ገና ቁጭ እንዳልኩኝ
ቀጥሮኝ እንዳገኘኝ
እከሌ ጨርሶ «ሰው አይደለም!» አለኝ
ምነው? ምን አ’ረገህ ?
«ሰው አይደለም!» ስልህ
እኮ! ምን አ’ረገህ?
«ሰው አይደለም!» አልኩህ።
ቢራችንን አዘን
በዝምታ ቆየን
እንደገና ደግሞ ሳሉን እየሳለ
አንገቱን ነቅንቆ «ሰው አይደለም!» አለ።
ሰው ይመስላል አልኩኝ
ስሜቱን ልረዳ ፊቱን መረመርኩኝ
ባ’ይኑ እየገረፈኝ
አይምሰልህ! አለኝ
ግንባሩ ታጠፈ ጥርሶቹን ነከሰ
ጠረጴዛ መታ፣ ቢራችን ፈሰሰ
ልጠራርግ መጥታ – ልጅት እያየችኝ
በፊቷ ምልክት ምን ሆኗል? አለችኝ
መዳፌን አሳየሁ፣ ከንፈሬን አስረዘምኩ
እኔም ልክ እንደሷው በምልክት መለስኩ
እሱ ግን ቀጠለ «ሰው አይደለም» ማለት
«ሰው አይደለም!» አልኩኝ እኔም ተመቸሁት
በቢራ ተራጨን በውስኪ ታጠብን
ስሙን እያነሳን «ሰው አይደለም!» አልን።
ልጅትም ጠጋ አለች
«ሰው አይደለም!» አለች
መሀላችን ሆና ቢራ ተጋበዘች
ሌላውም ሰማና «ሰው አይደለም!» ያዘ
ጋባዤ ደስ አለው ሁሉንም ጋበዘ
ሲጋራ እየማገ ሳሉን እየሳለ
እንደገና ደግሞ «ሰው አይደለም!» አለ
ከአፉ ተቀብለን «ሰው አይደለም!» አልን
ስሙን አወገዝን ሰው መሆኑን ሻርን
አመጣው መአቱን አጋዥ ሲበዛለት
በሀሜት ቢለዋ አረደው እንደከብት
እኛም በየተራ ቆርጠን ዘለዘልነው
በቢራ እያማግን ስጋውን በላነው።
የማታ የማታ ሲመሽ ወደ ማታ
ሻርፑን አንጠልጥሎ በጥቁር ካፖርታ
«ሰው አይደለም! ያልነው» ከኛ ጋር ሊጠጣ
መልኩን አሳምሮ ሰው ሆኖ ቢመጣ
«ሰው አይደለም!» ብሎ ሲናደድ የዋለው
ገና ከበራፉ መግባቱን እንዳየው
ተወርውሮ ሄዶ አነቀና ሳመው።
****
Leave a Reply