የኤርትራ ከኢትዮጵያ እንድትገነጠል በተደረገበት ጊዜ ታላቅ ሚና ከነበራቸው ባለስልጣኖች አንዱ አምባሳደር ኸርማን ኮኸን እንደነበሩ ይታወቃል። በምእራቡ አለም ደግሞ የቀድሞ ባለስልጣኖች ከጡረታ በዄላም ቢሆን ቁልፍ ሚና ሲጫዎቱ ይስተዋላል። በመሆኑም፤ አርሳቸው በዚሀ ጉዳይ ላይ ህሳበ ሲስንዘሩ ትኩርት መሰጠቱ አስፈላጊነቱን የጎላ ያደርገዋል።ከዚህ በመነሳት ስሞኑን አምባሳደር ኮኸን ይዘውልን ብቅ ያሉትን ጉዳይ አንዳንድ ገጽታዎች በዚህ ጽሁፍ ውስጥ እመረምራለሁ።
አምባሳደር ኸርማን ኮኸን በኤርትራ (ሻቢያ) ላይ የተባበሩት መንግስታት የጣለው ማእቀብ ሊነሳ ይገባዋል ብቻ ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ አሁን በተባበሩት መንግስታት ውስጥ ያላትን ቦታ ተጠቅማ እንዲያውም ስለማእቀቡ መነሳት በግንባር ቀደምትነት ዋናዋ ጠያቂ መሆን አለባት ሲሉ እንደተናገሩ አፍሪካን ኒውስ የተሰኘው ድረ ገጽ ላይ (ሲፕተምበር 28፣ 2017)፡ ሰፍሮ ይገኛል።
የአምባሳደር ኮኸንን ትእዛዝ መስል ንግግር ወይም ምክር ስንመረምር መነሳት ካለባቸው ጥያቄዎች ውስጥ
- በርግጥ ሻቢያ የሚፈልገው ማአቀቡ እንዲነሳለት ብቻ ነውን?
- የሻቢያ ላይ የተጣለውን ማእቀብ ለማስነሳት በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ይገባታልን?
- በዚህ ሁሉ መሀል የኢትዮጵያ ህጋዊና ታሪካዊ መብትና ጥቅምስ ይጠበቃልን ወይስ ይበልጥ ትጐዳለች? የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው
በርግጥ ሻቢያ የሚፈልገው ማአቀቡ እንዲነሳለት ብቻ ነውን?
የሻቢያ ፍላጎት ኸርማን ኮኸን አንደሚሉት የተጣለበት ማእቀብ እንዲነሳላት ማድረግ ብቻ ሳይሆን ትልቅ አጀንዳ ያዘለ ነው። ካሁን በፊት የአስመራ ባለስልጣኖች በተደጋጋሚ እንዳሉትና ባለፈው ሳምንት በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ሲካሄድ የሻቢያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኦስማን ሳላህ እንደተናገሩት “ኢትዮጵያ ለ15 አመታት በህገወጥነት ከያዘችው የኤርትራ ግዛት ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ለቅቃ እንድትወጣ የተባበሩት መንግስታት ተጽእኖ እንዲያደርግ” የሚልም ጭምር ነው። ይህ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያን ፍላጎት ቦታ ሳይሰጥ የተደረገውን የአልጀርስ ስምምነትም ኢትዮጵያ ትቀበል ማለት ነው። ይህ በኢትዮጵያ ላይ በአውሮፓውያን አቆጣጠር በ1994 እና ከዚያም በአልጀርስ ስምምነት የተፈጸሙ አድልኦና ኢፍትሀዊ ተግባሮች እንዳሉ ይቀጥሉ ብሎ በድጋሚ ማረጋገጥ ማለት ነው። እውነታው ይኸ ነው።
የሻቢያ ፍላጎት በራሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ በይፋ እንደተነገረው ከላይ የተጠቀሰውን ተግባራዊ ማድረግ ከሆነ ታዲያ አምባሳደሩ የሚሉትን በማድረግ የሀገራችን የኢትዮጵያ ጥቅም፣ ታሪካዊና ህጋዊ መብት መከበር ወዘተ ሊረጋገጥ የሚችለው ምኑ ላይ ነው? ኢትዮጵያ የምትጠቀመውስ እንዴት ነው፤ የሻቢያ ላይ የተጣለውን ማእቀብ ለማስነሳት ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን የሚኖርባት ለምንድን ነው? ብሎ መጠየቅ አግባብ ነው።
በኔ አመለካከት፣ ሀገራችን በመሪዎቿ እጅግ የተሳሳተ አሳፋሪ ተግባር ምክንያት ኤርትራን በተመለከተ አዘቅት ውስጥ ገብታለች። ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህት ማለያየት ብቻ ሳይሆን የሀገራችንን ታሪካዊና ህጋዊ የባህር በር መብት ወደጎን ተደርጎ፣ የአፋር፣ የኩናማ ወዘተ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ ጩኸቱን ቢያሰማም በፍጹም እናዳምጥም ተብሎ የመገንጠል ተውኔት ተካሂዷል። በዚህ ሂደት ውስጥም የኢትዮጵያ ጥቅም ታሪካዊና ህጋዊ መብት ቦታ አልተሰጠውም ነበር። የአልጀርስ ስምምነት አየተባለ የሚጠራው ስምምነትም የሀገራችንን ጥቅም እንደገነ አሳልፎ የስጠ አሳፋሪ ውል ነው።
