላይ፡ የቅዱሱ ኪዳን የኢትዮጵያ ልጆች፡ እስከዛሬ፡ ለ፯ሺ፭፻፮ (ለሰባት
ሽህ አምስት መቶ ስድስት) ዓመታት፡ አምነውበትና ሕይወት አድርገውት የኖሩት፥ አኹንም፡ እኛ
መሰሎቻቸው፡ ከእነርሱ ተረክበን እየኖርነው ያለነው፡ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት እግዚአብሔራዊ እውነት፡ ለእርስዎ፡ በትክክል እንዳልተገለጠልዎት ይታያል፤ የእኔን መጻሕፍት፡ አንብበውም ኾነ ሳያነብቡ፡ መልእክቱን፡ በመንፈሳዊው ብርሃን፡ ፍጹም አውቀውት የተረዱትም አይመስልም።
እንዲህ ከኾነ፡ እርስዎም፥ እኔም፡ ውድ ጊዜያችንንና የአእምሮ ኃይላችንን፡ በከንቱ ማባከን
አያስፈልገንም። እኔም፡ በመጻሕፍቴ ውስጥ የሠፈሩትን ሓተታዎች በሙሉ፡ እንደገና፡ ለእርስዎ
መዘብዘብ አይቻለኝምና፡ እነዚያን መጻሕፍቴን፡ የማንበቡን ተግባርና ኃላፊነት፡ ለእርስዎ፡ ለራስዎ፡ በባለአደራነት እንድተውልዎ፡ ግድ ይኾንብኛል።
መጻሕፍቴን አንብበዋቸው ከኾነ ግን፡ “እፎ እንከ፡ ኢተአምኑ ቃልየ? እስመ ኢትክሉ
ሰሚዐ፡ ነገረ ዚአየ። አንትሙሰ፡ እምአቡክሙ፡ ሰይጣን አንትሙ፤ ወፍትወቶ ለአቡክሙ፡ ትፈቅዱ ትግበሩ። …ዘሰ፡ እምእግዚአብሔር ውእቱ፡ ቃለ እግዚአብሔር ይሰምዕ፤ ወበእንተ ዝንቱ፡ አንትሙሰ፡ ኢትሰምኡኒ ፤ እስመ ኢኮንክሙ እምእግዚአብሔር።”
ማለትም፡ “በቃሌ የማታምኑት፡ ስለምንድር ነው? የምነግራችሁን ልታስተውሉ
ስለማትችሉ ነው። እናንተ፡ ከአባታችሁ፡ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ የእርሱን፡ የአባታችሁን ፈቃድ
ልታደርጉ ትወድዳላችሁ። …ከእግዚአብሔር የኾነ፡ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ግን፡
ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና፡ ስለዚህ፡ አትሰሙኝም።” ሲል መምህራችን ኢየሱስ ክርስቶስ
የተናገረው ቃል፡ በእርስዎ ላይ ተፈጻሚ ይኾናል። (ዮሓ. ፰፥ ፵፪-፵፯።)
እርስዎ፡ ይህን የመሰለውን፡ የተምታታና የተዘባረቀ ትችት ከሰጡ በኋላ፡ አኹንም፡ “ኢየሱስ
ክርስቶስ፡ ኢትዮጵያዊ አይደለም!” ካሉ፡ ታዲያ፡ “ማነው፧” ይላሉ? ለምን፡ ለዚህ ጥያቄ፡
አንዳችም መልስ ሳይሰጡ፡ በዝምታ አለፉት? በቀዮቹ ኦሪታውያን አይሁድና ኦርቶዶክሳውያን
ግብፆች፥ እንዲሁም፡ እርስዎን በመሰሉት ተከታዮቻቸው ዘንድ፡ “ሴማዊ ነው!”፥ በነጮቹ ዘንድ፡
“ያፌታዊ ነው!”፥ በጥቁሮቹም ዘንድ፡ “ካማዊ ነው!” ከተባለ፡ ትክክለኛ ማንነቱ፡ “ይኸኛው ነው!” ብለው፡ ለምን፡ ከሦስቱ፡ አንደኛውን መርጠው አላስታወቁም?
