በመጀመሪያ “የለውጡን (ሥሌት) የሰራሁት እኔ ነኝ” አለ – በዝምታ “አዎ ነህ” ተባለ
ቀጠለና “እዚህ ሀገር ሁለት መንግሥት ነው ያለው የአብይ እና የቄሮ [የኔ]” አለ አሁንም በዝምታ “አዎ ልክ ነህ” ተባለ
መንግሥት በዝምታ ያገነነው ኢመደበኛው የጃዋር መንግሥት በንግግር ብቻ ሳይገታ ውሳኔዎችን መሻር ማሳለፍ ጀመረ – በዝምታ መንግሥትነቱ ተረጋገጠለት
እነሆ አሁን ደግሞ ለውጡ በመጣባቸው ጥቅመኛ የመንግሥት ሰዎች፣ አኩራፊዎች እና ጥገኛ ባለሀብቶች በተቀነባበረ ሴራ “ኢመደበኛው መንግሥታችሁ ሊገረሰስ ነው” ተብሎ (“የመግደል ሙከራ” በሚል ፈጠራ) 67 ንፁሃን ምስኪኖች ያልተገራው ኢመደበኛ ስልጣኑ ይፀና፤ ምሽጉም ይጠነክር ዘንድ መስዋዕት ሆነው ቀረቡለት። ይሄን ጊዜ በዝምታ አያልፉም ስንል – ተናገሩ! ምን አሉ “አንተ ዐይን ነህ – እንደ ብሌናችን እንጠብቅሃለን”… [የባሰ አታምጣ ማለት ይሄኔ ነው….]
እኔ እንደ አንድ ለኦሮሞ ህዝብ ማንነት ጥያቄ እንደሚቆረቆር እና መልስ እንዲያገኝ የሚሻ ሰው የሰፊው ኦሮሞ ህዝብ ትግል እና መስዋዕትነት እንዲህ ባለ አንድ ግለሰብ እጅ ወድቆ እና ከግለሰቡ ህልውና ጋር ተቆራኝቶ ከማየት በላይ የሚያመኝ ነገር የለም።
መንግሥትም ሆነ የኦሮሞ ልሂቃን መፍትሄ እንዲሰጡ የምጠይቀው ይህ የመርህ መፋለስ እንዲስተካከል ነው! የኦሮሞ ልሂቃን – ትግሉ ግቡን እንዲመታ የግለሰቦች አጓጉል ትከሻ መለካካትን መቋጫ አበጁለት። መደበኛው መንግሥት – መደበኛ መንግሥትነቱን ያረጋግጥ! ካላረጋገጠ የምንገዛው ተጠያቂነት በሌለው ኢመደበኛ መንግሥት ነውና የህዝብ ጥያቄ መመለሱ ቀርቶ ደህንነቱም አደጋ ውስጥ በመውደቁ ዜጎች በሰቀቀን ውስጥ ሰብዓዊ መብታቸው ተጥሶ እንዲኖሩ ይገደዳሉ። እንግዲህ ይህ እንዳይሆን ህግና ስርዓት ይከበር – መንግስት የመንግሥትነት ግዴታው ነውና ደህንነታችንን ይጠብቅ ስንል እንጠይቃለን!”
Leave a Reply