በኤርትራ ላይ የሚካሄደው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ የሚጠረጠረውን በሰብዕና የሚፈፀም ወንጀል እንዲያካትት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ትናንት ወስኗል፡፡
ኤርትራ ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እንዲመረምር የተቋቋመው ልዩ አጣሪ ኮሚሽን ሥራውን በአንድ ዓመት እንዲያራዝም የተስማማው አርባ ሰባት አባላት ያሉት የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ክትትል አካል ነው፡፡
ምርመራው ሙሉ ተጠያቂነት ባለበት ሁኔታ እንዲካሄድ የምክር ቤቱ ውሣኔ አክሎ አሳስቧል፡፡
ኤርትራ ውስጥ ይፈፀማል የተባለውን ጅምላ የሰብዓዊ መብቶች ረገጣ የምክር ቤቱ የውሣኔ ሃሣብ ረቂቅ በአጀንዳነት እንዲያዝ ጥያቄ ያቀረቡት ጅቡቲና ሶማሊያ እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት የምርመራውን ጊዜ መራዘም “ኤርትራ ውስጥ እየተፈፀሙ ያሉ” ያላቸው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በጥልቅ እንደሚያሳስቡት አመልክቶ በአፍሪካዊያኑ የቀረበውን የምርመራው ጊዜ በአንድ ተጨማሪ ዓመት የማራዘም ሃሣብ እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ያሳየው ያለመተባበር አካሄድም እንዳሣዘነው የኅብረቱ ተጠሪ ገልፀዋል፡፡
በስብሰባው ላይ የተገኙት የኤርትራ መንግሥት ተጠሪ አቶ ተስፋሚካኤል ገራህቱ ለምክር ቤቱ የቀረበው የውሣኔ ረቂት መሠረተ-ቢስ ለሆኑት ውንጀላዎችና ሪፖርቶች ተቀባይነት ለማስሰጠት የሚደረግ ጥረት መሆኑን አመልክተው የምክር ቤቱ አባላት ረቂቁን እንዲቃወሙ ጠይቀዋል፡፡
ቻይናና ሩሲያ ውሣኔው ፍሬ አያስገኝም ሲሉ እራሣቸውን አግልለዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል እዚህ ላይ ያዳምጡ፡፡
Leave a Reply