ህግ ያልገዛውን ሀይል ይገዛዋል
ዛሬ ጦርነቱ ግልፅ ሆኗል። ኦፌኮ መንግሥትን ምንም አታመጣም እስኪ የምታደርገውን አይሃለሁ እያለው ነው። ኦቦ መረራ በስተርጅና ዋልታ ረገጥ ሆነው ፈንድተዋል። ሀይማኖት ውስጥ ያሸመቁ መናፍቃን ባደባባይ ፖለቲካውን ተቀላቅለዋል። ነውጠኛው ጃዋር ራሱን እንደ አሜባ አራብቷል። ጦርነቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ብቻ ላይ አይደለም ያጠነጠነው የሀገሪቱን መሰረት የመፈነቃቀል ስትራቴጂ ፊት ለፊት አንግቦ እንጂ።
ይህ ሀገር ላይ የተመዘዘ ሰይፍ የቱንም እምነት አይምርም። ሀገር ሳለች ነው እምነት፣ ክብርም፣ ራሱ መኖርም። ማንም ራሱን ካላሞኘ በስተቀር፣ ሁሉም በሰላም በማይኖርባት አገር ውስጥ የብቻዬን የሰላም ደሴት እፈጥራለሁ ሊል የሚቻለው አይደለም። እነሆ ዛሬ አንዳች ስውር፣ አንዳች ያልተገለጠ ምስጢር የለም። ዕቅዱ በገሀድ መተግበር ጀምሯል።
የባንዲራ መቃጠል፣ መረገጥና መዋረድ ሀገሪቱን ሊገጥማት ከሚችለው አደጋ አኳያ እየተስተዋለ ይሰጠው የነበረው አፀፋ እጅግ የለዘበ ነበር። ይህ አስተውሎና ሀላፊነት የተሞላው እሳቤ የነውጠኞችን ልብ ከማሳበጥና የአሸናፊነት ስነልቦናን እንዲጎናፀፉ ከማድረግ በቀር አንዳች ሲፈይድ አልታየም።
ዘለግ ብሎ ላሰበው ይቺ ሰንደቅ የተቀዳችው ከማርያም መቀነት ነው መባሉ የልዩነት ብሎም የመካረር ምክንያት ባልሆነ ነበር። እናታችን ማርያም በሁሉም ሀይማኖቶች ቅድስት ነችና። ቀስተዳመናም ቢሆን ለሁላችን አንድ በሆነው ሰማይ ላይ የሚዘረጋ፣ ላይናችን ትሩፋት፣ ለልባችን ትፍስህት የሆነ የፈጣሪ ድንቅ ጥበብ ነበር። አሁን ማ ይሙት ሰማዩ በቀስተዳመና ጥለት ሲጎናፀፍ ተመልክቶ ሀሴት የማያደርግ ሰብአዊ ፍጡር ለመሆኑ ማን ይሆን?
ጎበዝ ነገሩ ሁሉ እንዳይጥም እንዳይጥም እየሆነ ነው። እስኪ አሁን ይቺ መከረኛ ቤተክርስቲያን ማንን አሳልማ ነው ማንን የነፈገችው? እውን ለብርሀኑ የተዘረጋ መስቀል ለመረራ ታጠፈ? እስኪ አሁን መራራን የትኛው ካህን፣ የትኛው ደብር ነው መስቀል እንዳይሳለሙ ያቀባቸው?
ሰማእቱ አባታች ብፁእ አቡነ ጴጥሮስ “ምነው ኢትዮጵያን ጨከንሽባት፣ ምነው መቀነትሽን ታብቂባባት” አሉ እንጂ የት ጋር ነው ኦሮሚያ የሚል ቃል ካንደበታቸው የወጣው? ከነከሳት መርዝ ልቅመስ በፈጃት እቶን ልንደድላት ያሉት ለእምዬ ኢትዮጵያ እንጂ ለኦሮሚያ ነበርን?
