1. መግቢያ፣
አዲስ አበባ ብዙ ዋጋ ተከፍሎባታል ሲባል ነገር ለማጣፈጥ የተነገረ ወሬ ሳይሆን በተጨባጭ የሆነና የተደረገ መሆኑን እኔ በህይወቴ ያየሁትን እንዲት ገተመኝ እንደ ምሳሌ ልጥቀስ። ስሜ ደረጀ ተፈራ ይባላል ተወልጄ ያደኩት አዲስ አበባ ፊትበር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው። ሰፈራችን ለታላቁ ቤተመንግስት (ምኒልክ ቤ/መ) ቅርብ በመሆኑ የደርግ ቅልብ ወታደሮችም ሆኑ የወያኔ አጋዚ ጦር የአካባቢውን ጸጥታ ለማስከበር ብቻ ሳይሆን ኮረዶችንም ለማሽኮርመም እኛ ሰፈር አይጠፉም ነበር። በደርግም ሆነ በወያኔ አገዛዝ ዘመን አንድ ነገር ኮሽ ባለ ቁጥር ከቤተ መንግስት፣ የደርግ ቅልቦችና የወያኔ አጋዚ ጦር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር አና ከፓሊስ ገራዥ ደግሞ ፌዴራል ፖሊሶች ክላሻቸውን እያንቀጫቀጩ መጀመሪያ የሚመጡት እኛ ሰፈር ነበር። በዚህ ላይ ኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማ ወይም መለስ ዜናዊ ሊያልፉ ነው ከተባለ መንደራችን መግቢያ መውጫዋ ተዘግቶ በወታደር ትወጠራለች። በደርግ አገዛዝ ዘመን በነጭ ሽብርና በቀይ ሽብር ብዙ ሰው በየአደባባዩ ባለቀበት ወቅት ከሂልተን ሆቴል ፊትለፊት በሚገኘው የሰፈራችን መናፈሻ ውስጥ ኳስ እና አባሮሽ ስንጫወት በየዛፉ ስር በጥይት ተመተው የተገደሉ ወጣቶችን እናይ ነበር። በተለይ የሁለተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በህይወቴ የማልረሳው፣ እስካሁንም ድረስ አብዛኛው ታሪኩ በአዕምሮዬ ውስጥ ታትሞ የሚገኝ ነገር በመንደራችን ተከሰተ። ታሪኩ እንዲህ ነው፣ ቀኑን በትክክል ባላስታውሰውም ከትምህርት ቤት ተመልሼ ከሰዓት በኋላ ወደ 9 ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል። ሶስት የሰፈራችን ወጣቶች የ31 ቁጥር አውቶቡስ ማቆሚያ ፌርማታ አጠገብ ያለውን የጣውላ አጥር ተደግፈው እያወሩ ነበር። አንደኛው ወጣት ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ፣ ሁለተኛው ልጅ የ9ኛ ክፍል እና ሦስተኛው ደግሞ የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነበሩ። የአንደኛው ትንሽ ወንድም የእኛ እድሜ እኩያ ጓደኛችን ነው። ሲወራ እንደሰማሁት ከቤተ መንግስት ውስጥ የመጡ ሲቪል የለበሱ ሁለት ሰዎች በድንገት ወደ ቆሙት የሰፈራችን ወጣቶች በፍጥነት በመጠጋት ሽጉጣታቸውን አውጥተው ተኩስ ከፈቱባቸው። የ9ኛ ክፍል ተማሪ ያልኳችሁ ወጣት ጭንቅላቱን በመመታቱ ወዲያው ሲሞት፣ የ11ኛ ክፍል ተማሪው አንዱን ነፍሰ ገዳይ ገፍትሮ ነፍስ አውጪኝ ብሎ ቁልቁል ወደ መንደሩ ሮጠ፣ ሰውዬው ተከትሎት በመሮጥ የተኮሰው ጥይት ትከሻውን መታው ነገር ግን ጨክኖ በመሮጡ ነፍሱን አዳነ። የዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ የነበረው ወጣት ሌላኛው ነፍሰ ገዳይ ጆሮ ግንዱ ስር ተኩሶ ሲመታው በቁሙ ዝርግፍ ብሎ ወደቀ። ነፍሰ ገዳዮቹ ጊዜ ሳያጠፉ ከአካባቢው ተሰወሩ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪ ወጣቱ ፀጉሩ አፍሮና የለበሰው ጃኬት ጂንስ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፣ እንደ ታረደ እንስሳ ብዙ ደም ፈሰሰው፣ ነፍሱ ቶሎ ባትጣም አንድም ሰው መጥቶ ሊታደገው የሞከረ ግን አልነበረም። የረጋ ደሙ ላይ በአንድ ጎኑ ተኝቷል፣ እነዛ ትላልቅ አይኖቹን እየገለጠ አካባቢውን ይቃኝ ነበር፣ አንድ ጊዜ ከኔ ጋር ዓይን ለዓይን ተጋጨን፣ ደነገጥኩ፣ ልጅ እያለሁ ብዙ ጊዜ በህልሜ እየመጣ ከእንቅልፌ እባንን ነበር። የመንደራችንም ሰዎች ፈርተው ነው መሰለኝ እንደ ሌላው ጊዜ ቶሎ አልወጡም። እኛ ልጆች ስለሆንን እየተመላለስን የሚሆነውን እናያለን። ቀስ በቀስ ሰዎች እየተሰባሰቡ መጡ። አንድ ነጭ ቫን መኪና መጥቶ እሬሳቸውን ይዘው ሄዱ። ሰፈራችን ፊት በር አዘነች፣ ማቅ ለበሰች። ወደፊት ስናድግ፣ ትልቅ ስንሆን እንደነሱ ሃይ ስኩል እና ዩኒቨርስቲ ገብተን እንማራለን በማለት አርአያ ያደረግናቸው የሰፈራችን ወጣቶች ባጭር ተቀጩ። እኔ በሰፈሬ ያየሁትን ማንሳቴ የከተማው ነዋሪ የደረሰበትን እና ያሳለፈውን መከራ እንደ ምሳሌ ለማሳየት ያህል እንጂ በርካታ ተመሳሳይ ክስተቶች በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ይፈጸሙ ነበር።
በ1983 ዓ/ም ግንቦት 19 ለ 20 ንጋት ወያኔ አዲስ አበባ የገባ ሌሊት የወያኔ ግትልትል ሰራዊት በመንደራችን ውስጥ ሲተራመስ የነበረውን እስካሁን አስታውሰዋለሁ። በተለይ ንጋት ላይ የቤተ መንግስቱ ዋና በር (ፊትበር) ቆሞ የነበረ ታንክ ሲቃጠል ውስጡ የነበረ የT55 ሼል ፈንድቶ (ተፈናጥሮ) ጉማጁ እኛ ቤት የሳሎን በር ላይ ነበር ያረፈው። ያቺን የጭቃ ግድግዳና የእንጨት በር ብትንትኗን አወጣት። በ1997 ዓም ከምርጫው በኋላ በተፈጠረው ግርግር ደጇ ላይ ጨርቅ አንጥፋ ቲማትምና ሽንኩርት ትቸረችር የነበረች የአንዲት ምስኪን ሴት ልጅ በግምት እድሜው 15 የሚሆን ታዳጊ ወጣት በወያኔ አጋዚ ጦር በጥይት ጭንቅላቱን ተመቶ ሞቷል። በጣም የሚገርመው ልጁ በወያኔ ጥይት የተገለው ደርግ ከላይ የጠቀስኳቸው የሰፈራችን ወጣቶቹን ከረሸነበት የ31 ቁጥር የአውቶቢስ ፌርማታ ሃያ ሜትር አካባቢ በሚሆን ርቀት ላይ ነበር። እኔ በህይወቴ ባየሁት በደርግና በወያኔ/ ኢሃዴግ አምባገነን መንግስታት ብዙ አስፈሪና አስደንጋጭ ነገሮችን እኛ የፊትበር ነዋሪዎች አሳልፈናል። በመጨረሻም ሰፈራችንን አጥረው ከማስቀመጥ ውጪ ምንም ልማት ላይሰሩበት ሰፈሩን አፈራርሰው ነዋሪዎቹን በታተኑን። እናም ለኔ ለፊት በሩ ልጅ አዲስ አበባ በወያኔና በደርግ ጎረቤቶቼና የሰፈር ልጆቼ የተገደሉበት፣ በእስር፣ በዱላና በመሳሰለው የተሰቃዩባት፣ ከዛም ሌላ ደስታና ሃዘን ያሳለፍንባት፣ ኳስ ተጫውተን ያደግንባት፣ የተዳርኩባት፣ እትብቴ የተቀበረባት፣ … ሃገሬ ስትሆን ለጊንጪው ልጅ ለኦቦ ሽመልስ እና ለነስብሃት ነጋ ልጆች ግን አዲስ አበባ የምትታለብ ላም ነች።
2. የአዲስ አበባ ህዝብ ለከተማው የከፈለው ዋጋ (በትንሹ)፣
አዲስ አበባ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘቡን፣ እውቀቱን፣ ጉልበቱን፣ ጊዜውን አዋጥቶ በትውልድ ቅብብሎሽ የገነባት ከተማ ናት። በነፃም የተገኘች ሳትሆን ብዙዎች ዋጋ ከፍለውባታል። 6ኪሎ ቆሞ የሚታየው የሰማዕታት ሃውልትም ሆነ በቅርቡ ወደ ሙዚየምነት ተቀየረ የተባለው ማዕከላዊ እስር ቤት ህዝቡ በፋሽስቶችና በአምባገነኖች የደረሰበትን እንግልት፣ ሞትና ሰቆቃ የሚናገሩ ቋሚ ምስክሮች ናቸው። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ/ም ቁጥሩ ከ30 ሺህ በላይ የሚሆን የአዲስ አበባ ነዋሪ ህዝብ በግራዚያኒ ትዕዛዝ በአካፋ፣ በመጥረቢያና በጥይት ተጨፍጭፏል። ፋሽስቱ ግራዚያኒ የአዲስ አበባን ህዝብ ጃል ሜዳ ላይ ሰብስቦ ለነፃነታቸው የሚዋጉ የኢትዮጵያ አርበኞችን ከተማውን በጭለማ እየመጡ የሚያውኩ ሽፍቶች ናቸው በማለት ስማቸውን በማጥፋትና በመወንጀል ለእነሱ ስንቅ ያቀበለ፣ መረጃ የሰጠ፣ መንገድ ያሳየ የከተማው ነዋሪ ይገደላል፣ ንብረቱ ይወረሳል፣ በእሳት ይቃጠላል እያለ የአዲስ አበባን ህዝብ ሲያስፈራራና ሲደነፋ የሰሙት አቡነ ጴጥሮስ በአስተርጓሚ እንዲህ በማለት ለግራዚያኒ መልስ ሰጡት:- “ለመሆኑ ሽፍታው ማን ነው? የሰው ሃገር የወረረው ነው ወይስ ለሃገሩ ክብርና ነፃነት የሚሞተው? እነሱ ባለሃገሮችና ባለቤቶች ናቸው። ሽፍታው አንተ ነህና በሽፍትነት ከያዝካት ሃገር ለቀህ ውጣ!” በማለት በድፍረት ገሰፁት። በዚህ ንግግራቸው ግራዚያኒ በመበሳጨት አቡነ ጴጥሮስ እንዲታሰሩ አደረገ። እስር ቤት ሳሉ ግራዚያኒ ሰዎቹን ልኮ ቪላ ቤት፣ አውቶሞቢል መኪና እና የምትፈልገው ያህል ገንዘብ እሰጥሃለሁ ህዝቡ ለጣሊያን እንዲገዛ ስበክልኝ በማለት ሊያባብላቸው ሞከረ (ታከለ ኡማ እስክንድር ነጋን ከመታሰሩ በፊት አዲስ አበባን በተመለከተ እንስማማ V8 መኪናዬን እሰጥሃለው እንዳለው ተመስጌን ደሳለኝ በቅርቡ ፍትህ መፅሔት ላይ “አዲስ አቦ-ባ” በማለት አስነብቦናል)። አቡነ ጴጥሮስ በግራዚያኒ ማባበያ እንኳን ሊስማሙ ቀርቶ ጭራሽ በመቆጣት “ወገኖቼን፣ ሃይማኖቴን፣ ሃገሬን በገንዘብ አልሸጥም” በማለት “ህዝቡም መሬቱም ለጣሊያን እንዳይገዛ አውግዣለሁ” አሉ። በመጨረሻም አቡነ ጴጥሮስ በቆራጥነት እንዲህ አሉ – የሃገሬን እና የሃይማኖቴን ጠላት ጦር ወርውሬ ባልገድልም፣ በሞቴ ፈጣሪዬ ይበቀልልኛል በማለት እራሳቸውን ለመስዋዕትነት አሳልፈው ሰጡ። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ ከተማ ሐምሌ 22 ቀን 1929 ዓ.ም በግራዚያኒ የፋሽስት ወታደሮች በስምንት ጥይት ተደብድበው በጭካኔ ሲገደሉ ዓይናቸው የተጋረደበትን ጥቁር ጨርቅ አስፈትተው የገዳዮቻቸውን ዓይን በጀግንነት እያዩ፣ ህዝቡን በርቱ በማለት በመስቀላቸው እየባረኩ የሞት ፅዋውን የተጎነጩት። ከሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በተጨማሪ ለጣሊያን ማባበያም ሆነ ማስፈራሪያ ሳይሸነፉ የአዲስ አበባን ህዝብ ለፋሽስት መንግስት ተገዛ ብለን አንናገርም በማለታቸው የግራዚያኒ ወታደሮች ከየካ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እና በአዲስ አበባ ከሚገኙ የተለያዩ አድባራት ካህናቱን ሰብስበው እጅና እግራቸውን አስረው በእሳት አቃጥለው አሰቃይተው ገድለዋቸዋል፡፡ ከካህናቱ፣ ዳቆናቱና መዘምራኑ በተጨማሪ በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በፋሽስት ወታደሮች ተረሽነዋል፣ ከመኪና ጋር በገመድ ታስረው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እስከ ህይወታቸው ተጎትተዋል፣ ከአውሮፕላን ላይ ተወርውረው በጭካኔ ተገድለዋል።
በደርግም፣ በወያኔም ሆነ አሁን ባለው መንግስት በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ብዙ በደልና ግፍ ተፈጽሟል፣ የኮንዲሚንየም ቁጭ ይበሉ ተሰርቷል። የደርግ ቅልብ ወታደሮችና የመለስ ዜናዊ ፌዴራል ፓሊሶች የአዲስ አበባን ወጣት ጫማ ጥፊና ካራቴ መለማመጃቸው ነበር። ደርግ በስልጣን በቆየበት 17 የአገዛዝ ዓመታት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ተደብድበዋል፣ በእስር ተሰቃይተዋል፣ ቀይ ሽብር/ ነጭ ሽብር በሚል ብዙ ሺዎች በጥይት ተረሽነዋል። በ1997 ምርጫ ወቅት ከ200 በላይ ንጹሃን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በመለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትእዛዝ በህወሀት የአጋዚ ጦር ደማቸው በከተማዋ ጎዳናዎች በግፍ ፈሷል፣ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የአ/አ ወጣቶችን ወያኔ በጦላይ እና የተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ በማጎር ፀጉራቸው በደረቁ እየተላጨ በርሃ ውስጥ እንዲማቅቁ አድርጓል፣ በብዙዎች ላይ የአካልና የስነ ልቦና ጉዳት አድርሰዋል። በባለስልጣኑ ዳተኝነት እና እንዝላልነት በርካታ የከተማዋ ነዋሪ ላይ የቆሻሻ ክምር ተንዶበት ተቀብሯል፣ በልማት ስም መሬቱን ለመቸብቸብ ህዝቡን ያለአግባብ እያፈናቀሉ ከእድር ከሰፈሩ ነቅለውታል። የለገጣፎ፣ የሱሉልታ ህዝብ ቤቱ በላዩ ላይ በተረኞች ፈርሶ ሜዳ ላይ ተበትኗል። በኦሮሚያ ፓሊስና ልዩ ሃይል ከለላ በሚደረግላት ቄሮ በሚባል አሸባሪ ቡድን የከተማው ህዝብ ሰላም ደፍርሷል፣ ህዝቡ በመንግስት ላይ እምነት በማጣቱ ፅንፈኞች አደጋ ሊፈፅሙ ይችላሉ በሚል በስጋት እንዲኖር ሆኗል። መንግስት ተብዬውም ከወንጀለኞች ጎን ቆሞ ንፁሃን የከተማውን ወጣቶች አስሮ አንገላቷል። ይህ ሁሉ የአዲስ አበባ ህዝብ ለከተማው የከፈለው መስውልዕትነት ማሳያ ነው።
ላለፉት 30 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ ባልመረጣቸው፣ ከተማዋንና የህዝቡን ስነልቦና በማያውቁ፣ ለከተማው ራዕይ በሌላቸው ሌላ ተልዕኮና አጀንዳ ባላቸው የፓለቲካ ሹመኞችና ደላሎች አዲስ አበባ ስትደቆስና ስትዘረፍ ኖራለች። ከተፈራ ዋልዋ እስከ ታከለ ኡማና አዳነች አቤቤ ድረስ በህዝቡ ጫንቃ ላይ የተጫኑ ሹማምንት መብታችን ይከበር ባሉ የአዲስ አበባ ወጣቶችን እና መሪዎቻቸውን በሃሰት ክስ አንገላተዋል። ለውጥ መጣ ተብሎ የኦነግ መሪዎች ከተኙበት ተቀስቅሰው ከአስመራ ወደ ሃገር ቤት በገቡ ጊዜ የአዲስ አበባ የቡራዮ አካባቢ ነዋሪ ህዝብ እንደ መስዋዕት በግ ታርዷል። በአድዋ፣ በማይጨው፣ በካራማራ፣ በአምስቱ ዓመት የአርበኞች ትግል አባቶቹ በረሃ ለበረሃ፣ በየጦር ሜዳ ይዘው የተንከራተቱትን፣ ደማቸውን ያፈሰሱለትን፣ የጥንት ነገስታት ለዲፕሎማሲ ጉብኝት በሄዱባት ሃገራት የተውለበች የኢትዮጵያ ሰነደቅዓላማ ይዛችኋል በማለት የከተማዋ ነዋሪዎች በፓሊስ ተደብድበዋል፣ ሸሚዝና ሻሽ ሳይቀር እላያቸው ላይ ተቀዳዷል፣ በተቃራኒው ደግሞ በቡራዮ ነዋሪዎች ላይ፣ በቅርቡ ደግሞ በሻሸመኔ የንፁሃንን ደም ሲያፈሱ፣ ቤት ሲያቃጥሉና ህዝብ ሲያሸብሩ የነበሩ ፅንፈኞች ይዘውት ሲጨፍሩ የነበረውን በንፁሃን ደም የተነከረ የኦነግን ባንዲራ ፓሊሶች ምንም ሲሉ አልታዩም። በጥር ወር 2012 ዓ/ም በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 22 ማዞሪያ አካባቢ የቅድስት አርሴማ እና ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን በታከለ ኡማ ትዕዛዝ በሌሊት ለማፍረስ የመጡ አፍራሽ ግብረ ሃይሎች፣ በተለይም በአዲስ አበባ የውስጥ አሰራር የማይመለከታቸው የኦሮሚያ ክልል ፓሊሶች ህግ ከሚፈቅድላቸው ውጭ የሌላ ክልል ወይም ከተማ አስተዳደር የውስጥ ጉዳይ በመግባት የቤተክርስቲያኑን በር በመገንጠል ሚሊዮን ደንበሩ እና ሚካኤል ፋኖስ (ሚኪ) የተባሉ ሁለት የአዲስ አበባ ወጣቶችን ተኩሰው ሲገድሉ ብዛታቸው 21 የሚሆኑ ሌሎች የአዲስ አበባ ወጣቶችን ደግሞ በጥይት እሩምታና በዱላ ቀጥቅጠው ከፍተኛ ጉዳት አድርሰውባቸዋል። ባጠቃላይ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ከፋሽስት ጣሊያን እስከ ኦነግ/ ኦህዴድ የታከለ ኡማና አበበች አቤቤ ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ላይ የተፈፀሙ የሰብአዊና የዲሞክራሲ ጥሰቶች እንዲሁም በህዝቡ የደረሰው የጭካኔ ምግባሮች የአዲስ አበባ ነዋሪ ከከፈለው መሰዋዕትነት ውስጥ እጅግ ጥቂቱ ነው። ስለዚህ አዲስ አበባ በህይወት ላለነው ለእኛ እና ለመጪው ትውልድ ብቻ ሳትሆን፣ በጨካኞች እጅ የወደቁት የከተማችን ሰማእታትና አሁን በህይወት አጠገባችን የሌሉ ወገኖቻችን ጭምር ናት።
3. የነፍጠኛ ከተሞችን አከርካሪ መስበር፣
በአንድ አካባቢ የሚኖርን ህዝብ ብዛትና ስብጥር (Population Demography) በሃይል፣ በተፅዕኖ ወይም የተለያዩ ስልቶችን እና የመንግስትን ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም መቀየር ወይም ማዛባት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘና በወንጀልም የሚያስጠይቅ ነው። አሁን በኢትዮጵያ ባለው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የጎሳ የፌዴራል መንግስት አደረጃጀት መሰረት የክልሉ “ባለቤት” ነው ከተባለው ብሔር/ ህዝብ የተለየ የራሳቸው ቋንቋ፣ ባህልና ማንነት ያላቸው በክልሉ የሚኖሩ ማህበረሰቦች እንደ ስደተኛ መጤ እንጂ እንደ ሃገሩ ባለቤት የሚታዩ ስላልሆኑ የዜግነትና የዲሞክራሲ መብታቸው አይከበርም፣ በመንግስት የስልጣን መዋቅር ውስጥም የፓለቲካ ውክልና የላቸውም። በነገራችን ላይ የአንድ ክልል ባለቤት የመሆን መስፈርቱ የህዝብ ብዛት፣ ነባር የአካባቢው ነዋሪ መሆን፣ የ83ቱን የሽግግር መንግስት ምስረታ ኮንፍረስ ላይ መካፈል፣ በጥናት ላይ ተመስርቶ ህዝብ በሰጠው ሪፍረንደም/ ድምጽ መሰረት ወይም በሌላ ምክንያት መሆኑ ግልፅ አይደለም። ፈጣሪ ሰማይና ምድርን ልፍጠር ብሎ እንደፈጠረው ወያኔና ኦነግም የኢትዮጵያን ክልሎች እንፍጠር ብለው በ1983 ፈጠሩ ቢባል ይሻላል። ለማንኛውም ችግሩ ከላይ በተገለጸው የመብት ረገጣ የሚያበቃ ሳይሆን ዜጎች በፅንፈኞች ሃገራችሁ አይደለም ተብለው ድብደባ፣ ማፈናቀል፣ ዝርፊያ፣ የዘር ማጥፋት፣ የዘር ማፅዳት እና የተለያዩ ወንጀሎች ይፈፀምባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የክልል ባለስልጣናት በከተሞች ላይ ከገጠር ሰዎችን አምጥተው በማስፈር ነባሩ የከተማው ነዋሪ ህዝብ እንዲዋጥ በማድረግ የከተማው ህዝብ ቁጥርና ስብጥር (Demography) ተፈጥሯዊ ባልሆነ ሁኔታ እንዲዛባ ያደረጋሉ። የኦሮሚያው ም/ፕ አቶ ሽመልስ አብዲሳ “በህጋዊም ሆነ በህገወጥ መንገድ” በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰዎችን እያሰፈሩ መሆኑን በግልፅ መናገራቸው በተለይም ኢ/ር ታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ ህዝብ ነጥቆ ከ95ሺህ የኮንዲምኒየም ቤቶቻ ለኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ማደሉ፣ አሁንም በዛው መንገድ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መቀጠሏ ስለ አዲስ አበባ ህዝብ ግድ የሌላቸው መሆኑን ከማሳየቱ በተጨማሪ ይህ ስርዓት አድሏዊ ብቻ ሳይሆን ከዘመኑ ስልጣኔና አስተሳሰብ ጋር መሄድ የማይችል የበሰበሰ መሆኑን ያሳያል። አቶ ለማ መገርሳ ምርጫን ለማሸነፍና በቀጣዩም የአዲስ አበባን ፓለቲካና ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር ከተማን መቆታጠር አስፈላጊ መሆኑን እና ከግማሽ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ ማስፈራቸውን በራሳቸው አንደበት መናገራቸው ይታወሳል።
የኦሮሞ ፅንፈኞች በተለይ ለውጥ መጣ ከተባለበት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ መልክና ቅርፅ ከ16 ኛው ክ/ዘመን የቀጠለ የኦሮሞ መስፋፋት ያለ እስኪመስል ድረስ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልተነኮሱትና ያላጠቁት አጎራባች ክልል የለም። አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ አማራ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ አዲስ አበባና የመሳሰሉት ላይ የመሬት ይገባኛል በሚል ምክንያት ግጭትና ትንኮሳ ፈፅመዋል። በዚህም የተነሳ የንፁሃን ደም ፈሷል፣ ህዝብ ተፈናቅሏል፣ ንብረት ወድሟል። አዲስ አበባንም ካልዋጥን፣ ካልሰለቀጥን በማለት በየዕለቱ በሚፈጥሩት መቆሚያ በሌለው አዳዲስ ጥያቄዎች ለያዥ ለገናዥ አስቸግረዋል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሰዎችን ከሌላ አካባቢ በመኪና እየጫኑ በከተማ ዙሪያ ማስፈራቸው እና በመሃል ከተማ ውስጥ መሰግሰጋቸው፣ በአዲስ አበባ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ባጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ህንፃዎችን በማስገንባት እና ከከተማው መስተዳድሩ ቢሮዎችን በመከራየት የኦሮሚያ የክልል ሰራተኞችን ወደ መሃል ከተማ አዛውረዋል፣ ታኬ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ለተዛወሩት መኖሪያ ኮንዶሚኒየም ያድላል። ይህ ስራቸው የተቀናጀ ከመሆኑ አንጻር ከአንድ መዕከል በሚሰጥ ትዕዛዝ በመናበብ የሚፈጸም ይመስላል።
የነፍጠኛ ከተሞች ናቸው ብለው በፈረጇቸው በናዝሬት፣ በሃረር፣ በድሬደዋ፣ በጅማ እና በመሳሰሉት ከተሞች የህዝቡን ስብጥር በኦሮሞ የበላይነት ለመቀየር በክልሉ መንግስትና ፓርቲ አቋም ተይዞና በጀት ተመድቦ ላለፉት 30 ዓመታት በሰፈራ፣ በስራ ቅጥር፣ በባንክ ብድር እየሰጡ በንግድና በመሳሰለው በየከተሞቹ በአድልዎ ሲያሰፍሩ በተቃራኒው ደግሞ ኦሮምኛ ቋንቋ የማይናገሩ ኢትዮጵያውያንን በተጽዕኖ ለቀው እንዲሄዱ ሲያደርጉ ነበር። በጣም የሚገርመው ህገወጥ በሆነ መንገድ በየከተሞቹ የዲሞግራፊ ቅየራ ሲያደርጉ የኖሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን በጋራ በገነቧቸው ከተሞችና መንደሮች ላይ እንጂ እንደ ባህላቸውና ፍላጎታቸው ቢያንስ ክልላችን ባሉት ውስጥ የገነቡት አንድም ከተማ የለም። ተሰርቶ ያለቀን፣ የለማን ከተማ የኔ ነው ማለት ተገቢ አይደለም። ሳይሰሩና ሳይደክሙ ባቋራጭ የሰው ሃብትና ንብረት ነጥቆና አፈናቅሎ የራስ ለማድረግ መሞከር፣ ካልተቻለ ደግሞ እንደ ሻሸመኔ እና ቡራዮ በእኛ መሬት የኛን ቋንቋ የማይናገሩ መጤዎች ሃብት አፈሩ በሚል ተራ ቅናትና በዘረኝነት የዜጎችን ንብረት ማውደምና ህዝቡን በግፍ በመግደል ሰልፊ ፎቶ በመነሳት ፌስቡክ ላይ መለጠፋቸው ኦነጋውያን የክልሉን ፓለቲካና ትውልዱን ምን ያህል እንዳበላሹት የሚያሳይ ነው።
በአሁኑ ጊዜ የኦነግን ፖለቲካ የተወጉ የኦህዴድ/ ብልጽግና ባለስልጣናት የአዲስ አበባ ከተማን ዲሞግራፊ ለመቀየር ህዝብን ከሌላ አካባቢ እያመጡ ማስፈርና በነዋሪው መሃል የኛ ብሔር የሚሏቸውን ሰዎች መሰግሰጋቸውን ከቀጠሉ የከተማው የህዝብ ብዛት በየጊዜው እየጨመረ በመሄድ መጨረሻ ላይ ከተማው መሸከም ከሚችለው አቅም በላይ ስለሚሆን ቀውስ መፈጠሩ የማይቀር ነው (ከተማው ይፈነዳል)። ይህም ማለት የሥራ አጥነትና የድህነት ችግር እጅግ ይባባሳል፣ የጤና፣ የትራንስፖርት፣ የትምህርት እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ለማግኘት ለነዋሪው አስቸጋሪ ይሆናል፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የመኖሪያ ቤት እጥረትና የመሳሰሉት አሁን ካለው ችግርና እጥረት በላይ ይባባሳል፣ ህዝቡ በልቶ ለማደር ሲል ብዙ ነገር ውስጥ ሊገባ ይችላል፣ በተለይ በወጣትነት የእድሜ ክልል የሚገኘው የማህበረሰቡ ክፍል እንደጓደኞቹ ለብሶ ለመታየት፣ የራሱን ህይወት ለመምራት ሲል ወደ ህገወጥ ስራ ሊገፋፋ ይችላል። የዚህ ሁሉ ድምር ውጤት አጠቃላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ቀውስ በማስከተል የነዋሪውን ሰላም ያደፈርሳል። በሌላ አነጋገር ስርዓት አልበኝነትን ያስፋፋል፣ ዝርፊያና ሌብነት ይበራከታል፣ በሰላም ከቤት ወጥቶ መግባት አዳጋች ይሆናል። ከዚህም በተጨማሪ በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ሰው በመኖሩ የተነሳ ለአካባቢ ብክለት፣ ለውሃ እና ለዓየር ወለድ በሽታዎች ከማጋለጡም በተጨማሪ ከክልል በመጣው በአዲስ ሰፋሪ ህዝብ እና በከተማው ነዋሪ መሃል የባህል ግጭት (Cultural conflict) ሊከሰት ይችላል። በመሆኑም ችግሩ በግዜ ካልታረመ የሮም አወዳደቅ ታሪክ በአዲስ አበባ እንዳይደገም የግል ስጋት አለኝ። በታሪክ እንደሚታወቀው ባርባሪያን ሮምን በወረሩ ጊዜ ከተማዋ በሰው ጎርፍ በመጥለቅለቋ በከተማው አስቸጋሪ የሆነ ምስቅልቅል ሁኔታ ተከሰቶ ነበር። ሁሜታው ስርዓት አልበኝነት በከተማው እንዲስፋፋ አደረገ። በከተማው ውስጥ ለፍተው ጥረው የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በወሮበሎች ተዘረፉ፣ ሃብት ንብረታቸው ወደመ፣ በርካታ ንፁሃን ዜጎች በየመንገዱ ተገደሉ፣ መንግስት ህግና ስርዓትን ማስከበር ስላልቻለ በመጨረሻም የሮም መንግስት ፈረሰ፣ ህዝቡም ተበተነ፣ ከተማዋም የባርባሪያን መጫወቻ ሆነች። የአዲስ አበባ ህዝብም ከታሪክ መማር ካልቻለ በራሱ፣ በልጆቹና በሃገሩ ላይ እንደፈረደ ይወቀው። የከተማው ነዋሪ ህዝብ የአዲስ አበባን መስተዳድር በእጁ ማስገባት፣ እራሱን በራሱ ካላስተዳደረ ችግሩ ሊቀረፍ አይችልም። የምስለኔ ሹመት ሊቆም ይገባል።
አሁን ባለንበት ወቅት ፅንፈኛ የኦሮሞ ብሔርተኞች የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ተረጋግቶ ህይወቱን እንዳይኖር ስጋት ሆነውበታል፣ መንግስትም ከአጥፊዎቹ ጋር ነው የሚሞዳሞደው። በታሪክ የማትታወቀውና ከአንድ ትውልድ የዘለለ እድሜ የሌላት፣ ትናንትና በ1983 ዓ/ም ወያኔና ኦነግ ከዚህም ከዛም ገጣጥመው የኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ መሬት ላይ የሰፏት ኦሮሚያ የምትባል ክልል የዘመናት እድሜ ያስቆጠረችውን የትናንት በረራን የዛሬዋን አዲስ አበባን ከኋላ መጥታ ካልዋጥኩሽ፣ ካልሰለቀጥኩሽ እያለች ነው። በ2009 ዓ/ም ብዛታቸው አምስት የሚሆኑ የኦሮሞ ፓለቲካ ድርጅቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ የአዲስ አበባ ህዝብ የከተማው ነዋሪ እንጂ ባለቤት አይደለም፣ የከተማው ባለቤት ኦሮሞ ነው። በመሆኑም የከተማው ነዋሪ እንደ ቤት ተከራይ በባለቤቱ በጎ ፍቃድ የሚኖር እንጂ በከተማው ላይ የመወሰን መብት የለውም፣ የምኒልክ ሰፋሪ ወዘተ በማለት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ህዝብን ከዜግነት በታች በማውረድ ለማሸማቀቅ ብዙ ሞክረዋል። ፅንፈኛ ልሂቃኑ ልዩ ጥቅም ይገባናል በሚል ሽፋን እንደ ጥንቱ የገዳ ስርዓትና የሞጋሳ ባህላቸው የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ የጭቆና እና የብዝበዛ ቀንበራቸውን ለመጫን እየተራወጡ ይገኛሉ። አቶ ሽመልስ አብዲሳ ላሟም፣ ጥጃዋም፣ ወተቷም በእጃችን ገብተዋል ማለቱ ላሟ: ኢትዮጵያ፣ ጥጃዋ: አዲስ አበባ፣ ወተቷ ደግሞ ከኢትዮጵያ ካዝና እና ከአዲስ አበባ ህዝብ በታክስም፣ መሬቱን በመቀራመትም ሆነ በሌላ መንገድ በልዩ ጥቅም ስም ለመዝረፍ ያቀዱት እንደሆነ መገመት ይቻላል። በአንድ ሃገር ዜጎች መሃል አንዱ ከሌላው በኢኮኖሚ፣ በፓለቲካ ወይም በሌላ መንገድ ልዩ ተጠቃሚ የሚያደርገው፣ አሰራርና ፖሊሲ ከተዘረጋ ስርዓቱ የእኩልነትና የዲሞክራሲ ሳይሆን አፓርታይድ ነው።
