የኦሮሚያን ክልል በውክልና የሚያስተዳድረው ኦህዴድ አቶ መለስ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ውስጥ ውስጡን ሲንተከተክ የቆየው የድርጅቱ “የመስመር” ችግር ይፋ መሆኑን ተከትሎ በተፈጠረ ስጋት የኦሮሚያ ልዩ የፖሊስ ተወርዋሪ ሃይል እንደ ቀድሞው እንደማይታመን ተጠቆመ።
ሲቪል ሆነው በብርጋዴር ጀኔራልነት ስውር ማዕረግ የኦሮሚያን ፖሊስ ሲመሩ የነበሩት አቶ ደምመላሽ ገብረሚካኤል የፌዴራል ፖሊስ የማዕከላዊ መረጃና የወንጀል ኢንተለጀንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነርነት ቢዛወሩም አሻራቸው ኦሮሚያ ፖሊስ ውስጥ እንዳለ የሚጠቁሙት የጎልጉል ምንጮች፤ ክልሉ በፌዴራል ፖሊስ ደረጃ ያዋቀረው ተወርዋሪ ሃይል እየተደረገበት ያለው ክትትል ጥርጣሬው ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። አቶ ደምመላሽ አሁን በፌዴራል ደረጃ ያላቸው ኃላፊነት ቀድሞ በኦሮሚያ ከነበራቸው ሥልጣን ጋር ተዳምሮ የተወርዋሪው ልዩ ኃይል ጥርስ ውስጥ መግባት ዋና ተጠቃሽ መሆኑ ተገልጾዋል፡፡
የወደፊት እቅዱ ምን እንደሆነ ያላስታወቀው የፖሊስ አመራር በኦሮሚያ ለጎልጉል ዘጋቢ በሰጠው መረጃ “እንጠረጠራለን፣ ነጻነት የለንም፣ ወገናችን ላይ እርምጃ እንድንወስድ እንገደዳለን፣ ችግር ሲከሰት ‘የማያዳግም እርምጃ አልወሰዳችሁም’ በሚል እንገመገማለን” ሲል በአባላቱ መካከል ያለው መሰላቸት መስፋቱን አመልክቷል።
በተለያዩ የክልሉ እስር ቤቶች በርካታ ወገኖቻቸው በስመ ኦነግነትና በሃይማኖት ሰበብ መታሰራቸውን ያመለከተው ይሄው አመራር “ችግሩ እየሰፋ የሄደው ኦህዴድ ውስጥ የነበረው መከፋፈል ይፋ ከወጣ በኋላ ነው” ይላል። በየቀኑ የጸጥታ ሪፖርትና መረጃ ትንተና በሚል ግለሰቦችን መከታተልና ማሳደድ ላይ ያተኮረ ስራ እንደሚሰሩም አስታውቋል።
በከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉት የኦህዴድ አመራሮች ለህወሃት ስጋት እንዳልሆኑ የጠቆመው የኦሮሚያ ፖሊስ ልዩ ሃይል፣ አሁን የተከሰተው ልዩነት ከመካከለኛ ደረጃ አንስቶ እስከ ቀበሌ መዋቅርና በተዋረድ እስከ ዝቅተኛው ካድሬ ድረስ መውረዱ ችግሩን ከቀድሞው በተለየ አክብዶታል ይላል።
“ኦሮሚያን ራሱን ችሎ ለማስተዳደር ኦህዴድ ብቁ ነው” የሚሉት ክፍሎች በከፍተኛ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውና በማክረር ፖለቲካ ህወሃት በተደጋጋሚ እንደሚከሰው ለሌሎች ብሄረሰቦች ስጋት አለመሆናቸውን አባሉ ይናገራሉ። ጉዳዩ ቅስቀሳ እንዳይመስል በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “ከጁነዲን ሳዶ በኋላ በተዋቀረው የአባዱላ ካቢኔ ውስጥ የተካተቱት የበታችና የመካከለኛ ደረጃ አመራሮች ቀደም ሲል በአመለካከት ተፈርጀው የተገፉ ነበሩ። በኋላ ላይ አቋማቸውን በማስተካከልና ጊዜው እስኪደርስ ክልላችንን እያለማን እንቆይ በሚል አስተሳሰብ ኦህዴድን የተቀላቀሉ ናቸው” ሲል አስተያየቱን ያሰፍራል።
በከፍተኛ ደረጃ ያሉት አመራሮች በአብዛኛው በሙስና መጨመላለቃቸው ድርጅቱን ሽባ እንዳደረገው የማይሸሽገው የፖሊስ አመራር “ሁሉም ራሳቸውን ስለሚያውቁ ከዛሬ ነገ በሙስና ወንጀል እንከሰሳለን በሚል ስጋት ውስጥ መውደቃቸው ችግሩን ካላለዘበው በስተቀር ኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረው ግለት በቀላሉ የሚቀዘቅዝ አይሆንም” ይላል። በሌላ በኩል ደግሞ ኦሮሚያ ውስጥ ከጥቅም ጋር በተያያዘ አብዛኛው የህወሃት፣ የፌዴራል ፖሊስና የደህንነት ሃይሎች መነካካታቸው ስለሙስና በማንሳት እውነተኛ ግምገማ ከተነሳ መጫረሱ አስቀድሞ ሊከሰት እንደሚችል ያስረዳል። በማያያዝም በተለያዩ መድረኮች እስከ ገጠር ድረስ ከህዝቡ ጋር ሲወያዩ የሚቀርበው አቤቱታ እየከፋ መሄዱን ጠቁሟል።
“ድሮ ‘ደም መጣጭ በሽታ’ ሲባል አርሶ አደሩ ‘ወባ’ ይል ነበር” ይላል የፖሊስ ልዩ ሃይል አመራር። አሁን ግን ይህ ተቀይሯል። “ደም የሚመጥ በሽታ” ተብለው ሲጠየቁ መልሳቸውን የሚጀምሩት ያወጡትን ደረጃ በማስቀደም ነው። “ደም መጣጭ በሽታ አንደኛ ሙስና፣ ሁለተኛ ኤች አይ ቪ – ኤድስ፣ ሶስተኛ የወባ ትንኝ” እንደሆነ ነው። በክልሉ ያለው ሙስና እንዳማረራቸው በየጊዜው እንደሚናገሩና ከመንግሥት ፍትህ እንደሚፈልጉ ሪፖርት ቢያቀርቡም ምንም ምላሽ እንደማይሰጥ አውስቷል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ልዩ ሃይል አመራሮችና አባላት ውስጥ ቅሬታ እንዳለ ያልሸሸገው የጎልጉል ቀጥተኛ ምንጭ፤ የህወሃት ሰዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች፣ ኦሮምኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ የህወሃት ሰዎች በመካከላቸው መኖራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሩን እንዳባባሰው አመልክቷል። “ፖሊስ ባለው መረጃ መሰረት ኦህዴድ ስንት ቦታ ተከፍሏል?” በሚል ለተጠየቀው “ይህ የደህንነቱ ስራ ነው። ግን ማንም እንደሚያወቀው የህወሃት አገልጋይ ኦህዴዶች (ህወሃት/ኦህዴዶች)፣ ኦህዴድ ራሱን መቻል አለበት የሚሉ ኦህዴዶችና ሚዛን አይተው ለመወሰን የተቀመጡ አሉ” ሲል መልስ ሰንዝሯል። የመጀመሪያው ሃሳብ አራማጆች እስከታችኛው የቀበሌ መዋቅር ድረስ ተቀባይነት አላቸው። ግን ውስጥ ውስጡን በጓደኛሞች መካከል የሚወራ እንጂ ይፋ የወጣ ነገር አይደለም።
በድብቅ የብርጋዴር ጀኔራል ሹመት በመያዝ የክልሉን ፖሊስ ከጀርባ ሆነው ሲመሩ የነበሩት አቶ ደምመላሽና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ሁለቱም ሻሸመኔ አንድ መደብ ላይ የተገኙ ሲሆን አሁን አብረው በአንድ ተቋም የሚያገለግሉ ህወሃት/ኦህዴዶች መሆናቸው ይታወቃል።
ስማቸውን ሳይጠቅስ ድምጻቸው ለጥንቃቄ እንዲጎተት ተደርጎ በአሜሪካ ሬድዮ ኦሮሚኛ ክፍለ ጊዜ የቀረቡት የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ኦህዴድ ለሁለት መከፈሉን፣ እነሱም በህወሃት የሚመሩና ድርጅቱ ራሱን ችሎ መሄድ አለበት በሚሉ መካከል እንደሆነና ልዩነቱም ሰፊ መሆኑን ተናግረዋል።
“ከፍተኛ መባላት ተፈጥሯል” ሲሉ የተፈጠረውን አለመግባባት ስም ያወጡለት የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ጁነዲን ሳዶ ከባለቤታቸው ጋር በተያያዘ ብቻ ከፓርቲው አመራርነታቸው መወገዳቸውን ያስረዱት የኦህዴድ ሰው “የኢህዴግን ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ በማክበር የአቶ ሃይለማርያምን ሹመት መቀበል ይገባናል” በሚሉትና “የምርጫው አካሄድና ጥቆማ ትክክል አይደለም” በሚሉት መካከል የተፈጠረው ልዩነት አልተፈታም ይላሉ።
አቶ በረከትና አቶ ሃይለማርያም የመለስ የቅርብ ሰዎች እንደነበሩ የተናገሩት እኚሁ የኦህዴድ ሰው፤ አቶ መለስ ወደ ውጪ ሲወጡ ቁልፍ የሚሰጡት ለአቶ በረከት እንደሆነና የአቶ ሃይለማርያም ሹመት መነሻውም ቀደም ሲል በተፈጠረ “የቤተሰብ መሰል” ግንኙነት እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። አቶ መለስ በሞቱ ማግስት ከኢህአዴግ ምክርቤት እና ከፓርላማው ውሳኔ በፊት አቶ ሃይለማርያም ጠ/ሚ/ር ሆነው እንደሚቀጥሉ በመናገር በወቅቱ የተጠባባቂ ጠ/ሚ/ርነት ሥልጣን ይዘው እንደሚሠሩ አቶ በረከት በወቅቱ በሰጡት ቃለምልልስ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡ አቶ ሃይለማርያም ለፎርማሊቲ በፓርላማ ፊት ቀርበው ምህላ እንደሚፈጽሙ አቶ በረከት በግላቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይህንኑ ቤተሰባዊ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የኦህዴድ ሊቀመንበር አቶ አለማየሁ አቶምሳ ስብሰባ ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ስራ እንደማይሳተፉና ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሳይሰይም የተቀመጠው በህወሃት ጫና የተነሳ መሆኑንን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ ለቪኦኤ ከተናገሩት ለመረዳት ተችሏል። ጋዜጠኛ ነሞ ዳንዲ ያናገራቸው ሰው በትክክል የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል መሆናቸውን መረጋገጡና ለጥንቃቄ ሲባል ድምጻቸው እንዲሻክርና እንዲጎተት መደረጉን አስታውቋል።
ኦክቶበር 18/2012 የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም ንጉሴ ወልደሐና በሰጡት ምላሽ በድርጅቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለ ተናግረዋል። የጎልጉል ድረገጽ ጋዜጣ አስቀድሞ የዘገበውንና የሰንደቅ ጋዜጣ ለንባብ ያበቃውን የኦህዴድ የመከፋፈል በሽታ አስመልክቶ ሸምጥጠው ክደዋል።
አቶ አብርሃም ስማቸውን ሳይገልጹ የተናገሩትን አባል አስመልክቶ በግልጽ መናገር እንደሚችሉና፣ በድርጅቱ ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ የቆየ ባህል አንዳለ ተናግረዋል። በድርጅት ውስጥ መነጋገር፣ መከራከርና በሃሳብ ያለመግባባት እንደሚኖር ያወሱት አቶ አብርሃም በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ የድርጅታቸውንና የክልላቸውን እቅድ በማብራራት የተሰጣቸውን ጊዜ ወስደውታል።
ጎልጉል የኦህዴድን የመስመር መሳት ግምገማና “ይቅርታ የሌለው የመደብ ትግል ግምገማ” አስመልክቶ ሰፊ ዘገባ አስነብቦ ነበር። በወቅቱ የመደብ ትግል በአንድ ድርጅት ውስጥ ከተጀመረ መጫረስ ተጀመረ ማለት እንደሆነ መዘገባችንም አይዘነጋም።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
Anoolewako says
Ammas yoom iyyu tanaan bilisummaa!