ተጣፈ ተኔ «ወተህ ወርደህ የላብህን ወዝ ትበላለህ» ብለህ ወደ መሬት ከላከው የአዳም የልጅ፤ ልጅ፤ ልጅ፤ ልጅ፤ ልጅ፤ … አንዱ፤ ላንተ በሰማዬ ሰማያት ላለኸው አምላክ::
እነሆ ይችን ደብዳቤ በመልክተኛህ በመላኩ ገብርኤል በኩል ላንተ ስልክ፤ ካገኘህ ለራስህ በእጅህ እንዲሰጥ፤ ካጣህም ለእናትህ ለወላዲት አምላክ፤ እንዲሰጣትና እሷ እንድትሰጥህ አደራ ብዬዋለሁ::
አምላክ ሆይ !
ከጭቃ አድቦልቡለህ የፈጠርከው ሰውን ያህል ጨካኝ ፍጡር አንቱ እያልኩ፤ አንተን አንቱታ በመንፈጌ ከድፍረት እንደማትቆጥርብኝና ቁጣህ እንደማይበረታ አውቃለሁ፤ አንተታዬ የመውደዴና ላንተ ያለኝ የክበር መግለጫ መሆኑን አንተው ታውቃለህና!
ይኸውልህ ጉዳዩ እንዲህ ነው:
ፈጣሪ በጆሮው ላይ ተኝቶ የሕፃናትን ለቅሶ፤ የዕናቶችን ዋይታ፤ ያባቶችን ጣር፤ አልሰማ ብሏል፤ … ሕዝብ መከራው በዝቶ፤ የበደል ገፈቱ ገንፍሎ እየፈሰሰ፤ ዋይታውና ለቅሶው እንደ እሳተ ጎሞራ ላንቃውን ከፍቶ፤ የሰማዩን በር ሲለበልብ፤ ጮኸት በርክቶ፤ ፈጣሪ አልሰማ አለ::
ቤተ መቅደሱ ሲደፈር፤ ጽላቱ ሲቃጠል፤ ገዳማት ሲታረሱ፤ የሰማዕታት መቃብር ሲፈነቀል፤ እሱን ብለው ቅጠል በልተው ለሱ ያደሩ ባህታዊያን፤ በጃቸው መስቀል፤ በቀሚሳቸው ስር ሽጉጥ ባነገቡ ሃሳዊ መሲሃን … ሬሳቸው እንደ ፍሪዳ በቤተ መቅደሱ ሲዘረር፤ ሕዝብ በፀጉሩ ልክ መከራው በርክቶ፤ ችግር አጉቡጦ ሲደልቀው፤ ሆድና ጀርባው በረሃብ ሙጫ ተጣብቆ ሲያቃስት፤ የጎድን አጥንቱን ተደግፎ እየተንገዳገደ ወዳንተ ሲማጠን፤ በውሃ ጥም የደረቀ ምላሱን እየመጠጠ ወዳንተ ሲያንጋጥጥ፤ የነጠተፈ ኩሬ ከመሰሉ ዓይኖቹ ዕንባውን እየጨለፈ ወዳንተ ሲረጭ፤ መሬት እንኳን ቀብጣ፤ አፏን ከፍታ የምትውጠው፤ የድሆችን የደረቀ አጥንትና ጅማት ብቻ ሆኖ፤ ፈጣሪ በዓይኖቹ ማየት ተሳነው፤ እያሉ ያሙሃል::
ምን ማማት ብቻ ! በየመቅረዙ ጠዋትና ማታ ተጎልተው የሚያንሾካሹኩት ይኸንኑ ነው :: አልፎ ተርፎም ተደብቀው የሚያሽሟጥጡህም አልጠፉም፤ እንግዲህ እኔም ተደብቄ አብሬ ከማማህና ከማሽሟጥጥህ ይልቅ ልንገርህ ብዬ ነው፤ ይችን ደብዳቤ ልጥፍልህ የደፈርኩት::
ይኸው ገብሬል ምስክሬ ነው !
እነዚህ ልበ ድፍን የህሊና አልቦዎችና ገንዘብ አምላኩዎች፤ በመጥሃፍ ቅዱስህ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባል የጥቁሮችን ምድር፤ ከ 40 (ከአርባ ጊዜ በላይ) እንደጠቀሰካት እንኳን አይረዱም::
በተለይ፤ በትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 13 ቁጥር 23 ኢትዮጵያዊ መልኩን፤ ወይስ ነብር ዝንጉርጉርነትን ይለውጥ ዘንድ ይቻላልን? ያልከው ልቤን ጧፍ ሆኖ ያሞቀዋል፤ እራሴን ቀና፤ ትከሻዬን ከፍ አድርጌ እንድሄድና በኢትዮጵያዊነቴ ኮርቼ፤ እንድኖር ከሚያደርጉኝ ጥቅሶችህ አንዱ ሲሆን፤ … ላንተ ሁሉንም መንገር አያሻም ብዬ ተውኩት እንጂ፤ እኔ ባሪያህ ሁሉንም መደርደር አይገደኝም::
እናማ ይኸውልህ!
«የጠሏችሁን ውደዱ ብትለን » እሺ ብለን ብንወዳቸው እነሱ ጠሉን፤ « ቀኝ ጉንጫችሁን በጥፊ ቢመቷችሁ ግራውን ስጧቸው» ብትለን፤ ግራ ጉንጫችንን ብንሰጣቸው አልበቃ ብሏቸው፤ ሰውነታችንን በጥይት በሳሱት፤ በሳንጃ ዘከዘኩት፤ ተማሪዎች ልጆቻችን ከግድያ ለመዳን ወደ ቤተ መቅደስህ ቢሸሹ ከቤተ መቅደስህ እየጎተቱ ወስደው ለሞትና ለእስር ዳረጓቸው::
ምን ይኸ ብቻ!
ሕፃናት ለባርነት ተሸጡ፤ ሴቶች ልጆቻችን ለዝሙትና ለግርድና ተሰደዱ፤ ወንዶች ልጆቻችን ለአሽከርነት ተዳረጉ፤ በግፍ ብዛት የእናቶች አንጀት ተቋጠረ፤ ያረገዙበትን ማህጸን ረገሙ፤ ያጠቡበት ጡቶቻቸውን ጎንበስ ብለው በምሬት ነከሱ! ጎልማሶች በራሳቸው፤ በወላጆቻቸው፤ በምሽቶቻቸውና በልጆቻቸው ላይ በደረሰው በደል፤ ቁጭትና ንዴታቸው ገንፍሎ፤ መሬቷን በፍም አሎሎ ሊለበልቧት ቀኑ ተቃርቧል፤ በዛን ዕለት ከእሳቱ ወላፈን የሚያመልጡ እነማን ይሆኑ?!
ወይ ጉድ! ለካ ለዚህ ነበር፤ አያቴ ሃዘኑ በዝቶ፤ የዕምነት ዛቢያው ጠሞበት ሲንገዳገድ፤ ባንተ ላይ ያለውን የተደባለቀ ስሜት ሲገልጽ:
«የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፤
አለህም እንዳልልህ እንዲህ ይደረጋል፤» ብሎ ያዜመው? ሆሆይ!
ዛሬ ነው የተገለጠልኝ፤ ያኔ ትንሽ ልጅ ስለነበርኩ ልብ አላልኩትም ነበር! ዛሬ እኔ የልጅ ልጁም ልደግመው ምን ቀረኝ ብለህ?! በዕውነቱ ዝምታህ በእጅጉ በዛ፤ ትዕግሥትህ ከልክ አለፈ፤ ሕዝቤ ተሰቃየ፤ ለተፈጸመ ግፍ፤ ፍርድ ከሌለ ተጠያቂነት አይኖርምና ፍርድህ የግድ ይላል፤ የዘሩትን ሙጃ የሚያጭዱበት ቀን መቅረቡን ንገራቸው … ::
ደግሞ «የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» እያልክ የልብ ልብ ሰተህ አቀበጥካቸው፤ ከበሯቸውን እየደለቁ ጣቶቻቸውን አሹለው ዓይንህን ለመደንቆል የሚዳዳቸው ቀበጦች ፍጡሮችህን አደብ ግዙ በላቸው! በአምሳልህ የተፈጠርን ፍጡራን መሆናችንን እያወቁ፤ እኛን ሲበድሉ አንተን እንደበደሉ መሆናቸውን እንዴት አያውቁም ትላለህ? እነሱ የሚያደርጉትን ሁሉ ልቅም አድርገው ያውቃሉና፤ ፍርዱን ለአባትህ ተውለት::
ቆይ ቆይ የረሳሁት ጥያቄ አለኝ፤ ለመሆኑ መቼ ነው የምትመጣው?! የተወለድክባት ምድር አልናፈቀችህም? አቤት ያንተ ነገር፤ ለሰው ልጅ የሳሳ ልብ እየሰጠህ፤ ለራስህ በድርብ የተሰራ ልብ ነው ያለህ ልበል? እኔ ግን የተወለድኩባት አገሬና ሕዝቤ ይናፍቁኛል፤ የሕዝቤ መከራው መከራዬ፤ ሃዘኑ ሃዘኔ፤ በደሉ በደሌ፤ ስለሆነበኝ ነው ወዳንተ የምጮኸው፤ እናም ጩኸቴን አድምጥ!
የኔ ነገር እረስቼው ሳልነግርህ!
አንተ «ከበጎቼ መሃል አንዷ እንኳን ብትጠፋ እሷን ፍለጋ እሄዳለሁ ብለሃል»፤
እነሆ በጎችህን ጠብቁ ብለህ አደራ የሰጠሃቸው እረኞችህ፤ በጎቻቸውን የትም በትነው ለዚች ምድር ስልጣን እርስ በርሳቸው ሲጎነታተሉ፤ ሲወነጃጀሉ፤ ሲረጋገሙ … አብዛኞቹ በጎችህ በተኩላዎች ተበሉ፤ ብዙዎቹም ከቤተመቅደስህ ፊታቸውን አዞሩ::
እርስ በርሳቸው ይቅር መባባል ያልቻሉ፤ እንዴትስ አርገው ይቅር ማለትን ሊስብኩ፤ ይደፍራሉ? ሠላም፤ ፍቅር፤ መቻቻልን፤ የሚያስተምር ያንተን ቃል መሰበክስ እንዴት ይቻላቸዋል?
እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ!
በእንተ እዚትነ ማርያም መሃረነ ክርስቶስ! እንበል አሥራሁለት፤
የነገሩህን የማትረሳ የለመኑህን የማትነሳ አምላክ ሆይ !
ፍርድህን ሳላይ ብትጠራኝ እንደማልመጣ ካሁኑ ልንገርህ፤ ነገር ግን ፍትህ ለጎደለበት ሕዝቤ ፍርድህን በሰጠህ ማግስት፤ አንተ ሳትጠራኝ እኔው እራሴ መጥቼ በርህን አንኳኳለሁና ጠብቀኝ:: እኔን ቢያሻህ እንደ ሎጥ ሚስት የጨው ሃውልት፤ ከፈለክም በዕቶን እሳት ውስጥ ወርውረህ፤ ልንደድ፤ ልቃጠል፤ ብቻ ሕዝቤን አድን፤ ሕዝቤን መከራ በቃህ በለው፤ የእናቶችን ዕንባ በምህረትህ አብስ፤ የሕፃናትን ለቅሶ በደስታ ለውጥ፤ የአባቶችን የቆሰለ ልብ አሽር፤ በስደት የሚጉላሉ ወገኖቻችንን ወደ ጥቁሯ እየሩሳሌም ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ መልስ፤ አገራችንን የፍቅር፤ የሠላም፤ የወንድማማችና የተስፋ ምድር አድርጋት:: ሠርተን የምንኖርባት አገር እንጂ፤ እሷን የምንሸሽ ምድር አታድርጋት::
ጨካኞችን ወደ ልቦናቸው መልስ፤ ይቅር ማለትን አስተምራቸው፤ የታበየ ልቦናቸውን አስተንፍስ፤ ያቄመ ልባቸውን በይቅርታ ሙላው፤ በስስት የታወሩ ዓይኖቻቸውን ከፍተህ አብሮ ማእድ መቅረብን አስተምራቸው::
እነሆ በመጨረሻ:
ይችን ደብዳቤ ላንተ በመጣፌ፤ ለፈጣሪ አሳበቀ ብለው የሚከፋቸው ቢኖሩ፤ ባንተ አምሳል የተፈጠሩ፤ ልበ ድንጋዮችና የተንኮል ጎተራዎች ናቸውና፤ ለወገኖቻቸው የሚራራ ልቦና ለግሳቸው::
በአብ፤ በወልድ፤ በመንፈስ ቅዱስ፤
አሜን!
ተጣፈ በዕለተ ልደቱ ታኅሳስ 29 ቀን 2005 ዓ.ም. (07/01/2013)
(ፎቶ: በጸሃፊው የተላከ)
tefera says
Betam teru naw. Hule tafelet.
እስከመቼ says
ከቤተ ክርስትያን የሚመለሱትን መነኮሳት አየኋቸው። እርስ በርሳቸው ይነጋገራሉ። ቤተ ክርስትያኑም አልሄድኩም፤ አነሱንም ቀርቤ አሳልሙኝ አላልኩም። ንግግራቸው ግን ሳበኝ። በተለይም ኢትዮጵያ የሚል ቃል ሲናገሩ ስሰማ ቀንዴ ቆመ። መነኩሴን ደግሞ ፖለቲካ ውስጥ ምን አስገባው ብዬ!
መቼም ዛሬ ግዜና፤ ኢትዮጵያ ያለ ሁሉ ፖለቲከኛ፤ ኢትዮጵያ ማለት ፖለቲካ ሆኖ የለ! ታዲያ ጠጋ ብዬ በደንብ አዳመጥኳቸው። ደሞ ሰላይ የበዛበትና ሁሉም ነገር የስለላ ጉዳይ ስለሆነ ጠርጣሪው ብዙ ነው። እናማ እንዳይጠረጥሩኝ ብዬ፤ ፊቴን ወዲያ የጀሮዬን ቀንድ ወደነሱ አደረግኩና አዳምጥኳቸው። ያዳመጥኩት ጣመኝ። የበለጠ ተጠጋሁ። ሶስት መነኩሴዎች ነበሩ። በመቅመቆ የቀለመና አደፍ ያለ የመናኝ ልብሳቸውን በመልበሳቸው፤ ከየት እንደመጡና ምን እንደሆኑ ጠርጥሬያለሁ። እኩል ከነሱ ጋር መራመዴን ቀጥያለሁ።
“እናማ ይኼን ፈጣሪያችንን የሚያማውና የሚለምነው መብዛቱ!” አሉ የመጀመሪያው መነኩሴ።
“መጣፉ ያለውን እኮ ባያውቁት ነው።” አሉ ሁለተኛው መነኩሴ።
“እና እኛ ማስተማር አለብን። ለዚህም አይደል የመጣነው!” አሉ ሶስተኛው። ቀጥለውም፤ “መቼም ገዳማችን መመለሻ እማይኖርበት ደርሷል። ግና የኛ ሥራ ሰውን ማዳን ስለሆነ፤ እንመለሳለን ብለን ሳይሆን ማሰብ ያለብን፤ እንደወጣን እንቀራለን ነው። መቼም የሱ ፈቃድ አይታወቅምና፤ ብንሰቃይም፣ ብንገረፍም፣ ብንወቀርም፤ የሥጋችን ጉዳይ ነው።” አሉ።
ምን ይዘውት የመጡት ነገር አለ ብዬ፤ የጀሮዬን ግድግዳ በደንብ አስልቼ የበለጠ ተጠጋኋቸው። የመጀመሪያው መነኩሴ፤
“የመጀመሪያው ሥራችን ሰውን የራሱ ኃላፊ እንዲሆን ማስተማር ነው። እሱ ራሱ ተጠያቂ መሆን ያለበትን ጉዳይ ላምላኩ እየሠጠ፤ አምላክ ሁሉን አንተ አድርግልኝ ብሎ መለመኑን ያቁም።” አሉ።
“አዬ የርስዎ ነገር። የሰው ጉዳይ መቼ ተለወጠና! ያም ለኔ ያም ለኔ እኮ ማለቱ ነው እኛንም አስመርሮን ምነና ያስኬደን። ይኼው በመነንንበት አላስቀምጠን ብሎ ያስቸገረንና መልሶ ወደ መካከላቸው ያስመጣን ይኸው አይደል?” አሉ ሆነተኛው መነኩሴ።
ይቺን ይወዳል! እኒህ መነኩሴዎች ሰማዩን ሊያርሱት ነው፤ አልኩና ቀንዴን የበለጠ አሾልኩ።
“በመጣፉ፤” አሉና ሶስተኛው መነኩሴ ጀመሩ። “በመጣፉ ‘እኔ ሁላችሁም ስትመጡልኝ፤ እዚሁ ፍርዳችሁን እሠጣለሁ። ባላችሁበት ግን ተግባራችሁን እመዘግባለሁ እንጂ ጣልቃ አልገባም።’ ብሏል። ታዲያ ይኼንኑ ነው ማስተማር ያለብን። የሰው ልጅ ሁሉም እኩል ነው።” አሉ።
“አዩ አባታችን!” ሲሉ የመጀመሪያው መነኩሴ ጀመሩ። “ይች ሀገር ብዙ ችግር ደርሶባታል። ሰው እርስ በርሱ እየተላለቀ ነው። አጥፊውና ጠፊው ያንድ ሀገር ሰው ነው። ባንድ እንዲኖሩና ተግተው ሠርተው እንዲከብሩ ጥሩ ሀገር ሠጥቷቸው ነበር። ነገር ግን አንዱ በዳይ ሌላው ተበዳይ ሆኖ ልቅሶ ሀገሯን ሞልቷታል። ታዲያ የነፍሳቸውን እሱ ፍርድ ይሠጣል። ለሥጋቸው ግን፤ እርስ በርሳቸው መነጋገር አለባቸው።” አሉ።
“ይስሙንጂ!” ጠበቅ ባለ አነጋገር ሁለተኛው መነኩሴ ቀጠሉ። “እርስ በርሳቸው የሚባል ነገር የት አለ። ለኛ ተርፈውን የለ! ተኛ መጥተውብን ይኸው ከገዳማችን ወጣን። ዝም ብለን አናይ እንግዲህ። የነፍስ ቦታችንን የሥጋ አደረጉብን እኮ! እናማ እኛ ዝም እንዴት አንላለን? ሰውን አግጠህ ወደላይ አትይ። በጎንህ ያለው እንዳንተ ሰው ነው። እያልን እናስተምር።” አሉ።
አንገታቸውን ደፋ አድርገው ሲያዳምጡ የነበሩት ሶስተኛው መነኩሴ፤ “ድንቅ ብለዋል አባታችን። አኛም የወገናችን አካል ነን። ጥቂቶች ብዙኀኑን ሲያጠቁ ዝም ካልን እኛም ያጥቂዎች ወገን ሆንን ማለት ነው። ሰውን የምንነግረው፤ ‘የዴሞክራሲ መብትህን ካምላክህ ስይሆን ከራሰህ እጅ ነው ብለን ማስተማር አለብን።” ሲሉ ሁለተኛው መነኩሴ ከት ብለው ሣቁ።
“አባቶቼ! እኔ ከናንተ አላውቅም። እስኪ በሞቴ! እንዴት ብለን እኛስ አስተማሪዎች እነሱስ ደግሞ ተማሪዎች ሆነው፤ ከኛ የዴሞክራሲ ትምህርት ይፈልቃል? አምላክስ እንዴት ለሰው የሥጋ ፍላጎት ተጠያቂ ይሆናል?” አሉ።