ቴዲ ወደ ባህርዳር ሲያቀና “እንዘምራለን” ማለቱን ያስተውሏል! የጉዞውን አላማ እንዲያ ሲል ነበር ረቂቅ በሆነ መንገድ የገልጸው። በመዘመር እና በመዝፈን መሃል ያለውን ጥልቅ ልዩነት የማይረዳ ብቻ ነው ለሰሞኑ “አሲዮ ቤሌማ” እጅ የሚሰጠው። ከኮንሰርቱ ጀርባ ያለው “የፍቅር ጉዞ” የሚለው መሪ ቃል ውስጥም ከውቅያኖስ የጠለቀ መልዕክት አለ። ይህንን ቃል የተረዳ ብቻ ነው የተልእኮውን ስኬት ሊያበስር የሚችለው። ዝግጅቱ ኮንሰርት እንጂ ዳንኪራ አይደለም። ሁለት ወይንም ሶስት ሰዓት ብቻ የፈጀ ኮንሰርት። ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር የነገሰበት ኮንሰርት። ትንሳዔን አብሳሪ ኮንሰርት። መዝሙር ውስጥ መልዕክት አለ። የሚያንጽ፣ የሚያነቃቃ መልዕክት።
መላው በጠፋበት በዚህ ወቅት፤ ኢትዮጵያ የምትሻው የተስፋ ቃል ብቻ የሚደሰኩርላትን ሳይሆን ድልድይ የሚዘርጋላትን ሰው ነው። ጥላቻ ነግሷል። በሃገራችን ስር ሰድዶ፤ ቤተ እምነትን ሳይቀር አምሶታል፤ ጥላቻ – ጥላቻን ይወልዳል እንጂ ችግርን አይፈታም። እሱን ለማንገስ ላለፉት 27 ዓመታት ብዙ ድንጋይ ተፈንቅሏል። አዎ ጥላቻ በሽታ መሆኑን አይተናል።
ይህን ክፉ በሽታ ለማርከስ የፍቅርን ዳገት መውጣት ግድ ይላል። ጉዞውን ቴዲ ጀመረው። ጥላቻን የሚያከስሙ ዜማዎቹን የሰሙ … እነ ለማ መገርሳ እነ … እነ አብይ ተከተሉት። ለማ መገርሳ “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ማለቱ የቴዲ “ሲንድረም” ስለመሆኑ የሚጠራጠር ይኖር ይሆን?
ጎበዝ፣ ዘመኑንም እንቃኘው እንጂ! ሰው ለታቦት ንግስ ወጥቶ በዚያው የሚቀርበት ዘመን እኮ ነው ያለነው። ወገን የእሬቻን በዓል ለማክበር ሄዶ እስከዘላለሙ የማይመለስበት ወቅት ላይ ነን። ልቅሶና ሃዘንን ሰብሰብ ብሎ በጋራ የማይካፈሉባት ምድር፣ ምእመናን ለጸሎት ወጥተው የሚታፈኑበት ሃገር ላይ እንደተቀመጥን ለአፍታም አንዘንጋው። ኮንስርት ማድረግ ብርቅ የሆነበት ሃገር። ዳር ድንበር እንዲያስከብር የተላከ ወታደር መሃል ከተማ ገብቶ የወገን ደም የሚያፈስስበት ምድር! በዚህች ያልታደለች ሃገር፣ በዚህ አስከፊ ዘመን፣ “ጃ ያስተሰርያል”ን አጥንት ይዘን ስንጓተት አጃኢብ አይሆንም?
ይህ እሰጥ እገባ ልብ ላለው ሁሉ ቅንጦት ይሆናል። ነገሩን በደንብ የተረዳው ወገን፣ ከ 50 ሺህ ሕዝብ በላይ በታደመበት ዝግጅት ላይ “ምን ይፈጠር ይሆን?” እያለ የልቡ ትርታ ከፍ እና ዝቅ ይል ይሆናል እንጂ፣ ቀሪ ሂሳብ አያወራርድም። ጥሩ ዜና በሚናፈቅበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት፣ ሰማይ ላይ የወጣን የሕዝብ እምቅ ስሜት ተቆጣጥሮ በሰላም ማጠናቀቅ መቻል እጅግ የሚደነቅ ነገር ነው። ስለዚህም ጉዳዩ የገባቸው ዝግጅቱ “እንኳን በሰላም አለቀ!” ይላሉ። ሻንጣ በጀርባ ሸክፎ ማራቶንን መሮጥ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ የሚያውቀው ሯጩ ብቻ ነው።
እርግጥ ነው ሕዝብ ፍላጎቱን ገልጿል። የሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ማግኘት ነበረበት። የሕዝቡ ጫና ቀላል አልነበረም። ይህንን በተመለከተ ከቴዲ አካባቢ የሚሰማው ነገር የህዝብ ስሜትን ያለመረዳት ጉዳይ አይደለም። ስሜትን መረዳት እና ስሜትን መንዳት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። 26ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ቴዎዶር ሩዝቬልት በአንድ ወቅት ሲናገሩ “በመሪዎች እና በአለቃ መካከል ያለውን ልዩነት ሰዎች ይጠይቃሉ። መሪ ይመራል። አለቃ ደግሞ ይነዳል” ብለዋል። መንዳት እጅግ ቀላል ነው። ውል ለማስያዝ መምራቱ ነው ከባድ።
አራት አመታት ሙሉ ተከልክሎ የነበረ መድረክ፣ በሰላም እንዳያልቅ፣ እንከን የሚያሸትቱ ተንኳሾች አሰፍስፈው የሚጠብቁት ነገር ነበር። የጌታቸው ማንጉዳይ ጣልቃ መግባት ነገሮችን አስቀድሞ የመረዳት፣ አርቆ የማሰብ እና የመብሰል ውጤት ነው። በዚህ ፍቅር ጉዞ እቅድ ላይ “ጃ ያስተሰርያል” አልነበረም። ጉዞው ለመዝፈን ሳይሆን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። የሰላም እና የፍቅር መልዕክት። በዚያ ውስጥ ሃዘን አለ። በዚያ ውስጥ ብሶት አለ። በዚያ ውስጥ ቁጭትም አለ። በነገራችን ላይ በኮንሰርቱ ላይ ባለስልጣኖቹ በይገኙም ልጆቻቸው እና ሚስቶቻቸው በሙሉ ስቴዲየም ገብተው ከሕዝቡ ጋር ሲደሰቱ ነበር።
ሕዝብ በአንዲት ቃል ብቻ ማነሳሳት እጅግ ቀላል ነው። በረጅሙ የሚያይ ሳይሆን አጭሩን አላማ የመረጠ ይህንን ማድረግ ይቀልለዋል። ከዚህ ግፊት የሚገኘው ውጤት፣ ኪሳራ እንጂ ትርፉ ሚዛን ሊደፋ አይችልም። ጥይቱንም፣ ቀለሃውንም የያዙ ሃይሎች ሰፍ ብለው ይህችን ወቅት እንደሚጠብቁ አንዘንጋ።
እያወራን ያለነው ስለ “ሞብ” ስነ-ልቦና ነው። ሞብ የማህበረሰብ ስነ-ልቦና አካል ነው። የስነልቦና ምሁራን የሆኑት ጉስታቭ ሌቦን እና ሲግሞንድ ፍሬድ “ሰዎች አንድ አላማ ይዘው በሲሰባሰቡ በሚጋሩት የጋራ የሆነ አመለካከት፣ ግላዊ ሃላፊነትን ከአናታቸው አርደው ስለሚጥሉ፣ ምንም ነገር ከማድረግ አይቆጠቡም” ይሉናል።
ይህን ያህል ግዙፍ ኮንሰርት ይቅርና ሰዎቹ የራሳቸው የመቀሌው ስብሰባም “በሰላም አለቀ” ይሉን የለ? በረጅሙ እየተነፈሱ “የአዲስ አበባው ጥምቀት በዓል በሰላም ተጠናቀቀ” ብለውናል። በተዘዋዋሪ ሰላም የምትለው ቃል እንደ ዳይኖሰርስ ከምድሪቱ ጠፍታለች እያሉን እኮ ነው። ሰዎቹ እኮ አስከሬን አጅቦ የሚሄድን ለቀስተኛ እንኳን ማመን የተሳናቸው፣ በራስ ገመድ ተጠልፈው፣ የራሳቸውን ጥላ እንኳን የሚፈሩ፣… ምጥ ውስጥ ያሉ ናቸው። የፈሪ ዱላ ረጅም ነው እንዲሉ በጋራ ሆኖ ያዜመ ላይ ሳይቀር የሚተኩሱት ለዚህም ነው።
ትልቁን ጥበብ እና ማስተዋል የሚጠይቀው ሕዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ሊመጣ የሚችለውን ችግር ማስወገድ መቻል ነው። ይህ አርቆ ማሰብን ይጠይቃል። ቅዝምዝም ሲወረወር ጎንበስ ብሎ የሚያልፍ አስተዋይ ብቻ ነው። የሕዝብን ስሜት ማረጋጋት መቻል ራሱን የቻለ ጥበብ ይጠይቃል። ብሶት ያጋለው ሕዝብ ነው። እልህ የተናነቀው ሕዝብ። በቋፍ ላይ ያለ ሕዝብ። አንድ ነገር ለማድረግ ጥቂት ቃላት ብቻ ይበቃሉ።
ደግሞ ጨዋ ነው። መሪውን የሚሰማ – ለሚወድደው የሚታዘዝ ሕዝብ።
ሁሉም ነገር ግዜውን ጠብቆ ይከሰታል። ከዚህ ቀደም ቴዲ “ጃ ያስተሰርያል”ን ለምን አልዘፈነም ብለን ጮኸናል። ለጩኸታችን ምክንያቱ አጥጋቢ ይሁንም-አይሁን፣ ወቅቱ ይህንን ለማለት ይፈቅድ ነበር። ከአመታት በፊት “ጃ ያስተሰርያል” ሲዘፈን የነበረው ሁነታ አሁን የለም። አሁን ስለ ለውጥ እና ስለ አዲስ ንጉስ መምጣት አይደለም የምንጨነቀው። የመኖር እና የአለመኖር፣ የህልውና ጥያቄ ላይ ደርሰናል። የንጹሃን ደም በየቀኑ ይፈስሳል። ሃገር እንደጉድ ይዘረፋል። እየተካሄደ ያለውን ግፍ ቃላት አይገልፀዉም። ነገሩን ከስሜት መነጽር ወጣ አድርገን እንመልከተው። ፈጥኖ መፍረድ እና ፈጥኖ መናደድ ከአመክንዮ ሳይሆን ይልቁንም ከፍርሃት እና ከድንቁርና ጋር እጅ ለእጅ የሚሄድ ነገር ነው።
አሁን ነገሮች ተለዋውጠዋል። ወደድንም ጠላን፣ አገዛዙ ዳግማዊ “ዘመነ መሳፍንት” ውስጥ አስምጦን፣ እልቂት አፉን ከፍቶ እየጠበቀን ይገኛል። ሃገሪቱ አጼ «ቴዎድሮስ»ን ትሻለች። የአይሻልን ጦርነት በድል ተወጥቶ ዳግማዊው ዘመነ መሳፍንትን ማብቂያ የሚያውጅ ጀግና የማውጣቱን ነገር ግድ ይላል።
በቴዲ እና በአቡጊዳ ኢትዮጵያ የተጀመረው የፍቅር ጉዞ ይቀጥላል። ቀጣይዋ ከተማ ውቢቷ ናዝሬት / አዳማ ናት። በከተማዋ ቀደም ሲል የተዘራው የጥላቻ በሽታ በፍቅር ይታከማል። እነ ለማ መገርሳም በአዳማው ኮንሰርት ላይ ይገኙ ይሆናል።
ፍቅር ያሸንፋል!
ክንፉ አሰፋ
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ። ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ™ አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው።
Mulugeta Andargie says
ቴዲ ኣፍሮ በመንደሩ ሄዶ ማለትም (በባህር ዳር) ጨዋታውን በማሰማቱ ተደስቻለሁ!! ህዝቡም ጥሩ ኣቀባበል አድርጎለታል!! እኛ ጋ ቢመጣ ግን የሌላ ክልል ዘፈንና ታሪክ ይደሰኩርብናል!! የኛን ለራሳችን የሌላውን ለባለቤቱ ይሁን!!! ጌታ ቀረጥ ኣምሮት የኔን ለኔ የቄሳርን ለቄሳር እኮ ነው ያለው!!!
Tibebu says
ሙሉ በጥባጩ፣
ማን ሾመህና ነው ደልዳይ የሆንከው?
Tibebu says
ለካንስ አንዳርጌ ስምህ የተውሶ ነውና!