እንዴት ናችሁ!?
‹‹በዛሬዋ መሐል አዲስ አበባ መኪና ማቆምያ ማግኘት መኪና ከመግዛት ያልተናነሰ መታደልን ይጠይቃል›› በሚል ጦማሬን ልጀምር አስቤ ተውኩት፡፡ ለምን ተውኩት? ጠዋትና ማታ እንደ ፓስታ በተዝለገለገ የታክሲ ሰልፍ እግሩ ሸምበቆ እያከለ ለመጣ አዲስ አበቤ ዐረፍተ ነገሬ ቁጣን ይቀሰቅሳል ብዬ፡፡
የዛሬ አነሳሴ በአዲስ አበባ እየከፋ ስለመጣው የመኪና ማቆምያ ችግር ለመጻፍ ነበር፡፡ ሁለተኛ አንቀጽ ላይ ስደርስ የግዜርን ቁጣና የአንባቢን ተግሳጽ ፈርቼ ተውኩት፡፡ ነገሩ ለተራበ ሕዝብ ‹‹ኬክ የመጋገሪያ ስልቶች›› የሚል አጭር ስልጠና እንደመስጠት ሆኖብኝ ተውኩት፡፡
.እንዳዲሳባ ሕዝብ አንጀት የሚበላ አለ እንዴ? ከተማ ለመኖር በመፈለጉ ብቻ ፀሐይና ብርድ የሚፈራረቅበት አዲሳቤን የመሰለ ምስኪን ሕዝብ አለ? ካለ ንገሩኝ፡፡ ኡዝቤኪስታንም- ታጃኪስታንም ቢኬድ እንዳዲሳባ ዜጋ በየዕለቱ ወዶና ፈቅዶ አፈር ድሜ የሚበላ ከተሜ የት አለና? ጥሮ ግሮ ለመኖር በቆረጠ እግሩ እስኪቆረጥ መሰለፍ የሚገደድ ሌላ ሕዝብ አለ? ካለ ንገሩኝ፡፡ እኔ እንዲያውም ይህ ሁሉ ቅጣት ከምን የመጣ ነው ብዬ መልስ ሳጣ በ97 ለሰጠው ድምጽ ገዢዎቹ ዋጋ እያስከፈሉት ይሆን ብዬ ጠረጠርኩ፡፡ ከተሳሳትኩ አርሙኝ፡፡
‹‹ይህ ሁኔታ በሌላ አገር ቢሆን›› ግብር ከፋዩ ሕዝብ ምን ያደርግ ነበር ብዬም ለሽራፊ ሰከንድ አሰብኩ፡፡ ያለጥርጥር ሕዝብ ያምጻል፡፡ በቂ ትራንስፖርት ያልቀረበለት ሕዝብ መጀመሪያዉኑ ወደ ሥራ ለምን ይሔዳል፤ አይሔድም፡፡ ቢሔድም ግብር መክፈሉን ይተዋል፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትሩም ቢሆን መሠረታዊ መጓጓዣ በበቂ ኹኔታ ባለማቅረባቸው በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ይለቃሉ፡፡
እኛ ጋር የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡ ሕዝብ ለታክሲ እንጂ ለተቃውሞ ሰልፍ አይወጣም፡፡ የጥይት እራት እንደሚሆን ያውቃላ፡፡ የትራንስፖርት ባለሥልጣኑም ሥልጣን አይለቁም፡፡ እንዲያዉም ወንበራቸውን ያደላድላሉ፡፡ የትራንስፖርት ሚኒስትራችን አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ሰሞኑን ‹‹ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ›› መባላቸውን የምታውቁ ስንቶቻችሁ ናችሁ? ሳስበው ሳስበው የፒኤችዲ መመረቂያ ጽሑፋቸውን በአዲስ አበባ ሕዝብ የታክሲ አሰላለፍ ባሕርያት ዙርያ የሠሩ ይመስለኛል፡፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡
ዉድ በውጭ የምትኖሩ የአገሬ ልጆች!
ብዙዎቻችሁ የከተማ ሽምቅ ዉጊያ ያለው ሶሪያ አሌፖ ዉስጥ ብቻ ይመስላችኋል፡፡ በሸገር ዉስጥ በየዕለቱ የከተማ ሽምቅ ዉጊያ እንደሚካሄድ አታውቁም፡፡ አብራራለሁ፡፡
ወያላ ስድቡ አቶሚክ ቦንብ ነው፡፡ እሱን መቻል የጦርነት ጥበብን ይጠይቃል፡፡ በስድ ቃላት እየተሰደቡ ዝም ማለት በጦር ሜዳ ቋንቋ‹‹ስልታዊ ማፈግፈግ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ተጋፍቶ የታክሲ ወንበር ማግኘት ስልጣንን የመቆናጠጥ ያህል ፈተና ነው፡፡ በጦር ሜዳ ‹‹የቆረጣ ስልት›› እንለዋለን፡፡ የሸገር የታክሲ ሰልፍ ጥብቅ የኮሚዩኒስት ወታደር ሰልፍ ማለት ነው፡፡ እኔ እንዲያውም የሸገርን የታክሲ ሰልፍ ከአውሮፓ የተቃውሞ ሰልፍ ለይቼ አላየውም፡፡ እርግጥ ነው አስለቃሽ ጭስ የለው ይሆናል፡፡ አስለቃሽ ሽታ፣ አስለቃሽ ዝናብ፣ አስለቃሽ ጎርፍ፣ አስለቃሽ ንዳድ ግን በተሰላፊው ላይ በተከታታይ ይዘንባሉ፡፡ ታዲያ የኛ የታክሲ ሰልፍ ከአውሮፓና አሜሪካ የፖለቲካ ሰልፍ በምን ተለየ?
የሸገር ሕዝብ ከ97 በኋላ ሀሞቱ ፈሶ እንጂ እኮ እዚያው ለታክሲ በቆመበት መፈክር ቢያንጠለጥል ግሩም የሆነ ሕዝባዊ አመጽ ይሆንለት ነበር፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም፡፡
ዉድ የጦማሬ ታዳሚዎች!
ከትናንት በስቲያ በአምባሳደር ቲያትር በኩል ሳልፍ ‹‹ኢሉዥን›› ክለብን ይዞ ሐራምቤ ሆቴልን ታኮ ቶታሉ ጋር የሚደርስ የቦሊቪያ ዘንዶ የመሰለ ሰልፍ ተመለከትኩ፡፡ ምንድነው ታዲያ ፊልም ሰሪዎች ‹‹ቃና ቲቪ ገበያ ተሻማን ቅብርጥሶ የሚሉት›› ስል ወቀስኳቸው፡፡ የፊልም ሰልፍ መስሎኝ፡፡ የአዲሳባ ሰው Tragic የሆነ reality show መጀመሩን የት አውቄ፡፡ በሰልፉ ዉስጥ ልጅ ያዘሉ፣ ዕድሜያቸው የገፋ፣ እርግዝናቸው የገፋ፣ ዕድሜ ያጎበጣቸው፣ ኑሮ ያስጎነበሳቸው ሁሉም አሉበት፡፡ እውነቴን ነው ሁሉም በሰልፉ ተወክለዋል፡፡ ታዲያ ይሄ የታክሲ ሰልፍ ነው ወይስ የሽንፈት?
በቅርብ ጊዜ ዉስጥ የምሰማው የሬዲዮ ፋና ዜና የሚከተለው እንደሆነ ተገለጠልኝ፡፡
‹‹ወጣቷ ነፍሰጡር በታክሲ ሰልፍ ላይ ሳለች በሰላም ተገላገለች፡፡ መንግሥት ያደራጃቸው የአካባቢው ተራ አስከባሪዎች ያደረጉላትን እርዳታ አድንቃለች››
እውነት ነው፡፡ አንዳንድ ተራ አስከባሪዎች ለአካል ጉዳተኞች፣ ከነፍሰጡሮችና ለድኩማን የታክሲ ሰልፈኞች ሕዝቡን እያስፈቀዱም ቢሆን ቅድሚያ ለመስጠት ይታትራሉ፡፡ በተለይም መንግሥት ያደራጃቸው የካዛንቺስና ኡራኤል ተራ አስከባሪዎች በዚህ የተካኑ ናቸው፡፡ ተግባሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ኢህአዴግ ሁሉን በመልክ በመልክ ስላደራጀ ስልጣኑን ያደረጀ መስሎታል፡፡ የጃጀ ቀን ግን በደጉ ጊዜ ያደራጃቸው ዜጎች ተደራጅተው እንደ ዶሮ ይበልቱታል፡፡ ይህን ለማየት የሚያስችል ስፖኪዮ የሌለው ፓርቲ ነው ኢህአዴግ፡፡
ዉድ አንባቢዎቼ!
የሸገር ሰውና የታክሲ ታሪክ እንደ ሰልፉ ረዥም ነው፡፡
ለምሳሌ መቼለታ ወደ ፍርድቤት ስሄድ ሜክሲኮ ጋ ቼምበር ሕንጻን ያቀፈ የሚመስል ሰልፍ ዐየሁ፡፡ አላመንኩም፡፡ ሰልፉ የት እንደሚደርስ ለማየት ከራሴ ጋር አልህ ተጋባሁ፡፡ ብሄድ ብሄድ አያልቅም፡፡ አፍሪካ ሕብረት ጋር ከመድረሴ በፊት ተመለስኩ፡፡ አሁን ማን ያምናል ይሄን?
መቼ ለታ ማዘጋጃ ጉዳይ ልገድል ወጥቼ መሸብኝ፡፡ የመገናኛ ታክሲ ለማግኘት ፒያሳ ሄድኩ፡፡ ባቅላባ ቤቱ ጋ የሚጀምር ሰልፍ ተመለከትኩ፡፡ የታክሲው ሰልፍ ከፊልም ሰልፍ ጋር ተደርቧል፡፡ በሌላ አነጋገር ሁለት ሰልፍ አየሁ፡፡ አንዱ ኢህአዴግ የሚተውንበት ነው፡፡ አንዱ መዲ የምትተውንበት ነው፡፡ የታክሲው ሰልፍ ተስፋ ያስቆረጣቸው ወደ አምፒር የፊልም ሰልፍ ይሻገራሉ፡፡ የታክሲውን ሰልፍ መጨረሻውን ፍለጋ አምፒርን ዞርኩ፡፡ 4ኪሎ ሳልደርስ ተመለስኩ፡፡ አሁን ይሄን ማን ያምናል?
አስኮ መድኃኒዓለም ሰልፉ ተወዳዳሪ የለውም አሉኝ፡፡ እየሩሳሌም ሕንጻ ጋ የጀመረ አራዳ ሕንጻን ይሻገራል፡፡ አሁን ይሄን ማን ያምናል?
የሆስፒታል ወረፋ ጥቁር አንበሳ እንደሚሸ ጥ አውቃለሁ፡፡ የፖስፖርት ወረፋ ኢሚግሬሽን እንደሚሸጥ አውቃለሁ፡፡ የገቢና ወረፋ ሲሸጥ ግን ሰምቼ አላውቅም፡፡ ሰልፉ በከፋባቸው የአምባሳደር አካባቢ ሊስትሮዎችና የጎዳና ልጆች አንድ ብር እየተቀበሉ ለሴቶች የገቢና ወረፋ ይሸጣሉ ፡፡ አሁን ይሄን ማን ያምናል?
