የአገራችን አንድነትና ብሎም ሕልውና በቋፍ ባለችበት በዚህ ቀውጢ ወቅት ውይይቱ ሁሉ ማተኮር ያለበት ለሥጋቶቹ ምንጭና ምክንያት ስለሆኑት ስለ ዴሞክራሲ ደብዛ መጥፋት፣ ስለፍትህ መቅጨጭ. በብሔረሰቦች መካከል ስለሚታዩት ጥላቻና ግጭቶች እነዚህን የወለደው ሥርዓት ስለመለወጥ ብቻ መሆን አለበት ሌላው ሁሉ ገብስ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውጭ በሆኑ ጉዳዮች መነጋገር ሥርዓቱን ለውጦ ዴሞክራሲና ፍትህ ለማስፈን በሚደረገው ትግል ላይ ቀዝቃዛ ውሃ እንደመቸለስ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ሆኖም ዘላቂ የአገር ጥቅሞችን መዘንጋት የኋላ ኋላ ሕልውናን ወደ መፈታተን ደረጃ ሊደርሱ ይችላሉ አገር ከሌለ ዴሞክራሲ ምን ሊፈይድ ፍትህስ ምን ሊረባ?
ምናልባት የአገር ሕልውናን እስከመፈታተን ሊደርሱ ከሚችሉ ከዋነኛ የአገር እሴቶች አንዱ የባህር በር አለመኖር ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ሁኔታ በማይጨው ጦርነት ለሽንፈታችን ምክንያት ከሆኑ ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ኢትዮጵያ የገዛችው የጦር መሳሪያ በጅቡቲ በኩል ወደ አገር እንዳይገባ ፈረንሳይ መከልከልዋ እንደነበር መዘንጋት የለብንም፡፡
ኢትዮጵያ በምትገኝበት አደገኛ አካባቢ ሲሆን ጂኦፖለቲካውና ሃይማኖት ከስሌት ሲገባ የባህር በር በተለይም የኢትዮጵያ የአሰብ ባለቤትነት ጥያቄ ከሸቀጥ ማስተላለፍ በዘለለ የሕልውና ጥያቄ ሆኖአል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለኢትዮጵያ ሉአላዊነት ወሳኝነት እንዳለው እያወቁ “አሰብ አሰብ የምትሉት ምንድን ነው” እያሉ ይህንን ትልቅ ሕዝብን ያስጨነቀና እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ሲያጥላሉ ተደምጠዋል፡፡ በዚህ ላይ ብዙ ማለት ቢቻልም በተቃዋሚዎች መሃከል ሌላ አዲስ የጭቅጭቅ ርእስ ላለመክፈት ሲባል ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትዝብት እንተዋለን፡፡ ጥቅሙን ከሕዝብ በላይ የሚያውቅ የለምና፡፡
ኤርትራና ኢትዮጵያ በ1983 ዓ.ም የዓለም የሃይል አሰላለፍ ባልተገነዘቡ፤ የአካባቢው ጂኑፓለቲካና ሃይማኖታዊ ሁኔታዎችን ማገናዘብ ባልቻሉ ከዘር ወይንም ከጎሳ ውጭ ሌላ ነገር ለሚታያቸው የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ሁለዘርፍ ቁርኝትና መስተጋብር ከመጤፍ ባልቆጠሩ መሪ ተብዮች አመራር ስር ወደቁ ከዚያም ወንድም እህት የሆነው ሕዝብ በጦርነት ተላለቀ:: ኢትዮጵያ በታሪኳ በፍፁም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከቀይ ባህር አካባቢ ተገልላ በዓለም ትልቁ ወደብ አልባ ዝግ አገር ሆነች፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካም ታሪክ ወደ ተከታታይ ትውልድ ሲንቁረቁር ኢሕአደግ በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ የሚታወሱበት ዋነኛ ቅርስ (ሌጋሲ) ኤርትራን አስገንጥለው ኢትዮጵያን በእግር መንገድ እርቀት ወደብ አልባ ማድረጋቸው ይሆናል፡፡
እ.አ.አ በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል የተደረገው አሳዛኝና ዓላማ ቢስ ጦርነት እንደ ተደመደመ ሁለቱም አገራት ድርድር ወደ አልጄሪያ ከማቅናታቸው ቀደም ብሎ በአገርም በውጭም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ወደብ አልባ ከመሆን ጋር በተጓዳኝነት የኤኮኖሚ የስኩሪቲና የፖለቲካ ክስረቶች ለኢሕአደግ ለማስገንዘብ ኒው ዮርክ በተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ደጃፍ ከተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ጀምሮ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ያልማሱት ሳር የለም ማለሰት ይቻላል፡፡ ምናልባትም የአስብ ኢትዮጵያዊነትና የቀይ ባህር አፈሮች አንድነት ያህል የተተነተነ ኢትዮጵያዊ ጉዳይ የለም ማለት ይቻላል፡፡ አሰብን ወደ ኢትዮጵያ የሚያጥፍ የወሰን ሽግሽግ እንዲደረግ ይኸ ባይሆን ለሰላም ሲባል አሰብ በሁለቱም አገሮች የጋራ ባቤትነት (joint sovereignty) ስር ሆኖ ራስ ገዝ እንዲሆን ኢትዮጵያውያን ከአቀረቡአቸው አሳቦች ጥቂቶቹ ነበሩ፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥረቶች በአቶ መለስ አማካኝነት ኢሕአደግ የሰጠው መልስ ወይንም አስተያየት የዚህ ሐሳብ አቀንቃኞች ኋላ ቀር ነፍጠኞች ከጊዜው ጋር የማይራመዱ ጊዜ የማይለውጣቸው መሃይማን የሚል ስድብ ነፍጠኞች ነበር፡፡ አስብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የጭንቀት ምክንያት የሆነችው አገሪቷ ለወደብ አገልግሎት ለቀረጥና ለደሜራዥ ለመሳሰሉት ኢሕአደግ ሕዝቡን ሳያማክር በነፃ ለጅቡቲ የሰጠው ውሃ እንኳን ቅናሽ ሳያደረግ በዓመት ወደ ስድስት ቢልዮን ደላር የሚጠጋ ገንዘብ ለጅቡቲ በመክፈላችን ብቻም አይደለም፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ እጅግ ስተራተጂክ ከሆነው ከቀይ ባህር ባትገለል ሊኖራት ይችል የነበረው ጀኦ ፓለቲካ አቅም ዜሮ በማግባቱም ብቻ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ጉዳታቸው የላቀ ቢሆንም የኢትዮጵያውያን ዋናው ጭንቀት የሚመነጨው አስብ በኤርትራ እጅ ከገባች አቶ ኢሳያስ ምናልባትም ለኢትዮጵያ በጎ ለማይመኙና ለማያስቡ ሀይላት ወይን አገራት አሳልፈው ሰጥተዋት የኢትዮጵያ ደህንነትና ሉአላዊነት ለአደጋ ይጋጥል ከሚል ፍራቻ ነው፡፡ ይኸው እንግዲህ የተፈራው ደርሶ የኤርትራ ሕዝብ ሳያውቅና ሳይመክርበት አቶ ኢሳያስ አሳብን በራይ ስም ለሳውዲ አረቢያና ለዮናትድ አረብ ኤምሬት አስረከቡት፡፡ ቀደም ሲል አቶ መለስ ዜናዊ አሰብ ኢትዮጵያ ካተጠቀመችበት የግመል ውሀ ማጠጫ ይሆናል የሚል ራዕይ ታይቶት ይህንኑ ለሕዝብ አሳምቶ ነበር፡፡ ከአቶ መለስ አባባል ቀደም ብሎ “ኢትዮጵያውያ በአሁኑ ጊዜ ለኤርትራ ምንም ጥቅም የማይሰጥው አሳብ እራስዋ ኤርትራ ባትጠቀምበትም ለለየላቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች አሳልፋ መስጠትዋ የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ብለው ነበር”፡፡ (አሰብ የማን ናት! የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ 2003 ገጽ 190)
አቶ መለስ ዜናዊ 70% የዓለም ነዳጅ በሚተላለፍበት ስትራተጂክ አካባቢና የሚገኝ ወደብ ኢትዮጵያ ካተጠቀመችበት የግመል ውሀ ማጠጫ ይሆናል ማለቱ ካንጀቱ ሳይሆን በጉዳዩ እጅግ ይቆጩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ለማዘናጋት ነበር፡፡
አቶ ኢሳያስ አሰብን ለአረቦች ያስረከቡት ለአረቦች ከማከራየት ውጭ ለሌላ ጥቅም ሊውል አይችልም ከሚል አይደለም፡፡ አቶ ኢሳያስ አሰብን ለአረቦች አስረክበው አገራቸውን ለከፍተኛ አደጋ ያጋለጡት የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን በኢትዮጵያውያን በኩል ምን ያህል ቁጭት እንደስከተለ ስለሚያውቁ ኢትዮጵያ አንድ ቀን ወደቡን በኃይል ለመያዝ ትሞክራለች ከሚል ፍራቻ ሊሆን ይችላል ሆኖም ግን በኢሕአደግ የአገዛዝ ዘመን ይህ የማይታሰብ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር በዚህ ላይ የነበረው አቋም ከላይ የተጠቀሰውን ሲሆን የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ደግሞ የአቶ መለስን አቋም በማስተጋባት የካቲት 24 ቀን በ2002 ዓ.ም ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ኢሕአደግ ኢትዮጵያን የወደብ ባለቤት ለማድረግ ፍላጎት እንደሌለውና እንደማያምንበትም አረጋግጠው ነበር (አሰብ የማን ናት? ዝኒ ከማሁ ገፅ 60)
የእነዚህ የሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስተሮች አቋም አንድ ገጣሚ በውስጥ ወይራ አገላለጽ አስቀምጦታል ፡፡
ከጫካ ሰው ጋራ ቁማር ተጫውቼ
ወና ወጥቻለሁ አገር ተበልቼ
እኔም ስጠባበቅ ምርት እህሌን ላፍሰው
ከጫካ የወጣ ዝንጀሮ ጨረሰው
ይህ የአሰብ በአረቦች እጅ መግባት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብሎም ሕልውና ሊፈታተን ቢችልም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከቶም ጉዳት ሆኖ የማያውቀው ኢሕአደግ ድርጊቱን ይቃወማል ብለን አንጠብቅም ” ውሀ ሲጎድል ተሻገር፣ ዳኛ ቢኖር ተናገር” እንደሚባለው የኢትዮጵያ ሉዓታዊነት የሚቆረቆር ዳኛ (አስተዳዳሪ) ሲመጣ አቤት እንላለን፡፡
የአሰብ በአረቦች ቁጥጥር ስር መሆን ብዙ ለውጦችን አስከትሎአል፡፡ ቀይ ባህርን በምስራቅም በምዕራብም ዳርቻ ከመቆጣጠራቸውም በላይ ለዘመናት ሲያልሙትና ሲመኙት የነበረው የቀይ ባህር የአረብ ሀይቅነት እውን ሆኖላቸዋል፡፡ “የጎረቤት ሌባ ባያዩት ይሰርቃል ቢያዩት ይስቃል” እንደሚባለው እኛም ለኢትዮጵያን ኩታ ገጠም ጎረቤቶች መሆኑን በቀረብን፡፡ ምክንያቱም ከጉርብትናቸው ጋር ተያይዞ የሚመጡ ብዙ መዘዞችም አሉ፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ ለሚፈልቁ አሸባሪዎች ቀላልና በቅርብ እርቀት የምንገኝ ኢላማ ሆነናል፡፡ ባህር ማቋረጥ የሌለባቸው አክራሪ ወሀቢዎች በኢትዮጵያ በወንድምነትና በመፈቃቀር የኖሩ የተለያዩ ሃይማኖቶች ተከታዮች ግንኙነት በአክራሪ ዋሃቢዎች ሊደፈርስ ይችላል፡፡
በኤርትራውያን ላይ ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከኢትዮጵያውም በብዙ እጅ የበለጠና የከፋ ነው፡፡ በሳውዲ ንዳድ ይቃጠሉ የነበሩ ሼኮች ቱጃሮችና ልፁላን በነፋሻው አስመራ እየተሽሞነሞኑ ሕዝቡን ወደ ሁለተኛ ዜግነት ዝቅ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ከዚይም አልፎ በሂደት የጥንቱ የአክሱም ስልጣኔ አካል የነበረችው ኤርትራ ደብዛዋ ጠፍቶ አረባዊ ማንነት ሊጫናባት ይችላል፡፡ ከአርባና ከአምሳ ዓመታት በኋላ ሳውዲ አረቢያ የሚኖረው ሙቀት የሰው ልጅ ሊቋቋመው አይችልም ስለሚባል የውሉ ጊዜ ሲጠናቀቅ ተደላድለው ለዘመናት የኖሩ አረቦች ጓዛቸውን ጠቅላለው ለመውጣት ፈቃደኛ ይሆናሉ ወይ? ከመነሻው መለያየት የማይገባቸው የነበሩ ወንድማማች ሕዝቦች ኤርትራውያን ኢትዮጵያውያንና በስልጣን ጥመኞችና አርቆ ማሰብ በተሳናቸው መሪዎች ውሳኔ ቢለያዩም ተመልሶ የመተሳሰር ዕድል ይህ የአረቦች ጣልቃ ገብነት አጥብቦታል፡፡
አቶ ኢሳያስ ከአረቦች ጋር የተፈራረሙበት ውል የኤርትራን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ሕዝብ ወይንም የሕዝቡ ተወካዮች ያልመከረበት የአቶ ኢሳያስ የግል ውሳኔ በመሆኑ ጊዜው ሲያመች ኤርትራውያን ውሉን መሰረዝ እንደሚችሉ የኤርትራ ምሁራን አይጡትም፡፡ ኤርትራውያን ይህንን ውል የሚቃወሙ ቢሆን የኢትዮጵያውያን ሕዝብ እገዛ እንደማይለያቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በማይበጠስ የዘር፣ የቋንቋ የባህል፣ የሀይማኖት ወዘተ ሀረግ ተሳስረዋል፡፡ የሁለቱ አገራት መሪዎች የፈጠሩት እንጂ ሕዝቡ ዘንድ ዘልቆ የገባ ስሜት አይደለም፡፡ ተራው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኤርትራ ሕዝብ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን በተባበሩ ጊዜ ሕዝቡ ሲችል እየደበቃቸው ሳይችል ስንቅ እየሰጠ በእምባ እንደሸኛቸው ሰው ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ሃቅ ነው፡፡ ስለዚህ የአካባቢውን ጂኦ-ፓለቲካ በጥልቀት የገባቺው ህብረት ኃይል መሆኑን የተረዱ በዘረኝነትና በጎሰኝነት ደዌ ያልተለከፉ መሪዎች በሁለቱም አገር በሕዝብ ተመርጠው ስልጣን ሲጨብጡ በጠላት የማትደፈር፣ በልማት የዳበረች፣ በዓለምና በአፍሪቃ ጫና ልትፈጥር የምትችል አንድ የተዋሃደች በፌዴሬሽን የተሳሰረች አገር ሊፈጥሩ መቻላቸው ሲታሰብ በራሱ ያማልባል፡፡ የኢትዮጵያ ሰፊ ገበያ፣ ሰፊና ለም መሬት በአፍሪቃ በሁለተኛነት የሚመደብ የውሀ ሀብት ሁለቱም አገራት የታቀፉአቸው ብዙ ዓይነት ማድናት፣ በዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት ተስማሚ አየር፣ እጅግ ስትራተጂክ የሆኑ ሁለት ወደቦች ያለው አገር በጥቂት ጊዜ የበለጸገና የታፈረ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ በሁለቱም ሕዝቦች በኩል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ጉጉትም አለ፡፡ ጥያቄው እንግዲህ እንዲህ ዓይነት ራዕይ የሰነቁ እሩቅ አሳቢ ራሳቸውን እርሳቸው ለአገር ያደሩ መሪዎች ይኖራሉ ወደ …… ነው እንዲህ ዓይነት መሪዎች በሁለቱም አገራት ብቅ ካሉ ይህ በምድረ ገነት የተመሰለው አገር ዕውን ማድረግ ይቻላል፡፡
ለዚህ ለዘለቄታ ግብ የሁለቱም አገራት ሕዝቦች በተለይም ወጣቱ መነጋገር መተዋወቅ መግባባት ስለሚኖርበት ይህንን ዓላማ አንግበው የተነሱት እንደነቪዥን ኢትዮጵያና ኢትዮ ኤርትራ ሶሊደሪቲ ግሩፕ ሌሎችም ተመሳሳይ አላፊነት ለሚወጡ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚያደርጉት ጥረት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን ያበርታችሁ እንላለን፡፡
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
gud says
Eretrian cancers r gone forever .
They talk about ethiopia 24/7 though .
We have one final mission . Sending shabia & Eretrian empty pride to dust bin .
Takele says
Ayeeee Denkoro.
koster says
even landlocked Ethiopia will be history like Yugoslavia unless the home grown fascists are dismantelled by all means possible. I donot sea the need to talk of Assab now when even Ethiopia is in great danger.
Solomon says
Eritreawian they are still proud of their country even though they hate their dictator leader Essayas the same way we hate our TPLF Leaders. Let us be mindful instead of being so rude and writing nonesense stuff.