የትኛው ኦነግ ስለየትኛው ኦነግ መግለጫም ይሁን ተቃውሞ እንደሚሰጥ ግራ እስኪያጋባ የደረሰው ዕድሜ ጠገቡ ኦነግ ተከፋፍሎ አላልቅ ብሎ አሁን ደግሞ አንዱ በአንዱ ላይ ዕርምጃ እወስዳለሁ እያለ ነው። ኢትዮ ኤፍ ኤም ያጠናከረው ዘገባ እንዲህ ይነበባል።
ኦነግ ከፖርቲው ህግና ስርአት ባፈነገጠ መልኩ በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን አሳሳች መግለጫዎችን ሲሰጡ በነበሩ አመራሮቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።
የኦነግ ቃላ አቀባይ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት የተወሰኑ ሰዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን በመቅረብ አላስፈላጊ መግለጫዎችንና መልዕክት በማስተላለፋቸው ምክንያት በተፈጠረ ውዝግብ ላይ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በጠቅላላ ጉባኤ በዲሲፕሊን እንዲጠየቁ የሚያስችል ውይይት ማድረጉን ተናግረዋል።
በተለያዩ መገናኛ ብዙሀን በአመራሮች መካከል የርዕዮተ አለም ልዩነት እንዳለ የሚነገረው ትክክል አለመሆኑንም አቶ ቀጀላ ተናግረዋል፡፡
ይህ አይነት ነገር እንዲፈጠር ባደረጉት አመራሮች ላይ ግን የዲሲፕሊን እርምጃ እንደሚወሰድ ነግረውናል፡፡
ቀደም ብሎ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት መጋቢት ላይ ባደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ቀጣዩ ጉባኤ የፊታችን ታህሳስ 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ በመወሰኑ ይህም ጉዳይ በዚህ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ቀርቦ እንደሚታይ ነግረውናል፡፡
ከዚያ በፊት ግን ብሔራዊ ምክር ቤቱ ተሰብስቦ አሁን የተፈጠሩትን ጉዳዩች በመመልከት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ለጠቅላላ ጉባኤው ያቀርባል ብለዋል፡፡
የዲሲፕሊን እርምጃው የሚወሰድባቸው አመራሮች እነማን ናቸው? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ዝርዝር ጉዳዮች በውስጥ ጉዳይ የተያዙ በመሆናቸው መናገር አልችልም ብለውናል።
ኦነግ በአመራሮቹ መካከል የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት ያለመ ውይይት ታዛቢዎች ባሉበት ማካሄዱ ይታወሳል። (በያይኔአበባ ሻምበል፥ Ethio FM 107.8)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply