
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት በላይ በሆኑ ዓመታት ከባድ ጫናዎችን ተሸክማ ቆይታለች። ይልቁንም የሰሜኑ ጦርነት በውስጥም በውጭም ገፊና ሳቢ ምክንያቶችን ፈጥሮ ሲያናውጣት ቆይቷል። ይኸው ጦርነት ኹለት ዓመት ሊደፍን የዋዜማው እለት የተደረሰው የሰላም ስምምነት በጉዳዩ ላይ የብዙዎች ተስፋ እንዲያንሰራራ አድርጓል። ኢትዮጵያን ችግሮቿ ሁሉ የተቀረፉ ያህል ብዙዎች ተሰምቷቸዋል።
ሆኖም አሁንም ኢትዮጵያ የጎን ውጋት የሆኗት ችግሮች አሉ። የወሰንና አስተዳደር ጥያቄዎች፣ የታጣቂ ኃይሎች እንቅስቃሴ፣ የምጣኔ ሀብት መዳከም፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ጥቃቶች አሁንም ይስተዋላሉ። እናም ኢትዮጵያ ችግሮቿን ቁልቁል ደርድራ አንድ በአንድ በማስተካከል፣ እንደ ሰሜኑ ጦርነት ሁሉ በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ እንዲሁም በሌሎች ክልሎችም ሌሎቹንም ችግሮች እንድትቀርፍ ይጠበቅባታል። በሰብአዊ መብት፣ ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ምጣኔ ሀብት፣ ማኅበራዊና መሰል ዘርፎች ዙሪያ የሚሠሩ ባለሞያዎችም፣ መንግሥት ቀጣይ ትኩረቱን በቀሪ የኢትዮጵያ የጎን ውጋቶች ላይ እንዲያደርግ ሲያሳስቡ ይደመጣል። ይህንን ጉዳይ መነሻ በማድረግ የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ተከታዩን ሐተታ ዘ ማለዳ አሰናድቷል።
ኢትዮጵያ እንደ አገር በየዘመናቱ የሚገጥሟት ፈተናዎች፣ በየጊዜው ገጽታቸውን እየቀያየሩና እየተፈራረቁ ማደግ ያለባትን ያክል እንዳታድግ በግራ በቀኝ ወጥረው እንደያዟት የየዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። የአንድን አገር እድገት ከሚገቱ ችግሮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የጸጥታ ችግር በኢትዮጵያ ምድር እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የዘለቀ ሆኗል።
የዴሞክራሲ ባህል እምብዛም አልዳበረባትም ተብላ የምትወቀሰው ኢትዮጵያ በዜጎቿ ጤነኛ ያልሆነ የፖለቲካ ሽኩቻ፣ ዓለም ወደ ሥልጡን የፖለቲካ ባህል ተሸጋግሯል በሚባልበት በዚህ ወቅት በዚሁ በፖለቲካ ሽኩቻ በየአቅጣጫው ከግጭት እስከ ጦርነት አስከፊ ችግሮችን እያሳለፈች ትገኛለች። በተለይ ከ2008 ወዲህ በየአቅጣጫው እየተባባሱ የቀጠሉ የጸጥታ ችግሮች አንዳንዶቹ እየተባባሱ ቀጥለው ወደ ጦርነት ያደጉበት ሁኔታ ተከስቷል።
ከእነዚህም መካከል ከኹለት ዓመት በፊት ከፖለቲካ ሽኩቻ ወደ ጦርነት ያደገው የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት አንዱ ሲሆን፣ ከብዙ ጥረት በኋላ ጦርነቱ እንዲቆም ስምምነት ላይ ተደርሷል። የሰሜኑ ጦርነት በፌዴራል መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል በተፈጠረው የፖለቲካ ልዩነት የተቀሰቀሰ ቢሆንም፣ ለኹለት ዓመት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ኢትዮጵያ እንደ አገር ቀላል የማይባል ዘርፈ ብዙ ኪሳራ አስተናግዳለች።
ከሰሜኑ ጦርነት ውጪ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች አሁንም እልባት ሳያገኙ እንደቀጠሉ ናቸው። በተለይ በዋናነት በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው በመንግሥት “ሸኔ” ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል፣ በክልሉ በንጹሐን ዜጎች ላይ ከሚያደርሰው መጠነ ሰፊ ጥቃት በተጨማሪ፣ ወደ ሌሎች ክልሎች የመስፋፋት አቅም የፈጠረ ኃይል ሆኗል። ታጣቂ ኃይሉ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል እና ጋምቤላ ክልል ተስፋፍቶ ከዚህ በፊት ጥቃት ማድረሱ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያን አሁን ላይ በየአቅጣጫው የገጠማት የጸጥታ ችግር እልባት ሳያገኝ ቀናት ወራትን እየወለዱ፣ ወራት ዓመታትን እየወለዱ አሁንም ለዜጎች ሞትና እንግልት ምክንያት ሆነው ቀጥለዋል። በተለይ በኦሮሚያ ክልል በስፋት የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ኃይል በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ንጹሐን ዜጎችን መግደሉና ንብረት ማውደሙ እንደቀጠለ ነው።
ኦሮምያ ክልል በንጹሐን ዜጎች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት ጎን ለጎን በመንግሥት ኃይሎችና በሽብርተኛነት በተፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያዎች ይካሄዳሉ። ይሁን እንጂ፣ ታጣቂ ቡድኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ አካባቢዎችን እየተቆጣጠረ ጥቃቶችን እየፈጸመ ነው። ከሰሞኑ እንኳን የምዕራብ ወለጋ ዞን መቀመጫ የሆነችውን ነቀምቴ ከተማን ተቆጣጥሮ በንጹሐን ዜጎች ላይ ካደረሰው ጥቃት በተጨማሪ ንብረት መዝረፉና ታራሚዎች ከእስር ቤት እንዲወጡ ማድረጉ ተሰምቷል።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የታጣቂ ኃይሉ ጥቃት የተባባሰው፣ ከኹለት ዓመት በኋላ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ለማስቆም የሰላም ስምምነት ላይ በተደረሰበት ወቅት ነው። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ በሆነ መንዲ አካባቢ ሰሞኑን በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ወጊያ እንደነበር ሲዘገብ ነበር።
ታጣቂ ኃይሉ ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ጉምዝ አጎራባች አካባቢዎች መንገድ መዝጋቱን አዲስ ማለዳ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ከአዲስ አበባ ወደ ቤኒሻንጉል ክልል ዋና ከተማ አሶሳ የሚወስደው መንገድ ከኹለት ሳምንት በላይ መዘጋቱ ተሰምቷል። በዚህም አሽከርካሪዎች ከግምቢ ከተማ ማለፍ ባለመቻላቸው በያሉበት ቆመው ከርመዋል።
የግጭት አዙሪት
ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ግጭቶች ባያጧትም ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተከሰቱ ግጭቶች የተካረሩና ያስከተሉት ኪሳራ ቀላል የሚባል አይደለም። የችግሩን አሳሳቢነት የሚያጎላው ደግሞ አንዳንዶቹ ግጭቶቹ ማንነትን መሠረት ያደረጉ መሆናቸው ነው። በተለያዩ አካባቢዎች የማንነት መልክ የያዙ ግጭቶች አስከፊነትን እንዲጎላ የሚያደርገው በአንድ ወቅት ካጋጠመው ግጭት የዘለለ ተጨማሪ የግጭት አዙሪት ውስጥ የሚከቱ ችግሮችን ማስከተሉ መሆኑን የፖለቲካ ባለሙያዎች ሲገልጹ ይደመጣሉ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሰላለፍ በየጊዜው ግጭት የማያጣው ቢሆንም፣ በተለይ ከ2008 ወዲህ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለተከታታይ ዓመታት ያለ ማቋረጥ እስካሁን የቀጠለ ነው። አንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ የጸጥታ ችግሮች የተስተካከሉ ቢሆንም፣ በተለይ ኦሮሚያ ክልል አሁንም ተባብሶ በቀጠለው ግጭት በየቀኑ ንጹሐን ዜጎች የሚገደሉበትና የሚታገቱበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ኢትዮጵያ፣ ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ በገቡ የታጠቁ ኃይሎችና አሸባሪዎች በእጅጉ እየተፈተነች መሆኑን የሚያመላክቱ የጸጥታ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ቀጥለዋል። ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ የትጥቅ ትግልን ምርጫቸው ያደረጉ የታጠቁ ኃይሎችም ተበራክተዋል። እነዚህ ኃይሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን ሰላሟን እንድታጣና ዜጎቿ በጦርነትና በታጣቂዎች ጥቃት በግፍ የሚገደሉበትና የሚፈናቀሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ራሱን፣ ‹የለውጥ መንግሥት› ብሎ ከሚጠራው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ አካላት፣ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸውን ጨምሮ በየአካባቢው የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋል። በዚህም በየአካባቢው የሰላማዊ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዶ ንጹሐን ዜጎች በጅምላ የሚገደሉበት ሁኔታ በኢትዮጵያ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።
ንጹሐን ዜጎች በየአካባቢው በታጠቁ ኃይሎች ሲገደሉ፣ የታጠቁ ኃይሎች የሚንቀሳቀሱበትን አካባቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያሰፉ፣ በመንግሥት ተቋማትና ጸጥታ ኃይሎች ላይ እርምጃ ሲወስዱ፣ ሰዎችን ሲያግቱና እንዳሻቸው ሲዘርፉና ግብር ሲሰበስቡ ከድርጊታቸው የሚያስቆማቸው አካል በመጥፋቱ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ጨምሮ “መንግሥት የታጠቁ ኃይሎችን ጥቃት ማስቆም አልቻለም” የሚል ቅሬታ በመንግሥት ላይ በተደጋጋሚ ይቀርባል።
