የትግራይ ህዝብ የማይሳተፍበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አይኖርም❗️ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በትግርኛ ቋንቋ በነበራቸው ቆይታ፥ “በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የፌዴራል መንግስት ይሁን እኔ በበኩሌ የትግራይ ህዝብ የማይሳተፍበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ይኖራል ብለን በፍፁም አናስብም” ብለዋል።
“የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ምስረታ ጀምሮ እስከሁን ድረስ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ቆይቷል አሁንም እየተጫወተ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
“ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ አሁን ባለንበት ወቅት ሶስት ችግሮች አሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ከእነዚህም የመጀመሪያው ከለውጥ ጋር የተያያዘ ችግር ነው፣ ሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲና ህወሐት ካላቸው ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው፣ ሶስተኛው ደግሞ ልዩነት ማስፋት የሚፈልጉ አካላት የሚፈጥሩት ችግር ነው ብለዋል።
ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅና ከሚዲያ ጋር በተያያዘ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ ይሁን በሁሉም ክልሎች አሁን ያሉ ሚዲያዎች ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ ኖሮ አያውቅም፤ ይህ ሁሉም ሰው የሚያውቀው ሀቅ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ያሉ ሚዲያዎች በአጠቃላይ ችግር እንዳላቸው ይታወቃል። የመንግስት ይሁን፣ የግል ወይም የሀይማኖት ሚዲያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ችግር አለባቸው። የትግራይ ሚዲያዎችም ከዚህ ድክመት ለፃ አይደሉም ሲሉም ተናግረዋል።
ሰሞኑን በብሮድካስት ባለስልጣን የተወሰደው እርምጃ ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ በማባባስ ሚና ስለነራቸው ነው ብለዋል።
ባለስልጣኑ የወሰደው እርምጃ ሀገርን የማዳን ጊዜያዊ እርምጃ ብቻ ነው ብሎ መውሰድ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ እርምጃው የትግራይ ህዝብ አፍ እንዳይኖረው ተብሎ የተወሰደ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም ብለዋል።
የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ የህወሓት መሪዎች በፌዴራል መንግስት የሕግ የበላይነትና ዴሞክራሲ እንዲረጋገጥ እንደሚፈልጉ ሁሉ በትግራይ ክልልም እንደዛ መፍቀድ አለባቸው ብለዋል።
“በፌዴራል ብቻ ዴሞክራሲ ብለህ በክልል ዴሞክራሲ ሊኖር አይገባም ማለት አትችልም” ያሉ ሲሆን፥ ዴሞክራሲ በፌዴራልም ይሁን በክልል ለሁሉም ህዝብ እና ፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊ እንደሆነ ሊያውቁ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ “በምርጫ አስፈላጊነትና ግዴታ ላይ ልዩነት ያለን አይመስለኝም፤ ለምርጫ ቀጠሮ በመያዝ እየተዘጋጀን እያለን ሁሉም ሰው እንደሚያውቀው የኮቪድ 19 ፈተና አጋጥሞናል። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫ እስኪደረግ በስልጣን ያሉ አካላት እንዲቀጥሉ ወስኗል። ይህ ውሳኔ ለብልፅግናም ለህወሓትም ይሰራል። ለህወሓት ለብቻው አትችልም የሚል ውሳኔ የለም” ብለዋል።
ምርጫ ከአንድ ዓመት በኋላ የሚደረግ ጉዳይ ሆኖ እያለ የትግራይ ክልል መንግስት በሚሊየኖች የሚቆጠር በጀት መድቦ ክልላዊ መርጫ አካሄዳለው ማለቱ ይገርማል ብለዋል።
“በአንድ በኩል የኮሮና ቫይረስ ለትግራይ ስጋት አይደለም ማለት ነው?፤ እዛ ያለው ሰው ኮሮና አይይዘውም አይገድለውም ማለት ነው?’ ወይ ደግሞ ዘመናዊ የሆነ ህክምና እና መድሃኒት ስላለን ችግር የለውም ማለት ነው። ለመረዳት አስቸጋሪ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄ ለማንሳት ያስገድዳል ያሉ ሲሆን፥ ቫይረሱ ለኢትዮጵያ ይቅር ለአሜሪካም አስቸግሯል፤ ትግራይ ለብቻው ኮሮና ችግር አይፈጥርብኝም ብሎ ማመን እንዴት ቻለ የሚል ጥያቄ መነሳት ያለበት ይመስለኛል ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ መንግስት ሚሊየኖች በመመደብ ምርጫ ከሚያደርግ ሁለት ሶስት የውሃ ጉድጓድ ለምን አይቆፍርም? የፌዴራል መንግስት ተበድሮ ነው በመቐለ ከተማ ውሃ እየሰራ ያለው። በአክሱምም የውሀ ችግር አለ። በበብዙ የትግራይ ዞኖች የውሀ ችግር በብዛት ይታያል። ወይ ደግሞ አንድ ሆስፒታል ለምን አይሰራም? አንድ ትምህርት ቤት ለምን አይገነባም? ሲሉም ይጠይቃሉ።
“ሁኔታው በዚህ መልኩ ሲታም ዝም ብሎ ምርጫ ከማካሄድ በዝርዝር ገምግሞ የተሻለ መንገድ መምረጥ ለህወሓት ይሁን ለትግራይ ህዝብ ጥሩ ይመስለኛል” ሲሉም ገልፀዋል።
“ከዚህ ውጭ የፌዴራል መንግስት በክልል ጉዳይ እጁን አስገብቶ አያውቅም፤ ለቀጣይም አያደርገውም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ይህ ማለት ግን የፌዴራል መንግስት ሀላፊነት አሳልፎ ይሰጣል ማለት አይደለም፤ ህገ መንግስቱ ባስቀመጠው የፌዴራል ስልጣን መሰረት የሚሰራው ይሆናል ብለዋል።
የፌዴራል መንግስት ለትግራይ ክልል ከሚገባው በጀት ይሁን ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች አንድ ሳንቲምም ቢሆን አላጎደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ለወደፊትም እንደማያደርግ እና ይህን ለማድረግ ህጉ እንደማይፈቅድለትም አንስተዋል።
“የትግራይ ክልል መንግስት ግን የፌዴራል መንግስት ህጋዊ አይደለም፣ አናወቀውም፣ አናምንበትም፣ ከሱ ጋር ለመስራት አንችልም እያለ የበጀት ብቻ ጥያቄ በማንሳት እርምጃ ወሰደ ማለት የሚገባ አይመስለኝም” ሲሉም ተናግረዋል።
ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በተመለከተም “በአሁኑ ወቅት መልካም የዲፕሎማሲእና ፀጥታን የተመለከተ ግንኙነት አለን” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ።
በኢኮኖሚ በኩልም የስልክ፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትና በሌሎች ዘርፎችም በጋራ መስራት መጀመሩን ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ቀስ እያለ ወደ ተሻለ ደረጃ ሊደርስ የሚችል መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ግንኙነት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ከሆነች ትግራይም አብራ ትጠቀማለች፤ የትግራይ ጥቅምም የኢትዮጵያ ጥቅም ነው፤ ነጣጥለህ ትግራይ ብቻዋን ትጠቀማለች ወይም ትጎዳለች የሚል ግምገማ እንደማይሰራም ገልፀዋል።
በቅርቡ በኤርትራ በነበራቸው ቆይታም ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር በተለይም በልማት እና በሁለቱ ሀገራት ግኑኝነት ላይ መምከራቸውን አስታውሰው፤ በሁለቱም ሀገራት በኩል በተሻለ ደረጃ የመስራት ፍላጎት ስላለ በቅርቡ እየተሻሻለ እና እያደገ ይሄዳል የሚል እምነት እንዳላቸውም አስታውቀዋል። (ምንጭ፥ ፋና)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply