ከትህነግ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው የሰራዊት አባላት ላይ ከ8 ዓመት እስከ 18 ዓመት የሚደርስ የፅኑ እስራት ውሳኔ ተላለፈ።
የደቡብ ዕዝ ቀዳማዊ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በተለያዩ ወንጀሎች ተሳትፎ በነበራችውና ከትህነግ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው የሰራዊት አባላት ላይ ከ8 ዓመት እስከ 18 ዓመት በሚደርስ የፅኑ እስራት ውሳኔ ማስተላለፉ ተገለፀ።
ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም በዕዙ ጠቅላይ መምሪያ በዋለው ችሎት የተሰየመው የዳኞች ምድብ 8 የክስ መዝገቦችን መርምሮ ነው ውሳኔ የሰጠው።
በዚህ መሰረት፣
በ1ኛ መዝገብ እነ ኮሎኔል ካህሱ ሀብቱ ፀልይ፣ ኮሎኔል ሀጎስ አሰፋ ወልደንጉሴ እና ሌተናል ኮሎኔል ሀይላይ ገብሩ ገብረተክላይ
በ2ኛ መዝገብ ሻምበል ባሻ ክፍሌ ፍስሃ
በ3ኛ መዝገብ ኮሎኔል ክፍሌ ፍስሃ
በ4ኛ መዝገብ ሃምሳ አለቃ መብርሃቱ ጥላየ
በ5ኛ መዝገብ መሰረታዊ ወታደር መኮነን ክንፈ
በ6ኛ መዝገብ ሃምሳ አለቃ ፈረደ ይባስ
በ7ኛ መዝገብ ምክትል አስር አለቃ ሀጎስ በርሄ
በ8ኛ መዝገብ ምክትል አስር አለቃ ክፍሌ ንጉሴ የክስ መዝገባቸው እንዲታይ መደረጉም ታውቋል።
በዚህ መሰረት በ1ኛ መዝገብ ክሳቸው ሲታይ የነበረው እነ ኮሎኔል ካህሱ ሀብቱ ፀልይ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ሰራዊቱ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በግዳጅ ላይ ተሰማርቶ እያለ የትግርኛ ተናጋሪ የሰራዊት አባላትን ብቻ ነጥሎ በመሰብሰብ ከተቋሙ የአመራር እርከን ውጪ ለጥፋት ስራዎች የሚያግዝ አደረጃጀት ፈጥረዋል ተብሏል።
በዚህ አደረጃጀት በመታገዝም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ድርጊት በሚመሯቸው የሰራዊት አባላት ዘንድ ለመድገም አቅደው ሲሰሩ መቆየታቸው በክስ መዝገባቸው ሰፍሯል።
ተከሳሾቹ ከእነሱ ብሄር ውጪ አብረዋቸው የሚሰሩ ከፍተኛ አመራሮችን በመግደል ሙሉ ሰራዊቱን ወደትግራይ ይዘው ለመግባት አቅደው እንደነበርም በችሎቱ ተነስቷል።
በተለይም የህግ ማስከበር ዘመቻው እንደተጀመረ የትግራይ ተወላጅ የሰራዊት አባላት ወደ አንድ ማዕከል መሰብሰባቸውን ተከትሎ ተከሳሾቹ የተመደቡላቸውን ጥበቃዎች በመግደልና ወደ ኬኒያ በመውጣት ኤምባሲ ሄደው የትግራይ ህዝብ እየተበደለ ነው በማለት የሃገራቸውን ስምና ዝና ለማጉደፍ ሲሰሩ ነበር ብሏል ችሎቱ ።
በቀሩት 7 መዝገቦች የታዩት የሰራዊት አባላት ሰራዊቱን ወደትግራይ ልዩ ሃይል በመመልመል፣ የሽብር ወሬዎችን በመንዛት፣ ተቋሙን በሚያፈርሱ ተግባራት ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን፣ በህጋዊ ፍቃድ ሽፋን የትግራይን ልዩ ሃይል የሚያሰለጥኑ አባላትን ወደቦታው በመላክ፣ በሰራዊቱ ውስጥ አንድነት እንዳይኖር ስጋቶችን በማስፈን፣ በህቡዕ ተደራጅቶ ሰራዊቱን ለማፍረስ በመጣር እና መላው የሰራዊት አባል በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚያደርጉ ተግባራትን በሰፊው ሲተገብሩ መቆየታቸው በችሎቱ ተጠቅሷል።
በዚህ መሰረት የግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤት የአቃቤ ህግን የቅጣት ማክበጃ እንዲሁም የተከላካይ ጠበቃን የቅጣት ማቅለያ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከሳሾችን ያስተምራል፣ ሌሎች የሰራዊት አባላትን ያስጠነቅቃል በሚል ከ8 ዓመት እስከ 18 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል ሲል ኢቢሲ ዘግቧል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply