
በተለያዩ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና ኬላዎች ከ13 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው ልዩ ልዩ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ሥር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
የተያዙት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ሳይፈፀምበት ከመስከረም 4 እስከ 9/2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ወደ ሀገር ሊገባ የነበረ ማሽላና ስንዴ፣ ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዝ የነበረ ሲጋራ፣ በሕዝብ ማመላሻ ሚኒባስ ሲጓጓዝ የነበረ የሽጉጥ ጥይት፣ በጭነት ተሸከርካሪ ሲጓጓዝ የነበረ የክላሽ ጥይትና የሞባይል ስልኮች ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከሀገር ሊወጣ ሲሉ የተያዙ የቁም ከብቶች፣ የብር ጌጣጌጥ፣ የአሜሪካ ዶላርን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦች፣ ልባሽና አዳዲስ አልባሳት ይገኙበታል።
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተሽከርካሪ ክፍል ውስጥ በመደበቅና ጨለማን ተገን አድርጎ ለማሳለፍ ሲሞከሩ በፍተሻ ተደርሶባቸው፣ ኬላን ጥሶ ለማለፍ ሙከራ በማድረግና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከተደበቁበት ቦታ ክትትል በማድረግ የተያዙ መሆናቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ዕቃዎቹ በሐረር፣ በነጌሌ ቦረና፣ በቱሉ ዲምቱ፣ በጋላፊ፣ በባሕርዳርና በድሬዳዋ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና ኬላዎች የተያዙ መሆናቸውን ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
That is great! ,የጉምሩክና የጠረፍ ጥበቃ ደህንነቶች ተቀናጅተው ከሰሩ በቢሊዮን የሚቆጠር ሕገወጥ ንብረትና ሐብት ዝውውርን መቆጣጠር ይቻላል።