በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ወደ ጎንደር አቅንተዉ ነበር፡፡ በደመቀ መኮንንና በገዱ አንዳርጋቸዉ የተመራዉ ከፍተኛ አመራር ቡድን ሦስት ዋናዋና ቁልፍ ተልዕዎኮችን ለማሳካት ከባህርዳር እንደተንቀሳቀሰ የጎልጉል ድረገጽ ጋዜጣ የብአዴን ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ አንደኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመራዘሙን አስፈላጊነት ለህዝብ ለማሳመን፤ ሁለተኛ የነጻነት ኃይሎች በሀገር ሽማግሌዎች አደራዳሪነት ከአገዛዙ ጋር ዕርቅ እንዲያወርዱ ከሚያስችሉ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ለመምከር፤ በሦስተኛ ደረጃ የተያዘዉ ተልዕኮ አብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ በአማራና በትግራይ ህዝብ መካከል የተፈጠረዉን ቅራኔ በኃይማኖት አባቶች የምኩራብ ስብከት አማካይነት እንዲበርድ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አቅጣጫ በሰሜን ጎንደር ዞን ሀገረ-ስብከት ሥር ላሉ አድባራት በአቡነ ኤልሳዕ በኩል መልዕክቱን ማድረስ የሚሉት ሦስት ጉዳዮች የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ወሳኝ ተልዕኮዎች ነበሩ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህወሓት/ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተገምግሞ አዋጁ በመሀል አገር፣ በደቡብና በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል እንደወትሮዉ ሁሉ አንጻራዊ ሰላም ቢሰፍንም፤ በሰሜን ምዕራብና በኦሮሚያ ከፊል ቦታዎች ሠላምና መረጋጋቱ በአደባባይ የሰፈነ ቢመስልም በሥራ አስፈጻሚዉ ግምገማ “አስተማማኝ” አለመሆኑ ታምኖበታል፡፡ በተለይም በሁለቱም ግዙፍ ክልሎች የጦር መሳሪያ ዝዉዉሩ እየጨመረ መሄዱ፤ በጎበዝ አለቆች የሚመሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም ከህወሃት/ኢህአዴግ ኃይሎች ጋር የደፈጣ ዉጊያ የሚያካሂዱ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለተጨማሪ ሦስት ወራት እንዲራዘም መደረጉ ይነገራል፡፡
ይህንን የህወሓት/ኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወሳኔ “በህዝብ ዉይይት” እንደዳበረና ይሁንታ እንደተሠጠ ለማስመሰል በጎንደር ከተማ “ህዝባዊ ስብሰባ” እንደተጠራ የሚገልጹት የጎልጉል የመረጃ ምንጮች፤ ስብሰባዉ የሰሜን ጎንደር ዞን ብአዴን ጽ/ቤት አዳራሽ የካቲት 13/2009ዓ.ም ረፋድ 4፡00 ሠዓት ላይ በብአዴን ከፍተኛ አመራሮች መሪነት ተካሂዷል፡፡
በስብሰባዉ ላይ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የዕርድ፣ ማህበራትና አደረጃጀት አመራሮች፣የሙያ ማህበር ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደሩና የክፍለ ከተማ የብአዴን መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል፡፡
በደመቀ መኮንን ንግግር የተከፈተዉ ይሄዉ ስብሰባ ገና ከጅምሩ የአጀንዳ መስመሩን የለቀቀ ነበር፡፡ “የጋለ ህዝባዊ ስሜት የተንጸባረቀበት ስብሰባ” እንደሆነ የሚጠቁሙት የመረጃ አቀባዮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመራዘሙን ጉዳይ በተመለከተ በስብሰባዉ ላይ የተገኙ አንድ የአገር ሽማግሌ የሰጡት አስተያየት የተሰብሳቢዎችን ልብ የነካ ነበር፤ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አነሳችሁት አላነሳችሁት ጎዳናዉ ላይ በጥይት የወደቁ ልጆቻችን ህይወት አይመልስም፤ እናንተም መግደላችሁን ላታቆሙ ለምን ታባብሉናላችሁ?” ያሉት የአገር ሽማግሌዉ ንግራቸዉን ሲጨርሱ “የደርግን መጨረሻ ማስታወስ ብልህነት ነዉ” ሲሉ ምክር አዘል ማስጠንቀቂያ ለግሰዋል፡፡
ከንግዱ ማህበረሰብ ተወክለዉ የተገኙት ታዋቂዉ የባህል ልብስ ነጋዴ ሐጅ ሐሰን አሊ “የከተማዋ የንግድ እንቅስቃሴ ማዕከል የሆነዉ ቅዳሜ ገበያ ምክንያቱ ዛሬም ድረስ ባልተገለጸልን ሁኔታ 446 ሱቆች በእሳት ቃጠሎ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡ በዚህ የተበሳጨ ነጋዴ ራሱን እንዳጠፋ እኔና የአካባቢዉ ሰዎች ምስክሮች ነን፤ ትዳር ፈርሷል፤ ልጆች ተበትነዋል፤ ጎንደር በቴሌቪዥን ዜና እንደሚነገርላት የተረጋጋች ከተማ አይደለችም፤ ማህበራዊ ቀዉሱ የከፋ ነዉ፤ ይሄን መላ ካላላችሁ ምኑ ላይ ነዉ መንግስትነታችሁ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ከኃይማኖት አባቶች ተወክለዉ ከተገኙት መካከል የፊት አቦ አቡነ አረጋዊ ደብር አለቃ የሆኑት አለቃ መኮንን ወልዱ በበኩላቸዉ “አሁን በልዑል እግዚአብሔር ሥም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡፡ ጎንደር በታሪኳ በደርቡሽ ወረራ ጊዜ አንድ ዘመን ብቻ ብርሃነ መስቀሉን በአደባባይ አላከበረችም፡፡ ከስንት እና ስንት ዘመናት በኋላ ዘንድሮ ጎንደር ላይ የመስቀል በዓል በአደባይ ሳይከበር ቀረ፡፡ እናስ እናንተን ከወራሪዉ ደርቡሽ ለይቶ ማየት ብንቸገር ትፈርዱብን ይሆን? የጥምቀት በዓልስ ቢሆን ከካህናቱ መስቀል በላይ ጠመንጃ አንጋቹ በዝቶብን ለክርስቶስ ከብር ዝቅ ብለን በዓለ ጥምቀቱን አከበርን፡፡ ሌላዉ ቢቀር አላፊ ነን ብላችሁ እንዴት ማሰብ ተሳናችሁ? ሁላችንም ስናልፍ የምንቀበርባትን ቤተክርስቲያን እንዲህ ፈተና ማብዛት በጎ አይደለም ልጆቼ” በማለት አባታዊ ግሳጼ እንደሰጡ የጎልጉል መረጃ ምንጮች ዘግበዋል፡፡
ስብሰባዉ በተደጋጋሚ “አካሄድ፣ ሥነ-ሥርዓት…” በሚሉ ቃላት በተደጋጋሚ ይቋረጥ እንደነበር የገለጹት ምንጮች የብአዴን መካከለኛ አመራሮች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸዉን ጥያቄዎች ለከፍተኛ አመራሩ አቅርበዋል፡፡
በተለይም ህዝባዊ አመጹ ከተነሳ ወዲህ ከመስከረም እስከ ጥር ድረስ በከተማዉ አራት መቶ ሃያ ስድስት ባዶ ቦታዎች የጨረቃ ቤት እንደተሰራባቸዉ፤ የሀሰት የሥም ንብረት ዝዉዉር በዉልና ማስረጃ በኩል እየተፈጸመ እንደሆነ፤ ከመንግስትና ከግል ተቀጣሪዎች ከሚሰበሰበዉ የገቢ ግብር ዉጪ የንግድ ግብር ይህ ነዉ በሚባል ደረጃ እንዳልተሰበሰበ፤ ሆቴሎች በቱሪስት እጦት ሠራተኞቻቸዉን ለመቀነስ እንደተገደዱ፤ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች በከፍለ ከተማና በከተማ አስተዳደሩ መካከለኛ አመራሮች በኩል “ከአቅም በላይ” ሆነዋል በሚል ለከፍተኛ አመራሩ ተጠይቋል፡፡
“ይህ ሁሉ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግር ሲደርስ አመራሩ የት ነበር?” የሚል ኃይለ ቃል የተናገረዉ ደመቀ መኮንን ሰሚ አልባ ስብከቱን ሲያሰማ እንደዋለ የምንጮቻችን ዘገባ ይጠቁማል፡፡
ከወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ያለዉን ጉዳይ፤ የአማራና የትግራይ ክልል ድንበር ማካለል ጉዳይ በተለይም የግጨዉ መሬት ጉዳይ አንዲሁም በእስር ላይ ያሉትን የማንነት ጥያቄ አስተባባሪዎችን የተመለከቱ ጥያቄዎች በስብሰባዉ ተሳታፊዎች በተደጋጋሚ የተነሱ ነበሩ፡፡
“የወልቃይት ጉዳይ በህዝበ ዉሳኔ እንዲወሰን የፌደራሉ መንግስት ከትግራይ ክልል ጋር በመተባበር በቅርቡ እንቅስቃሴ ይጀመራል፡፡ የክልል ድንበር ማካለሉን ጉዳይ እንደ ድርጅትም እንደ ክልልም በጋራ ለመስራት ሥራዎች ተጀምረዋል” ያለዉ ደመቀ መኮንን ንግግሩ በስብሰባዉ ተሳታፊዎች ጩኸት በተደጋጋሚ ለማቋረጥ ተገድዷል፡፡
“ህዝቡ እየጠየቀ ያለዉ እናንተ እንድትወርዱ ነዉ እንጂ የወልቃይት ጉዳይ በህዝበ ዉሳኔ እንዲፈታለት አይደለም፡፡ ደግሞስ የፌዴራሉ መንግስትና የትግራይ ክልል ምንድነዉ ልዩነታቸዉ? አማራነት በህዝበ ዉሳኔ አይነጠቅምም፤አይገኝምም” በሚሉ ኃይለ ቃላት ተቃዉሞዉን ያሰማዉ ወጣት ደሳለኝ ኃይሉ ከስብሰባዉ መጠናቀቅ በኋላ ምሽት 3፡00 ሠዓት ላይ ከመኖሪያቤቱ “በኮማንድ ፖስቱ ትፈለጋለህ” በሚል እንደተወሰደ የጎልጉል የአካባቢዉ ምንጮች አአስታውቀዋል፡፡
ስምምነት በሌለዉ መልኩ በተጠናቀቀዉ ስብሰባ፤ ተሳታፊዎች ባይቀበሉትም የሚከተሉት ዉሳኔዎች በከፍተኛ አመራሩ ለተሰብሳቢዎች ተገልጸዋል፡፡
አንደኛ የጎንደርና አካባቢዉ ሠላም በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመጋቢት 28/2009 አስከ ሰኔ28/2009 ድረስ ለተጨማሪ ሦስት ወራት እንደሚቀጥል፤
ሁለተኛ በየአካባቢዉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የከተማዋና የአካባቢዉ ነዋሪዎች ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ፣ የህገ ወጥ የጦር ማሳሪያ ዝዉዉር ለአካባቢዉ አለመረጋጋት የስጋት ምንጭ በመሆኑ በጋራ እንዲከላከሉ፤
ሦስተኛ የጎንደርና አካባቢዉ ህዝብ ከትግራይ ጋር ሠላማዊ ግንኙነት እንዲኖረዉ ይህንንም የኃይማኖት አባቶች ኃላፊነት እንዳለባቸዉ ተማጽኖ አዘል ዉሳኔ በንባብ አሰምተዋል፡፡
ገዱ አንዳርጋቸዉ በቀሰስተኝነት ስሜት “አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድማማች ህዝቦች…” የሚሉ ቃላትን እየደጋገመ ሲጠቀም በተስተዋለበት ስብሰባ፤የደመቀ መኮንን ንግግር በአንጻሩ ተደጋጋሚነት ባለዉ መልኩ በስብሰባዉ ታዳሚዎች ተቋርጧል፡፡ ይህም “የብአዴን መካከለኛ አመራሮች ከከፍተኛ አመራሩ ጋር ተናብበዉ መስራት እንዳቃታቸዉና የመዋቅር መሽመድመድ የታየበት የሽንፈት ስብሰባ ነበር” ሲሉ ስብሰባውን የተከታተሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል፡፡ ሁኔታውን ሥር ከሰደደ የአመራር ክሽፈት አንጻር የሚመለከቱ ግን “እነ ደመቀ በቅቷቸዋል፤ ብአዴን ደግሞ እንደ ድርጅት አከርካሪው ላይ ተቆርጧል” በማለት በመካከለኛና በከፍተኛ አመራሩ መካከል ያለውን ከፍተኛ አለመናበብ እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡
የጎንደሩ ህዝባዊ አመጽ ተራዛሚነት በጦር መሳሪያ ለማስቀጠል ከሚተጉ የነጻነት ኃይሎች መካከል በወገራ በኩል በተለይም አጅሬ፣ አምባ ጊዮርጊስና አንቃሽ አካባቢ ያሉት የነጻነት ኃይሎች በህዝቡ ጥላ ስር ታቅፈዉ ጥቃት ከማድረስ አልቦዘኑም፡፡ የነጻነት ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሽምግልናና ዕርቅን ጨምሮ ረዘም ያለ መንገድ ለመጓዝ የሞከሩት የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ሙከራቸዉ በተደጋጋሚ ከሽፏል፡፡ “ዕርቅና ሠላም የተባለው ሙከራ ከጀርባዉ ያዘለዉን ሸፍጥና ሴራ ቀድመዉ የተረዱት የነጻነት ኃይሎች ለሽምግልና የላኳቸዉ ሰዎች በተደጋጋሚ ተመልሰዋል” የሚሉ ወገኖች “የነጻነት ኃይሎች በራቸዉ ለዕርቅ ዝግ ነዉ” ሲሉ አስተያየታቸዉን ለጎልጉል ሰጥተዋል፡፡
“የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች እንደ ገና ዳቦ ከላይም ከታችም እሳት እየፈጃቸዉ ነዉ፡፡ ከላይ የህወሓት የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ጫና ከታች በኩል ደግሞ የህዝብ ዓይናችሁን ላፈር ባይነት በግልጽ ይታያል” የሚሉት ሌላኛዉ የጎልጉል አስተያየት ሰጪ “እሳቱን ለማጥፋት ብቸኛ አማራጭ ህዝባዊ ዝንባሌ ማሳየት” መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ሲቀጥሉም፤ “ዞረም ቀረም የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች እንደ ድርጅትም ሆነ እንደ ክልል እየመጣባቸዉ ያለዉን ህዝባዊ ተቃዉሞ ማስተንፈስ አልቻሉም፡፡ መካከለኛ አመራሮችም የግርግር ክፍተቶችን ተጠቅመዉ በመሬት ወረራ፣ በሀሰት ሥም ንብረት ዝዉዉርና በቀረጥና ግብር ተመን ላይ ይፋዊ ቅርምት ዉስጥ እንደ ገቡ እርስ በርሱ በሚጣረስ መልኩ በስብሰባዉ ላይ “ከአቅም በላይ ችግር” በሚል በራሳቸዉ አንደበት የራሳቸዉን ገመና መግለጻቸው የእነርሱን አለማፈር ብቻ ሳይሆን ድርጅቱ የማይወጣበት ቅርቃር ውስጥ መግባቱን” ያሳያል ብለዋል፡፡
የብአዴን የመዋቅር ወገብ እየተቆረጠ ለመሆኑ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ድርጅቱ “የኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የሥርዓቱ ጠንቅ ነዉ፤ በጋራ ልንታገለዉ ይገባል” በሚል መዋቅራዊ መሽመድመዱን ለመሸፋፈን ቢሞክርም ህዝብ ፊት እንደ ብአዴን፤ ድርጅታዊ አቋምን ማሳየት እንደ ተሳናቸዉ የጎንደሩ ስብሰባ አስረጅ ምሳሌ ነዉ፡፡
“እነዚህን የታሪክ አተላዎች ሙሉ በሙሉ ነቃቅሎ ለመጣል ጊዜዉ አሁን ነዉ” በሚሉና “የለም የብአዴንን መካከለኛ አመራሮችን አቅም ከነ መዋቅሩ ወደ ህዝባዊ ዝንባሌ መቀየር ይቻላል” በሚል ተስፋ ከመካከለኛ አመራሮች ጋር ግንኙነት መፍጠር የጀመሩ ወገኖች መኖራቸዉን የጎልጉል የመረጃ ምንጭ ዘገባ ያመለክታል፡፡
በወታደራዊ ዉጥረት ዉስጥ የምትገኘዉ ጎንደር ከተማ እንደተለመደዉ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮችን አሸማቃ አሰናብታለች፡፡ የህወሓት የበቀል ጅራፍ አብዝቶ የሚጎበኛት ጎንደር ጊዜ የሚነግረን ሀቅ ቢኖርም በእስካሁኑ ሂደት መከራዋን መሻገር ተስኗታል፡፡ እንደ ጎልጉል የመረጃ ምንጭ ነዋሪዎቿም ለአደባባዩ አመጽ ዝግጁ ይመስላሉ፡፡ ዳግማዊዉ አመጽ በቅርብ ጊዜ የሚፈጠር ከሆነ አመጹ በቀላሉ እንደማይገታ ይገመታል፡፡ ምናልባትም አመጹ እስከ እርስ በርስ ጦርነት እንደሚደርስ አስተያየት ሰጪዎች ስጋታቸዉን ይጠቁማሉ፡፡ የብአዴን አከርካሪ መቆረጥ ከኦህዴድ ተመሳሳይ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ ከተቻለ ህወሓትን ኅልውና እንደሚያሳጣው በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (https://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
dergu temelese says
ለወዝቶ አደሮች
ከአመዳሞች
ይብላኝ ለእናንተ ምርጥ ለምትበሉት፣
ይብላኝ ለእናንተ ውስኪ ለምትቀዱት፣
በአምስት አስራ እንድ በቁምሳ ስሌት፣
እኛማ እያለቅን በርሀብ እርዛት፣
በህይወት ከመኖር ይሻለናል ሞት፡፡
ቁርስ ለንደን በልታችሁ ምሳችሁ ናይሮቢ፣
እራት አዲስ- አባ በሼራተን ግቢ፣
ዓለምን ስትቀጩ ብርን ስትገድቡ፣
ለእኛ ጥፋት እንጂ ልማት አታስቡ፡፡
ወስኪ ጠጥታችሁ በቀል ስታገሱ፣
የድሀውን ድርሻ ስታግበሰብሱ፣
ሞትን ስትሸሹ ምስኪኑን ስትገድሉ፣
ያጣ ወንድማችሁን በጥይት ስትቆሉ፣
የህግ እስረኛውን በእሳት ስትቀቅሉ፣
ዝም ብሎ ሲያይ አይኖር ፈጣሪ ሀያሉ፣
የዘራችሀትን እናንተም ታጭዳላችሁ፣
አምላክ ዕድሜ ሰጥቶን ለማየት ያብቃችሁ፡፡
በአቅላችሁ ሆናችሁ በደሉን አስታውሱ፣
ድሀ ከመረረው አይሳሳም ለነፍሱ፣
ምኑ ሊቀርበት የምድሩ ህይወት፣
ተቆራምዶ አይኖርም ለእናንተ መውዛት፡፡