መጋቢት 20/ 2006 ዓ.ም ሶዶ ውስጥ ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ በነበረበት ወቅት ለእስር የተዳረጉት የወላይታ ዞን የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ድብደባና ወከባ እንደተፈጸመባቸው የፓርቲው የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ጌታነህ ባልቻ ገለጹ፡፡
በወቅቱ ታስረው ከነበሩት መካከል ወጨፎ ሳዳሞ የወላይታ ዞን ምክትል ሰብሳቢ፣ ታደመ ፍቃዱ የወላይታ ዞን አደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣ አቶ ጻድቁ ወ/ስላሴ የወላይታ ዞን የፋይናንስ ኃላፊ፣ አቶ ቴዎድሮስ ጌታ የዞኑ የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ እና አቶ ቦጋለ የፓርቲው አባል ይገኙበታል፡፡ ጠዋት 4 ሰዓት ላይ የታሰሩት የዞኑ አመራሮች ምግብ፣ ውሃና ልብስ እንዳይገባላቸው ተከልክሎ እንደነበርም የአካባቢው አመራሮች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡
“ከዚህ በፊት ሁለት የፓርቲው አመራሮች በአራዳ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ለፓርቲው ስራ የሚገለገሉባቸውን ሰነዶች ተወስዶባቸዋል፡፡ የዞኑን መዋቅር ለመጎብኘት ከአዲስ አበባ ወደ አካባቢው የተጓዙ ሶስት የፓርቲው አመራሮችና የአካባቢው ተወካዮች ታስረው ስራቸው ከመስተጓጎሉም ባለፈ መገልገያ እቃዎቻቸውን ተቀምተዋል፡፡” ያሉት አቶ ጌታነህ በአሁኑ ወቅት የሚደረገው እስርና ወከባ ከቀደመው የቀጠለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ቅዳሜ መጋቢት 20 የታሰሩት የወላይታ ዞን የፓርቲው አመራሮች ከምሽቱ 4፡00 አካባቢ ከእስር ቢለቀቁም ሲም ካርዳቸውን በመስበር ከጥቅም ውጭ እንዳደረጉባቸው እና በራሪ ወረቀቶችን፣ ሰነዶችንና ሌሎች የመገልገያ መሳሪያዎችንም እንደቀሟቸው ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምሽት የተፈቱት ታሳሪዎች ወደ ቤታቸው በሚያቀኑበት ወቅት የአራዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ታጠቅ፣ በሶዶ ከተማ የአራዳ ክ/ከተማ አስተዳደር አቶ ጌታቸው መኮንን፣ የአራዳ ክ/ከተማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ዝናቡ ተክሌ፣ የአራዳ ክ/ከተማ ደንብ አስተባባሪ አቶ መስከረም፣ እንዲሁም አቶ ተሾመ፣ አቶ ደጉና ሌሎች ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች የሰማያዊ ፓርቲ ወላይታ ዞን አደረጃጀት ኃላፊ የሆነውን አቶ ታደመ ፍቃዱ እና የዞኑ ም/ሰብሳቢ የሆነውን አቶ ወጨፎ ሳዳሞ በመደብደብ ጉዳት እንዳደረሱባቸው ከአካባቢው መዋቅር የተገኘውን መረጃ በመጥቀስ አቶ ጌታነህ ባልቻ ለዝግጅት ክፍላችን አስረድተዋል፡፡ (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)
Leave a Reply