በሐዋሳ ለጊዜው የጉዳቱ መጠን ያልታወቀ የእሣት ቃጠሎ መድረሱን በአደጋው ያዘኑ ገለጹ፡፡ ከስፍራው እንደተሰማው ለሰኞ አጥቢያ የተነሳው ቃጠሎ ምናልባትም በከተማዋ ታሪክ ከፍተኛው ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ አደጋው ሲደርስ የእሣት አደጋ “አገልግሎት” በነዋሪዎች ላይ ቅሬታ አስነስቷል፡፡
ለሰኞ አጥቢያ ሌሊት ላይ ነፍሳት ባረፉበት ወቅት የደረሰው የእሣት አደጋ መነሻው በትክክል ባይታወቅም ማምለጥ የሚቻልበት ባለመሆኑ አሟሟቱ የከፋ እንዳደረገው ለማወቅ ተችሏል፡፡ የተለያዩ ወገኖች በምስል ይፋ ያደረጉት ቃጠሎ እንደሚመለክተው የእሣቱ መጠን በቀላሉ የሚቆጣጠሩትና አደጋውን የሚቀንሱበት እንዳልነበረ ያስረዳል፡፡
በሐዋሳ ታሪክ ከፍተኛ ነው የተባለው ይህ ቃጠሎ በህይወት ላይ ያደረሰው አደጋ በትክክለኛው ቁጥሩ ባይገለጽም ከሥፍራው የደረሰን አጭር መልዕክት እንደሚያስረዳው ከሰባት የማያንሱ መሞታቸውን ከ23 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቃጠሎ ደርሶባቸው የተጎዱ እንዳሉ፤ ሌሊት የተነሳ ቃጠሎ በመሆኑ መረጃ ለመሰብሰብ ቢያስቸግርም ደረሰ የተባለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ቀውስ ከዚህ የበለጠና ምናልባትም ኅሊናን የሚጎዳ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡
በዚሁ በደረሰን አጭር መልዕክት እሣቱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የከተማዋ የእሣት አደጋ ብርጌድ “እውን ሐዋሳ የእሣት አደጋ ብርጌድ አላት?” የሚያሰኝ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ለመባሉ ምክንያቱ በዝርዝር አልተገለጸም፡፡ ምናልባትም አደጋው ሌሊት ላይ መከሰቱ በሰው ህይወት ላይ የተመዘገበውን አኻዝ ከሚገመተው በላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን በደረሰው የህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት የተሰማውን ልባዊ ሐዘን በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢህአዴግ በዛሬው (ሰኞ) ዕለት የሚከተለውን ዜና አሰምቶዋል:: የሞቱት ቁጥር አከራካሪ ቢሆንም በሚቀጥሉት ቀናት ሊጨምር እንደሚችል ከሁሉም አቅጣጫ እየተሰማ ነው፡፡
በሃዋሳ ከተማ ቅዳሜ ምሽት 1 ስዓት ላይ በደረሰ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል።
አዲሱ ገበያ ተበሎ በሚጠራው አካባቢ ላይ በደረሰው አደጋ 1 አመት ከስድስት ወር የሚሆን ህፃን ህይወቱ አልፏል።
አንዲት እናት ደግሞ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
በመምሪያው የወንጀልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር በላይ የኔው፥ የእሳት አደጋውን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የተቻለው ከ40 ደቂቃ በኋላ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡና የከተማዋ አስተዳደር ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ እሳቱን መቆጣጠር መቻሉንም ነው ኢንስፔክተር በላይ የገለጹት።
በአደጋው የደረሰው የንብረት ውድመትና መንስኤውን የማጣራት ስራም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ቤቶቹ የተሰሩባቸው ቁሳቁሶችና በወቅቱ የነበረው ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እሳቱን በቀላሉና በፍጥነት ለመቆጣጠር አዳጋች አድርጎት ነበር ነው ያሉት ዋና ኢንስፔክተሩ።
በአደጋው የተጎዱ ከ500 በላይ ሰዎችም ጊዜያዊ መጠለያ ተሰርቶላቸዋል ብለዋል።
በቀጣይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማቋቋም ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን የተለያዩ ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል። (በብርሃኑ በጋሻው ኤፍ.ቢ.ሲ)
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Leave a Reply