ዓላማዎ፡ የሓሰቱ አባትና የፀረ ኢትዮጵያ ባዕዳኑ መሣሪያ በመኾን፡ የእግዚአብሔርን እውነት
ለማፍረስ እንጂ፡ ለማነጽ የተነሣሡ አለመኾኑ፡ በዚህ አድራጎትዎ ይታወቃል።
እኛ ግን፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስቱ የኖኅ ልጆች፡ የጋብቻ ውሕደት እንደተወለደውና
በመጨረሻው የሕይወት ዘመን፡ ከድንግል ተወልዶ፡ ፍጥረተ-ዓለሙን በሙሉ፡ በቤዛነቱ ላዳነው፡
ለመሢሁ ቃለ እግዚአብሔር፡ ቀዳሚ አርአያነት፥ ከዚህ የተነሣም የመጀመሪያው መልከ ጼዴቅ
ለመኾን እንደበቃው፥ እንደኢትዮጲስ፥ “ኢትዮጵያዊ ነው!” እንላለን። “ኢትዮጵያዊ” የሚያስሰኘው፡ ይህ፡ ከሦስቱ የኖኅ ልጆች፡ ማለትም፡ ከሴም፥ ከካምና ከያፌት፡ የዘር ውሕደት መወለድ ነውና። በባለምሥራቾቹም (በወንጌላውያኑም) መጻሕፍት የተመዘገበው፡ የኢየሱስ ክርስቶስ፡ የትውልድ ሓረግ፡ ይህንኑ እውነታ እያረጋገጠ ይገኛል።
እንዲህ ካልኾ ነ፡ ታዲያ! እርስዎስ፡ ለምን፡ “ሕዝበ እስራኤልን ከእግዚአብሔር ጋር
ያስተዋወቃቸው አብርሃም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አብርሃምን የባረከውና አብርሃምም ዐሥራትን ለእሱ ያወጣለትና አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋራ ከመተዋወቁና እግዚአብሔርን አምላኪ ከመሆኑ በፊት የእግዚአብሔር ካህን የነበረው ግን መልከጸዴቅ ነው፡፡ ይህ ሰው ኢትዮጵያዊ ነበረ ወይም ነው፡፡” ብለው ጻፉ?
አዩ! መንፈስ ቅዱስ፡ እንዴት ፊትዎን ጸፍቶ፡ የእግዚአብሔርን እውነት እንዳናገረዎና
እንዳጻፍዎ ይመለከቱት!? ታድያ! መልከ ጼዴቅ፡ እንዲህ ኢትዮጵያዊ ከኾነ፡ ኢየሱስ ክርስቶስም፡ እንደእርሱ፡ “ኢትዮጵያዊ” መኾኑን፡ አምኖ መቀበል፡ የማያፈናፍን የእውነት ግዴታ መኾኑ አይደለምን? አዎን! ነው እንጂ።
እስኪ፡ ከቻሉ፡ በውስጥዎ ሰፍኖ፡ በገሃድ ከሚታየው፡ የግል ጥላቻና ክፉ ቅንዓት፡ ራስዎን፡
ለጥቂት አፍታም ቢኾን፡ ንጹሕና ነጻ ያድርጉና፡ የእግዚአብሔርን እውነት፡ በቅንነት ዓይንና በበጎ
ማስተዋል ይመልከቷት!
እርስዎ፡ ራስዎን፡ ማነኝ ይላሉ? “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” የሚሉ ይመስለኛል። “ኢትዮጵያዊ
ነኝ!” ካሉ፡ ታዲያ! “ምንድን ነኝ?” ወይም፡ “ማነኝ?” ማለትዎ ነው? “ኢትዮጵያዊነት” ከቶ
ምንድር ነው? ምን ማለት ነው? በእኔ በኩል፡ የቅዱሳት መጻሕፍትን ምስክርነት በመጠቃቀስ፡
መጻሕፍቶቼ ኹሉ፡ የሚናገሩትና የሚያስረዱት፥ የሚያትቱትና የሚያብራሩት፡ ስለዚሁ፡
ስለኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያዊነት፥ ስለኢትዮጵያዊውና ስለኢትዮጵያዊቷ ነው። ስለኢትዮጵያና
ስለኢትዮጵያዊነት፡ ከዚህ የተለየ፡ የእርስዎ፡ የትርጓሜ ሓተታ ካለዎ ደግሞ፡ እስኪ፡ ያንን፡ እባክዎን ያሰሙን?
ነገር ግን፡ እርስዎ፡ በእውነት፡ “ኢትዮጵያዊ ነኝ!” ካሉ፡ ኢየሱስ ክርስቶስ፡ “ኢትዮጵያዊ
ነው!” የሚለው ይትበሃል፡ ደስ ሊያሰኝዎ ይገባል እንጂ፥ ያም ባይኾን እንኳ፡ ይህን ከመሰለው፡
በዘለፋ ከተመላው፡ የተቃውሞ ትችትዎ በፊት፡ “እስኪ፡ በቅድሚያ፡ በበለጠ ይብራራልኝ!” ሊሉ
ይገባ ነበር እንጂ፡ እንዴት፡ ይህን ያህል፡ የቁጣና የንዴት ቃላትን እስከማስጻፍ የሚያደርስዎ ኾነ!? ይገርማል!
በእርስዎ ላይ አድሮ፡ ይህን ዓይነቱን የድፍረት ትችት፡ በተለያየ መልኩ እንዲሠነዝሩ
ያደረገው መንፈስ፡ በቀጥታ፡ ፀረ-ኢትዮጵያውና ባዕዱ እንጂ፡ የመንፈስ ቅዱስ ቅኝት አለመኾኑን
አስተካክሎ ያመለክታል።
በመጻሕፍቴ ውስጥ ካወሳኋቸው፡ ከእነዚህ የቅዱሳት መጻሕፍት ጥቅሶች መካከል፡ የቅርቦቹንና
የተለመዱትን፡ ለዓይነት ያህል፡ ባለመሰልቸት፡ አንድ ኹለቱን፡ እዚህ ላይ እስኪ ላውሳቸው!
እነዚህም፡ “ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር!” ማለትም፡ “ኢትዮጵያ፡ እጆቿን፡
ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች!”፥ ደግሞም፡ “አኮ፡ ከመ ደቂቀ ኢትዮጵያ፡ አንትሙ ደቂቀ
እስራኤል! ይቤ እግዚአብሔር፡ ዘኵሎ ይመልክ ስሙ።” ማለትም፡ “ስሙ፡ ‘ኹሉን የሚገዛ’ የተባለው እግዚ’አብሔር፡ ‘እናንተ የእስራኤል ልጆች! እናንተ እኮ፡ በእኔ ዘንድ፡ እንደኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁም!’ አለ።” የሚሉት የእግዚአብሔር ቃላት ናቸው። ታዲያ! በእነዚህ ሕያዋን፡ የአምላክ መልእክቶች ውስጥ፡ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል፡ ማንን የሚያመለክት ይመስልዎታል? ለማን የተሰጠስ መስሎ ይታይዎታል? (መዝ. ፷፯፥ ፴፩። አሞ. ፱፥ ፯።)
“ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል፡ “ኢትዮጲስ” ከተባለውና ኢየሩሳሌምን ቈርቍሮ ከነገሠባት፡
ከመጀመሪያው መልከ ጼዴቅ የተወረሰ ሲኾን፡ ኋላ፡ በመጨረሻው የሕይወት ዘመን፡ ከዚሁ ከመልከ ጼዴቅ ዘር ተገኝታ፡ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደችው፥ ከዚህ ማንነቷ የተነሣም፡ የሰው ዘር ኹሉ እናት ለመኾን የበቃችው፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ካልኾ ነች በቀር፡ ከቶ፡ ሌላ ማንን ልትኾን ትችላለች? ሌላ፡ ማንንም ልትኾን አይቻልም። ቃሉስ፡ ለማን ሊሰጥ ይቻላል? ይህ፡ “ኢትዮጵያ” የሚለው ቃል፡ ለቅድስት ድንግል ማርያም ካልኾነ በቀር፡ ለሌላ፡ ለማንም ሊሰጥ፡ ከቶ አይቻልም።
የአምላክ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፡ እንዲህ፡ “ኢትዮጵያ” ከኾነች፡ ልጇ ኢየሱስ
ክርስቶስም፡ በእርግጥ፡ “ፍጹሙ ኢትዮጵያዊ ነው!”። አዎን! ለቅዱሱ ኪዳን፡ ታማኞች ኾነው
የተገኙ፡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያትም ኹሉ፡ ልጆቿ ኾነው፡ “የኢትዮጵያ ልጆች” ይባላሉ።
እርስዎም፡ በጽሑፍዎ እንደመሰከሩት፡ መልከ ጼዴቅ፡ ኢትዮጵያዊ መኾኑን እያወቁ፡
አይሁድ፡ ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ለማጥፋት በመሞከር፡ “አባትና እናት፥ የትውልድም ቍጥር
የሉትም!” ብለው፡ ሓሰቱን እንደጻፉ ኹሉበመጻፋቸው፥ ቀደም ብለውም፡ ሙሴ፡ ወደኢትዮጵያ
መጥቶ በመኖር፡ በኢትዮጵያዊነቱ፡ ኢትዮጵያዊቷን ሲጳራን አግብቶ፥ ከርሷ ልጆችን በመውለድ፡
እስከመጨረሻው፡ በኢትዮጵያዊው ሥርዓት፡ ከእርሷ ጋር ብቻ፡ በኪዳነ አዳም ወሔዋን ተወስኖ
በመኖሩ፡ እኅቱና ወንድሙ ጭምር ቀንተውበት፡ በክህደትና በዓመፅ በተነሡበት ጊዜ፡ በፈጣሪያቸው ቍጣ፡ በመቅሠፍት እንደተቀጡ ኹሉ፡ አኹንም፡ የእርስዎ ጽዋ፡ የእነዚህኑ የቀደሙትን ደፋሮች አይሁድ ዕጣ እንዳይኾን፡ ያስፈራልና፡ ወደተፈጥሮአዊውና ኪዳናዊው ኢትዮጵያዊ ማንነትዎ ተመልሰው፡ ራስዎን፡ ለእውነተኛው ንስሓ እንዲያበቁ እመክርዎታለሁ።
እንግዴህ፡ “ኢትዮጵያዊነት”፡ “ፍጹሟ ኢትዮጵያ” በኾነችው፡ በድንግል ማርያምና “ፍጹሙ
ኢትዮጵያዊ” በኾነው፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ሰውነት የተከሠተው ሲኾን፡ እርሱም፡ ንደእውነተኛው
