አይሲስ በሊቢያ ተጨማሪ ኢትዮጵያውያንን መያዙን ከአይሲስ ያመለጠው ኢትዮጵያዊ ለቪኦኤ ገለጸ፡፡ እርሱንና ሌሎችን በአይሲስ እንዳይወሰዱ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ማስጣላቸውን ተናገረ፡፡
ይኸው ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው ወገን እንደተናገረው እኛን ከአይሲሲ ያዳኑን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ናቸው፤ በሀገራችን በፍቅር ነው የኖርነው ክርስቲያኖቹን ለይታችሁ አትወስዱም በማለት ሙስሊሞቹ እንደተከራከሩላቸው፤ እንደጮሁላቸው አስረድቷል፡፡ በዚህም ምክንያት እርሱና ሌሎች ላሁኑ ከመሞት ተርፈዋል፤ ከዚህ ወዲህ የሚሆነውን ግን ለመናገር እንደማይችልና ሁሉንም “እግዚአብሔር ነው የሚያውቀው” በማለት በእምነት እየጠበቁ መሆናቸውን ከተሰወረበት ቦታ ለአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋዜጠኛ ተናግሯል፡፡
ይኸው ከአይሲስ ያመለጠው ኢትዮጵያዊ ከዚህ በፊት ቤንጋዚ ላይ ከሌላ የትግራይ ተወላጅ ጋር ተይዘው በኤሌክትሪክ እንደተቃጠሉና ከሞት እንደተረፉ አስረድቷል፡፡ ድብደባውባ ቃጠሎው የደረሰባቸው አይሲሶች “እስልምናን እንዲቀበሉ” በሚያስገድዷቸው ጊዜ እንቢ በማለታቸው እንደሆነ ገልጾዋል፡፡
ይኸው ሊቢያ ትሪፖሊ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ወገን ለቪኦኤው ሰለሞን አባተ እንደገለጸው ማክሰኞ እለት ቁጥራቸውን ለመግለጽ ያልቻለው እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ታፍሰው መወሰዳቸውንና እርሱና ሌሎች ተደብቀው ማምለጣቸውን ተናግሯል፡፡ ከተወሰዱት መካከል እርጉዝ ሴት፣ ህጻን ልጅ እና ሰሞኑን ቀዶ ጥገና ተደርጎላት ከሆስፒታል የወጣች እንደሚገኙበት አስረድቷል፡፡
በተለይ ቤንጋዚ ላይ “በግድ እስልምናን” እንዲቀበሉ ሲያስገድዷቸው እምቢ ያሉትን ከሙስሊም ኢትዮጵያውያን ለይተው ለመውሰድ አሲሶች በሞከሩበት ጊዜ “ባህላችን አይፈቅድልንም፤ አብረን (ከክርስቲያኑ ጋር) ተፋቅረን የኖርን ነን፤ እዚህ በስደት ልንለያይ አንችልም” ብለው ሙስሊም ኢትዮጵያውያኑ እሪ በማለታቸው በርካታዎች ከግድያ ማምለጣቸውን በድጋሚ ገልጾዋል፡፡
የወደፊቱን ለማወቅም ሆነ ለመናገር እንደማይችል “እግዚአብሔር አንድ ነገር እንዲያደርግ” ከመጸለይ ሌላ ምንም እንደሌለው በቃለ ምልልሱ ወቅት ተናግሯል፡፡
የቪኦኤውን ሙሉ ዘገባ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡
ቅንብር: ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply