
* “ዓለም እያዘነብን እየሳቀብን ነው አንድ እንሁን” – ዘመነ ካሤ
አርበኛ ዘመነ ካሴ “ዓለም እያዘነብንም እየሳቀብንም ነው” በማለት “መተው ነገሬን ከተተው” እንደሚባለው በመተው “አንድ እንሁን” የሚል ጥሪ አሰማ። ፋኖ ኢትዮጵያን ሠርቶ ምስራቅ አፍሪካን ያረጋጋል ብሏል፤ አንድነት ለመፍጠር “አንድ ማንኪያ ቅንነት” ነው የሚያስፈልገው አለ። በጎጃም እና በደቡብ ጎንደር የተሰማራው የአገር መከላከያ በበኩሉ ስም፣ ቦታና ኃላፊነት ጠቅሶ በፋኖ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል። የዘመነ መልዕክት የተሰራጨው የመከላከያ መረጃዎች እኩል ቀን ነሐሴ 16 በሪፖርት መልክ ይፋ ከሆነ በኋላ ነው።
“የዕለቱ መልዕክት” በሚል የአማራ ፋኖ በጎጃም መሪ ዘመነ ካሴ “በቃ መተው እንልመድ” ሲል የተለያዩትን የፋኖ አመራሮችና አደረጃጀቶች ዘርዝሮ ” … አንድ መሆን አለበት” በማለት በተለይ ዛሬ ጥሪ ያቀረበበትን የተለየ ጉዳይ ባይጠቅስም “… ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪካችን የረባ ለትውልድ የሚጠቅም ፍሬ የለዉም …. የመዘላለፍና የመጠፋፋት ነው” በማለት ወቅሷል።
የአገር መከላከያ በተመሳሳይ ቀን ረፋዱ ላይ በፌስቡክ ገጹ ረፋዱ ላይ በደቡብ ጎንደርና በጎጃም ኦፕሬሽን ማካሄዱን አስታውቆ፣ “…. በዚህ ዘመቻ ከተደመሰሱት አመራሮቻቸው መሀል ረዳት ኢንስፔክተር ስሜነህ መለሰ የፋግታ ፖሊስ አባል የነበረ፣ ኢንጅነር ዋሲሁን አለነ ኤፍሬም አጥናፉ የሚባል ብርጌድ አመራር የነበረ፣ ተሻገር አደመ የዚሁ ብርጌድ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረ፣ ምህረቱ አበበ ብርጌድ ምክትል አዛዥ፣ ግዛቸው ደሳለው ፋይናንስ ሠራተኛና የአካባቢው ፅንፈኛ መሥራች ታህሳስ 2017 ቆስሎ ያመለጠ ቀንደኛ ዘራፊ፣ ደሴ ባዜ የአባጋስ ሻለቃ አዛዥ፣ ቃኛቸው ተበጀ የሻለቃው ሎጅስቲክስ ይገኙበታል” ሲል ሰፊ ዝርዝር ያለው መረጃ አጋርቶ ነበር።
“ይህ ትግል አንድ ይሆናል። አንድ ሆኖ አማራን ከፈጽሞ ጥፋት ይታደጋል። አንድ ሆኖ ኢትዮጵያን አንድ ያደርጋል። ኢትዮጵያን ሠርቶ ምስራቅ አፍሪካን ያረጋጋል። የሰላምና የመረጋጋት ተስፋዎች ሁሉ ከፋኖ መንደር ይቀዳሉ” ሲል ዘመነ የትግሉን ከፍታና ልቀት አስገንዝቧል።
ዘመነ “የአማራ ትግል እስክንድርን ከሀብቴ፣ ዘመነን ከደረጀ ፣ ዝናቡን ከመከታው፣ አስረስን ከፋንታሁን ሙሀባ፣ ደሳለኝን ከሄኖክ፣ ምሬን ከሳሚ፣ ጌታ አስራደን ከስሜነህ ሙላቱ … ሳይለይ ቶሎ አንድ መሆን አለበት። ትግሉ ዛሬ አንድ መሆን አለበት። የርዕዮት፣ የመስመርና የሀሳብ ልዩነቶች በዝግ ውይይት ይታረቃሉ። ይከረከማሉ” ሲል የአንድነት ጥሪ ያሰማው ከዚህ ከተጠቀሰው የአገር መከላከያ ኦፕሬሽን ጋር በተያያዘ ይሁን በሌላ የተገለጸ ነገር የለም።
“ሰርገው የገቡ እጆች በጥንቃቄና በጥበብ ይቆረጣሉ። የአንድ መከረኛ ህዝብ ልጆች ነን። ይብቃንና ማንንም ሳንጥል ማንንም ሳናንጠለጥል አንድ እንሁን። ዓለም እያዘነብንም እየሳቀብንም ነው። ድርጅታችን የአማራ ፋኖ በጎጃም ለዚህ የተቀደሰ እርምጃ እንደሁልጊዜው ሁሉ ዝግጁ ነው። በቃ መተው እንልመድ። መተው ነገሬን ከተተው ነውና ብሂሉ” ያለው ዘመነ ካሴ፣ ደጋፊዎች ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስቧል።
አክሎም “መሰዳደቡን መዘላለፉን እንተወዉ። ዘመናዊ የፓለቲካ ታሪካችን የረባ ለትውልድ የሚጠቅም ፍሬ የለዉም እንጅ የመዘላለፍና የመጠፋፋት ነው። ከተማርንበት እሱ በቂ ነው” ብሏል።
በመልዕክቱ ማጠቃለያ “አሁን ወደ ሥራ” እንግባ ያለው ዘመነ ካሴ፣ አፋብኃ በቅጡ ጤናማ ሆኖ ይሰራል። አፋህድ እና አፋብኃ አንድ ይሆናሉ።አለቀ” ሲል የጥሪውን ግብ አስቀምጧል። ይህ ይሳካ ዘንዳ የሚያስፈልገው አንድ ማንኪያ ቅንነት ብቻ እንደሆነም አመልክቷል።
የፋኖ አደረጃጀትን ወደ አንድ ኅብረት ለማምጣት በተደጋጋሚ ጥረቶች የተካሄዱ መሆናቸው ይታወሳል። በተለይ አራቱንም የፋኖ አደረጃጀቶች (እስክንድርንም ጨምሮ) ወደ አንድ ዕዝ ለማምጣት በተደረገው ስብሰባ የዘመነ ሰዎች አመራሩን ወደ ጎጃም ለመውሰድ ባደረጉት ሙከራና በጠነሰሱት ሤራ፤ ይህም ይፋ በመውጣቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
የአሜሪካው አምባሳደር ማሲንጋ ላቀረቡት ጥሪ እስክንድር በእንግሊዝኛ ምላሽ በመስጠቱና በቀጣይም ለድርድር የተዘጋጀ የተጠናከረ ቡድን ሆኖ መውጣቱ ያሳሰበው ዘመነ የሻዕቢያ ትዕዛዝም ተጨምሮበት እነ ምሬ ወዳጆንና ሌሎች ደጋፊዎቹ ሰብስቦ ኅብረት ለመፍጠር መሞከሩ ይታወሳል። ሆኖም ዘመነ የኅብረቱ መሪ እኔ ካልሆንሁ በሚል ባስነሳው ጭቅጭቅ የታሰበው ኅብረት ከአንድ ቀን የፎቶ ሥነስርዓት ማለፍ አቅቶት ተበታትኗል።
በርካታ የፋኖ ኅብረት አደረጃጀቶችን እኔ ካልመራሁት በሚል እብሪትና ራስ ወዳድነት አፍርሷል በማለት ዘመነን የሚከስሱ ወገኖች ያሁኑን ጥሪውን ጠላቱን ለመጉዳት ብሎ የተሻገረበትን ድልድይ እያፈረሰ እንደመጣ ግለሰብ አድርገው ይቆጥሩታል። ድልድይ አፍራሹ የጠላቱን መጎዳት ብቻ ነበር ያሰበው በኋላ ግን ራሱም መመለስ አቅቆታል፤ ዘመነም እንዲሁ ነው። ፋኖን እኔ ካልመራሁት በሚል ስሁት እሳቤ “በምድር ላይ እኔና እስክንድር ብቻ ብንሆን አንጣላም” ካለው ወዳጁ እና ከሌሎችም ተቃቅሮ አሁን የአንድነትና የኅብረት ጥያቄ ቢያቀርብ ምላሹ “ድልድዩ ፈርሷል” የሚል ይሆናል በማለት በምሬት ይናገራሉ።
መከላከያ ያስነበበው ዘገባ እንደሚከተለው ይነበባል፤
“በጎጃም እና በደቡብ ጎንደር የተሰማራው ሠራዊት 81 የጽንፈኛውን ቡድን አባላት ደመሰሰ” ሲል የአገር መከላከያ ያሰራጨው ዜና ከስር ሙሉ በሙሉ ቀርቧል። ፋኖ በየትኛውም አደረጃጀቱ ዜናውን አላስተባበለም።
ምስራቅ ዕዝ እና በስሩ ያሉት ኮሮች ባደረጉት ልዩ ስምሪት የጽንፈኛው ቡድንን አከርካሪ የሰበሩ ውጤቶች አስመዝግበዋል። ጽንፈኛው የሚዲያ ግርግር ለመፍጠር በሁሉም የጎጃም እና የደቡብ ጎንደር ዞኖች ሽብር ለመፍጠር ቢያስብም ሀሳቡ መና ቀርቶ 81 አመራሩን እና ተዋጊዎቹን አጥቷል።
ምስራቅ ዕዝ በደቡብ ጎንደር በእብናት ፣ በሊቦ ከምከም ፣ በፋርጣ፣ በእስቴ፣ በደራ ወረዳዎች ቀበሌዎች ባደረገው ስምሪት ጽንፈኛውን የገባበት ገብቶ ደምስሶታል። በሰሜን ጎጃም ባሉ ደቡብ ሜጫ፣ደቡብ አቸፈር፣ ሰሜን ሜጫ ወረዳዎች ቀበሌዎች ውስጥ ተሰግስጎ የነበረውን ዘራፊ ቡድን የማጽዳት ግዳጅ ተወጥቷል።
በአዊ ብሑረሰብ ዞን በዳንግላ፣ በፋግታ ለኮማ፣ ድማማ አንገረብ እና በሌሎች ወረዳዎች ውስጥ ባሉ ቀበሌዎች ባደረገው ዘመቻ ጽንፈኛውን የገባበት ገብቶ ነው የቀጠቀጠው። በምዕራብ ጎጃም ቋሪት፣ አበስቃን፣ ጉልሽ፣ ጎሽ ሜዳ፣ አየለች ገበያ፣ ሰከላ ወረዳ ቀበሌዎች ላይ እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም አነደድ ወረዳ ጉዳለማ ከተማ ኮሮች ህግ የማስከበር ግዳጃቸውን በብቃት ተወጥተዋል።
በነዚህ ስኬታማ አፕሬሽኖችን ከተደመሰሱት በተጨማሪ 44 የጥፋት መልዕክተኞች ቁስለኛ ሆነዋል። አስራ አንድ ሲማረኩ ፣ አስራ ሁለት እጃቸውን ሰጥተዋል ። ሌሎች አስራ ሁለቱ ጥቃቱን መቋቋም ተስኗቸው ሲሸሹ በአባይ ወንዝ እና በጎርፍ ተበልተው ህይወታቸው አልፏል። በውሀ ከተውሰዱት መሀል አዲሱ መንበር የኤፍሬም አጥናፉ ብርጌድ ፅ/ቤት ሃላፊ የነበረ ፣ ጉምዜ እና በዛብህ የሚባሉ የጽንፈኛው አመራሮች ይገኙበታል።
አንድ አር ፒ ጂ/ላውንቸር ከነቅንቡላው፣ አንድ ፒ ኬ ኤም/መትረየስ፣ 85 የድሽቃ ጥይት፣ 27 የነፍስ ወከፍ መሳሪያ፣ 60 የመትረየስ ጥይት፣ 103 የኤ ኬ ኤም ጥይትን ጨምሮ ሌሎች ጽንፈኛው ለጥፋት ሲጠቀምባቸው የነበሩ ተሸከርካሪዎች እና 22 ሞተር ሳይክሎች እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተለይም በሠራዊታችን ቁጥጥር ስር የዋለውና የጽንፈኛው መሪ ያስመረቀው “ዘሪሁን 13 የአዲሱ ትውልድ ሮኬት ሚሳዔል” በሚል ቁርጥራጭ ብረት ቀጣጥለው የሰሩት የውሸት መሳሪያ ህዝቡን ምን ያህል እንደናቁትና በውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደሚያታልሉት ያጋለጠ ነበር። ጽንፈኛው ዘመናዊ ሮኬት ሰርቻለሁ በሚል ከህብረተሰቡ በርካታ ገንዘብ በመዋጮ ስም ዘርፎበታል።