ዐምሓራነት፥ ወይም፡ እንደእውነተኛው ክርስቲያንነት ኹሉ፡ ሦስቱን የዓለም ታላላቅ የዘር ግንዶች አዋሕዶ አንድ ያደረገ፡ የእግዚአብሔር ሥርዓት እንጂ፡ ዛሬ፡ በአንድ ወገን፡ በምድረ ኢትዮጵያ፡ ለዝንተ ዓለም፡ አንድ ኾኖ የኖረውን ሕዝብ፡ “አገው!”፥ “ትግሬ!”፥ “ጕራጌ!”፥ “ኦሮሞ!”፥ “ሓዲያ!”፥ “ዐደሬ!”፥ “አፋር!”፥ “ሱማሌ!” ተባብሎ፥ በሌላ በኩል ደግሞ፡ በመላው ዓለምም፡ “ሴማዊ!” ወይም፡ “ቀይ!”፥ “ካማዊ!” ወይም፡ “ጥቁር!” እና “ያፌታዊ!” ወይም፡ “ነጭ!” ተባብሎ እግዚአብሔር አምላክ፡ በተፈጥሮና በቤዛነቱ አንድ ያደረገውን ሕዝብ፡ በዘር፥ ወይም፡ በገላ ቀለም የሚለያየው፡ የሰዎች የአገዛዝ ፈሊጥ አይደለም።
እዚህ ላይ፡ ሳይወሱ የማይታለፉ፡ ኹለት ቍም ነገሮች አሉ፤ እነዚህም፦
፩ኛ. በትችትዎ መነሻ፡ “እነኝህ “አባቶች” ተከታዮች እያፈሩ መጡና ዛሬ ላይ እነሱ
የሚሉትን የሚያምኑ ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባሉ ሰዎችን እያየን ነው፡፡ እነዚህን እንግዳ
አስተምህሮዎቻቸውንም በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (social media) በከፍተኛ ደረጃ እየናኙት ይገኛሉ፡፡ …ይህ እንቅስቃሴ በቸልታ ሊታይ የሚገባው አይደለም፡፡” ሲሉ የሠነዘሩት አስተያየት፡ ትኩረት ሊሰጠውና ሊተችበት የሚገባ ኾኖ አግኝቼዋለሁ።
በዚህ አስተያየትዎ፡ እነሆ፡ በመንፈስ ቅዱስ ጸጋና በረከት፡ የብዙዎችን ልብ፡ በመለኮታዊው እውቀትና በእውነተኛው ንስሓ፡ በበለጠ እየማረከ ሲኼድ በሚታየው፡ በዚህ፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት አገልግሎት መጠናከርና መስፋፋት፡ እርስዎና እርስዎን የመሰሉት ደካሞችና አስጠቂዎች፡ እጅግ የተደናገጣችሁና የተሸበራችሁ ይመስላል። ይኸውም፡
በሰይጣናዊው የክፋትና የጥፋት ድቡሽት ላይ የቆመውና በቅዱሱ ኪዳን ላይ በፈጸማችሁት ፡
የክህደትና የዓመፅ፥ የአምልኮ አመንዝራነትም ኃጢኣት፡ የህልውና መሠረታችሁ፡ በስብሶ፡ ሊወድቅ እያዘነበለ መኼዱን፡ ይኸው፡ በገዛ ዓይናችሁ እያያችሁ በመኾናችሁ ነው።
የዚህ ምክንያቱ ግልጽ ነው፦ ራሷ “ኢትዮጵያ” የኾነችው፡ የአምላክ እናት ድንግል ማርያም፡ በአገርነትና በእናትነት፥ በተዋሕዶ ሃይማኖትነትና ንግሥትነት፥ ራሱም፡ “ኢትዮጵያዊ” የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ፡ በፈጣሪነትና በአባትነት፥ በሊቀ ካህናትነትና በንጉሥነት በሚመሯት፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፡ ባለፈው ነሓሴ ፲፮ ቀን፥ ፳፻፭ ዓመተ ምሕረት፡ አንድ ታላቅ ቃለ ዓዋዲ (የአዋጅ ቃል)፡ ለመጀመሪያ ጊዜ፡ ለፍጥረተ ዓለሙ መታወጁ ይታወሳል።
ይህ አዋጅ፡ በኢትዮጵያ እና በሕዝቧ ላይ፤ ለሦስት ሽህ ዓመታት ጸንቶ የኖረው፡ የኦሪታውያኑ አይሁድ እርሾ እና በመጨረሻዎቹ የአንድ ሽህ ስድስት መቶ ዓመታት ውስጥ ደግሞ፡ በኦርቶዶክሳውያኑ ግብፃውያን ጠንቅ፡ ተጠናክሮ የቀጠለው፡ የፀረ ኢትዮጵያው የክፋት
ኃይል፡ አኹን፡ በቅዱስ ኪዳኗ ኢትዮጵያ፥ እውነተኞች ኪዳናውያንና ታማኞች ኪዳናውያት ልጆቿ፡ ቆራጥነትና ጀግንነት፡ ለአንዴና ለዘለዓለሙ እንዲወገድላቸው መደረጉን ያበሠረውና ያረጋገጠው መለኮታዊ ክሥተት ነው።
በዚህ መለኮታዊ ክሥተት አማካይነት፡ በእግዚአብሔር እውነትና በመንፈስ ቅዱስ አምልኮ፥ በፍጹም ፈቃደኛነትና በልባዊ ንስሓም፡ እያንዳንዳቸው፡ እየራሳቸውን፡ በነፍስ ወከፍ፡ ከዚያ፡ ከፀረ ኢትዮጵያው የክፋት ኃይል፡ ነጻ ለማውጣት፡ በእምነት የተዘጋጁ ሰብኣውያን ፍጡሮች ኹሉ፥ ወንዶችም፥ ሴቶችም፡ ለተገዢነቱ ብቻ ሳይኾን፡ ለባርነቱ ጭምር፡ ተሽመድምደው
እንዲያጎበድዱ፥ እስከዛሬም ድረስ፡ በየዘመናቱ፡ ላልተቋረጠው፡ የእርስ በርስ ዕልቂት ዳርጓቸው፡
ሲያስጨራርሳቸው የኖረው፡ ያ፡ የዲያብሎስና የባዕዳኑ የአገዛዝ ቀንበር፡ ከኹለንተናቸው ተሽቀንጥሮ እንደተጣለላቸው አውቀውና ተገንዝበው፡ እጅግ ደስ ብሏቸው፡ ይህን ቸርነት ያደረጉላቸውን ፈጣሪያቸውንና ቅድስት እናቱን ሲያመሰግኑ ይኖራሉ።
ከዚህ የተነሣ፡ በአኹኑ ዘመን፡ እግዚአብሔር፡ በመልኩ የፈጠረው እና “ከእኛ፡ እንደአንዱ ኾነ!” ያለው፡ ሰብኣዊ ፍጡሩ፡ ባስገኛቸው፡ የሥነ እውቀት ፍሬዎች በመጠቀም፡ ማንኛውም ምድራዊ መንግሥት ሊቋቋመውና ሊከላከለው፥ ሊቆጣጠረውና ሊያስወግደው ባልቻለው ማዕበላዊ ኃይል፡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን፡ የመላው ዓለም ኅብረተሰብ ጭምር፡ በረቂቁ የኅዋ መስመር ሳይቀር፡ እርስ በርሱ ለመገናኘትና አሳቡን፡ በቀጥታና በግልጽ ለመለዋወጥ በመቻሉ፡ ያ፡ እርስዎና እርስዎን የመሰሉት ኹሉ፡ የክፋትና የጥፋት ሰይጣናዊ ምሥጢራችሁን፡ በጨለማ
ሠውራችሁ ያሳለፋችሁት፡ የጭቆናና የግፍ አኗኗር፡ በመንፈስ ቅዱስ፡ መለኮታዊ ብርሃን፡ ግድቡ
ፈርሶ፡ ሰው ብቻ ሳይኾን፡ ፍጥረተ ዓለሙ ኹሉ፡ በእግዚአብሔር የእውነትና የእውቀት ጸጋ፡ በነጻነት የሚጥለቀለቅ ኾኗል።
ስለዚህ፡ በሰማያዊውና በምድራዊው ፍጥረታተ-ዓለማት ዘንድ፡ በምልዓት በሰፈነችው፡ በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፡ የኪዳናውያንና የኪዳናውያት ልጆቿና
ዜጎቿ፥ ነጋሢዎቿና ካህናቷ ብዛት፡ ገና፡ እንደባሕሩ አሸዋና እንደሰማዩ ከዋክብት፡ እጅግ በርክቶ፡
ሊቈጠር እስከማይቻልበት መጠን የሚደርስ እንደሚኾን፡ እርግጠኛ ኾነው ይጠባበቁ!
