• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የታገደው ድፍረት ፊልም የይገባኛል ጥያቄ አስነሳ

September 7, 2014 10:42 pm by Editor Leave a Comment

አንጀሊና ጆሊ ኤግዚኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር የሆነችበትና ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ዲፕሎማቶችና የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት በብሔራዊ ቴአትር ሊመረቅ የነበረው ድፍረት ፊልም፣ በፍርድ ቤት እግድ ከተቋረጠ በኋላ የይገባኛል ጥያቄ ማስነሳቱ ታወቀ፡፡

በአሜሪካ በሰንዳንስ ፊልም ፌስቲቫል ተሸላሚ ከሆነ በኋላ የፊልሙ በአዲስ አበባ መመረቅ በብዙዎች በጉጉት እየተጠበቀ ነበር፡፡ እንዲህ የተጠበቀው ፊልም ሊመረቅ በታሰበበት ዕለት ከአሥራ አምስት ደቂቃዎች በላይ ሊታይ አልቻለም፡፡ በብሔራዊ ቴአትር እየታየ ፌደራል ፖሊስ ደርሶ ሊያቋርጠው የግድ ሆኗል፡፡

aberash bekele bbc
አበራሽ በቀለ – ፎቶ: BBC

ፊልሙ በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የሚያጠነጥነው አስገድዶ የደፈራትን የ29 ዓመት ወጣት በገደለችው የ14 ዓመት ታዳጊ አበራሽ በቀለ (በፊልሙ ሒሩት) ሕይወት ዙሪያ ነው፡፡ ደፋሪዋ ሕፃኗን በጠለፋ ሊያገባትም ሙከራ አድርጐ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ጉዳዩን ሰምተው ጥብቅና ቆመውላት ራስን ለመከላከል በሚል በነፃ እስከተለቀቀችበት ጊዜ ድረስ፣ አበራሽ በግድያ ክስ ተመሥርቶባት ማረሚያ ቤት ነበረች፡፡

በአቶ ዘረሠናይ ብርሃኔ መሐሪ የተጻፈውና ዳይሬክት የተደረገው ይህ ፊልም በዚህ ዓመት በሰንዳንስ ፊልም ፌስቲቫል ተሸላሚ መሆኑን ተከትሎ፣ የታሪኩ ባለቤት በሆነችውና ፈቃደኝነቷን እንዳልተጠየቀች በምትናገረው ወ/ሪት አበራሽና የወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ወንድምና የታሪኩ ጸሐፊ ነኝ በሚሉት አቶ ፍቅሩ አሸናፊ ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡

የፍርድ ቤት እግዱ እንደሚያሳየው በከሳሽነት የቀረቡት አቶ ፍቅሩ አሸናፊና ወ/ሪት አበራሽ በቀለ ሲሆኑ፣ ተከሳሾቹ ደግሞ አቶ ዘረሠናይ ብርሃኔ፣ ኃይሌ አዲስ ሥዕሎች ድርጅትና ትሩዝ ኤይድ ሚዲያ ድርጅት ናቸው፡፡

ክሱ እንደሚያስረዳው ድፍረት የተሰኘው ፊልም ተመርቆ ለሕዝብ ዕይታ ቢውል በከሳሾች ሞራላዊና ኢኮኖሚያዊ መብት ላይ የማይተካ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል በመገንዘብ፣ ፍርድ ቤቱ ፊልሙ ለሕዝብ ዕይታ እንዳይውል ወይም እንዳይመረቅ ጭምር እገዳ ጥሏል፡፡ በተጨማሪም በተከሳሾች ላይ ሊደርስ ለሚችል ኪሳራ ከሳሾች 50 ሺሕ ብር በዋስትና አስይዘዋል፡፡

ወ/ት አበራሽ እንደምትለው ፊልሙ በርሊን እስከተመረቀበት ጊዜ ድረስ ምንም ዓይነት መረጃ አልነበራትም፡፡ ከሰባት ወራት በፊት ግን አቶ ዘረሠናይን አግኝታው በፊልሙ ላይ ዕውቅና እንዲሰጣት፣ የተወሰነ ገንዘብም እንዲከፍላት እንደምትፈልግ ገልጻለት የነበረ ቢሆንም ይህ ሳይሆን ቀርቷል፡፡

የፊልሙ ሥራ የእሷን ደኅንነት ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ አይደለም በማለት የምትወቅሰው ወ/ት አበራሽ፣ ምንም እንኳ ሁኔታውን ለማስረዳት ብትሞክርም ከአቶ ዘረሠናይ በመጨረሻ ያገኘችው መልስ አዎንታዊ አለመሆኑን ትናገራለች፡፡ “ከተፈጠረው ነገር ጋር በተያያዘ የምኖረው ተደብቄ ነበር፡፡ ይኼ ፊልም ግን ታሪኩን እንደ አዲስ ቀስቅሶ የእኔንም የቤተሰቦቼንም ሕይወት አደጋ ላይ ጥሎታል፤” ትላለች፡፡

ወ/ት አበራሽ የደፈራትን ሰው ከገደለች በኋላ በኦሮሞ የእርቅ ባህል ጉማ መሠረት ቤተሰቦቿ ካሳ ከፍለው ነገሩ ተቋጭቶ ነበር፡፡ በስምምነቱ መሠረት እሷም ቀዬዋን ጥላ ለመውጣት ተስማምታ እንደነበር የምትናገረው አበራሽ፣ “በባህሉ መሠረት ሴት ገድላ ካሳ መክፈል አትችልም፡፡ ስለዚህም ወደ አካባቢዬ እንዳልመለስ የሟች ቤተሰቦች ያስጠነቀቁኝን በመስማትና ለቤተሰቦቼ ደኅንነት ስል ለዓመታት እዚያ ሳልደርስ ቀረሁ፤” ብላለች፡፡

ዘረሠናይ ብርሃኔ መሐሪ
ዘረሠናይ ብርሃኔ መሐሪ

በአሁኑ ወቅት ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችን ለማገዝ የሚሠራ ሀረም በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በመሥራት ላይ የምትገኘው ወ/ት አበራሽ፣ በሕይወቷ ብዙ ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፈች ትናገራለች፡፡ የትውልድ ቦታዋ ቀርሳ አርሲን የለቀቀችው ወ/ት አበራሽ ሁለተኛ ደረጃ እስክትደርስ የኖረችው ቀጨኔ ሕፃናት ማሳደጊያ ውስጥ ነበር፡፡ ታሪኳ ተካትቶ በተሠራ ዘጋቢ ፊልም አማካይነት ታገኝ የነበረው ገንዘብ ኮሌጅ ስትገባ መቋረጡን ታስታውሳለች፡፡ ስለዚህም በነበረባት የገንዘብ ችግር የኮሌጅ ትምህርቷን ለማቋረጥ መገደዷን፣ ከዚያም ወደ ዱባይ እስከሄደችበት ጊዜ ድረስ በአንድ ትንሽ የፊልም ሲዲ ማከራያ ሱቅ ውስጥ መሥራቷን ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

አቶ ዘረሠናይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ እንደተናገረውና አቶ ፍቅሩ እንደሚሉት ስለታሪኩ መጀመሪያ አቶ ዘረሠናይ የነገረው ለእርሳቸው ነው፡፡ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. በ2005 ሲሆን፣ አቶ ፍቅሩ እንደሚሉት የፊልሙ ሐሳብ የተወሰደው ከእሳቸው በመሆኑ ፊልሙን በጋራ ለመሥራት አስበው ነበር፡፡ “ከ2008 በኋላ አቶ ዘረሠናይ እኔን ለማናገር አልፈለገም፡፡ እንዲያውም ይደበቀኝ ጀመር፤” ይላሉ፡፡

የፊልሙን መሠራት ሲጠባበቁና ነገሮችን ሲከታተሉ እንደነበር፣ የአበራሽን ይሁንታም እንዳገኙ አቶ ፍቅሩ ይናገራሉ፡፡ አቶ ዘረሠናይ ግን ለእሷም ለእሱም የታሪኩ ሐሳብ ባለቤት እንደመሆኑ ዕውቅና ሳይሰጥ መቅረቱን ያስረዳሉ፡፡ “ያለሷ ታሪክ ፊልሙ አይሠራም ነበር፡፡ ባትደፈር፣ በጥንካሬ ደፋሪዋን ባትገድለው ኖሮ ታሪክ አይኖርም ነበር፤” ይላሉ አቶ ፍቅሩ፡፡

በፊልሙ ውስጥ ሌላ ባለታሪክ የሆኑትና በወቅቱ የ14 ዓመቷ ታዳጊ ጠበቃ የነበሩት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ለፊልሙ ዳይሬክተር ታሪካቸው በፊልሙ እንዲካተት ፈቃድ መስጠታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይህንንም ያደረጉት ታሪኩ በፊልም መሠራቱ የኢትዮጵያ ሴቶች የመብት ጥያቄን ያራምዳል፣ ስለጠለፋና ስለጥቃት ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል በሚል እንጂ “የእኔ ታሪክ ይነገር” በሚል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ለአበራሽ ጥብቅና በቆሙላት ጊዜ ከዚያም በኋላ አበራሽ በመኖሪያ ቤታቸው ተቀምጣ እንደነበር ቅርበትም እንደነበራቸው የሚያስታውሱት ወ/ሮ መዓዛ፣ ለረዥም ዓመታት ግን ከአበራሽ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው እንደቆዩም ይናገራሉ፡፡

ከፊልሙ መሠራት በኋላ ግን የታሪካቸው በፊልም መሠራት ለአበራሽ የሚከፍተው የዕድል በር ይኖራል በሚል ማፈላለግ መጀመራቸው የሚናገሩት ወ/ሮ መዓዛ፣ ስለጉዳዩ በነገሯት መሠረት በመጨረሻ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ደራርቱ ቱሉ የአበራሽን ስልክ ቁጥር እንደሰጠቻቸውና እንዳገኙዋት ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

መዓዛ አሸናፊ
መዓዛ አሸናፊ

“ደውዬ ወደ አዲስ አበባ አስመጣኋት፡፡ አሁንም ያለችው እናቴ ቤት ነው፡፡ የእኔ ቤት ወጣ ስለሚል ነው እዚያ እንድትቀመጥ ያደረግኩት፡፡ ከመጣች ወደ ሰባት ወራት ገደማ ሆኗል፤” የሚሉት ወ/ሮ መዓዛ፣ ወ/ት አበራሽን አሁን እየሠራችበት ያለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንድትቀጠር ያደረጉት እሳቸው እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ወ/ሮ መዓዛ እንደገለጹት ወ/ት አበራሽ ወደ አዲስ አበባ እንድትመጣ ያደረጉት ፊልሙ ጀርመን በርሊን ውስጥ ሊመረቅ በተቃረበበት ጊዜ ነበር፡፡

ለታሪኳ ባለቤት ወ/ት አበራሽ በፊልሙ ሥራ ተሳታፊ ከሆኑት ግለሰቦች ሁሉ ቅርበት ያላት እርሷ እንደመሆኗ የታሪኳ ባለቤት ተጠቃሚነትን በሚመለከት ለወ/ሮ መዓዛ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ምላሽ፣ “መጠቀም እንዳለባት አምናለሁ፡፡ አቶ ዘረሠናይም በዚህ ያምናል፡፡ ይህን ለማድረግም በጣም ፈቃደኛ ነው፡፡ እሷም የምትጠብቀው ነገር አለ፡፡ ችግር የፈጠረው እንዴት በሚለው ላይ አለመነጋገር ነው፤” ብለዋል፡፡

ወንድማቸው አቶ ፍቅሩ አሸናፊም ፊልሙ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውን በሚመለከት፣ ወንድማቸውና የድፍረት ፊልም ዳይሬክተርና ከፕሮዲዩሰሮቹ መካከል አንዱ የሆነው አቶ ዘረሠናይ ምንም እንኳ የጓደኝነታቸውን ደረጃ መናገር ባይችሉም፣ ጓደኛማቾች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ወንድማቸው ስለ እርሳቸው ለጓደኛው አቶ ዘረሠናይ ሲያወሩ የፊልም ባለሙያ የሆነው አቶ ዘረሠናይም ታሪኩን ወደ ፊልም ለመቀየር ትልቅ ፍላጐት እንዳደረበትና የፊልሙ መነሻ እንዲህ እንደነበር፣ ከዚህ ውጪ ግን በወንድማቸውና በአቶ ዘረሠናይ መካከል ሌላ ጉዳይ ይኑር አይኑር የሚያውቁት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡ ግጭቱ ቀላል እንደሆነ ስለዚህም በጣት በሚቆጠሩ ቀናት ውስጥ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል፡፡

የፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ዘረሠናይ ብርሃኔ በእጁ ላይ ያለው የፍርድ ቤት እግድ ብቻ በመሆኑ ስለክሱ ዝርዝር ነገር ሳያውቅ በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይፈልግ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡ የባለታሪኳ ወ/ሮ አበራሽ ፈቃድን ማግኘት አለማግኘቱን በተመለከተም አቶ ዘረሠናይ ምንም ማለት አለመፈለጉን ገልጿል፡፡ ጠበቃው ዓርብ ነሐሴ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ የክሱን ቻርጅ ለማግኘት ፍርድ ቤት እንደነበሩና የክሱን ዝርዝር እንዳወቁ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ ገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ዓርብ እኩለ ሌሊት ድረስ ከእሱ በኩል የተሰማ ነገር አልነበረም፡፡

የፊልሙ እግድ ለብሔራዊ ቴአትር ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. አሥራ አንድ ሰዓት ላይ መድረሱን ከሳሾች ቢጠቁሙም፣ የቴአትር ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሽመልስ እግዱ የደረሰው አሥራ አንድ ሰዓት ከሃያ አምስት ላይ እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት እግዱ በደረሰበት ወቅት 1,200 ያህል እንግዶች አዳራሹ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አሥር ያህሉ አምባሳደሮችና ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡ በአሳጋጆቹ በኩል የነበረው አቀራረብ አስቸጋሪ ስለነበርና በሌላኛውም በኩል ፊልሙን ለማቋረጥ ያለመፈለግ ነገር ስለነበር፣ በአጋጣሚው የአገር ገጽታ እንዳይበላሽ በጥንቃቄ ለመያዝ ቴአትር ቤቱ የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል ብለዋል፡፡

“የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይከበራል፡፡ ይህ ምንም ዓይነት ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን በሁሉቱም በኩል የነበረው ነገር ወደ ግጭት የሚያመራ ዓይነት ስለነበር ነገሩ በሰላም እንዲፈታ ፖሊስ ጠርተናል፡፡ ምክንያቱም እኛ ያለን የፀጥታ ኃይል ያን ማድረግ አይችልም ነበር፤” ሲሉ አቶ ተስፋዬ የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር ዜና)

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: News Tagged With: Left Column

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • የ-አብሮነት ማኅበር የመረጠው ሕቡዕ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ይፋ ሆነ November 5, 2025 12:06 pm
  • “የኢሳያስ አፈወርቂ ውድቀት አይቀሬ ነው … “ፅምዶ” ራዕይ ዓልባ” ነው – ሼትል ትሮንቮል October 26, 2025 10:15 pm
  • አሜሪካ ስላልተቀበለችው ነው “የሽሽግር መንግሥት” ስብሰባው በአምስተርዳም ተካሄደው October 25, 2025 11:09 pm
  • በዓባይ ግድብ ምረቃ፡ የሕዝብ ደስታ፣ የቴድሮስ ካሳሁን ዝምታ September 14, 2025 04:27 am
  • ኢትዮጵያ የውኃ ኑክሊየር ማብላያዋን ልታስመርቅ ነው  August 29, 2025 11:46 pm
  • መከላከያ በፋኖ አመራሮች ላይ እርምጃ ወሰደ፤ ዘመነ በ“አንድ ማንኪያ ቅንነት” አንድ እንሁን አለ August 23, 2025 12:35 am
  • ፋኖን በፋይናንስና በሎጂስቲክስ የሚደግፉ የጎጃም ባለሃብቶች ከስደት ሊመለሱ ነው August 14, 2025 12:42 am
  • የበቀለ ገርባ የአሜሪካ ጥገኝነት ማመልከቻ ውድቅ ተደረገ August 13, 2025 12:16 pm
  • ሞዐ ተዋሕዶ “ነጻ አውጪ ግምባር” – ሞነግ August 13, 2025 12:58 am
  • የሃይማኖትና የመንግሥት ጥምረት በረከት ወይስ መርገም?  August 5, 2025 09:18 pm
  • የባከነ የስደት ሕይወት ከደባርቅ እስከ ኖርዌይ July 29, 2025 05:44 pm
  • “በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን”፤ ቲፒኤፍ July 22, 2025 01:28 am
  • Rusted screws, metal spikes and plastic rubbish: the horrific sexual violence used against Tigray’s women July 4, 2025 01:48 am
  • በሞርሞን ቤ/ክ ዕርዳታ የኪዳነምህረት ኦርቶዶክስ ቤ/ክ ማምለኪያ ሥፍራ አገኘች July 2, 2025 01:28 pm
  • የበረከት ስምዖን “አየር ላይ ትዕይንት” አየር ላይ ተበተነ July 2, 2025 01:24 am
  • “ዐቢይ ይውረድ፣ እኛ እንውጣ፣ በተራችን እንግዛ” ስልቴዎች (ስብሃት፣ ልደቱ፤ ቴዎድሮስ) June 11, 2025 01:56 am
  • ኤሊያስ መሠረት የሚሠራው ለማነው? ለብጽልግና? ወይስ …? June 3, 2025 01:27 am
  • በግንቦት 20 – የሁለት መሪዎች ወግ May 28, 2025 02:01 am
  • በፈቃዳቸው የተመለመሉ ወጣቶች ሁርሶ ሥልጠና ጀመሩ May 22, 2025 09:11 am
  • ድብቁ ሤራ ሲጋለጥ – “ሦስትን ወደ አራት” May 21, 2025 01:01 am
  • ከትግራይ ሾልኮ የወጣው ምሥጢራዊው ሰነድ ምንድነው? May 20, 2025 09:18 am
  • በደቡብ ጎንደር በጸዳሉ ደሴ የተመሩት 72 ታጣቂዎች እጃቸውን ሰጡ May 19, 2025 02:24 pm
  • የተመሠረተው የፋኖ አደረጃጀት ዋነኛ ዓላማው ድርድር መሆኑ ተነገረ May 14, 2025 11:07 pm
  • ከፍተኛ የፋኖ አመራሮች መገደላቸው ተነገረ May 6, 2025 10:40 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2025 · Goolgule