በዚህ ዘመቻ ከተደመሰሱት አመራሮቻቸው መሀል ረዳት ኢንስፔክተር ስሜነህ መለሰ የፋግታ ፖሊስ አባል የነበረ ፣ ኢንጅነር ዋሲሁን አለነ ኤፍሬም አጥናፉ የሚባል ብርጌድ አመራር የነበረ፣ ተሻገር አደመ የዚሁ ብርጌድ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበረ ፣ ምህረቱ አበበ ብርጌድ ምክትል አዛዥ ፣ ግዛቸው ደሳለው ፋይናንስ ሰራተኛና የአካባቢው ፅንፈኛ መስራች ታህሳስ 2017 ቆስሎ ያመለጠ ቀንደኛ ዘራፊ ፣ ደሴ ባዜ የአባጋስ ሻለቃ አዛዥ ፣ ቃኛቸው ተበጀ የሻለቃው ሎጅስቲክስ ይገኙበታል።
በዚህ ስምሪት የተደመሰሱት የጽንፈኛው አመራሮች በቡድኑ ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበራቸው። በተለይም ሃምሳ አለቃ ደሴ አባይነህ የዘራፊው ዋና ስምሪት ሰጪ እና ሎጀስቲክስ፣ መሪጌታ ብርሃኑ ጌታነህ የቀጣናው አወያይ እና ፖሊቲካ አስልጣኝ ወደ መንግስት ፅንፈኛው የሰላም ጥሪ እንዳይቀበል ቃለ መህላ የሚየስገባና እየሰበከ ሲያዋጋ የነበረ፣ አንተነህ መሠረት ከዚህ በፊት መንገድ ትራንስፖርት ሙያተኛ የነበረ ከመጀመሪያው ጀምሮ ፅንፈኛን ያደራጀ የመንግስት መሣሪያ ከሚሊሺያ ያስወረደ አሁን የሻለቃ ምክትል አዛዥ የነበረ በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ቀለባቸው አፈር ሆኗል።
የሠራዊታችንን ምት መቋቋም ያቃታቸው የጽንፈኛው አመራሮች በዋሉበት የማያድሩ ፣ ህይወታቸውን ለማትረፍ በየጥሻው እና ጉራንጉሩ መደበቂያ ሲፈልጉ የሚውሉ ፣ የሠራዊታችንን መምጣት ምልክት ሲያዩ በመጨነቅ ከመሞት ለመሰንበት በመደበቅ ህይወታቸውን የሚያራዝሙ ሆነዋል።
ምስራቅ ዕዝ በቅርቡ በጀመረው በዚህ አዲስ ስልት ፣ ሠራዊታችን አስቸጋሪ መልክዓ ምድሮችን በቀንም ሆነ በድቅድቅ ጨለማ በጽናት በማለፍ፤ ዝናብ፣ ጭቃ፣ የወንዝ ሙላት፣ ብርድ እና ሌሎች የተፈጥሮ መሰናክሎችን በመቋቋም ባደረጋቸው እልህ አስጨራሽ ስምሪቶች ህዝብን እፎይ ያስባሉ ውጤቶችን አስገኝቷል።
በዚህ ወር ከነሐሴ 9 ቀን ጀምሮ ባሉት ቀናቶች በተካሔደው ልዩ ኦፕሬሽን የአማራ ክልል የሰላም እና ፀጥታ ሀይሎች፣ የመስተዳድር አካላት እና ኅብረተሰቡ መረጃ እና ሌሎች ድጋፍ በመስጠት ለሰላማቸው እንዲጸና ያላቸውን አጋርነት በተግባር አሳይተዋል።
ሠራዊታችን እነዚህን የህዝብ ሰላም አደፍራሾች በጸረ-ሽምቅ ከያሉበት እያሰሰ ፣ እየከበበ እና እየመነጠረ አጽድቶ ህግ ያስከብራል። ዘመቻው ሰላም አደፍራሾች እስኪጠፉ የሚቀጥል ሲሆን ሰራዊታችን ክልሉን ከጽንፈኞች የማጽዳት ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ





Leave a Reply