፪ኛ. “‘ኢትዮጵያይ ዐምሐራይ’ የሚባል ሃይማኖት ያሉትን ድርጅት መሥርተው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምን ይደረግ?” ያሉት፡ እነማንን ማመልከትዎ እንደኾነ አላወቅሁም።
የእኛዪቱ ግን፡ ምናልባት፡ እርስዎም፡ በአኹን ጊዜ፡ በይፋ ሊያውቁ እንደሚችሉት፥ ከዚህም በላይ፡ ተደጋግሞ እንደተገለጠው፡ በምድራውያን ሰዎች ሳይኾን፡ በመለኮታውያኑ ሥሉስ ቅዱስ እና በእመ አምላክ ቅድስት ኢትዮጵያ ድንግል ማርያም፡ ግዙፉንና ረቂቁን፥ ሥጋዊዉንና መንፈሳዊዉን ፍጥረቷን የምትመራውና የምትንከባከበው፡ የምትመግበውና የምታስተዳድረው፡ ኢትዮጵያ፡ እግዚአብሔር መንግሥት መኾኗን፡ በአዋጁ፡ የምሥራች ቃል ላሳውቅዎ እወድዳለሁ።
ከዚህ የጽሑፍዎ አቀራረብና ከአስተያየትዎ አሠነዛዘር፡ በቀላሉ ለመረዳት እንደሚቻለው፡ እርስዎ፡ የፀረ ኢትዮጵያና የዐምሓራ ጥላቻ ዐባዜ የተጠናወተዎ፥ ከዚህ የተነሣም፡
የጐሠኛነት ጠንቅ ያጠቃቸው ክፍሎች ወገን መኾንዎ፡ በገሃድ ይታወቃል።
መደምደሚያ
እንግዴህ፡ ከላይ፡ በጥቂቱ የተጠቀሱትንና እነርሱን የመሰሉትን፡ የብሉያቱንና የሓዲሳቱን
መጻሕፍት፥ እንዲሁም፡ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር፡ እንደቃል ኪዳኑ፡ በሰብኣውያን ፍጡራኑ ኹሉ ልቦና ላይ የጻፋቸውን ቅዱሳት ቃላቱን፡ ምስክር በማድረግ፡ ከቅዱሱ ኪዳን የተነሣ፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ኢትዮጵያዊ ነው!” ደግሞም፡ “‘የእግዚአብሔር ልጆች’ የተባሉት ኹሉ፡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ናቸው!” ብሎ የምሥራቹን ዜና መናገርና መጻፍ፡ በርስዎ ዘንድ፡ እንግዳ ትምህርት የኾነ ነገርን ማሳወቅ ነውን? መቀባጠርና መዘባረቅ ነውን? በቁም መቃዠት ነውን? ጤንነትን የማጣትና ልብስን እስከመጣል የሚያደርስ፡ የዕብደት ምልክት ነውን? ሓሰትና ክህደት ነውን፧ ዕብለትና ስግብግብነት ነውን? ስስትና ስርቆት ነውን? ሓሰተኛ መምህርነት፥ ሓሰተኛ ነቢይነትና ሓሰተኛ ክርስቶስነት ነውን? በእግዚአብሔር ላይ መቀለድና ማሾፍ ነውን? ንቀትና ሰይጣናዊነትም ነውን?