ከሥራቸው ጋር በተገናኘ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ በአንድ ዓለም ዐቀፍ ተቋም ውስጥ የሚሠሩ ኢትዮጵያዊ የሰብዓዊ መብት ባለሙያ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ መንግሥት የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ከማስከበር አንጻር ሦስት ግዴታዎች እንዳሉበት ይገልጻሉ። እነሱም ሰብዓዊ መብቶችን የማክበር፣ የማስከበር እና የማሟላት ግዴታዎች ናቸው። ይሁን እንጂ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ዐቀፍ ሰብዓዊ መብት ሕግ የተጣለበትን ግዴታዎች እየተወጣ አለመሆኑን የሚያሳዩ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዜጎች ላይ እየተፈጸሙ ነው ይላሉ።
ባለፉት አራት ዓመታት ታጣቂ ኃይሎች ከፍተኛ ችግር ከፈጠሩባቸው አካባቢዎች ኦሮሚያ ክልልና ቤኒሻንጉል ጉምዝ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ በሌሎች አካባቢዎችም አልፎ አልፎም ቢሆን የጸጥታ ችግር ሲፈጥሩ ይስተዋላል። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች አንዳንዶቹ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ፣ መቀመጫቸውን ኤርትራ አድርገው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥርዓትን ለመጣል የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።
በወቅቱ በኤርትራ በርሃ መሽገው የትጥቅ ፖለቲካ ትግል ላይ የነበሩ እንደ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ (ጋሕነን)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር (አጉጉም)፣ የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ ግንቦት ሰባትና ሌሎችም ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የሚታወስ ነው።
በ2010 ወደ ሥልጣን የመጡትን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መቀመጫቸውን በጎረቤት አገራት አድርገው በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች በመንግሥታዊ ለውጡ ተስፋ አድርገው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸውን ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት ወቅት ገልጸው ነበር።
ለረዥም ዓመታት በጎረቤት አገራት በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የፖለቲካ ስምምነት ባለመፈጠሩ ወደ ትጥቅ ትግል መመለሳቸው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንድታስተናግድ ምክንያት መሆኑን የሰብዓዊ መብት ባለሙያው ያነሳሉ። በዚህም ኢትዮጵያ እንደ አገር ከደረሰባት ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በተጨማሪ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የውጭ ጫና እንድታስተናግድ ምክንያት ሆኗል ይላሉ ባለሙያው።
የሕይወት ነገር
የሰብዓዊ መብቶች መከበር የአገርም ይሁን የዜጎች መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ከሰብዓዊ መብቶች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና የኹሉም ሰብዓዊ መብቶች መከበር መሠረት የሆነው በሕይወት የመኖር መብት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች እየተጣሰ ነው። በሕይወት የመኖር መብት ጥሰት እንዳይፈጸም መንግሥት ቀዳሚ ኃላፊነት በሕግ የተጣለበት ቢሆንም፣ በየጊዜው በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ግድያዎችን መንግሥት ማስቀረት አለመቻሉ በስፋት ይነሳል።
ለዚህም እንደ ማሳያ የሚጠቀሰው ዜጎች ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል ቀድመው በሚያሳውቁበት ሁኔታ ሳይቀር፣ በወቅቱ የደኅንነት ከለላ ባለማግኘታቸው የጥቃት ሰለባ መሆናቸው አንዱ ነው። መንግሥት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት ማስጠበቅ አልቻለም የሚለው ትችት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጭምር ሲቀርብ ነበር።’በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች በሚያደርሱት ጥቃት በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ግድያ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች ያመላክታሉ።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኦሰመኮ) ከሰኔ 2013 እስከ ሰኔ 2014 ባለው አንድ ዓመት ውስጥ በኢትዮጵያ ስላለው የሰብዓዊ ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት፣ በሕይወት የመኖር መብት ባለፈው 2014 በሕይወት የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ እንደወደቀ ቀጥሏል ብሏል።