ጀሞ የሸገር አዲስ ክስተት ናት፡፡ ከዓመታት በፊት ኪራይ ቀንሶ ኪስ ለማደለብ ሲባል ጀሞ መኖር ተጀመረ፤ አሁን ኪራይ ጨመረ ኪስ ቀለለ፡፡ ቢሆንም ጀሞ ለትራንሰፖርት ምቹ ናት፡፡ ከአራዳ፣ ከፒያሳ፣ ከሜክሲኮ፣ ከአየር ጤና፣ ከጦርኃይሎች ቅጥቅጥ አውቶቡስና ታክሲ በየሰዓቱ ወደ ጀሞ ይዘምታሉ፡፡ 103 ቁጥር ባስ የጀሞ ጀመዐ ባለዉለታ ናት፡፡ የጀሞ ኮንዶሚንየሞች ያን ሁሉ ሕዝብ እንዴት ስልቅጥ አድርገው እንደሚውጡት አላውቅም፡፡ ጀሞ ቤት ተከራይቶ ከተማ ማምሸት የማይታሰብ ነበር፡፡ እድሜ ለላዳ ታክሲዎች፡፡ መላ ፈጠሩ፡፡ ሜክሲኮ ጋ የላዳ ወያሎች ‹‹ጀሞ በላዳ- ጀሞ በላዳ›› እያሉ ይጣራሉ፡፡ ብቻ ተንቀባሮ መሳፈር የለም፡፡ 4 ሰዎች እያንዳንዳቸው 25 ብር ከፍለው ወደ ዞሮ መግቢያቸው ይከንፋሉ፡፡ ወደሚያፈሰው ኮንዶምንየማቸው፡፡ ሊወድቅ እንደሚችል የሚገመተው ኮንዶሚንየማቸው፡፡
መገናኛ ብዙ ሕዝብ ይሰለፋል፡፡ ሲመሽ ጦር ሜዳ ነው፡፡ ሰሚት ኮንዶሚንየም አንድ 10ሺ ሕዝብ ይኖራል፡፡ በምን ይሳፈር? ላዳዎች ይደርሱለታል፡፡ ‹‹ኮንዶምንየም በላዳ!›› እያሉ ይጣራሉ፡፡ የግድ ቤቱ ማደር ያለበት ሰው 25 ብር በነፍስ ወከፍ እየከፈለ ተሸማቆ ይሳፈራል፡፡ ተሳፋሪው ላይ ተመሳሳይ ስሜት ይታያል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ አምስት ኮከብ ሆቴል ምሳ የተጋበዘ ይመስል ቁልጭ ቁልጭ…
ክቡራትና ክቡራን የጦማሬ ተሳፋሪዎች!
በሸገር የሚገርመው ነገር እየበዛ ከመምጣቱ የተነሳ በቅርቡ መገረም እንዳይቀር እሰጋለሁ፡፡ ለምሳሌ በዶዘር አፈር ስለማሰው የወረገኑ ሕዝብ ላውጋችሁ፡፡
የወረገኑ ነዋሪ ለዓመታት ለአሸዋ በተሰሩ ሲኖትራኮች እየተጫነ ቤቱ ይገባ ነበር፡፡ እናቶች ሲኖው ላይ ለመውጣት ሲሉ ቀሚሳቸው እየተተረተረ ተሸማቀዋል፡፡ ልጆች እንደወታደር ክፍት መኪና ላይ ሲጫኑ አልቅሰዋል፡፡ ይህ ዕለታዊ ትራጄዲ ነበር፡፡ የወረገኑ ሕዝብ የአፍሪካ መዲና እምብርት ዉስጥ እየኖረ በጋሪ ይሳፈር ነበር፡፡ አማሮ ግን አያውቅም፡፡ ትራንስፖርቱ ከዛሬ ነገ ይሻሻልልኛል ብሎ ሲጠብቅ ጭራሽ ከቤቱ ነቀሉት፡፡ እንደ ሰው ሳይሆን እንደሚስማር ነው የነቀሉት፡፡ የወረገኑ ሕጻናት ትምህርት ቤት ደርሰው ወደቤት ሲመለሱ ቤታቸው ፈርሶ ጠበቃቸው፡፡ እንዴት እንደሚደነግጡ ማሰብ በራሱ የማል፡፡
ይሄ ሕገወጥ የሆነ መንግሥት ‹‹ሕገ ወጥ ግንባታ›› ሲል አለማፈሩ፡፡ ሕዝብ ሕገወጥነትን ከማን ተማረ! የመሬት ወረራን ማን አስጀመረ! ብቻ ተውት፡፡ አሁን ወረገኑ የነ ጄኔራል እንቶኔ የጎልፍ መጫወቻ ለመሆን ዲዛይን እየተሠራላት ነው፡፡ ለነዋሪዎቹ አውቶቡስ ማቀበል የተሳነው መንግሥት ከሰሞኑ ለአፍቃሪ ጎልፍ ጄኔራሎቹ የጎልፍ መኪና ግዢ ይፈጽማል፡፡
ዉድ የአገር ሰው ጦማር ታዳሚዎች!
ዉሌን እንዳልስት እርዱኝ፡፡ ትራንሰፖርት በሸገር ትናንት ዛሬና ነገ የሚል ነበር የዛሬው ወጋችን፡፡
እናቴ የአልጋ ልብስ ዕቁብ ገብታ አውቃለሁ፡፡ ሻል ያለ ገቢ ያላቸው የአሁን ጊዜ እናቶች የመኪና ዕቁብ ለመግባት ተገደዋል፡፡ቅንጦት እንዳይመስላችሁ፡፡ ተቸግረው፡፡ ምን ያድርጉ፡፡ ልጃቸውን ከትምህርት ቤት ለማውጣት ታክሲ ሲጠብቁ ይመሻል፡፡ ትምህርት ቤት ያለችው ልጃቸው በመሐሉ ትራባለች፡፡ ትጠማለች፡፡ ታለቅሳለች፡፡ እናቶች ሲጨንቃቸው ዕቁብ ገቡ፡፡ ለመኪና፡፡
በተለይ በመያዶች ዉስጥ የሚሠሩ ሻል ያለ ገቢ የሚያገኙ ሴቶች የመኪና ዕቁብ አባላት ሆነው አቶዝ እየሸመቱ ነው፡፡ ዕቁቡ የደረሳት ሴት በርሷ መስመር የሚኖሩ ዕቁብተኞችን ከቤት ስትወጣ የማድረስ፣ ወደ ቤት ስትመለስ የመሸኘት የሕሊና ግዴታ ይጣልባታል፡፡ ነዳጅ እየተጋገዙ መሙላት የተለመደ ነው፡፡ ይህ የትራንስፖርት ሕመም የፈጠረው ሻል ያለ ገቢ ባላቸው የሸገር ሴቶች አእምሮ የተመታ መላ ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ መንግሥት የመታቸው መላዎች ሁሉ ግን ከሽፈዋል፡፡ ባቡሩ የትራንሰፖትርት ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈቶታል የሚለው ፕሮፓጋንዳ እንዳሮጌ ጎማ ተንፍሷል፡፡ ባቡሩ ከማለዳ እስከ ምሽት የሰው ሰርዲን አጭቆ ሰሜን-ደቡብ፣ ምሥራቅ ምዕራብ ይመላለሳል፡፡ ሰው ግን ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም፡፡ ፐብሊክ ባሶች ለጥቂት መሥሪያ ቤቶች ካልሆነ ለብዙኃኑ የፈየዱት ነገር የለም፡፡ መንገድ ሲያጨናንቁ እንጂ ችግር ሲፈቱ አልታዩም፡፡ የኦሮሚያ ታርጋን የለጠፉ ድጋፍ ሰጪ ታክሲዎች በያቅጣጫው ዉር ዉር ይላሉ፡፡ ዉቅያኖስን በሾርባ ማንኪያ ሆኖባቸዋል፡፡ በግንቦት 20 ሥራ የጀመረው ሸገር አውቶቡስ ‹‹መልኬ በቃኝ›› ሆኖ ቀርቷል፡፡ ገና ሥራ ከመጀመሩ ሁለት የከፉ የትራፊክ አደጋዎችን ያስተናገደው ‹‹ሸገር ባስ›› በመከላከያ ኢንጂነሪንግ በለብ ለብ ሲመረት የፍሬን ችግር ሳያጋጥመው አልቀረም፡፡
የመከላከያ ቢሾፍቱ አውቶቡሶች የከተማ አውቶቡሶችን ቀለም ተለቅልቀው በገፍ ወደ ሥራ ቢገቡም ወር ሠርተው ወገቤን ይላሉ፡፡ ተደጋጋሚ የትራፊክ አደጋዎችን በማድረስም ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም፡፡ ተረግመዋል መሰለኝ ቶሎ ይገረጅፋሉ፡፡ ከሆላንድ የሚመጣው ዳፍ አውቶቡስ ደርግን አገልግሎ ኢህአዴግን አስቀጥሏል፡፡ የሥርዓቶቹ መመሳሰል እንዳለ ሆኖ ዘመን ተሻጋሪነቱን ግን የሚደነቅ ነው፡፡ ትናንትና የተመረቱት ቢሾፍቱ ባሶች ግን ሥርዓት ቀርቶ የአድዋ ድልድይን መሻገር ተስኗቸዋል፡፡
ዉድ የዚህ ጦማር ታዳሚዎች!
እውነት አላችኋለሁ በዛሬዋ ሸገር መኪና ከቅንጦትነት ወጥቶ መሠረታዊ ቁስ ሆኗል፡፡ ኬክ ሳይሆን ዳቦ ሆኗል፡፡ በከተሜነት የመዝለቅ ሕልውና የሚወሰነው ተሸከርካሪን ይዞ በመገኘት ሆኗል፡፡ መኪና የገዛ ትዳሩ ይሰምርለታል፡፡ በታክሲ ምክንያት ትዳር እየተናጋ ነው፡፡ ባል ያመሻል፤ ሚስት ታመሻለች፡፡ ንፋስ ይገባል፤ ትዳር ይፈርሳል፡፡
የተሸከርካሪን አስፈላጊነት ተረድተዋል፤ ወላ ባንኮች- ወላ ፕሮጀክቶች፡፡ የመኪና ብድር ተስፋፍቷል፡፡ ዘመን ባንክ ጥሩ ደመወዝተኞችን ለመኪና መግዣ ያበድራል፡፡ በረዥም ጊዜ ክፍያና በሚቆነጥጥ የወለድ መጠን፡፡ ንግድ ባንክ ቆጥቡና መኪና ልሸልማችሁ ይላል፡፡ ዘመን ባንክ ጥሩ ብር ቆጥቡና ከሃይሌ ገብረስላሴ ሱቅ ጥሩ ሀዩንዳይ መኪና ገዝቼ ልሸልማችሁ ይላል፡፡ ሁሉም ባንኮች መኪኖቹን በአብይ ቅርንጫፎቻቸው በር ላይ ላስቲክ አልብሰው አቁመዋቸዋል፡፡ እግረኛውና የታክሲ ሰልፈኛው በደጃቸው ባለፈ ባገደመ ቁጥር ላሀጩን ያዝረክርካል፡፡
የመኪና ሎቶሪ ተበራክቷል፡፡ ከግድቡ ጀምሮ እስከ አርበኞች ማኅበር ድረስ የከተሜውን ስስ ብልት ተሸከርካሪ እንደሆነ ተረድተው ‹‹መኪና እንሸልማለን›› እያሉ በየሰኮንዱ 3 -3 ብር ይገፈግፉታል፡፡ ሕዝቡ በሥራ ተስፋ ቆርጦ በሎቶሪ ተስፋ ያደርጋል፡፡ የአንድ ሕዝብ መውደቅ የሚጀምረው ደግሞ ያኔ ነው፡፡ በዕድል ያመነ ለት፡፡
በሙሔ ሀዘን ጨርቆስ- ለዋዜማ ራዲዮ
Leave a Reply