በ1994ቱ ሬፈረንደምም ሆነ በአልጀርስ ስምምነቱ ከኢትዮጵያ ይልቅ ትልቊ የሀገራቸን ባለስልጣኖች ትኩረታችው የኤርትራን ጥቅም ማስከበር እንደነበር ይታወሳል።
ኸርምን ኮኸን የሚሉት የኤርትራን መገንጠል ተቀባይነት እንዲያገኝ መለሰ ዜናዊ በጽሁፍ እንደጠየቀው ሁሉ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን ላይ ያለው ክፍል እንደ ቀድሞው ሁሉ የሻቢያን ጥቅም ለማስጠበቅ ግንባር ቀደም ሆኖ መሰለፍ አለበት ነው። ከ1991- 1998 ኤርትራን በተመለከተ የተሰራው ስህተት ሁሉ አሁንም ባዲስ መልክ ይደገም ነው።
ይህን እጅግ የተዛባ አመለካከትን መቀብል ኢትዮጰያ የደረስባትን በደል የሚያስቀጥል ብቻ ሳይሆን የደረስባት በደል ይበልጥ እንዲጠናክር የሚያደርግም ነው። እስካሁን ያገኘው ሁሉ ሳይነካካ እንዳለ ሆኖ ተጨማሪ ግዛትን (ዛልአንበሳ፣ አልኢቴና ወዘተ)፣ ለሻቢያ የሚያስረክብ ነው። ኢትዮጵያ በባህር በር ላይ የሚኖራትን የይገባኛል ጥያቄም በፍጽም እንዳታነሳ አሁንም ተጨማሪ ግዴታ ውስጥ የሚያስገባት ሀሳብ ነው።
ኸርማን ኮኸንም ሆኑ የሻቢያ መንግስት የሚጠይቁት ነገር የመጨረሻ ውጤቱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለ ባህር በር ተከባ ሁልጊዜ በአደጋ ጥላ ስር እንድትኖር የሚያደርግ ነው ። ዛሬ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የራሷን ባህር በር ለሻቢያ አስረክባ ያላትን ሀብትና ንብረት ሁሉ ለጂቡቲና ለአስመራ ስትገብር ትኑር የሚል ፍርደገምድል አመለካከት ነው።
ይህ በኢትዮጵያ ላይ በበደል ላይ በደል መጨመር ነው። ለሀገሩና ለነጻነቱ ቀናኢ የሆነውን ኢትዮጵያዊም በተደጋጋሚ እጅግ ታላቅ ውርደትን እንዲቀበል ተስፋ እንዲቆርጥና አንገቱንም በሀፍረት እንዲደፋ በድፍረት የሚጋብዝ ነው።
“ጉልበተኛ ያደረገው ሁሉ ትክክል ነው“ የሚል ጭፍን አመለካከት ከሌለን በስተቀር በማንኛውም መመዘኛ ቢሆን ለኢትዮጵያ ጥቅም ቅድሚያ እሰጣለሁ ለሚል ከፍል ይህ ከላይ የተጠቀሰው ተቀባይ ሊሆን አይችልም። ስለሆነም የአምባሳደሩ ምክር ወደ ጎን ሊገፋ፣ ውድቅ ሊደረግ ይገባል::
ሻቢያም ሆነ ደጋፊወቹ ለየራሳቸው ጥቅም እንደሚቆሙ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም ከሁሉም በፊት ለሀገራችን ጥቅም ልንቆም ይገባል። በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በመጨረሻው አመታቱ አሁንም ሀገራችንን እስከመጨረሻው ችግር ላይ የሚጥልና የሚያዋርድ ተጨማሪ ስምምነት እንዳይፈጽም እንዲያውም ያለፈውን ስህተት ለማረም ወቅቱ የሚጠብቀውን እርምጃ እንዲወስድ አስፈላጊውን ግፊት ልናደርግበት ይገባል።
ስርአቱ በርግጥም “የኢትዮጵያ ከፍታ” የሚፈልግ ከሆነ አንዱ ተጨባጭ ማሳያ የሀገራችንን ታሪካዊና ህጋዊ መብት ማስከበር ነው።
እነ ጀነራል አበበ፣ ሰየ አብርሀ፤ ታምራት ላይኔ፤ ገብሩ አስራት፤ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ወዘተ ከመንግስት ስልጣን ከወጡ በኋላ መንግስታቸው ኤርትራን በተመለከተ የወሰደው አቋም እጅግ የሚያሳፍራቸው ታሪካዊ ስህተት እንደሆነ ደግመው ደጋግመው ሲጽፉና ሲናገሩ አዳምጠናል አንብበናል አይተናል።
እነርሱና ሌሎችም ሁሉ አሁን በሀገራችን ዘላቂ ጥቅም ላይ እየተተበተበ ያለውን ሴራ በግልጥ በመቃወምና በስርአቱም ላይ ተጽእኖ በማሳደር በእውነትም ለቃላቸው የቆሙ መሆናችውንና ለሀገራችን ህጋዊና ታሪካዊ መብትም መከበር እንደሚታገሉ ማስመስከሪያ ጊዜው አሁን ነው እላለሁ።
በተለያየ አጋጣሚ በሀገራችን ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ዛሬ ስልጣኑን ያገኛችሁ ሀገርን እንወዳለን የምትሉ ሁሉ፣ በትላንት ስህተት ላይ ጣት ከመጠቆም አልፋችሁ ከደረቅ ድርጅታዊ አይዲኦሎጂ ተላቃችሁ ለሀገርና ህዝብ ዘላቂ ጥቅም ያላችሁን አቋም ልታሳዩ የምትችሉበት ጊዜ ቢረፍድም አሁንም ሀገርንና ህዝብን ለመታደግ የምትችሉበት እድል በእጃችሁ ውስጥ ነው አላለሁ።
በፖለቲካ ተቃዋሚነት ለተሰለፍነው ሁሉም ይህ ከፊት ለፊታችን የተደቀነ ታሪካዊ ፈተና ነው።ለሀገራችን ታሪካዊና ህጋዊ መብት እንቆማለን ወይስ “በምድር ላይ ያለው እውነታ” በሚል ራስን መታለያ ተተብትበን የህወሀት/ሻአቢያን ውሳኔ ተቀብለን እንቀጥላለን? ጊዜው ምላሽን ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ ምሁራንና ሀገር ወዳዶችም እውቀታችሁንና የምርምር ችሎታችሁን አሁንም ለሀገራችን ታሪካዊና ህጋዊ መብቶች መከበር አበክራችሁ የማዋል አስፈላጊነትን አንደማትዘነጉት ሁሉ ከተለያየ አቅጣጫ የሚሰነዘረውንም አማላይ ጩኸት ልታጋልጡት በአለም አቀፍ መድረክም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ ልትናገሩ ፣ለሀገር ጥቅምም ልትከባበሩ ይገባል እላለሁ።
በመጨረሽ የሀገራችን የወደፊት እጣ በአርበኛ ልጆቿ እጅ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም የሀገሪቱ ዜጋ ለመብቱ መከበር ከሚያደርገው ትግል ጎን ኤርትራን በተመለከተም የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገራዊ ህጋዊና ታሪካዊ መብቱንና ጥቅሙን ጎን ለጎን ሊያሰኬደው እንደሚችል ማሳየት ይገባል እላለሁ። አንድ ሰው ባንድ ጊዜ መብላትም መራመድም እንደሚችል ሁሉ፣ ሙሉ ለሙሉ ለዴሚክራሲያዊና ሰብአዊ መብቱ መታገልና ለሀገሩ ህጋዊና ታሪካዊ መብት መታገል እንደሚችል ማሳየት ይገባል እላለሁ።
“ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” መሆኑ እንጂ እንደኔ እንደኔ ሀገራችን በሻቢያ የደረሰባትን በደልና በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1994 “ሬፈረንደም” የተሰራባትን ደባ በቅርብ የታዘብ ሰው ሌላ ቁስል ከመቀስቀሰ ይልቅ ቢያንስ አርፎ ቢቀመጥ የተሻለ ይሆን ነበር። አምባሳደር ኸርማን ኮኸንም የኢትዮጵያና ኤርትራን ጉዳይ በተመለከተ ራቅ ብሎ ከመመልከት ውጭ ሌላ ተግባር ውስጥ ሲገቡ በህዝባችን ኣእምሮ ውስጥ ትልቅ ቁስል እንደሚቀሰቅስ ቢገነዘቡት መልካም ይሆናል።
እስካሁን እንዳየሁት፤ የህዝባችንን የአእምሮ ቁስል የተረዱትና ምን ያክል ጥልቀት ያለው ጉዳት እንደደረሰበት በትክክል ያወቁት አልመሰለኝም። ቃለመጠይቆቻቸውን በተደጋጋሚ እንዳደመጥኩትና ጽሁፎቻቸውንም እንዳነበብኩት በኢትዮጵያውያን ላይ ለደረሰው መንፈሳዊ ቁስል፤ የስሚት መስበር ወዘተ የርህራሄ ስሜትን የሚጠቁም “ጉዳታችሁ ይሰማኛል” የሚል መልእክት ከቶውንም ላገኝባቸው አልቻልኩም።
ስለዚህም አሁንም ያንን ቁስል ግምት ውስጥ ባለማስገባት እንደፈለጉ “ይኸ ይሁን ያ ይሁን” ሲሉ ተደምጠዋል። ከዚህም አልፈው እንዲያውም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ተበዳይ ኢትዮጵያ አሁንም አጎንባሽ እንድትሆን ይጋብዛሉ። ይህ ሁሉ ስለራሱና ስለ ታሪኩ ጥልቅ ግንዛቢና ታላቅ ኩራት ለሚስማው ህዝባችን ታላቅ ስድብ ነው። ነገሩ የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል እንደሚባለው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነትም ላይ ዘመቻው ከሁሉም አቅጣጫ ሆኗል::
በኔ እይታ የኤርትራና ኢትዮጵያን ቀውስ ለመፍታት ሀገራችን ኢትዮጵያና ህዝቧ የተጫነባቸውን ኢፍትሀዊ ውሳኔና ውርደት እውቅና የማይሰጥ፤ ለዚህም ምላሽ ሊሰጥ ያልተዘጋጀና የማይችል ማንኛውም ሙከራ ችግሩን እጅግ ከማወሳሰብና ካሁኑ ትውልድ አልፎ ለቀጣይ ትውልዶች የቂም እና የበቀል ስሜት ከማውረስ ውጪ በረዝሙ ሲታይ የሚያመጣው ፋይዳ የለም።
የአምባሳደር ኸርማን ኮኸን ተደጋጋሚ ምክርም በዚሁ ማእቀፍ ውስጥ የሚሽከረከር ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ምክራቸው አስመራ ላይ የተቀመጠውን መንግስት ለጊዚውም ቢሆን ይጠቅመዋል፣ ለሌሎችም ይመች ይሆናል። ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ግን በስነ ልቦና በህዝቧ አንድነት በሀገራዊ ደህንነት በኢኮኖሚ ዋስትና ወዘተ እጅግ ይጎዳል። ኢትዮጵያን ያዋርዳል የጐረቤቶቿ ጥገኛም ያደርጋታል::
የኢትዮጵያውያንን ጥቅም ማስጠበቅ የኢትዮጵያውያን ፋንታ ነው። ለእኛ ጥቅም መቆም ያለብን እኛ ነን። የኢትዮጵያ ሀገራዊና ዘላቂ ጥቅም ከሁሉም ነገር በላይ እንደሆነ አንርሳ። የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ አሁንም አልረፈደም፤ ድምጻችንን እናሰማ፤ እንደቀደምት ወላጆቻችን ባለራእይ እንሁን።
አክሊሉ ወንድአፈረው (ethioandenet@bell.net)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Dibekulu says
This article’s writer reminds me of the creature that buries its head in the sand in order not to see the real danger around it. He is still living in the past and 26 years behind what the facts on the ground are! Eritrea is gone, its ports are its sovereign property and NO ONE can undo that! People like this article’s writer have only one dimensional sight, they only see what they prefer to see, very often ignoring the periphery. The Eritrean & Ethiopian people can cooperate, work together and support each other. They can be the strongest allies in Africa but all this can happen only when those who dream about reversing Eritrean sovereignty change their mind and accept the reality. Otherwise, Eritrea will be attracted farther and farther to geopolitical spheres of influence that may not be beneficial to Ethiopia. This of course, is detrimental to Ethiopia’s short term and in the long term, harmful to both peoples interests. I hope those Ethiopian brothers & sisters of good will who believe in cooperation and friendship based on mutual respect will prevail over those who have hegemonic intentions. Otherwise, we will be stuck in playing a lose-lose game for generations to come.
Tesfa says
ምናለ ኣስተሳሰባቸዉን ሰፋ ቢያደርጉት በሁለቱም በኩል ያሉት አንባገነ ኖች: በቃንስ ቢሉ በሁለቱም ወገን ያለዉ ህዝብ አልተመቸዉም : በሰላም በፍቅር ስንት እድሎች እያሉልን ስደት ብቻ ሆነ በጐሳ መቆራቆስ: በዛ ያለው ግትር : በዛ ያለዉ የሌቦች ሰብስብ:ህዝቡን እሾህ ሆኑበት: ኣምላኬ እረ ይብቃቹ በለን።