ጽሑፍዎ፡ በእግዚአብሔር የእውቀት ብርሃን እንዲህ ገሃድ የኾነችውን፡ የኢትዮጵያዊነትን
እውነት፡ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ሲጥሩ የኖሩትን፡ የእግዚአብሔርና የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን
ድርጊት ያስመሰለዎን፡ ይህን ዓይነቱን ትችት፡ በአኹኑ ጊዜ፡ እንዲህ በከረረ ኹኔታ ማቅረብዎ፡
እንኳንስ የሚያሳዝን፡ የሚያስገርምም አይደለም፤ የሚጠበቅ ነውና።
ምክንያቱም፡ እርሱ፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡ ያን መለኮታዊና ትስብእታዊ ተልእኮውን ለመፈጸም፡ በምድር ላይ፡ እርስዎን በመሰሉት ወገኖች መካከል በተመላለስበት ጊዜ፡ እነዚህን፡ አኹን፡ እርስዎ፡ በእኔና እኔን በመሰሉት ኹሉ ላይ የሠነዘርዋቸውን ዘለፋዎች ብቻ ሳይኾን፥ “አብዷል!፥ ሰይጣናትንም፡ ከሚሠቃዩት በሽተኞች የሚያስወጣቸው፤ በአጋንንት አለቃ፡
በብዔል ዘቡል ነው!” ተብሎ መሰደቡ ብቻ ሳይኾን፡ ራሱንም፡ [ሎቱ ስብሓት!] ሰይጣን አለበት!” ማለታቸው፡ በይፋ ተጽፎ፡ በየጊዜያቱ፡ ያለማቋረጥ እየተነበበ ስለሚሰማ ነው።
በኢትዮጵያ፡ የእግዚአብሔር መንግሥት፥ እንዲሁም፡ በኪዳናውያን ኢትዮጵያውያንና
ኪዳናውያት ኢትዮጵያውያት አገልግሎት ላይ ያለዎት፥ የበኩልዎ የግምገማ ውሳኔ ይህ ከኾነ፡ ታዲያ! በዚህ ግብርዎ፡ በዚህ ዓለም፡ በሕይወተ ሥጋዎ፥ በሚመጣውም፡ የነፍስ ህልውናዎ፡ ምን
እንደሚደርስብዎ ተገንዝበውታልን? አልመሰለኝም።
ምን እንደሚጠብቅዎ፡ ለመገንዘብ ይቻልዎ ዘንድ፡ በመለኮታዊው ቃል የተነገረውን የፍርድ
ዓይነት፡ ገላልጦ የሚያስረዳዎትን፡ አንድ ጽሑፍ፡ ከዚህ መልስ ጋር አያይዤ አቅርቤልዎታለሁ።
እርሱም፡ በሊቀ ሊቃውንትነት ዝና፡ እጅግ የታወቁ ለነበሩ፡ አንድ ግለሰብ፡ ጽፌውና ልኬው የነበረ ግልጽ ደብዳቤ ነው። በትኩረትና በማስተውል እንዲመለከቱት የምጋብዝዎ፡ በአክብሮት ነው።
ያም ደብዳቤ፡ በአጠቃላይ ይዘቱና ግቡ፡ የእርስዎን የሚመስል ሲኾን፡ በአርእስቱ አቀራረብ
ብቻ፡ ጥቂት ለየት ማለቱ ነው፦ ይኸውም፡ የእርስዎ፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ላይ ያተኮረ
ሲኾን፥ የእርሳቸው ደግሞ፡ በቅድስት እናቱ፡ በድንግል ማርያም ማንነት ላይ ያተኮረ መኾኑ ነው።
ለንስሓ ፍሬ የሚያበቃዎ፡ መልካም ንባብ ይኹንልዎ!
http://ethkogserv.org/letters/Aleqa%20Ayalew/Le'Aleqa%20Ayyalew%20Tamm'ru%20Mets'haf%20Mels%202002%20A%20M.pdf