በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምሮ በርካታ ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ውሎ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለሕዝብ ተደራሽ እንዲደረግ ምክር ሐሳብ ቀረበ።
የፍርድ ቤት ውሎ በቀጥታ ሥርጭት ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆንና ሌሎች አማራጮችን ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው፣ የኢፌዴሪ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ነው።
በተቋሙ ዋና እንባ ጠባቂ እንዳለ ኃይሌ (ዶ/ር) ተፈርሞ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተላከው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ ለዳኞችና ዓቃቢያነ ሕግ፣ ለተጠርጣሪዎችና ለችሎት ታዳሚዎች ደኅንነትና ጥበቃ አመቺ በሆነ ሰፊ አዳራሽ ችሎት ማስቻልን የመጀመርያ አማራጭ አድርጓል። የፍርድ ቤቱን ውሎ ሁሉም የመንግሥትና የግል፣ የሕትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ አካላት ብቻ እንዲዘግቡት ማድረግና በዘገባዎቻቸው የችሎቱን የምርመራ ሥራ በሚያውኩ ወይም በሚያደናቅፉ፣ የችሎቱን ነፃነትና ገለልተኛነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ በሚያደርጉ ትክክለኛ ያልሆነ ዘገባን በማያሠራጩት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ በመውሰድ ለሕዝብ ሚዛኑን የጠበቀ መረጃ እንዲቀርብ ተቋሙ ሁለተኛ አማራጭ አድርጎ አቅርቧል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን በአንድ ወገን በመንግሥትና በግል የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን በሌላ በኩል በመንግሥትና በግል የሕትመት መገናኛ ብዙኃን መካከል የጨረታ ውድድር አድርጎ፣ አሸናፊው ሚዲያ በቀጥታ ሥርጭት የፍርድ ቤት ውሎ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲደረግ ሦስተኛ ምክረ ሐሳቡን አቅርቧል። በችሎት ተገኝተው የፍርድ ቤት ውሎን መከታተል ለሚፈልጉም ደግሞ በፕላዝማ ቴሌቪዥን ተደራሽ ማድረግም ሌላው አማራጭ መሆኑንም እንባ ጠባቂ ተቋም አክሏል።
የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ስለዴሞክራሲ ሥርዓት አሠራር እንዳብራራው፣ ግልጽ የሆነ የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገለጫ ነው። ግልጽ የሥልጣን ክፍፍል ባለባቸው ዴሞክራሲያዊ አገሮች ደግሞ ነፃነቱ የተጠበቀ፣ የግልጽነትና የተያቂነት አሠራር የተላበሰ የዳኝነት አካል (ፍርድ ቤት) መኖር፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት እንደ ቁልፍ መሣሪያ ተደርጎ እንደሚቆጠር ጠቁሟል። የፍርድ ቤቶች የግልጽነትና የተጠያቂነት መገለጫ ተደርገው ከሚወሰዱት መካከል፣ በግልጽ ችሎት ማስቻልና በምክንያት የተደገፉ ውሳኔዎችን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ መሆኑንም ገልጿል። ከመዝገብ መክፈት እስከ ፍርድ አፈጻጸም ያለው የፍርድ ቤቶች የዳኝነት አሰጣጥ አሠራር፣ በአደባባይ በግልጽ ችሎት የሚከናወን መሆኑን ከማንኛውም ተቋም በላይ በባህሪው፣ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት የተጋለጠ ተቋም እንደሚያደርገውም አክሏል።
በሕገ መንግሥቱ እንደተመለከተው ፍርድ ቤቶች ከሦስቱ የመንግሥት አካላት አንዱ መሆኑን ያስታወሰው እንባ ጠባቂ ተቋም፣ በዜጎች ላይ ሊወሰን የሚገባን ጉዳይ ለነፃና ገለልተኛ ፍርድ ቤት የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት፣ የፍርድ ቤቶችን የፍርድ ሒደትና ውሳኔ አስመልክቶ መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማሠራጨት ነፃነት፣ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጠ መሆኑን ጠቁሟል። ፍርድ ቤቶችም ሕግ የመተርጎም ኃላፊነታቸውን ከማንኛውም የመንግሥት አካል፣ ባለሥልጣንም ይሁን ወገን ጫናና ተፅዕኖ ነፃ ሆነው በተከራካሪ ወገኖች የሚነሱ፣ የሕግና ፍሬ ነገር ክርክሮችን፣ ሕግንና ሕግን ብቻ መሠረት አድርገው፣ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት ለሆነው ሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድና በተጠያቂነት መንፈስ የማከናወን ተቋማዊና የሙያ ኃላፊነት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቷል።
የፍርድ ቤቶች የፍርድ ሒደት እንዴትና በምን አግባብ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መልኩ መከናወን እንዳለበት፣ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና በመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ እንዲሁም በወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች በግልጽ መደንገጉን ተቋሙ አስታውሷል። የተጠርጣሪ የወንጀል ክስና የፍርድ ሒደትን አስመልክቶ መረጃን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፣ የወንጀል ክሱን የሚያሰናክል፣ ፍትሕን የሚያጨናግፍ፣ የፍርድ ሒደቱን ሚዛናዊነት ወይም ገለልተኛነት የሚያዛባ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም መረጃ ለሕዝብ ሊቀርብ እንደሚገባ ተናግሯል። ለሕዝብ፣ ለሰላምና ፀጥታ አስጊ ወይም ለሕዝብ መልካም ፀባይ ወይም ግብረገብነት አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም የፍርድ ሒደትና የፍሬ ነገር ክርክር ለማንኛውም ሰው ግልጽ በሆነ ችሎት መታየት እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ (21) እና በአዋጅ ቁጥር 25/1988 አንቀጽ (25 እና 26) መደንገጉንም ተቋሙ አስታውቋል።
ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲወስን፣ ሊወስን የሚገባውን የሕግና የፍሬ ነገር ክርክርና የፍርድ ሒደትን ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የማስቻል መሠረታዊ ዓላማ፣ በውስን ክልከላና በሰፊ ግልፀኝነት መርህ፣ የፍርድ ቤቶችን የፍርድ ሒደትና ውሳኔ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የማግኘትና የማሠራጨት መብትን ተግባራዊነት፣ የችሎቱ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ የፍርድ ሒደት ላይ የሕዝብን የመወሰን አቅም ማጎልበት መሆኑንም ተቋሙ አስታውቋል። የወንጀል ጉዳይ የፍርድ ሒደት በግልጽ ችሎት ማስቻል ወንጀል ያልፈጸሙ ሌሎች ዜጎች ከመሰል የወንጀል ድርጊት እንዲቆጠቡ በማስተማር ረገድ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አክሏል። በአጠቃላይ የፍርድ ሒደት በግልጽነትና ተጠያቂነት ስለመከናወኑ ለሕዝብ መረጃ በማቅረብ ነፃና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙኃን የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዙም እንባ ጠባቂ ተቋም ገልጿል።
በግልጽ የፍርድ ቤቶች አሠራርና ተጠያቂነት ወይም መረጃ የማግኘትና የማሠራጨት መብት ተጠቅሞ የችሎትን ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሐዊ የፍርድ ሒደትን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ አደጋ ላይ መጣል የተከለከለ መሆኑን ጠቁሞ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በንግግር፣ በሕትመት ወይም በሌላ መንገድ ችሎቶችን ወይም የፍርድ ሒደትን ካወከ ወይም በሌላ ካደናቀፈ በወንጀል ሕግ አንቀጽ ከ449 እስከ አንቀጽ 451 ለተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆንም አስታውቋል።
የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ምክንያት በማድረግ በደረሰው የሕይወትና የንብረት ውድመት ተጠርጥረው ታዋቂ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ጉዳያቸው በግልጽ ችሎት እየተካሄደ መሆኑን የጠቆመው እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ነገር ግን አንዳንድ ተጠርጣሪዎች የችሎት ውሎን ለመዘገብ በፍርድ ቤት የሚገኙት የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ብቻ መሆናቸውን እየገለጹ መሆኑን ተናግሯል። እነሱም ለሕዝብ ይፋ የሚያደርጉት መረጃ የመርማሪ ፖሊስን የምርመራ ውጤትና የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ብቻ መሆኑንና ይህም ሚዛናዊነት የጎደለው ዘገባ መሆኑን መግለጻቸውን አክሏል። በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ የችሎቱን ውሎ የሚዘግቡና የሚፈልጓቸው ሚዲያዎች እንዲገቡ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ለፍርድ ቤቱ ቅሬታ ማቅረባቸውንም ተቋሙ ገልጿል። የድምፃዊውን ግድያ ተከትሎ በአንዳንድ የክልል ከተሞች በደረሰው የሰውና የንብረት ጉዳት፣ በርካታ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ አመራሮችና አባላቶች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መታሰራቸውን አስታውሶ፣ ድርጊቱ ተራ ወንጀል ሳይሆን በተቀነባበረ መንገድ አገርን ለማፍረስ፣ አንድነትን ለመበታተንና የሕዝቦችን አብሮነት አደጋ ላይ ለመጣል የተፈጸመ ከባድ ወንጀልና ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሆኑን በሁሉም ሚዲያ ለሕዝብ ጆሮ እንዲደርስ መደረጉንም ተቋሙ አብራርቷል።
ከፖሊስ የምርመራ ውጤት ጀምሮ ያለውን የፍርድ ሒደትና የመጨረሻ ውሳኔ በችሎት በአካል ተገኝቶ መከታተል፣ መዘገብና ሚዛናዊ መረጃ እንዲቀርብለት የሚፈልገው ዜጋ ቁጥር እጅግ በጣም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል መሆኑንም ተቋሙ ጠቁሟል። ከወቅታዊው የኮሮና ችግርና የማስቻያ አዳራሽ ችግር አንፃር ፍርድ ቤቶች በችሎት ተገኝቶ የፍርድ ቤቱን ውሎ ለመከታተል የሚፈልገውን ሁሉ ማስተናገድ እንደሚከብድና እንደማይቻል ተቋሙ እንደሚረዳ ጠቁሞ፣ የሰጣቸውን ምክረ ሐሳቦች (አማራጮች) በመጠቀም ፍርድ ቤቱ እንዲያስተካክል ጠይቋል። የችሎት ውሎ ሒደት ከሳሽና ተከሳሽ ለችሎቱ የሚያቀርቡትን በማስረጃ የተደገፈ ክርክር፣ ዳኞች በችሎት የሚሰጡትን ትዕዛዝና ውሳኔ እንደሚያካትት ገልጾ፣ ሚዛናዊ መረጃ የማግኘትና የማሠራጨት ነፃነት በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለምና በዜግነት ልዩነት ሳይደረግ ለማንኛውም ሕጋዊ ሰው የተሰጠ ሕገ መንግሥታዊና የተፈጥሮ ሕግ መሆኑን አስረድቷል። በመሆኑም የችሎቱን ውሎ ሊዘግቡ ፍርድ ቤት የተገኙትን ገሚሶቹን ከልክሎ ገሚሶቹን ማስገባት በሰዎች መካከል ሕጋዊ ያልሆነ ልዩነት እንዲፈጠር ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠር፣ በችሎትም አሠራር ላይ የነፃነትና ገለልተኛነት ጥያቄ እንዳያስነሳ ፍርድ ቤቱ በትኩረት ሊያጤነው እንደሚገባ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳስቧል። (ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር)
Leave a Reply