በዓለምአቀፍ የአሸባሪዎች ቋት በሽብርተኝነት እስካሁን ተመዝግቦ የሚገኘውና በትግራይ መሽጎ የተቀመጠው ህወሓት የተሰኘው የበረሃ ወንበዴዎች ቡድን ነገ ለሚደረገው የፌዴሬሽን ምክርቤት ስብሰባ አጀንዳ ካልተላከልኝ አልሰበሰብም በማለት ነሐሴ 27 ቀን 2012 ዓ.ም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጻፈው ደብዳቤ አስታውቆ ነበር።
ከዚህ በመቀጠል ደግሞ አገር አስገንጣይ በረኸኞቹ የተከማቹበት ምክርቤቱ በትግራይ ክልል ሊካሄድ የታሰበውን ምርጫ ለማስቆም በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚተላለፍ ማንኛውም ውሳኔ ጦርነት አዋጅ እንደሚቆጥረው ባወጣው መግለጫ አስታውቋ። ከአሃዱ ሬዲዮና ከቢቢሲ አማርኛ ያወጡትን ዘገባ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበናል።
መግለጫው የወጣው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከቀናት በፊት ነገ ቅዳሜ የሚካሄድ አስቸኳይ ስብሰባን መጥራቱን አስመልክቶ ነው።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለአባላቱ ባስተላለፈው ጥሪ ላይ 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ አስቸኳይ ስብሰባ ነሐሴ 30/2012 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከማሳወቅ ውጪ በምን አጀንዳ ላይ ውይይት እንደሚካሄድ የገለጸው ነገር ባይኖርም፤ የትግራይ ክልል ሥራ አስፈጻሚ በክልሉ በሚካሄድ ምርጫ ላይ የሚሰጥን ውሳኔ እንደማይቀበለው ከወዲሁ አሳውቋል።
የክልሉ ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ የፌደሬሽን ምክር ቤት የጠራውን አስቸኳይ ስብሰባ “ያልተለመደና አጀንዳው የማይታወቅ” ሲል ቢጠቅሰውም በትግራይ የሚካሄደው ምርጫን የሚመለከቱ ውሳኔዎች ሊተላለፉ እንደሚችሉ ባስቀመጣቸው ሃሳቦች አመልክቷል።
የሥራ አስፈጻሚው መግለጫ እንዳለው “ምርጫውን ለማስቆም ወይም ለማደናቀፍ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወስደው ማናቸውም ውሳኔ እንደጦርነት አዋጅ ይቆጠራል” ከማለቱ በተጨማሪ “በዚህ ምክንያት ለሚፈጠር ችግር ተጠያቂው የፌዴሬሽን ምክር ቤትና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል” ሲል ብሏል።
በዚህም ምርጫውን ለማስቆም የሚተላለፍ ውሳኔ ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ “ሕዝቡ በምርጫ የሚያስተዳድረውን አካል እንዲመርጥ ሊበረታታ የገባዋል እንጂ ይህን ሂደት ለማስቆም የሚደረግ ጥረት ፀረ ዲሞክራሲያዊ” መሆኑን አመልክቷል።
መግለጫው በትግራይ ክልል ስድስተኛው ዙር ምርጫ ጊዜውን ጠብቆ እንዲካሄድ ከወራት በፊት ውሳኔ መተላለፉን አስታውሶ፤ ይህንንም ለማሳካት በክልሉ ያሉት የሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን እያከናወኑ በመሆናቸው ክልሉ በምርጫው “ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ በሕዝብ ውሳኔ መሰረት ቀጣዩ የክልሉ መንግሥት የሚቋቋም ይሆናል” ብሏል።
ቀደም ሲል የትግራይ ክልል ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች በተለየ ምርጫውን በተናጠል ለመካሄድ መወሰኑን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህ ውሳኔ ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ ክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ከሚያደረገው እንቅስቃሴ እንደቆጠብ አሳስቦ ነበር። ክልሉም ይህንን በመቃወም ምላሽ ሰጥቶ ምርጫውን በማካሄድ ገፍቶ ለምርጫው ከአንድ ሳምንት ያነሰ ጊዜ ቀርቷል።
ሐሙስ ምሽት የወጣው መግለጫ ሕዝቡን በማሳተፍ ለሁሉም ግልጽ በሆነ ሁኔታ ምርጫውን ለማካሄድ ወደ ፍጻሜው መደረሱን ጠቅሶ በዚህ ጊዜ የሚደረግ ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት “በአገሪቱ ህልውና ላይ አደጋን የሚጥል መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ሲል አስጠንቅቋል።
በዚህም መሰረት ምርጫው በአገሪቱና በክልሉ ሕግ መሰረት የሚካሄድ በመሆኑ በማንኛውም ጣልቃ ገብነትና ጫና ሂደቱ እንደማይቆም አመልክቶ “ሕዝቡም ይህንን ለመመከት እንዲዘጋጅ” ጥሪ ከማቅረቡ በተጨማሪ የአገሪቱ “ብሔር ብሔረሰቦችና ፌደራሊስት ኃይሎች” ከጎኑ እንዲቆሙ ጠይቋል።
በመላው አገሪቱ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ በሕዝብ ተወካዮች እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢወሰንም የትግራይ ክልል ምርጫውን በተናጠል ለማካሄድ ወስኖ ጳጉሜ 04/2012 ዓ.ም ለማካሄድ ተዘጋጅቷል።
ይህንን በተመለከተም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም የሚያሳስብ ደብዳቤ ለክልሉ መጻፉ ይታወሳል።
ምክር ቤቱ በዚህ ደብዳቤው ላይ እንዳመለከተው የትግራይ ክልል የተሰጠውን ማሳሰቢያ ሳይቀበል ቀርቶ “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል” ድርጊቱ የሚገፋ ከሆነ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት “በሕገ መንግሥቱና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር እንደሚገደድ” አስጠንቅቆ ነበር።
ለዚህም የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በሰጡት ምላሽ የደረሳቸው ማስጠንቀቂያ ሕገ መንግሥታዊ መሰረት የሌለው መሆኑን በመግለጽ “የሕገ መንግሥት መርሆዎችን የሚጥስ፣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትነትን የሚጻረር” በመሆኑ የትግራይ ክልል መንግሥትና ሕዝብ እንደሚቃወሙት ገልፀው እንደማይቀበሉት አሳውቀዋል።
በክልሉ የታቀደው ምርጫ ሊካሄድ ቀናት የቀሩት ሲሆን አጀንዳው ምን እንደሆነ እስካሁን ያልታወቀ አስቸኳይ ስብሰባ የፌዴሬሽን ምክርቤት ለማካሄድ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው የትግራይ ክልል ይህንን መግለጫ ያወጣው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply