እነ ጃዋር መሐመድ መንግሥትን ኮንነው የፍትሕ ተቋማትንና ፍርድ ቤትን አመሠገኑ
ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተሰጠ
በድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግሥት ከሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ላለፉት 71 ቀናት በእስር ላይ ያሉት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የጊዜ ቀጠሮና የቅድመ ምርመራ የፍርድ ቤት ሒደቶች መጠናቀቃቸውንና የምርመራ መዝገቡ መዘጋቱን አስመልክቶ፣ “ያለ ጥፋታችን እንድንታሰር አድርጎናል” ያሉትን መንግሥትን ኮንነው የፍትሕ ተቋማትንና ፍርድ ቤትን አመሠገኑ።
ተጠርጣሪዎቹ ቅሬታቸውንና ምሥጋናቸውን የገለጹት ከሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የጊዜ ቀጠሮ ችሎቱን ሒደት ሲያይ የነበረው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ወንጀል ችሎት፣ ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በምርመራ መዝገቡ ላይ የተለያዩ ትዕዛዞችን ሰጥቶ ሲዘጋ በሰጡት አስተያየት ነው።
አቶ ጃዋር መሐመድ አስተያየት መስጠት እንደሚፈልግ ለፍርድ ቤቱ ገልጾ ሲፈቀድለት እንደተናገረው፣ ሲታገሉ የነበረው የፍትሕ ሥርዓቱ እንዲስተካከል ነበር። አሁን በታሰሩበት ወቅት ባዩት የፍርድ ቤት ሒደት ተስፋ ስላገኙ ደስተኞች ነን ብሏል። ይህ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የታየው መሻሻል እስከ ወረዳ ፍርድ ቤቶች እንዲተገበር መሠራት አለበት ብሎ፣ “ያላችሁበትን ጫና እናውቃለን፣ ለእኛም ያሳያችሁንን ክብር ዓይተናል፣ እናመሠግናለን፤” ሲል ተናግሯል።
ዳኞች ለሕግና ለሕገ መንግሥቱ ብቻ ታማኝ ሆነው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት እንዲሠሩም አደራ ብሏል። ለሁሉም ተጠርጣሪዎች የፌዴራል ፖሊስ አባላት ላደረጉላቸው እንክብካቤ አክብሮትና ጥበቃ እንደሚያመሠግኑ የገለጸው ተጠርጣሪ አቶ ጃዋር ጠበቆቻቸው ሳይጠሯቸውና ሳያውቋቸው ስላደረጉላቸው የሕግ ድጋፍ ምሥጋና አቅርቧል።
መንግሥት ያሰራቸው ሰርቀው፣ ገድለው ወይም ደፍረው ሳይሆን በፖለቲካ አቋማቸው ስለተጣሉና ሥጋት ስለሆኑበት መሆኑን የገለጸው አቶ ጃዋር፣ ዜጎችን ወይም የፖለቲካ ተቃናቃኞችን በማሰር፣ በመግደል ወይም በማባረር የተገነባ አገር እንደሌለ ጠቁሞ፣ የፍትሕ ሥርዓቱን በመጠቀም የፖለቲካ ባላንጣ ለማስወገድ ጥረት ማድረግ የትም እንደማያደርስ ተናግሯል። እንደ ኦሮሞ ሕዝብ የታሰረና የተገደለ ሕዝብ እንደሌለና በድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ እንኳን በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች በእስር ላይ መሆናቸውን አክሏል።
“በመግደልና በማሰር ለውጥ የሚመጣ ቢሆን ኖሮ የት በተደረሰ” ያለው አቶ ጃዋር መግደልና ማሰር አገር እንደሚያፈርስና እንደሚጎዳ፣ ልማትም ሆነ ብልፅግና ሊመጣ ስለማይችል አዋጭ የሚሆነው በልዩነቶች ዙሪያ ቁጭ ብሎ መወያየት መሆኑን ጠቁሟል። ሕዝብና አገር እንዲኖሩ ከተፈለገ ፍትሕን ማክበር አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን በመጠቆም፣ ዳኞችም ቢሆኑ ለሕጉና ለሚለብሱት ጋወን ታማኝ ሆነው እንዲሠሩ አደራውን አስተላልፏል።
አቶ በቀለ ገርባም ተመሳሳይ ምሥጋና ለፍትሕ ተቋማትና ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ፣ እሳቸው ቀደም ብሎ በነበረው የአገር አመራር ወይም ሥርዓት ውስጥም በእስር ማሳለፋቸውንና ችሎቶች ጭፈራ ቤት የሆኑበት፣ መሳቂና መሳለቂያ እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን ግን ያ በመቅረቱ የተሻለ የፍርድ ቤት ሥራና ችሎት በማየታቸው ቆመው ማመሥገን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። “ክብር ለሰጠ ክብር መስጠት ያስፈልጋል” ያሉት አቶ በቀለ ለፌዴራል ፖሊስ አባላት፣ ለዓቃቢያነ ሕግና ለፍርድ ቤቱ ክብር እንዳላቸው ገልጸዋል።
የዋስትና መብትን በሚመለከት የሚገርማቸው ነገር ቢኖር ሲከሰሱበት የቆዩበት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 ወይም ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግታዊ ሥርዓቱ በሚፃረር መንገድ፣ በቀጥታም ይሁን በእጅ አዙር የአገሪቱ አንድነት እንዲፈርስ. . . የሚል ድንጋጌ በመጥቀስ ዋስትና እንዳይፈቀድላቸው መደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ የሕግ ድንጋጌ ከአሥር እስከ 25 ዓመታት ወይም ነገሩ ሲከብድ እስከ ዕድሜ ልክና ሞት ድረስ ያስቀጣል ስለሚል፣ ተጠርጣሪን የዋስ መብት ለመከልከል ይጠቀሙበት እንደነበር አክለዋል። አቶ በቀለ አክለው እንደገለጹት አሁን ደግሞ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 ድንጋጌን በመጥቀስ ወይም በሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥት ሥርዓት ላይ የሚደረግ የወንጀል ድርጊት ማለትም በኃይል፣ በዛቻ፣ በአድማ ወይም ሕገወጥ በሆነ በማናቸውም መንገድ በማሰብ የፌዴራል ወይም የክልልን ሕገ መንግሥት የተቋቋመን ሥርዓት የማፍረስ የወንጀል ድርጊትን የሚያቋቁመው ድንጋጌ በመጥቀስ፣ የዋስትና መብታቸው መገደቡ የሕጉን ዓላማ ያልተከተለ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕጉ ዓላማ መሆን ያለበት ተጠርጣሪውን ወይም ተከሳሹን በሚጠቅም ሁኔታ መተርጎም ሲገባ እየተደረገ ያለው የተገላቢጦሽ መሆኑንም አክለዋል። በመሆኑም ነፃነታቸውን፣ አገራቸውን፣ ሀብታቸውንና ቤተሰባቸውን እንዳያጡ የፍትሕ አካላት ትክክለኛውንና ሕጉና ሕጉን ብቻ መተግበር እንዳለባቸውም ጠይቀዋል። ተቋማትን እያፈረሱ መሄድ አደጋ ስለሆነ አገርን ለማልማት ከተፈለገ፣ “ሁላችንም የድርሻችንን እንድንወጣ መደረግ አለበት” ብለዋል። በአገር ጉዳይ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መመካከር እንጂ እስራት ምንም እንደማይፈይድ ተናግረዋል። በቆዩባቸው የእስር ቀናት የፍትሕ አካላት ላደረጉላቸው ሁሉ “እናመሠግናለን፣ እግዚአብሔር ይስጥልን” ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ በዕለቱ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ዓቃቤ ሕግ በቅድመ ምርመራ መዝገብ የሚያሰማቸውን ምስክሮች (ከ15ቱ አሥሩን አስመስክሮ) አሰምቶ ማጠናቀቁን በመግለጽ፣ የክስ መመሥረቻ ጊዜ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት አንቀጽ 109 ድንጋጌ መሠረት 15 ቀናት እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ ላይ የተነሳውን ተቃውሞና በተጠየቀው የዋስትና መብት ላይ ብይን ለመስጠት ነበር።
ፍርድ ቤቱ ነሐሴ 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስቻለው ችሎት አቶ በቀለና አቶ ጃዋር ምንም እንኳን ለየብቻቸው የታሰሩ ቢሆንም፣ እንዲገናኙ ወይም እንዲቀላቀሉ የሰጠው ትዕዛዝ ስለመፈጸሙ ሲጠይቅ ተጠርጣሪዎች እንዳልተፈጸመ ተናግረዋል። ለምን እንዳልተፈጸመ የተጠየቁት በፌዴራል ፖሊስ የእስረኛ አስተዳደር ክፍል ተወካይ በሰጡት ምላሽ፣ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለአለቃቸው ማስተላለፋቸውን ተናግረው ለምን እንዳልተፈጸመ ግን መረጃ እንደሌላቸው አስረድተዋል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች ከደንበኞቻቸው ጋር እንዲገናኙ የተፈቀደላቸው ጊዜ አጭር መሆኑን ጠቁመው ያንንም ቢሆን በአግባቡ መጠቀም እንዳልቻሉ ላቀረቡት አቤቱታ፣ የፌዴራል ፖሊስ ተወካዩዋ በሳምንት ሦስት ጊዜ እንዲገናኙ በተባለው መሠረት እየሠሩ መሆኑንና በመካከር በቀጣይ ጠዋትና ከሰዓት ሙሉ ቀን የሚያገኙበትን አሠራር መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል። ጠበቆቹም በተወካይዋ ምላሽ ተስማምተዋል።
አቶ ጃዋርና አቶ በቀለ እንዲገናኙ እንዲደረግ የተሰጠው ትዕዛዝ ለምን እንዳልተፈጸመ የፌዴራል ፖሊስ ተወካይዋ በግልጽ እንዲያብራሩ ፍርድ ቤቱ በድጋሚ ሲጠይቅ፣ አቶ ጃዋር በመሀል በሰጠው አስተያየት አባላቱ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ለመፈጸም እንዳይችሉ የሚያደርግ ጣልቃ ገብነት መኖሩንና ከእነሱ በላይ መሆኑን ተናግሯል። የዚህ አገር የፍርድ ቤት ትዕዛዝን መፈጸም ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለውን ለማረጋገጥ እንጂ፣ ከፖሊስ አባላቱ በላይ መሆኑንም አክሏል። የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይከበራል ወይስ አይከበርም የሚለውን ለማወቅና ፍርድ ቤቱ እንዲረዳው ለማድረግ ያህል ጥያቄውን ማንሳቱንም ጠቁሟል።
ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ የክስ መመሥረቻ ጊዜ በማለት የጠየቀው 15 ቀናት “ሊፈቀድ ይገባል ወይስ አይገባም” የሚለውን ጭብጥ በመያዝ ከተገቢው የሕግ ድንጋጌ አንፃር በመመርመር ብይን መስጠቱን ተናግረዋል። እንደገለጸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(4) ድንጋጌ መሠረት በቁጥጥር ሥር የዋለ ተጠርጣሪ የተፋጠነ ፍትሕ ማግኝት እንደሚገባው መደንገጉ፣ ይኸው ድንጋጌ ኢትዮጵያ ተቀብላ የሕገ መንግሥቱ አካል ያደረገችው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም የሚያረጋግጡት መሆኑን ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌ (አይሲሲፒአር) አንቀጽ 9(3) የአፍሪካ ሰብዓዊ መብት ቻርተር አንቀጽ 7(መ) ድንጋጌና ሌሎችም አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን በመጥቀስ የተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብቶች መከበርና የተፋጠነ ፍትሕ የማግኝት መብት እንዳላቸው መደንገጉን ችሎቱ ጠቁሞ፣ የተጠርጣሪ ጠበቆች ያነሱትን የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት ጥያቄ እውነትነት አረጋግጧል።
በሌላ በኩል ዓቃቤ ሕግ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 81(1) ጠቅሶ ያቀረበው የቀዳሚ ምርመራ ሒደት ሕግን የተከተለ መሆኑን አረጋግጦ በአንቀጽ 38(ለ) ድንጋጌ መሠረትም፣ ዓቃቤ ሕግ ቀዳሚ ምርመራን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት የማቅረብ ሥልጣን እንዳለውም አስረድቷል። እሱንም በአንቀጽ 94 ድንጋጌ መሠረት ለሚመለከተው ፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚችል የሕግ ድንጋጌ እንዳለው ጠቁሞ፣ ነገር ግን ክስ የመመሥረቻ ጊዜ 15 ቀናት በአንቀጽ 109 ድንጋጌ መሠረት ሲጠይቅ በአንቀጽ 37 ድንጋጌ መሠረት ምርመራና የቅድመ ምርመራ ምስክርነት በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ መደረጉን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም በእነ አቶ ጃዋር መዝገብ የተካተቱትን 14 ተጠርጣዎች በሚመለከት ፍርድ ቤቱ ሲመረምር በአቶ ሐምዛ አዳነ፣ አቶ ሸምሰዲን ጠሀ፣ አቶ ቦና ትብሌና ጋዜጠኛ መለስ ድሪብሳ ላይ የቀዳሚ ምርመራ ምስክርነት እንዳልተሰጠባቸው ማረጋገጡን ገልጿል። በመሆኑም የቀዳሚ ምርምራ ሲሰማ ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ስለወሰደ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ከጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት ውስጥ ክስ መሥርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ አሥሩን ተጠርጣሪዎች በሚመለከትም፣ ዓቃቤ ሕግ ምንም እንኳን የቀዳሚ ምርመራ ምስክሮች ሲያሰማባቸው የቆና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 109 ድንጋጌን ጠቅሶ 15 ቀናት የክስ መመሥረቻ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም፣ የተጠየቀው ሁሉ ይፈቀዳል ማለት እንዳልሆነ አስረድቷል።
በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ያሰማቸው ምስክሮችን ቃል በሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 91 ድጋጌ መሠረት የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሬጅስትራር ለሚመለከተው ፍርድ ቤት እንዲልክና ዓቃቤ ሕግም ተጠርጣሪዎቹ ከሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ እስከ መስከረም 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ክስ መሥርቶ መቅረብ እንዳለበት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ዓቃቤ ሕግ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ክስ የሚመሠርት ከሆነ ተጠርጣሪዎች በሚከሰሱበት የወንጀል ድርጊት የሚጠቀሱት የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎች ከ15 ዓመታት በላይ የሚያስቀጡ መሆናቸውን ስለጠቆሙና ፍርድ ቤቱም ስለተቀበለው፣ ተጠርጣሪዎች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉንም ፍርድ ቤቱ አስታውቋል።
በመጨረሻም አቶ ጃዋርና አቶ በቀለ እንዲገናኙ የተሰጠው ትዕዛዝ ለምን እንዳልተፈጸመ የፌዴራል ፖሊስ እስረኞች አስተዳደር ኃላፊ ምክንያቱን ገልጸው ከመዝገቡ ጋር እንዲያያይዙ ትዕዛዝ በመስጠት፣ የቀዳሚ ምርመራና የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ መዘጋቱን በማሳወቅ ከሁለት ወራት በላይ የቆየው መዝገብ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት መመለሱን አስታውቋል።
(ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
GI Haile says
የሕግ ተቋሙ ትከከለኛውን ስራ ያለ አድልዎ ይሰራል የሚለውን ምስክርነት መስማታችን እራሱ ለአገራችን ተስፋ ነው። የሕግ ተቋም ሪፎርሙ ተግባራዊ መሆኑ ትልቅ ተስፋ ነው። እናመሰግናለን። ኣቶ በቀለና ጀዋር መሃመድ የሰሩት ወንጀል በመረጃ ከቀረበ ከአስራ ኣዐምስት አመት በላይ የሚያሳስር መሆኑ እጅግ ኣስደንጋጭ ደግሞ ከደረሰው አደጋ አንፃር ደግሞ የሞት ፍርድ ፐሚያስከትልም ነው። ከ300 በላይ የሰው ነፍስ የቀጠፈ ንብረት ያወደመ ግርግር በመሆኑ ለነዚህ መሪዎች መልከም ወሬ የለም።