ጌታቸው ረዳና መሰል የህወሓት ጁንታዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ከ40 በላይ ተሽከርካሪዎችና የግል ሰነዶቻቸው መያዛቸው ተገለጸ።
የጁንታው ቃል አቀባይ የሆነው ጌታቸው ረዳና መሰሎቹ ከመከላከያ ሰራዊት የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ለማምለጥ ሲጠቀሙባቸው የነበሩት እነዚሁ ተሽከርካሪዎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ቁጥጥር ስር መግባታቸውን የ32ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋዬ አስታውቀዋል።
እንደ ኮሎኔል ደጀኔ ገለጻ፤ ተሽከርካሪዎቹ የተያዙት ከማይጨው 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዴላ ወረዳ ነው።
ተሽከርካሪዎቹ ውስጥ በተደረገው ፍተሻም የከሀዲው ቡድን አመራር አባላት መታወቂያ፣ ፓስፖርትና የተለያዩ የግል ሰነዶቻቸው መገኘታቸውን ኮሎኔል ደጀኔ አስታውቀዋል።
የግል ሰነድ ከተገኘባቸው የጁንታው አባላት መካከል የቀድሞው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት እንደሚጠቀሱ ኮሎኔል ደጀኔ ተናግረዋል።
ከተያዙት ተሽከርካሪዎች ውስጥ እጅግ ዘመናዊና በአሻራ የሚከፈቱም እንዳሉበት ኮሎኔሉ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት ፍተኛ ድጋፍ እንዳለው ገልጸው፤ በተለይም ከ10 ሺህ ህዝብ በላይ በማይጨው ስታዲየም ሰብስበው የማረጋጋት እና የማወያየት ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚሁ ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት ጁንታው በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲያደርገው ለነበረው መፍጨርጨር ከመንግስት ሰራተኞች የወር ደመወዝ ላይ በመቁረጥ ለሚሊሻውና ለታጣቂዎቹ ደመወዝ ይከፍል እንደነበር ህዝቡ በምሬት መናገሩን ኮሎኔሉ አስታውቀዋል።
ነዋሪዎቹ አሁን ይህ በመቅረቱ መደሰታቸውን እንደገለጹላቸው ኮሎኔሉ ተናግረዋል።
ህዝቡ እንደ ስልክና መብራት ያሉ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን መንግስት በፍጥነት እንዲመልስላቸው ማንሳታቸውን ገልጸው፤ በመንግስት በኩል እየተደረገ ባለው ርብርብ እስከ ኮረም ያለው ጥያቄ መልስ ማግኘቱንና በቀጣይም የተቀሩት ከተሞች ጥያቄ እንደሚመለስ አስታውቀዋል። (በእያሱ መሰለ፤ ኢፕድ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
አቡሃይ ታከለ says
ዴላ ወረዳ ከማይጨው ከተማ ወደ የት አቅጣጫ ነው የሚገኘው? ጁንታው መኪና እያሽከረከረ ወደ ማይጨው አካባቢስ እንዴት ሊመጣ ቻለ? አሁን ተደብቆበታል እየተባለ ወደ ሚነገረው ተንቤን ቆላማ አካባቢዎችስ እንዴት ሄደ? እንደሚገባኝ ከሆነ ከማይጨው እስከ ተንቤን እጅግ በጣም እሩቅ ነው። ግልጽ አይደለም። እኔ እንደሚመስለኝና ጁንታው አምልጧል።