ከኮንዲምኒየም ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ቀደም ብሎ ያነሱት የነበረው ጥያቄ ለተፈናቀለው ገበሬ በቂ ካሳ አልተከፈለውም፣ የኦሮሞን ገበሬ ህወሃቶች አፈናቅለው የኮንዲምኒየም ህንፃ ዘበኛ ነው ያደረጉት በሚል ነበር (በወቅቱ እነሱም ስልጣን ላይ የነበሩና የጥፋቱ ተጠያቂዎች ናቸው)። አሁን ግን ጥያቄያቸውን ለውጠው የህንፃው ባለቤት የኦሮሚያ ክልል እንጂ አዲስ አበባ አይደለም እያሉ ነው። ምክንያቱን ሲጠየቁ የሚመልሱት መልስ ህንፃዎቹ የተሰሩት እኛ ክልል መሬት ውስጥ ነው። ይህንን ያሉብበት ከደርግ ጊዜ ጀምሮ የሚታወቀውን የአዲስ አበባ ካርታ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት እያለ አዲስ ካርታ በመስራት የኦሮሚያን ክልል እና አዲስ አበባን መስተዳድር የሚያወዛግቡ የኮንዲሚኒየም ህንፃዎችን ቆርጠው ወደ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በማስገባት ነው። ስለዚህ አሁን የኦሮሚያ ባለስልጣናት እራሳቸው የሰሩትን ካርታ እየጠቀሱ አንዲት ጡብ ያላቀበሉትን፣ ሽራፊ ሳንቲም ያላወጡበትን ከንዲሚኒየሞች በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ስለሆኑ የኛ (ኬኛ) ናቸው እያሉ ነው። ኦሮሚያ ከመፈጥሯ በፊት አዲስ አበባ መዘጋጃና መስተዳድር መኖራቸውን እዚህ ላይ ማስታወስ እወዳለሁ።
4. ማጠቃለያ፣
ከተማችንን ከጥፋት ለመታደግ ሁሉም የአዲስ አበባ ነዋሪ በሚችለው አቅም ለትግሉ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል። ትግሉን እነ እስክንድር ጀምረውታል፣ ከእኛ የሚጠበቀው እነሱን መከተል ነው። ምንም ጥረት ሳያደርጉ ዝም ብሎ መመልከቱ አዲስ አበባም እንደ ትናንትናዋ የበረራ ከተማ በታሪክ እስከመረሳት ልትደርስ ትችላለች። የነገን አርቀው ማየት የቻሉት ብሩህ አዕምሮ ያላቸው እነ እስክንድር ነጋና ጓደኞቹ በሃገራችን ላይ እየመጣ ያለውን ከባድ ችግር ለህዝቡ ለማስረዳት ሞክረዋል፣ ህዝቡ ካልተደራጀ መብቱን መጠየቅም ሆነ ማስከበር እንደማይችል በተለያዩ መድረኮች ላይ አሳስበዋል። እስከ አሜሪካ ኒዮርክ የተባበሩት መንግስታት ጽህፈት ቤት ድረስ በመሄድ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሃገራችን ላይ በፅንፈኛ ቄሮ ተብዬዎች እያንዣበበ ስለሚገኘው የዘር ማጥጥፋት ስጋትን ለማስረዳት ሞክረዋል። ቂመኛው መንግስት ችግሩን ከማስተካከል ይልቅ እነ እስክንድርን ማሰር እንደ መፍትሄ በመውሰድ እያንገላታቸው ይገኛል።
ትውልድ እንዳይጠፋ፣ ሃገር እንድትቀጥል የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሚችለው ሁሉ ተረባርቦ ሃገሩንና ወገኑን ከጥፋት መታደግ ይጠበቅበታል። ሃገራችን እንደ ሶማሌ ወይም እንደ ሶሪያ ከተበታተነች፣ የመንግስት መዋቅር ከፈረሰ፣ ህዝቡ ከተበተነ በኋላ ዳግም እንደ ጨርቅ ሰብስቦ መስፋት አይቻልም። ጆሮ ያለህ ስማ፣ ሃገሬን እወዳለሁ የምትል፣ ሁሉ ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለውን ስብከት ለጊዜው ትተን ሃገራችን ዓይናችን እያየ ከመፍረሷ በፊት አንድ ነገር ማድረግ አለብን። እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ፓለቲካን እንፈራ ይሆናል ነገር ግን ስለ ህልውና መታገል ፓለቲካ ሳይሆን ሃገራችንን ከጥፋት መታደግ ነው። ሃገራችን እንዳትፈርስ ወገናችን እንዳይበተን መታገል የመኖር ያለመኖር ትግል እንጂ ፖለቲካ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ፅንፈኛ ኦሮሞዎች እያደረጉ ያሉት ፓለቲካ ሳይሆን የዘር ፍጅት፣ የዘር ማፅዳት፣ ተወልደን ያደግንበትን ሃገራችንን መቀማት ነው። ስለዚህ ሁሉም ሃገር ወዳድ የራሱን ጥረት ያድርግ መፍትሄው መለመን ወይም መለማመጥ ሳይሆን መታገል ብቻ ነው።
ትናንት በሃገራችን የነበሩ ፈጠጋር፣ ዳዋሮ፣ እናርያ፣ ቢዛሞ፣ በረራ እና የመሳሰሉ ስማቸው በታሪክ ሲጠቀስ የምንሰማቸው ዛሬ በአካል የሉም። በመሆኑም ህዝቡ ከታሪክ ተምሮ በህብረት መቆም መቻል አለበት። በአሶሳ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በወለጋ፣ በቡርራዮ፣ በአጣዬ፣ በጌድዮ በቅርቡ ደግሞ በሻሸመኔ ሰርቶና ለፍት በሚኖረው ሰላማዊ ህዝብ ላይ የፈፀሙት አረመኔያዊ ድርጊታቸው ሳይፀፅታቸው አሁንም በአዲስ አበበን “በህግም ከህግም ውጪም” ለመዋጥ እየዶለቱ ነው። ለዘመናት በመላው ኢትዮጵያውያን ስትገነባ የመጣችውን አዲስ አበባን ሁሉ ነገር ኬኛ የሚሉ የኦሮሞ ፅንፈኞች ሊውጧት አሰፍስፈዋል። ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ለመብትህ፣ ለህልውናህ፣ ለነፃነትህ፣ ለልጆችህ ካልታገልክ መጪው ዘመን አስፈሪ ነው። ትግሉ የህልውና ትግል ስለሆነ ይሉኝታ ለማያቁ፣ አንተም ይሉኝታ ሳይኖርህ ትግልህን ከጓዳ ወደ አደባባይ ፊትለፊት አምጥተህ ነጻነትህን እና ክብርህን ማስመለስ መቻል አለብህ።
“ድል ለዲሞክራሲ”
ደረጀ ተፈራ ከፊትበር (ከፈረሰው ሰፈር)
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣበ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Ayhonim Mignoti says
This the dirtiest opinion produced by the stupid and insane person living in Finfinne. All stated in his false accusation of the government and Oromo people has no ground except politically motivated ideas to swallow other ethnic groups that doesn’t belong to the ethnic group of the mad writer with limited knowledge and understanding of history. The mad-man wanted to tell to the world that Ethiopia belonged to the Abyssinian tyrannical rulers and others are invaders. It is here that the fallacy starts – the owners of the land is considered as invaders and the invaders as indigenous.
shiferaw berkineh says
ወንድሜ አንተ የጨነቀህ የኦሮሚያና የአዲስ አበባ ድንበር ና ያሳዘነህ በጥቂት ብር ተሰርቶ ስለሚያልቀው ኮንዶሚንየም ነው።በአሁኑ ግዜ ይህ መሰረታዊ ጥያቄ አይደለም።መሰረታዊ ጥያቄ መሆን የነበረበት የአዲስ አበባ የክልል የመሆን ጥያቄ እንጂ ቀደም ብሎ በኦሮሚያ መሬት ላይ ስለተሰራ ህንፃ መሆን የለበትም።የአዲስ አበባ ህዝብ እየተዳደረ ያለው ከሌላ ክልል በመጡ ሰዎች ነው።ይህ ማለት የአዲስ አበባ ህዝብ እንደ ህዝብ ተንቋል።አዲስ አበባ ወጣት የላትም ማለት ነው።በደርግ ዘመን አዲስ አበባ ክልል ነበረች ዛሬ ግን ከሌላ ክልል በመጣ ከንቲባ ስትደዳደር የሚገርም ነው።መሠረታዊ ጥያቄ የክልልነት እንጂ ትንሽ ነገር ስለ ህንፃ ስለ ኮንደሚንየም በዚህ ወቅት ማውራት ሚዛን አይደፋም።አገራችን በአሁኑ ግዜ የመፍረስ አደጋ ላይ ትገኛለች አሁን በስልጣን ላይ ያለውን የብልፅግና ፓርቲ በመደገፍ እና በቀጣዩ ምርጫ እንዲያሸንፍ በማድረግ ቢቻ ነው ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ማድረግ የምንችለው።ሌሎች ፓርቲዎች ኢዜማን ጨምሮ ቢመረጡ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብየ ነው የምገምተው።ኢትዮጵያ እንደ አገር ለማስቀጠል ቢቸኛው መፍትሔ ብልፅግና ፓርቲ ቢቻ ነው።
Tesfaye says
አዲስ አበባ
==========
የአንድ አካባቢ ባለቤትነት በአካባቢው በሚኖሩ ሕዝቦች ምርጫ ይወሰናል፡፡ ከ150 አመት በላይ ኢትዮጵያዊያን የደም ዋጋ ከፍለው የገነቡትን ከተማ አንድ ጽንፈኛ ተነስቶ የእኔ ብሔረሰብ ከተማ ነው ይላል፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከተማ ብቻ ሳትሆን የአፍርካዊያን ሁሉ ከተማ መሆኑዋን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ትንሽ እንዴ 21 ክፍለ ዘመን ሰው ማሰብ ለሁላችንም ይጠቅማል፡፡ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች አይጠቅሙንም፡፡
እንንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአዲስ አበባ መኖር መሥራት መብት ነው የባለበትነት ጥያቄ ግርግር ግን ጉንጭ ማልፋትና በሀገር መቀለድ ነው፡፡