“የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን” የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን የሚለውን ቃል ለምን በትእምርተ ጥቅስ እንዳስቀመጥኩት የገባችሁ ይመስለኛል፡፡ ጣቢያው ስሙ እንደሚጠቁመው የሀገር የብዙኃን መገናኛ ሳይሆን እራሳቸውን በመንግሥት ስም ያደራጁ በአብዛኛው ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ተፃራሪ የሆነ ጥቅም ፍልጎትና ዓላማ ያለው ቡድን ዓላማ ማራመጃ ከሆነ ዐሥርት ዓመታት አልፏልና ነው መትእምርተ ጥቅስ ማስቀመጤ፡፡
ይህ የብዙኃን መገናኛ ሕግና ሕዝብ እንዲሆን የሚጠብቀው ነገር ግን የመንግሥት (የሕዝብ) መሆን ያልቻለው ብሔራዊ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ (የምርአየ ኩነትና የነጋሪተ ወግ) ጣቢያ ትናንትና በ19-12-2006 ዓ.ም. የግል የኅትመት የብዙኃን መገናኛዎችን በተመለከተ “ያልተገሩ ብዕሮች” በሚል ርእስ ዘጋቢ ፊልም ሲል በሠየመው ዝግጅት ዝግጅቱ ምንም እንኳን ዘጋቢ ፊልም (ምትርኢት) ለመሰኘት የሚያበቃውን ሞያዊ መስፈርት (discipline) የያዘ ፊልም (ምትርኢት) ባይሆንም ባለሞያ በሌለበት ቤት ይህ ይሆናል ብለን አንጠብቅምና ብቻ ግን ሊሉ የፈለጉትን ነገር ባይሉም ሊሉ የፈለጉት ነገር ገብቶናልና በቀረበው ዝግጅት ላይ ከ1 ብሔራዊ የብዙኃን መገናኛ ፈጽሞ በማይጠበቅ የወረደ አዘገጃጀት ወይም ደረጃ ከወትሮአቸው የተለየ ባይሆንም በእውነት አሳፋሪ የሆነ ፍጹም ጭፍን እና ሚዛናዊነት የጎደለው ዝግጅት አቅርቦ ነበር፡፡ ነገሩ “አመድ በዱቄት ሲስቅ” ዓይነት ነው የሆነብኝ፡፡
ስለ እውነት ከሆነ ይህንን ዝግጅት ያዘጋጁ ሰዎች ጭንቅላት ያላቸው ቢሆኑና ለሞራል (ለቅስም) ሕግጋት ተገዥ ቢሆኑ ኖሮ “እኛስ ማን ነንና” በሚል ተገቢ የኅሊና ጥያቄ ጣታቸውን በሌላ ላይ ለመጠቆም ባልደፈሩም ነበር፡፡ ነገር ግን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ሰዎቹ ከሰብእናቸው አኳያ ይህ የኅሊና ጥያቄ ጨርሶ የሚሰማቸው አይደሉምና እነሱም በብዙ ጊዜ እጥፍ የረከሱበትን ጉዳይ በሌሎች ላይ ሲያነሡ ቅንጣት እንኳን አልሰቀጠጣቸውም ፡፡ ይህ እነሱ በግሉ የኅትመት የብዙኃን መገናኛዎች ላይ ያነሡትን ጥያቄ ለጣቢያው ቢነሣበት ምን ያህል በስንት ጊዜ እጥፍ ቀለው እንደሚገኙ አሳምሮ ለሚያውቀው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማቅረብ መድፈራቸው የሚያሳየው ነገር ቢኖር ወይ የሰዎቹን ጤነኛ አለመሆን፣ ወይ ድንቁርናቸውን፣ ወይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ንቀት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ሊገልጽ የሚችለው አንዳችም ቁምነገር የለም፡፡
ይህ ዝግጅት የግሉን የብዙኃን መገናኛ
- በፈጠራ ወሬ
- ሚዛናዊ ባለመሆን
- በስም ማጥፋት
- የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ለአደጋ በመዳረግ ወንጀሎች ከሷል ፡፡
ስለእውነት ጊዜና ቦታ አይበቃንም እንጅ እነዚህን እያንዳንዳቸውን ክሶች በመጥቀስ ጣቢያውን ከሀገርና ሕዝብ ጥቅም በተፃራሪ ወይም የተለየ የራሳቸው ጥቅም ፍላጎትና ዓላማ ያለውን ቡድን ጥቅም ፍላጎትና ዓላማ ለማስጠበቅ ጣቢያው በአሁን ሰዓት በሕዝብ ዘንድ ያለው አመኔታ “መቸም አታምኑንም አሁን ሰዓቱ ከምሽቱ 2 ሰዓት ሆኗል” ተብሎ በሚገለጽበት ደረጃ ደርሶ ምን ምን ዓይነት የፈጠራ ወሬዎችን ሲነፋብን እንደኖረና እንዳለ፣ ሚዛናዊነት የሚባል የሞያው ደረጃ መኖሩን ቃሉን እናኳን ጨርሶ ሰምተው የሚያውቁ እስከማይመስሉበት ድረስ የሕገ መንግሥታቸውን ድንጋጌዎች አሽቀንጥረው በመጣል ፍጹም ኢፍትሐዊ የሆነ የአንድ ወገን ወይም የቡድን ጥቅም ፍላጎትና ዓላማ መንዣ ወይም ማራመጃ እንደሆነ፣ የስንት ዜጎችን ክብርና ማንነት ከብዙኃን መገናኛ ፈጽሞ በማይጠበቅ ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ባለሆነና በማናውቀው ባእዳዊ ሥነምግባር በጎደለው አቀራረብና ሰብእና ስም እንዳጠፋ ክብር እንዳጎደፈ፣ የሀገራችንን እና የሕዝቧን ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት የጎዱ ያጠፉና ለአደጋ የዳረጉ ለማፈራረስ ለማባላት ያሴሩ የጥፋት ፕሮፖጋንዳዎችን (ልፈፋዎችን) እና መርዘኛ ስብከቶችን ለመርጨት በምን ያህል የጠላትነት ስሜትና የሞራል (የቅስም) የሞያ ዝቅጠት ወርዶ እንደረከሰባቸው እንደፈጸማቸው አሳምረን መተንተን በቻልን ነበር ፡፡
የመንግሥት (የሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች ምርጫ ደረሰም አልደረሰ ኖረም አልኖረ ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የእምነተ አስተዳደር ማኅበራት) አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን (መመሪያዎቻቸውን) እና የፖለቲካ (የእምነተ አስተዳደር) አስተሳሰብ አመለካከታቸውን ያለ ምንም ቅድመ ሆኔታዎችና ክልከላ ለሕዝብ ማድረስ እንዲችሉ ወይም እንዲያስተናግዱ ሕገመንግሥታዊ ግዴታ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ መሬት ላይ ያለው ሀቅ ግን እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ዘፈኖችን አንኳን ሳይቀር ደጋፊነቱ በግልፅ የማይታወቅ ዘፋኝ ዘፈን የማይደመጡበትና የማይስተናገዱበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ ደጋፊ አለመሆኑ ወይም ተቃዋሚ መሆኑ የታወቀ ዘፋኝ ዘፈን ከሆነማ ዘፈኑ መደመጡ ወይም መስተናገዱ ጨርሶ የማይታሰብ ነው፡፡ ይህ አሠራር ግን ፍጹም ሕገ ወጥ ነው፡፡ አገዛዙ ይሄንን ማድረግ የሚችለው ወይም መብቱ ያለው እንደ ሬዲዮ ፋና ባሉ የራሱ የሬዲዮ (የነጋሪተ ወግ) ጣቢያዎቹ እንጅ በመንግሥት(በሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች አልነበረም፡፡ ነገር ግን ሕግ አይገዛቸውምና ያለ አንዳች መሳቀቅ ይሄንን ሕገ ወጥ ድርጊት የገዛ ሕገ መንግሥታቸውን በመጻረር መንቀሳቀሳቸውን በሰፊው ተያይዘውታል፡፡ እንግዲህ ይህ የሕዝብ (የመንግሥት) የብዙኃን መገናኛ ከገዛ ሕገ መንግሥታቸው ድንጋጌ በተፃራሪ ከስሙ በስተቀር ከመንግሥት (ከሕዝብ) ንብረትነት ወጥቶ የቡድን መጠቀሚያና ንብረት አድርገው እንዴት እየተገለገሉበት እንዳሉ በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡
ከእርሰ ጉዳችን ያወጣናል እንጅ ይህ ጉዳይ ማለትም ከሕግ ውጭ ከመንግሥት (ከሕዝብ) ንብረትነት እጅ ወጥቶ የቡድን አድርጎ የመጠቀሙን ነገር በብዙኃን መገናኛው ላይ ብቻ የቆመ አይደለም፡፡ ሀገሪቱን ጨምሮ የመንግሥት (የሕዝብ) ንብረት የሆኑ ተቋማትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ በትምህርት ተቋማት ዜጎች መሠረታዊ ከሆኑ ከዜግነት መብቶቻቸው አንዱ የሆነውን ያለምንም ልዩነት የመማር መብት ተነፍገው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አባል ካልሆናቹህ መማር አትችሉም ተብሎ ምን ዓይነት ግፍ እየተሠራ እንደሆነ የምናየው ነገር ነው፡፡ ወያኔ ይህን ማለት ይችል የነበረው በራሱ በግሉ በፓርቲው የግል ገንዘብ ያሠራው የትምሕርት ተቋም ቢኖር ኖሮ ነው እንጅ በኢትዮጵያ ሕዝብ ገንዘብ በተገነቡት አልነበረም፡፡ በገሀድ እያየነው ያለነው ጉድ ግን ለምን! አይሆንም! የሚላቸው መብቱን ጠያቂ ሕዝብ ስለሌለ ሌላው ቀርቶ የእምነት ተቋማት እንኳን ከሀገርና ከሕዝብ ንብረትነት ወጥተው የቡድኑ ንብረት እንዲሆኑ በመደረጋቸው የቡድኑን ኢፍትሐዊ ጥቅም እንዲያስጠብቁ ተደርገዋል፡፡ ስለእውነት ከሆነ ይህ ሕዝብ በታሪኩ እንደዚህ ዘመን የተናቀበት የተዋረደበት የተደፈረበት መጫወቻ መቀለጃ የሆነበት ዘመን አፍን ሞልቶ ከቶውንም የለም አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ሁሉ ውርደት ንቀትና መደፈርም ግንባር ቀደም ተጠያቂው እራሱ ሕዝቡ እንደሆነ አስባለሁ፡፡
አሁን የመንግሥት (የሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች እጅግ በባሰ ሁኔታ እያጠፉ ስለሆነ የግሎችም የማጥፋት መብት አላቸው እያልኩ አይደለም ያለሁት፡፡ እዚህም እዛም ስሕተት ይኖር ይሆናል ከስሕተት የጸዳ ነገር የለምና፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት እንደ ስሕተት የተቆጠሩባቸው ነገሮች 95% በላይ ወይ ያልተደረጉ አልያም ስሕተት ተደርጎ ሊቆጠር የማይገባ ነው፡፡
በየትኛውም ሀገር ማየት እንደሚቻለው የግል ብዙኃን መገናኛዎች ማለት አማራጭ የብዙኃን መገናኛዎች ናቸው፡፡ ይህም ማለት በመንግሥት የብዙኃን መገናኛዎች በተለያየ ምክንያት ሽፋን የተነፈጋቸውን ወይን እንዲስተናገዱ ላልተፈለጉት ለሕዝብ ለሀገር ለዜጎች ጉዳዮች ሽፋን በመስጠት በአማራጭነት ሕዝብን ማገልገል ማለት ነው፡፡ አለዛማ ማለትም የመንግሥት የብዙኃን መገናኛዎች ተቀይደው ተይዘው የሚያወሩትን ለመድገም ከሆነ የግል የብዙኃን መገናኛዎች ምን ጥቅም ሊኖራቸው ይችላል? ምንም ዓይነት ፋይዳ አይኖራቸውም “መንግሥት” እንዲባልለት የፈለገውን ነገርማ በተሻለ አቅም የመንግሥት (የሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች ይከውኑታልና፡፡ ውስን የሆነውን የሀገርና የሕዝብን ሀብትና ንብረትን ከማባከን ውጭ ምንም የሚተክሩት ነገር የለም፡፡ በመሆኑም አገዛዙ ሐሳብን ያለገደብ በነፃነት የመግለጽ ሕገመንግሥታዊ መብት ሰጥቻለሁ እያለ የግል የብዙኃን መገናኛዎችንም ሕገ ወጥ በሆነ ምንገድ ጨምድዶ ይዞ እየተጠቀመባቸው አንዳለው የመንግሥት (የሕዝብ) የመገናኛ ብዙኃን ሁሉ በአንድ ዓይነት ወይም በተመሳሳይ ቅኝት ሥሩ ብሎ ሊያስገድድ የሚችልበት አንድም ዓይነት ሕጋዊ መሠረት ያለው አሠራር ጨርሶ እንደሌለ ሕዝብ እንዲያውቀው እወዳለሁ፡፡
እዚህ ላይ በአማራጭ ድምፅነት ሊያገለግሉ የሚችሉት የግል የብዙኃን መገናኛዎች ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደ የአሜሪካ ድምፅ እና ዶቸቨሌ ያሉ የሰብአዊ እና የዴሞክራሲያዊ (በይነሕዝባዊ) መብቶች ጉዳይ ይገዱናል ያገቡናል ያሳስቡናል የሚሉ መንግሥታት የሬዲዮ (የነጋሪተወግ) ጣቢያዎችም በአማራጭ ድምፅነት ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡ እራሳቸውን እንደሚገልጹትም የተመሠረቱት የኢትዮጵያን ሕዝብ በአማራጭ ድምፅነት ማለትም “ከመንግሥት” የብዙኃን መገናኛዎች የማያገኘውንና ሊያገኘው የማይችለውን መረጃ ለመስጠት እና ለማገልገል ነው፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት የብዙኃን መገናኛዎች በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት ወዲህ በተለይም የአሜሪካ ድምፅ በረጅሙ የወያኔ እጅ አቅማቸው ተዳክሞና እጃቸውን ተጠምዝዘው ቀድሞ የነበራቸው ጥንካሬ ትጋትና አቅም ድራሹ ጠፍቶ የነበራቸው ክብርና ሞገስ ተደማጭነትና ተአማኒነት እያሽቆለቆለ አማራጭነታቸው ቀርቶ አገዛዙ በሕገወጥ መንገድ እየተጠቀመባቸው እንዳሉት የመንግሥት (የሕዝብ) የብዙኃን መገናኛዎች ስለአገዛዙ የሚደሰኩሩትን መልሰው የሚያስተጋቡ ለመሆን ተገደዋል፡፡
በዚህ ዘጋቢ ፊልም (ምትርኢት) በጅምላ የተከሰስነው የተወነጀልነው የግል የኅትመት የብዙኃን መገናኛ ብዙኃን ጸሐፍትና ጋዜጠኞች ምን ምን ዓይነት አጸያፊና ዘግናኝ የግፈኞችንና የአንባገነኖችን ሰቆቃና ግፍ በመጋፈጥ በሚቀፍ በሚዘገንን ማስፈራሪና ዛቻ ሥጋትና ሰቀቀን ውስጥ በማለፍና ዋጋም በመክፈል ሥራው እንደሚሠራ ቀን ወጥቶልን ፍትሕ ሰፍኖልን እስኪሰማ ድረስ ምሬቱንና መቅፈፉን ሊገምት የሚችል ዜጋ መኖሩን እጅግ እጠራጠራለሁ፡፡ ይህ ሁሉ እናት ሀገራችንንና ተወዳጅና የሚያሳዝን ሕዝቧን ከገቡበት ማጥ ለማውጣት ልጆቿ የግድ የሚከፍሉት ዋጋ በመሆኑ ይሄው ዐይናችንን አፍጥጠን ተጋፍጠናል፡፡ ከእነዚህ አገዛዙ ከሚፈጥራቸው ጫናዎች መሰናክሎች ወከባዎች ጋር መሥራት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነም መገመት አያዳግትም፡፡ የግሉ የኅትመት የብዙኃን መገናኛ ይሄ ሁሉ ጉድ እያለበት ወያኔ እንዳቀረበብን ክስ ሁሉ እሱም በጅምላ በመኮነን ክስና ወቀሳ የሚያቀርብ አካል ካለ በእውነት ማስተዋልና ማገናዘብ የተሳነው የዜግነት ኃላፊነትና ግዴታ የማይሰማው የማይገደው በመሆኑ በራሱ እጅግ ሊያፍር ይገባል፡፡ በጣምም እናዝናለን፡፡
ወያኔ እንደምንም ብሎ ሀገሪቱ ሌሎች የዜግነት ግዴታቸውን የተረዱ ዋጋ ቢያስከፍልም ግድ መሆኑን የተረዱ ደፋር ጋዜጠኞችንና ጸሐፍትን እስክታፈራ ድረስ ሰሞኑን በቀረበባቸው ከባድ ክስ ምክንያት ሳይወዱ በግድ ተሰደው የተለዩን ወንድሞችን ለመተካት ዓመታትን ማስቆጠራችን ግድ መሆኑ አይቀርም፡፡ ወንድሞች ሆይ! ስለተለያቹህን ኃዘኔ እጅግ የበረታ ነው ነጻ ሆነን የምንገናኝበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ተስፋየ የጸና ነው፡፡
ወያኔ በግል የብዙኃን መገናኛዎች የወሰደው እርምጃ የለየለትና ዐይን ያወጣ አምባገነንነት ነው፡፡ ሕዝባችን ይህንን ኢፍትሐዊና አምባገነናዊ እርምጃ በምንም ዓይነት በዝምታ ሳትመለከት በፍጥነት መብቶችህን በእጅህ እስክታስገባ ድረስ ለትእግሥትህ ልክ በማበጀት ይህንን የበሰበሰ ግፈኛ አገዛዝ በቃህ! ማለት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
አገዛዙ ይህንን የሚያደርግበት ብቸኛው ምክንያት ከጊዜ ወደጊዜ እየከፋ እየተባባሰ የመጣውንና የሚሄደውንም ግፍ፣ ሙስና፣ በደል፣ የሀገር ክህደት ወንጀሎች እንዳይገለጡ እንዳይጻፉ እንዳይታወቁ እና ወደአንተ እንዳይደርሱ ለማድረግ ነውና፡፡ ይህንን ልትታገስ አይገባም፡፡ ካልሆነ ግን ያለ አባትህ ባርነትህን አምነህ እንዳረጋገጥክላቸው ዕወቀው፡፡ በዚህም የከፋ ቀን እንጂ የተሻለ ቀን እንደማይመጣ ላረጋግጥልህ እወዳለሁ፡፡ታዲያ ፍላጎትህ ይህነውን?
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
amsalugkidan@gmail.com
(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
Leave a Reply