
በቀጣይ በጀት ዓመት ደግሞ 20 ቢሊዮን ብር ተመድቧል
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚውል የ15 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር (300 ሚሊዮን ዶላር) ድጋፍ ለማድረግ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና የኤርትራ ዳይሬክተር ኦስማኔ ዶኔ ጋር ተፈራርመዋል።
የድጋፍ ስምምነቱ በጦርነቱ በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭት የተጎዱ አካባቢዎችና ማህበረሰብ ለመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ስራዎችን በአስቸኳይ ለመደግፍ ያለመ ነው።
ድጋፉ በተመረጡ የግጭት ተጎጂ ወረዳዎች የጤና፣ የትምህርትና የውሃ መሰረት ልማት መዘርጋት ብሎም ለፆታዊ ጥቃት የተጋለጡ ሴቶችን ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም ይውላል ተብሏል።
የፌዴራል መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በተያያዘው ዓመት 5 ቢሊየን ብር መመደቡን ያስታወሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ በጀት ዓመት ደግሞ 20 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልፀዋል።
የዓለም ባንክ ለመልሶ ግንባታ የሚውል ፕሮጀክት ያደረገው የልማት ፋይናንስ ድጋፍ በጦርነቱ ከደረሰው ውድመት አንፃር ከፍተኛ ባይሆንም ለተጎዱ አካባቢዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ግን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዓለም ባንክ ድጋፍ በጦርነቱ በድርቅ፣ በኮቪድ-19ና በዓለም አቀፍ ክስተት የተጎዳውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለማገዝ ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ታምኖበታል። (አዲስ ሚዲያ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply