የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሕወሓት ዘርን መሠረት አድርጎ በማይካድራ በፈፀመው የንጹሐን ዜጎች የግድያ ወንጀል መንስዔ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ጠየቁ።
አባላቱ ይህንን እና ሌሎች መሰል ወቅታዊ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቅርበዋል። የተደረገው ፍጹም ጭካኔያዊ እና አረመኔያዊ ድርጊት እጅግ እንዳሳዘናቸውም አያይዘው ገልጸዋል። ተግባሩም የጦር ወንጀለኝነት መሆኑንም አበክረው ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አክለውም፤ የሀገርን እና የህዝብን አደራ ተቀብለው ግዳጃቸውን እየተወጡ በነበሩት የሰሜን ዕዝ የሠራዊት አባላት ላይ የሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን የወሰደው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትም እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። በየትኛውም የህግ መመዘኛ ተቀባይነት እንደሌለውም አስረድተዋል።
የፓርላማ አባላቱ በተጨማሪም፤ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን በእልህ እና በቁጭት ተነሳስቶ በአጭር ጊዜ ለተጎናጸፈው ድል ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። የተለያዩ የሸብር ወሬዎችን እና የማሳሳቻ ዘዴዎችን ሁሉ ተቋቁሞ ላሳየው ጽናትም ምስጋና አቅርበዋል።
ቀደም ሲል ለዓመታት የተዘረጋላቸውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን በመተው እና በማና አለብኝነት ዕብሪት የቀሰቀሱትን ጦርነት በከፍተኛ ብልሃት እና ትዕግሥት መርቶ በወሳኝ መልኩ በማጠናቀቁም መንግስትን አመስግነዋል። (ዜና ፓርላማ)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply