ኃይሌ ሆቴሎች በጣና ዳርቻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ግዙፍና ዘመናዊ ሪዞርት ለማልማት እንዳቀደ ታወቀ።
ጎርጎራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቀጣይ ለማልማት ካሰቧቸው ሦስት የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ነው። ኃይሌ ኩባንያው በጎርጎራ በዓይነቱ ከዚህ በፊት ከተገነቡ ሪዞርቶች ለየት ያለ ሪዞርትና የመዝናኛ ማዕከል ለመገንባት እንዳቀደ ለሪፖርተር ተናግሯል። ሪዞርቱ የሚገነባው ቀድሞ ጎርጎራ ሆቴል ተብሎ በሚታወቀው በአሥር ሔክታር ቦታ ላይ ነው። ይህ ቦታ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ማሠልጠኛና የቀድሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ያርፉበት የነበረ ሥፍራ ነው።
ፕሮጀክቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሪዞርትና መዝናኛ ማዕከል፣ ሰው ሠራሽ ባህር ዳርቻና ቪላ ቤቶች ግንባታ ያጠቃልላል። “ጎርጎራ ድብቅ ገነት ነው። ውኃው ንፁህና ጥልቀት ያለው በመሆኑ ለዋናና ለጀልባ ሽርሽርና ሌሎች የውኃ ላይ ጨዋታዎች ምቹ ነው፤” ያለው ኃይሌ፣ ኩባንያው የውጭ ባለሀብቶች በሽርክና ለማስገባት እያሰበ እንደሆነ ተናግሯል። “ብቻችንን የታለመውን ውጤት ላናመጣ እንችላለን፤” ብሏል።
ኃይሌ ሪዞርት በሕግ ጉዳዮች ላይ እየሠራ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ የመጀመርያ ዙር ንድፍ ሥራ እንደተጀመረ ታውቋል።
በተያያዘ ዜና ኃይሌ ሪዞርት በአዳማ ከተማ በ400 ሚሊዮን ብር የገነባው ባለ አራት ፎቅ ዘመናዊ ሆቴል ባለፈው ሳምንት ሥራ ጀምሯል።
በ12,000 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው አዳማ ኃይሌ ሪዞርት 110 መኝታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የልጆች መጫወቻ ሥፍራ፣ ጂምናዚየም፣ ስፓ፣ ምግብ ቤቶችና የተለያዩ መጠን ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች አሟልቶ የያዘ ነው።
የሆቴሉ ግንባታ ሦስት ዓመት እንደፈጀ የገለጸው ኃይሌ፣ ሆቴሉ አንድ ዘመናዊ ሆቴል ሊኖረው የሚገባው አገልግሎቶች ሁሉ እንዲማሉ መደረጉን ገልጿል። ፕሮጀክቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገበት ተናግሯል። ኃይሌ ሪዞርት የማስፋፊያ ሥራ ለማከናወን ከአጠገቡ የሚገኘውን ባዶ ቦታ እንዲሰጠው ለአዳማ ከተማ አስተዳደር አመልክቷል።
“ምክር ቤቱ የሠራነውን ሥራ ተመልክቶ ከሆቴሉ አጠገብ ያለውን ባዶ ቦታ ቢፈቅዱልን ቅንጡ የእንግዳ ማረፊያ ቤቶች እንገነባበታለን፤” ብሏል። የአዳማው ሆቴል ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር ለ300 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ታውቋል።
ኃይሌ ሪዞርት ሰባት ሆቴሎች ያሉት ሲሆን፣ 1,400 ሠራተኞች ያስተዳድራል። በቅርቡ የሐዋሳና አርባ ምንጭ ሆቴሎቹ የትሪፕ አድቫይዘር 2020 ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል።
ኃይሌ ሪዞርት ሦስት ሆቴሎችን በአዲስ አበባ፣ ሶዶና ኮንሶ በመገንባት ላይ ሲሆን፣ በጎርጎራና ደብረ ብርሃን ዘመናዊ ሆቴሎች ግንባታ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል። “የመንግሥት ቢሮዎች ቢሮክራሲን በመቀነስ የተቀላጠፈ አገልግሎት ቢሰጡን ተጨማሪ የኢንቨስትንመንት ፕሮጀክቶች ቀርፀን ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። የአርባ ምንጭ ሪዞርት ግንባታ አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ብቻ ነው የፈጀብን። አገራችን ትልቅ የቱሪዝም ዕምቅ ሀብት አላት። ከእኛ የሚጠበቀው ጠንክሮ መሥራት ነው፤” ብሏል። ቀጣዩ የኢንቨስትመንት መዳረሻው ደብረ ብርሃን እንደሆነች ኃይሌ አረጋግጧል። (ቃለየሱስ በቀለ፤ ሪፖርተር)
Leave a Reply