አገር ከፈረሰ፣ እምነት ከተፋለሰ በኋላ ምን ላይ ተቆሞ ነው ዴሞክራሲውስ የሚገነባው፣ ፍትሁስ የሚበየነው? መንግስት ባለበት ሀገረመንግስት ባደባባይ የምፅአት ቀን ሲታወጅ ለማን አቤት ይሏል።
የኦሮሚያ ፖለቲካ የመናፍቃን ዋሻ ሆኗል። የአክራሪዎች ሰይፍ በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ ተመዟል። ሸዋ በራሱ ቤተክርስቲያን ላይ ጦር እንዲሰብቅ ክተት ተብሏል። ክርስቲያን በክርስቲያን ላይ እንዲነሳ ነጋሪት ተጎስሟል። የገብረጉራቻ ህዝብ አባት አያቱ በደም ሳይቀር፣ በነብስ ሳይቀር የተዋጁላትን እምነቱን እንድትዋረድ፣ እንድትመክን የጃዋር አበጋዝ የእርኩሰት መነባንቡን ሲያዝረበርብ ተስተውሏል። ደብረሊባኖስ በፅንፈኞች መዳፍ ስር እንድትወድቅ በፒኮሎው ጃዋር በኩል ቄሮና ቀሬ ክተቱ ተብለዋል። ይህ እየሆነ ያለው ኦፌኮ በሚዘውረው፣ ጃዋር በሚሾፍረው የአክራሪዎች ጎራ ነው።
እዚህ ከተደረሰ ቀጣዩን ለመተንበይ ጠንቋይ መሆን አያስፈልግም። ካህናትን እረዱ፣ ምእመናንን ጨፍጭፉ፣ አብያተ ክርስቲያናትን አቃጥሉ መባሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።
እቺ ቤተክርስቲያን ጠላቶቿ ተበራክቷል። ከከፍታዋ ለማውረድ፣ ክብሯን ለመናድ፣ ህልውናዋን ለማጥፋት ረጅም፣ በጣም ረጅም መንገድ ተኬዷል።
መላው የእስልምናም፣ የፕሮቴስታንትም ሆነ የዋቄፌታ አማኞች ከዚች ግፉእ ቤተክርስቲያን ጎን ልትቆሙ ይገባል። የአንዱ መኖር ለሌላው ዋስትና እንጂ ጠር አይደለም። ካንዱ በደል ሌላው ቢያጎል እንጂ አይከስብም።
ቤተክርስቲያንም ብትሆን ምእመኑን ከአመፅ ማቀቧ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአመፅ በመለስ ባሉ ማናቸውም ተቃውሞዎች ጎምዘዝ ኮምጨጭ ማለት አለባት። አባቶች የጀመሩትን እስኪጨርሱ ድረስ መዘናጋት የለባቸውም። ስሜት ሲንር ጠብቆ የሚፈነዳ፣ አንዴ ቦግ አንዴ እልም የሚል ሳይሆን ግብ ሳይደርስ የማይቆም ትግል ያስፈልጋል። ፅንፈኞች የሚዘሯቸው መርዞች በህግ አግባብ እየተነቀሱ በሰላማዊ መንገድ ለህግ አስፈፃሚ አካላት እንዲቀርቡ ሊደረግ ይገባል።
የፖለቲካ ድርጅቶችም ከትርምስ ለማትረፍ፣ ጠላትን ለመቀጥቀጥና ሌላ ፅንፍ ለማደራጀት ከመጠቀም ይልቅ መንግስት ላይ ጠንካራ ተፅእኖ በማሳረፍ፣ ለምርጫ ቦርድ የተሰነዱ መረጃዎችን በማቅረብ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግም በነዚህ ወንጀለኞች ላይ ክስ እንዲመሰረት ለማድረግ በዚህና በዚህ መሰል እውነቶች ላይ አንድነት ልትፈጥሩ ይገባል። ለምርጫ ቦርድም እንዲህ አይነት አካሄዶችን በዝምታ ማለፍ ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶችን ማስከተሉ አይቀርምና፣ አሁን ያልተወሰደ እርምጃ ለወደፊቱ በሚደረጉ ተመሳሳይ ድርጊቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ የሞራል ልእልናን ያሳጣልና፣ ጠንከር ያለ ህጋዊ እሮምጃ መውሰድ የጊዜው አይታለፍ ጥያቄ ነው።
መንግስት እንደመንግሥት መከበር፣ መታፈር አለበት። መንግሥት እንደ መንግሥት መከበርና መታፈር ካልቻለ የሚዋረደው ህዝብ ነው፣ የሚደፈረው ሀገር ነው። ስለዚህ ለህግ አንገዛም ላለ ሞገደኛ ሀይል ጉልበት አማራጭ ሆኖ ሊገራው ይገባል። ያለችን አንድ ሀገር ናት፣ ልንኮራባትና ልንታበይባት ሲገባን እስከመቼ ተሸማቀንና ተሸምቀን እንኑርባት። እስከመቼ ባበጡ ተረኞች አንገታችን ይሰበር፣ ልባችንስ እንክት ይበል። መረጥንህም አልመረጥንህም ሀገራችን በእጅህ ናትና ትጠብቃት ትታደጋት ዘንድ ግዴታም አደራም አለብህና ኢትዮጲያ ከነውጠኞች ከአክራሪዎች ፍላፃ ጠብቃት። ጉልበት ለጉልበተኞች ግድ ነው። ህግ ያልገዛውን ሀይል ይገዛዋል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Leave a Reply