ድሬ ቲዩብ በመባል የሚታወቀው በአማርኛ “ትልቁ” የድህረ ገጽ እና ድህረ ምስል አውታር፣ ሰሞኑን አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሁለት ጥያቄ ጠይቆ ነበር።
1ኛው የኢትዮጵያ መሪ (ፕሬዝዳንት) ማን ናቸው? የሚል ሲሆን
2ኛው ደሞ የአሁኑ የአዲስ አበባ ከንቲባ ስማቸው ማን ይባላል? የሚሉ ናቸው ።
ሕዝቡም እንደ አቅሙ ትክክለኛውን መልስ ለማግኘት ጥሯል። ሙላቱ አስታጥቄ፣ እንዳለ አድምቄ፣ አሰፉ ደባልቄ፣ ዶቅዶቄ፣ ቦሎቄ፣ አረቄ እና ወዘተ። የጎዳና ተዳዳሪ ልጆች መለስ ነው አዲስ አበባን የቆረቆራት (ወይም ከንቲባዋ መለስ ነው) ሲሉ፣ የጥበቃ ሰራተኞች “ማን ነበር? ይገርማል!” በማለት አለማወቃቸውን አሳውቀዋል። ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ እና ኩማ ደመቅሳም ያሉም አሉ። ይህ እንግዲህ የአዲስ አበባ ከተማ ነው። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ። መረጃ በአማካኝ፣ ከማንኛውም የሀገሪቱ ክፍሎች (ወይም ክፍለሃተ ሀገሮች) “በወያኔኛ” “ክልሎች” በፍጥነት ለሕዝቡ ይደርሳል ተብሎ የሚገመትበት ቦታ።
ጠያቂው (ማለቴ የድሬ ቲዩብ ድህረኛ) በመጨረሻ የአማሪካ ሀገር ፕሬዝዳንት ማን ይባላሉ ብሎም ጠይቆ ነበር ። ይህንን ጥያቄ የሳተ (ወይም የተሳሳተ ተጠያቂ አላየንም)። እኛም ከዚህ ተነስተን የሚከተለውን እንላለን:-
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ወደ ሰሞኑ የሃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር አንድ ወደ ሗላ እንመለስና ያሉቱን እንቃኛለን።
እንዲህ ነበር ያሉት “አሁን ጥናቱ ከሰጠን ኢንፑት አንዱ እና ትልቁ የዚህን ችግር ዴብዝ በአግባቡ አመራሩ እንዲያይ፣ በውስጡ ድንጋጤ እንዲፈጠር፣ ለማድረግ የሚያስችል፣ ከመፈከር የዘለለ ” ከዚህ በፊት መልካም አስተዳደር ችግር አለ፣ እዛ ጋ ችግር አለ፣ መሬት ላይ ችግር አለ፣ ገቢዎች ላይ ችግር አለ፣ እእእ፣ ጨረታ ግዢ ላይ ችግር አለ፣ ከሚባለው አልፈን፣ ሪሊ ምንድነው ያለው የሚል፣ ሳምፕል ሊሆን ይችላል ‘ኢት ዳዝንት ማተር’፣ ሁሉን አካባቢ አጥነትህ አይደልም ችግር የምታውቀው፣ ሳይንሳዊ የሚያስብለውም ይሄ ነው፣ ሳይንሳዊ የሚያስብለውም ጥናቱ ሪፕረዘንታትቪ መሆኑን መራዳት ላይ ብቻ ነው”
እንግዲህ እርሶም እንዳሉት ፣ እኛም ትንሽ እንደሚገባን፣ ይህ ‘የኢትዮጵያ መሪ (ፕሬዝዳንት) ማን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ሪፕረዘንታቲቭ ነው። ሪፕረዘንታቲቭ የሚያስብለውም በአዲስ አበባ ከተማ፣ አማራው፣ ጉራጌው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ አፋሩ፣ ኩናማው፣ ሃዲያው፣ ከምባታው፣ ኩናማው፣ አደሬው፣ ኮንሶው እና ወዘተ ታጭቆ የሚኖርበት ከተማ ነውና፣ የሀገሪቷን ህዝቦች የፖለቲካዊ ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን፣ በስም እንኳ ከማያውቁት መንግስታቸው ጋ ያላቸውን መስተጋብር ያሳያል። ይህ ምርጫው (ይሄ መቶ ፐርሰንት ተመረጥን ) ወይም መቶ ፐርሰንት አሸነፍን የተባለውን ምርጫ ማለቴ ነው፣ ምን ያህል በአሽዋ ላይ አይተሰራ ቤት እንደሆነም ማሳያ ነው። ምክንያቱም እንደ ጋሽ ሃይለማርያም አባባል “ሁሉን አካባቢ አጥነትህ አይደልም ችግር የምታውቀው፣ ሳይንሳዊ የሚያስብለውም ይሄ ነው፣ ሳይንሳዊ የሚያስብለውም ጥናቱ ሪፕረዘንታቲቭ መሆኑን መራዳት ላይ ብቻ ነው” እኛም እድሜ ለድሬ ቱብ (አለቆቹ በዚህ ጉዳይ ምን ያህል ደስተኛ እንደሚሆኑ ባላውቅም)፣ ያስተላለፈው መልእክት ግን የህዝቡን ገሃዳዊ ፖለቲካዊ የኑሮ ሁኔታ የሚያስይ ሪፕረዘንታቲቭ ጥያቄ እና መልስ ነው፣ “ሳይንሳዊ የሚያስብለውም እሱ ነው!”
መራራው ብልግና ፣ መሪውን 100% የመረጠ ሕዝብ፣ መሪው ማን እንደሆነ አለማወቁ ነው፣ አሳፋሪው ታሪካዊ ውርደት “አባቱን ሳያውቅ ስለ እንጀራ አባቱ የሚያወራ ትውልድ ባለበት ሀገር፣ “ሕዝቡ ከመቼውም ግዜ በበለጠ ሁናቴ ለልማት እየተነቃነቀ ያለበት ጊዜ ላይ ነን” ብሎ ማለቱ ላይ ነው። እውነቱ ህዝቡ መሪውን አያውቅም። መሪውን የማያውቀው ደሞ መሪውን ስላልመረጠ ነው። እውነቱ ህዝቡ የአሁኑ የኢትዮጵያ መሪ ማን ነው ስትለው “ሙላቱ አስታጥቄ” ብሎ የመለሰው፣ ሙላቱ አስታጥቄ ከአንድ የሀገር መሪ የተሻለ ነገር የሰራ ሰው ስለሆነ በጭንቅላቱ ውስጥ የምስተጋበረው ስም በሥራ ደጋግሞ የሰማው ነው። የጎዳና ተዳዳሪዎች የአዲስ አበባ ከንቲባ ማን ነው ሲባሉ “መለስ ዜናዊ” ያሉት፣ ከሞቱ ባሻገር፣ በሚንከላውሱበት ጎዳና ላይ፣ “አባይን የደፈረ መሪ” የሚለውን ጸሓይ ያነተበውን የመለስን ፎቶ ሲያዩ፣ ምናልባት አዲስ አበባንም፣ ኢትዮጵያንም የደፈረ እና ያስደፈረ መሪ ሊሆን ይችል ይሆናል ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰው ይሆናል።
አዎ ጥናቱ (ሁለት ጥያቄ አለን) ሪፕረዘንታቲቭ ነው። የህዝቡን የፖለቲካ አቋም ያሳያል፣ የወያኔን መጻኢ እጣ ፈንታ ያሳያል፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ የገባችበትን ውርደት እና የትውልድ ክሽፈት ያሳያል። “ኢት ዳዝንት ማተር” አስር ሰውም ይጠየቅ አንድ መቶ ሰው፣ ግን የህዝቡን ቀለም ያንጸባረቀ ነውና።
ስለዚህ እኔም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ አለኝ
1ኛ ወያኔ ምርጫውን በስንት ፐርሰንት አሸነፍኩ ይላል?
2ኛ ለቀጣዩ አምስት ዓመት ምን እያደረጋችሁ ለመኖር አስባችሁ ይሆን?
ቸር እንሰንብት
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
በለው ! says
>> ይህ ጥያቄ በሌሎች ሀገሮችም ይነሳል መልሱ ተመሳሳይም መሆኑ ያስገርማል…ሕዝቡ ምንም የጎደለበት የለምና ይበላል፣ ይጠጣል፣ ሲከፋው አመፅ፣ አድማና ተቃውሞ፣ ማሰማት መብቱ እንደሆነ ያምናል…ዕለታዊ ኑሮው ቢቻል ሠርቶ ባይችል በመንግስት ተደጉሞ ሌሎች በመሠረቱት ተቋም ተደስቶ ይኖራል።
የእኛ ቤት ጥያቄው ሁለት ብቻ መሆኑ በጀን! መልሱ ሁሉ ትክክል ነው። ባይሆንስ?
ምርጫና አማራጭ የሌለው ሕዝብ፡ ነቅሎ የሚወጣው የጠላውን ተባብሮ ለመቅበር ነው።ውብ ሀገር ድንቅ ሕዝብ!
(፩) አቶ መለስ ይመሩ በነበረ ዘመን በቡደን (group leadership)በምርጥ ዘር (አብሮ አደግ የሠፈር ልጅ፣ በዘር ጋብቻ፣ በክልል ነዋሪና ዝምድና) ስለነበር በሕገ መንግስቱ አንድ ገፅ ተኩል የተሰጣቸው ሙሉ የማይበረዝ፣ የማይገሰስ፣ የማይሸራራፍ ሥልጣን ሁሉም አጆች አሳቸው ላይ ሲቀሰር እሳቸው እጃቸውን ወደ ገደል ቀስረው ለሕዝቡ ይታዩ ነበር። በእሳቸው ዘመን የነበሩ ባላሥልጣናት ዕውቅና ለማግኘታቸው ሁሉም በተራ ከጎናቸው እየተሰለፉ ፎቶ ተነስተዋል በጭራሽ አይረሱም ።
(፪)በኀይለማርያም ድንገተኛ መተካካት ሁሉ ነገር ተነነ “እሳቸውን መተካት ከባድ ነው ከፊትም፣ ከኋላም፣ ከጎንም፣ ሆናችሁ እርዱኝ አሉ።”አማራር (collective leadership) በኅብረት(በደቦ) ከፊትም ከኋላም ከጎንም ያሉ ሁሉ አለቃ ሆኑ በዱላ ቅብብል ወቃው!!በኀይለመለስ ከብርና ረዥም የሕይወት ዘመን ለእሳቸው የተመኙ መለስ ኖረ አልኖረ…ፋጡማ ኖረች አልኖረች… ደለለኝ ኖረ አልኖረ እኛ ባወጣነው ራዕይ አስቀጣይ ታመኝ አገልጋይ አግኝተናል።”ሲሉ ደነፉ…ሕዝቡ መሪ ሳይሆን ገዢና ናዛዡ በዛበት ፈዘዘ ደነዘዘ ማን ምን እንደሆነና ምን እንደሚሰራ ተጭበረበረና ተጥበረበረ!!
***ተረስተው ማንነታቸው ተረግጦ የነበረ ህወአት የፈጠራቸው (ሬድዋን ሁሴን..ሽፈራው ሽጉጤ …ሽመልስ ከማል..ሽፈራው ተክለማርያም ..ዓለምነው መኮንን) የመሳሰሉ ፅንፈኛና ጎጠኞች እየተገረፉም ከፊት በዩኒቨርስቲ የሚቀሰቅሱና አመፀኛን የሚፈለፍሉ ከኋላ መጡ ጭራሽም ከህወአት/ኢህአዴግ ዓላማና ፍላጎት ውጭ የራሳቸውን የግል ቁርሾና የዘር ግንድ ቆጠራ ዘለፋና ስድብን የዘር ማጥፋትን በግልፅ በነፃ ሚዲያ መሰበክ ተጀመረ።በህወአት ታጋይ ሥም እማሉ በኢህአዴግ ጥላ ሥር ያሉም አድናቂና አዋላቂዎችም የሙስና መር ኢኮኖሚ ሞኖፓሊን ተከልለው እየበሉና እያባሉ እራሱ ነፃ ያወጣና ኮትኩቶ ያሳዳጋቸውን ታጋይ ወላፈኑ ደርሰው ተሰብስቦ ለይስሙላም ተንጫጫ…አሁን ምንጠራው ይጀምራል ሕዝብ ይደብናል።
***እንግዲህ ትውልዱ አያት ቅድመአያቶቹን እንዳያነሳ ታሪክ እንዳያነብ አዲስ ተፅፎ እስኪሰጠው እንዲጀዝብና እንዲጃጃል ቡና ቤት በብዛት ተከፈተ፣የአውሮፓ እግር ኳስ ጨዋታ አድናቂ እንዲሆን ቢራ በብዛት ተመረተ፣ እንዲመክንና እንዲባክን እስታዲየም በብዛት ተሠራ፣ከገጠር ከአባት እናቱ ንብረትና ቀዬ እንዲለቅ በካድሬና በደላላ ተዘመተበት፣ ከተማ ገብቶ የባለግዜዎችን(ዘመነኞችን) ህንፃ እንዲሰራ ሲሚንቶና ደንጋይ ተሸካሚ፣ በኋላም ዘበኛ እንዲሆን ተገፋ የቤተሰቦቹ ንብርት ተዘረፈ፣ ተወረሰ፣ ተቸበቸበ።አብዛኛው ወጣት ገርድ፣ ዘበኛ፣ ሎተሪ አዟሪ፣ ሸቃይ፣ ጭራሽም ሴሰኛና ሱሰኛ ሆነ።ያለፈው ፳፭ ዓመት የጥፋት ራዕይ ሲሳካ ድርቅ፣ ርሃብ ፣ድኅነት፣ በሽታም በተለጠጠ መልኩ ቀጠለ።
____ ይህ ትውልድ ነዋሪ ሳይሆን አኗኗሪ ስለሆነ ካኒቴራ፣ ባርኔጣ፣ የአንገት ልብስና የቀን አበል እየሰጡ በ፲፩ ባንዲራ ፫፻፷ ቀን ስለሚያስጨፍሩት መገዛቱን እንጂ በመብቱ ተጠቅሞ በፍላጎትና በምርጫ ያስቀመጠው ባለሥልጣን ወይንም መንግስት ለመኖሩ እርግጠኛ አደለም። ስለዚህ ይፈራል! ይደናገረዋል! ይጨነቃል! ያፍራል!ይርበተበታል!ይሸማቀቃል!ግን ይባንንና ይስቃል። እሳቁ አለቁ”ያዢ ያጣች ሀገር” ጥያቄ አታብዙ ሠላም ለሁሉም