በዓመቱ በመንግሥት የጸጥታ አካላትና ከመንግሥት ውጭ በሆኑ የታጠቁ ኃይሎችና ቡድኖች በርካታ ጥሰቶች መፈጸማቸው በዓመታዊ ሪፖርቱ የገለጸው ኢሰመኮ፣ በተለይም በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ከሐምሌ ወር 2013 ጀምሮ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መስፋፋቱን ተከትሎ፤ የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው፣ የመለየት መርሕን ባለመከተላቸው እና ያልተመጣጠነ ጥቃት በመፈጸማቸው በአፋር እና በአማራ ክልሎች ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ኃይሎችና በተለይም በትግራይ ኃይሎች ሆነ ተብሎ በተወሰዱ እርምጃዎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች ከፍርድ ውጭ ተገድለዋል። እንደ ኢሰመኮ ሪፖርት ግድያው ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ አረጋውያንን እና አካል ጉዳተኞችንም (በተለይም የአእምሮ ሕሙማንን ወይም የማኅበረ ሥነ-ልቦና ጉዳት ያለባቸውን ሰዎች) ይጨምራል።
በኦሮሚያ ክልል በተለይ በወለጋ ዞኖች ከነሐሴ ወር 2013 ጀምሮ እስከ ሰኔ 30/2014 ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል በተደጋጋሚ በፈጸመው ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ ሕፃናትና ሴቶችን ጨምሮ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ሪፖርት ያመላክታል። “በተለይ በሰኔ ወር 2014 ታጣቂ ኃይሉ በምዕራብ ወለጋ ግምቢ ቶሌ መንደር እና ቄለም ወለጋ ዞን ባደረሰው ጥቃት በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው የአማራ ብሔር የገጠር ከተማ ነዋሪዎች ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ በግፍና በጭካኔ ተጨፍጭፈዋል” ሲል ኢሰመኮ በሪፖርቱ አመላክቷል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል፣ በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ ከአሪ ብሔረሰብ የመዋቅር ጥያቄ ጋር በተገናኘ፣ በኮንሶ ዞን በልዩ ወረዳ ጥያቄ፣ በኮንሶ ዞንና በአሌ ልዩ ወረዳ መካካል ባለው በእርሻ መሬት ይገባኛል ጥያቄ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ በራስ አስተዳደር ጥያቄ፣ በደራሼ ልዩ ወረዳ ጊዶሌ ከተማ እና በአካባቢው በጋርዱላ ዞን መዋቅር ጥያቄ እና በጉራጌ ዞን በመስቃን እና በማረቆ ወረዳዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ጨምሮ በሌሎችም የክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሲነሱ የነበሩ ከአስተዳደራዊ መዋቅር እና ከድንበር ጋር የተያያዙ ግጭቶች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተወሰደ እርምጃ ቁጥራቸው ገና በትክክል ያልታወቀ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ እና የመንግሥት አስተዳደር አባላት መገደላቸውን የኢሰመኮ ሪፖርት ያመላክታል።
ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት ከሚደርሱት አቤቱታዎች መካከል፣ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት አቤቱታዎች በሕይወት ከመኖር መብት እና ከአካል ደኅንነት መብት ቀዳሚነት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቁሟል። እንዲሁም ከኢ-ሰብአዊ ወይም ጭካኔ ከተሞላበት አያያዝ/ቅጣት የመጠበቅ መብት፣ ከእስረኞች አያያዝ መብቶች፣ ከሕገ ወጥ እስር፣ ከዋስትና መብት እና ከፍትሕ የማግኘት መብት፣ ያለአግባብ መቀማት እና የተለያዩ የንብረት መብቶችን የሚመለከቱ አቤቱታዎች፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶችን፣ ሰብአዊ እርዳታ የማግኘት መብትን፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመሥራት መብትን፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብትን፣ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የእኩልነት መብትን የሚመለከቱ አቤቱታዎች እንደቀረቡለት ጠቁሟል።
ምን ይሻላል?
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በየአቅጣጫው ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን እያስተናገደች ትገኛለች። በተለይ ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና እንግልት ምክንያት የሆኑ አስተዳደር ጥያቄ ተከትሎ የሚከሰቱ ግጭቶች እና የታጣቂ ኃይሎች መበራከትና የሚያደርሱት ጥቃት እልባት ካላገኙ፣ ግጭቶች ያስከተሏቸውን ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ማቃለል እንደማይቻል የየዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ ይመክራሉ።
የሰሜኑን ጦርነት ለማቆም የተደረሰው ስምምነት እውን መሆን ትልቅ ችግር የሚያቃልል ቢሆንም፣ ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር ያሉ ችግሮች እልባት ካላገኙ ሌላ የጎን ውጋት መሆናቸው እንደማይቀር ብዙዎች ከወዲሁ እየገለጹ ነው።
ኢትዮጵያ በጦርነት ያስተናገደችውን ዘርፈ ብዙ ኪሳራ መልሶ ለመገንባት ከባድ የቤት ሥራ መሆኑን እየተገለጸ ነው። የሰሜኑን ጦርነት ለማቆም የተፈረመው “የግጭት ማቆም ስምምነት” በሚገባ ተግባራዊ ከሆነ እና ጦርነት ካላገረሸ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የትምህርትና የጤና ተቋማትን ጨምሮ በጦርነቱ የወደመውን ለመመለስ 20 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ተነግሯል።
የሰሜኑ ጦርነት በሰላም እንዲፈታ ከተደረሰው ሰላም ስምምነት በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ችግሮች እልባት ማግኘታቸው ለኢትዮጵያ ሰላም ወሳኝ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ጠቁመዋል። ሰብሳቢው እንደሚሉት፣ በተለያዩ አካባቢዎች በወሰንና አስተዳደር እንዲሁም በፖለቲካ ልዩነት ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ የታጠቁ ኃይሎች በኩል ያሉ ችግሮች የሰላም ስምምነቱን ከማስፈጸም ጎን ለጎን እልባት ማግኘት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የወሰንና አስተዳደር ጥያቄዎችም ይሁኑ ለዜጎች ሞት ምክንያት የሆኑ የታጠቁ ኃይሎች ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እልባት ማግኘት እንዳለባቸውም መብራቱ ይመክራሉ። ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን የሚያነሱት ሰብሳቢው፣ በአንድ በኩል ያሉ ችግሮች ተፈትተው በሌላ በኩል ያሉት ካልተፈቱ አሁንም የኢትዮጵያ ችግር መቀጠሉ እንደማይቀር ይገልጻሉ። በመሆኑም፣ በተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል ላይ ከሚገኙ አካላት ጋር መንግሥት ያለውን ልዩነት በውይይት መፍታትና ግጭቶችን ማስቀረት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የተለያዩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች የሰሜኑን ጦርነት በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሱን አስመልክቶ ባወጡት መግለጫ፣ ለሰላም ስምምነቱ ድጋፋቸውን አሳይተዋል። የኢትዮጵያ ሰላም ሙሉ እንዲሆን፣ ከሰሜኑ ጦርነት ውጪ ያሉ የጸጥታ ችግሮች በሰላማዊ ውይይት እልባት ማግኘት እንዳለባቸው ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል በጥቅምት 23/2015 የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያ ችግሮችን ፖለቲካዊ እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ የሚያስችል የሚበረታታ እና አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ፣ የሰሜኑ ጦርነት መቆሙ ብቻ የኢትዮጵያን ሙሉ ችግር ስለማይፈታ በኦሮሚያ ክልል ያለውን ጨምሮ የታጠቁ ኃይሎች እና መንግሥት የገቡበትን ግጭት ለማስቆም ሰላማዊ ውይይት ምርጫ እንዲሆን መክሯል።
በትግራይ የተፈጠረው ግጭት እልባት ማግኘቱ ብቻ በመላው ኢትዮጵያ የሚፈለገውን ሰላምና መረጋጋት ሊያመጣ እንደማይችል ጽኑ እምነቴ ነው ያለው ኦፌኮ፣ በኦሮሚያም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች በተመሳሳይ ሁኔታ በሰላማዊ መንገድ ካልተፈቱ በኢትዮጵያ የምንመኘውን ሰላምና ደኅንነት ማስፈን አይቻልም ብሏል።
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች በፖለቲካዊ መንገድ ለመፍታት አሁን እያካሄደ ያለውን ወታደራዊ እርምጃ እንዲያቆም እና ወደ ትግራይ የዘረጋውን ሰላማዊ እጁን በተመሳሳይ ወደ ኦሮሚያም እንዲዘረጋ እናሳስባለን። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ መላ ኢትዮጵያውያን እና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በአጠቃላይ በኦሮሚያ ያለው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ እንዲቆምና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ አስፈላጊውን ሁሉ ጫና እና ድጋፍ እንዲያደርጉ ኦፌኮ ጥሪውን በድጋሜ ያቀርባል›› ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) በበኩሉ፣ የሰላም ስምምነቱን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር በሌሎች አካባቢዎች ካሉ የታጠቁ ኃይሎች ጋር ያለውን ችግር ለመፍታት መንግሥት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልግ ጠይቋል።
ኢትዮጵያ የገጠሟት የጸጥታ ችግሮች በዜጎች ላይ ከሚያደርሱት ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በተጨማሪ፣ በአገር ላይ የሚያደርሱት ውስጣዊና ውጫዊ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም። እነዚህ ዘርፈ ብዙ ጫናዎችን ለማቃለል መንግሥት ቅድሚያ የዜጎችን ደኅንነት ማረገጋጥ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚጠበቅበት የሚገልጹት የሰብዓዊ መብት ባለሙያው፣ ግጭቶችን በሂደት በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት ጥረት ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያስከትሉት ችግርና ጫና ቀላል አለመሆኑን የሚያነሱት ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በጊዜያዊነት በዜጎች ሕይወት ላይ ከሚያደርሱት ችግር በተጨማሪ ውስብሰብ ችግሮችን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ መገንዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል። (አዲስ ማለዳ፣ ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
ፁፉን አነብብኩት የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ ነዉ ምን መደረግ አለበት ትላላችህ
ከአባቴም አይደለ ወይንም ከእናቴ እድሌ ሆነና አጥረ ቁመቴ ይለናል ፍሬው ሃይሉ የሃገራችን ችግር ውስብስብ ነው። ይህ ደግሞ የምድሪቱ እድል ፈንታ ወይም በምድሪቱ ላይ ሃጢአት ሰለበዛ አይደለም። ለነገሩ በደል ሰማየ ሰማያትን አልፏል። ግን ሌሎች ሃገሮች በበደል ባህር ውስጥ እየዋኙ ሃገር ሆነው ይኖሩ የለ። ስለዚህ የኢትዮጵያ በደሏ በዝቶ ነው ለምትሉ እረፉና ራሳችሁን እዪ ነው የምለው። እንዲህ አይነቱ እይታ ግን እራስን ካለማየትና በሌላው ላይ ለማሳበብ የሚመከር የደካሞች አስተሳሰብ ነው። የችግሩ ምንጭ እኛው ነን። የሃገሪቱ ህገ መንግስት አይዞአችሁ ተገዳደሉ፤ ለዘርና ለቋንቋችሁ ቁሙ፤ ክልላችሁን አጽኑ እስከ መገንጠል ድረስ ተፋለሙ እያለ የኢትዪጵያ አንድነት እያሉ የቃላት ጫወታ መጫወቱ ፉርሽ ነው። በሃገሪቱ በተለያዪ ክፍሎች ሰዎች በገጀራ ሲገደሉ፤ ቤታቸው ሲቃጠል፤ ድረሱልን የሚለውን ጥሪ እየሰሙ ቆመው ከበላይ አካል ትዕዛዝ አልተሰጠንም በማለት ሰው ሆድ ሲቀድድ፤ በእሳት ሲቃጠል ለእርዳታ እጅ ያልዘረጉ የመንግስት ታጣቂዎች ስንት ናቸው? ምድሪቱ ትቁጠራቸው።
የሃገሪቱ የጎን ውጋቶችን አሁን ባለው የፓለቲካ እይታና የአፓርታይድ ህገመንግስት ምንም አይነት ዋግምት ቢጠቀሙ ሰቅዞ አላራምድ ያላትን ህመም ማዳን አይቻልም። በምድሪቱ ላይ ሁሉን ነክ የሆነ አትራፊ እሳቤ ለማስገኘት የሰውን አስተሳሰብ መለወጥ አስፈላጊ ነው። ያኔ ህዝብና መንግስት አብረው እየሰሩ በመራመድ ሃገራዊ ፍቅርና ቁርኝትን መፍጠር ይቻላል። አፈር ገፊዎችና የቀን ሰራተኞችን ገድሎ ጃሎ የሚል አሜኬላ ትውልድ በሚራወጥባት በሃበሻ ምድር ሰው በሰውነቱ እስካልተለካ ድረስ ጭራሽ የምድሪቱ መከራ በዚህም በዚያም እሳት እየጫረና እያስጫረ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ሲጀመር በምድር ላይ ፍትህ ርትዕ የሚባል ነገር የለም። ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ የመርዝ ጋዝ ተጠቅማ ስትጨፈጭፍ የያኔው ሊግ ኦፍ ኔሽን በዝምታ ነበር ያየው። የዛሬው ተመድ የአሜሪካ ተላላኪና ጉዳይ አስፈጻሚ ነው። ዛሬ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ሰራዊቱን በተኙበት ያረድትንና ተጽፎና ተነግሮ የማያልቅ ጭካኔ በአፋርና በአማራ ህዝብ ላይ ከፈጸሙትና በመፈጸም ላይ ከሚገኙት አውሬዎች ጋር ተሰልፈው ኡኡታ የሚያሰሙት ምዕራባዊያን ከእውነት ጋር ከተላለፉ ቆይቷል። በየትኛውም የዓለም ክፍል አሜሪካ የራሷን ወታደራዊ አውሮፕላን ተጠቅማ አፈንጋጭ ሃይሎችን ያጓጓዘችበት ይፋዊ ሰነድ የለም። የአሜሪካ የውጭ ፓሊሲና እውነት በታሪክ ተገናኝተው አያውቅም። በዚህ ዙሪያ ላይ ከተጻፉ መጽሃፍቶች መካከል John Perkins – The Secret History of the American Empire የሚለውን ብቻ በማንበብ ምን ያህል በዓለም ፓለቲካ እሳት እየጫሩ የሃብት ገፈፋ እንደሚያደርጉ ያሳያል። አንድ ኢትዮጵያዊ ጸሃፊ እንዳሉት አሜሪካኖች ከወያኔ ጋር የሙጥኝ ያሉበትን ጉዳይ ሳንረዳ ሰላም አይኖርም። እስማማለሁ!
አሁን እንሆ ከወደ አዲስ አበባ የሚነገረንና በሰሜን ያለው ሁኔታ ጭራሽ አይገናኙም። ወያኔና ጦሩ አብረው ምግብ በሉ፤ ሲጋራ አጨሱ፤ ሙታናቸውን በጋራ ቀበሩ የሚለው ሁሉ የብልጭታ ወሬ ነው። ከቦታው ከወያኔ ጋር ተፋጠው ያሉ የሚነግሩን ሌላ ነው። ሌላው እጅግ የሚያስገርመኝ የኢትዮጵያ ሰራዊት እህል አጨደ ሰበሰበ ወዘተ እያሉ ሲናገሩ አለማፈራቸው። የኢትዮጵያ ሰራዊት የወያኔ የቀን ሰራተኛ ነው ወይስ ሰላምና ጸጥታን የሚያስጠብቅ የታጠቀ ሃይል? 20 ዓመት ሙሉ ያደረገው ተረስቶ አይደል እንዴ በዘር ተለይቶ የተጨፈጨፈው። የብልጽግናው መንግስት እነዚህ ሰዎች ጊዜ እየገዙና የተበተነና የደከመ ሰራዊታቸውን እያሰባሰቡ እንጂ ጭራሽ ለሰላም ጊዜና ሥፍራ የሚሰጡ ስብስቦች አይደሉም። እየገደሉ መሞት ነው መሪ ቃላቸው። ለውጊያ እንዲያመቻቸው ነው የኤርትራ፤ የአማራ፤ የአፋር ጦር ይውጣ የሚሉት ከአሜሪካ ጋር ተናበው።
ፓለቲካ ቄራ ውስጥ እንደገቡ ውሾች ሰውን የሚያናክስና የዛሬው ጉራ ነገ በሽንፈትና በመበተን የሚተካ ቋሚነት የሌላው የእብዶች ፍልስፍና ነው። ላስረዳ። በነጮቹ መስከረም 30 2022 ራሺያ ከዪክሬን ላይ Donetsk, Kherson, Luhansk and Zaporizhzhia oblasts ሃገሬ ነው ብላ በማወጅ በሞስኮ አደባባይ ሰው አስጨፍራ በያዘቻቸው ግዛቶች ላይ ምርጫ ሆነ በማለት የራሽያ ምድር ናቸው ተባሉ። አሁን በእነዚህ ስፍራዎች ያለው ጉዳይ ያው በዜና የምናየው ስለሆነ መድገም አያስፈልግም። የፓለቲካ እብደት እንደዚህ ነው። በቅርብ 8 ቢሊዪን ገባ የተባለው የዓለም ህዝብ በዚህም በዚያም ይቀናነሳል። ያም ሆኖ ግን አብሮ የመኖር ስልቱ ከበፊቱ ይልቅ አሁን እየተፈተነ ይገኛል። የኢትዪጵያንም የፓለቲካ ውጋትና ትንቅንቅ ማየት ያለብን ከዓለም የፓለቲካ አሰላለፍ ጋር ነው። የአሜሪካና የአውሮፓ ለወያኔ የንስሃ አባትና ቋሚ ተከራካሪ መሆናቸውም ሚስጢሩ ምሥራቅ አፍሪቃን የራስ ቀጠና ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያን አስመልክቶ በተለይም ከኤርትራ ጋር ሰላም መሆኗ ብዙዎችን አስከፍቷል። በኤርትራ ላይ የማያባራ ማዕቀብ የሚያደርጉትም ኤርትራን ለማስጎብደድ ነው። ማን ቢሰማ። በኤርትራ ላይ የሚያደርጉት ጫና በዝምባብዌ ላይ ሲያደርጉ ከነበሩት የክፋት ኮሮጆ የተቆነጠረ ነው። የሚፈልጉት ለጥ ሰጥ ብሎ አሜን እሺ ምን ልታዘዝ የሚላቸው የሃገር መሪ ነው። በአሁኑ አማርኛ ተላላኪ መንግስት። የኤርትራው መሪ የምዕራቡን ዓለም ክፋት ጠንቅቆ ያውቀዋል። አክ እንትፍ ያላቸውም ለዚያ ነው። አሁን በሰበባ ሰበቡ ኢትዪጵያንና ኤርትራን ለማላትም እየተሰራ እንደሆነ እናውቃለን። ወረፋው የነጭ መገዳደል ነው እነርሱ ይገዳደሉ። እኛ ለዝንተ ዓለም በእነርሱ ሴራ ስንገዳደል ኑረናል። ልብ ያለው እጅ ወደ ላይ ብሎ ለሰላም በአፍሪቃ ምድር ሊቆም ይገባል እንጂ የተውሶ መሳሪያ ይዞ እንዘጥ እንዘጥ እያሉ ሰው ማሸበርና መዝረፍ ትርፍ አያመጣም።
የብልጽግናው መንግስት ኦነግ/ሸኔ በህዝብ ላይ የሚያደርገውን ጭፍጨፋ የሚመሩት ውስጡ የተሰገሰጉ የአሁንና የቀድሞ የእድሜ ልክ ፓለቲከኞች ናቸው። በልመና የታጠቀና ህዝብን የሚያሸብር ሃይልን ወደ ሰላም ማምጣት አይቻልም። ወያኔም ሆነ ሌሎች ተባራሪ የጥፋት ሃይሎችን መመከት የሚቻለው ሰውን በማደራጀት፤ በማስታጠቅ፤ በማስተማርና ፍትህ ባለበት መንገድ እጃቸውን የሰጡ ሁሉ ከጥፋታቸው ጋር ተመጣጣኝ ቅጣት በመስጠት ነው። ግን ስብሃት ነጋንና ቤተሰቡን ከእስር የፈታ መንግስት ስለ ፍትህ ምን ያውቃል? አሁን ማን ይሙት መንግስቱ ሃ/ማሪያም የወያኔ መሪዎች ከፈጸሙት በደል የላቀ ፈጽሟል? ባጭሩ የሃገሪቱ ውጋት በከተማና በገጠር ይቀጥላል። ያው የሄደ የመጣው ለህዝብ፤ ለሃገር፤ ለክልልህ፤ ለቋንቋህ፤ ለሃይማኖትህ ወዘተ እያሉ ሲያላትሙን ይኖራሉ። በቃኝ!
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የሥነ ዜጋ እውቀት ማለትም የሀገርን ትርጉም ካለማወቅ ተጀምሮ በፍትሕ አለመኖር የሚያበቃ ነው።