• Skip to primary navigation
  • Skip to content
  • Skip to primary sidebar

Goolgule

Ethiopian News

  • ስለ እኛ/about
  • አስፈንጣሪዎች/links
  • ቤተ መዝገብ/archives
  • አድራሻችን/contact
Header Banner Image
  • Home
    ዋና ገጽ
  • Editorials
    ርዕሰ አንቀጽ
  • News
    ዜና
  • Socio-Political
    ማኅበራዊ-ሽከታ
  • Religion
    ሃይማኖታዊ
  • Interviews
    እናውጋ
  • Law
    የሕግ ያለህ
  • Opinions
    የኔ ሃሳብ
  • Literature
    ጽፈኪን
    • Who is this person
      እኚህ ሰው ማናቸው?
  • Donate
    ለባለድርሻዎች

የእነ እስክንድር ክስ እንዲሻሻል ተጠየቀ

September 23, 2020 11:08 pm by Editor Leave a Comment

ዓቃቤ ሕግ በመሠረተባቸው ክስ የሕዝብ ሰላምንና የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል፣ ሥልጣንን በኃይል ለመያዝና የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተዘጋጅተዋል በማለት የዋስትና መብታቸው እንዳይፈቀድላቸው መከራከሩን በመቃወም ለፍርድ ቤቱ ምላሽ የሰጡት እነ አቶ እስክንድር ነጋ፣ መንግሥት ወይም ዓቃቤ ሕግ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደኅንነት የሚያስብ ከሆነ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው፣ በመጪው አገራዊ ምርጫ እንዲሳተፉ መደረግ እንዳለበት ለፍርድ ቤት ተናገሩ።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ዋስትና እንዲከበርላቸው የጠየቁት፣ የተመሠረተባቸውን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብር ተግባራትና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አንደኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት መስከረም 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ካነበበላቸው በኋላ፣ ስለመብት የሚያነሱት ጥያቄ ካላቸው እንዲናገሩ ጠይቋቸው ነው።

እነ አቶ እስክንድር የተከሰሱት በመጪው አገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ ባሉበትና ሕዝቡም ድምፁን ሊሰጣቸው ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ሳለ መንግሥት ውጥረት ውስጥ በመግባቱ መሆኑን ጠቁመው፣ ምርጫው በሕዝብ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለሕዝብ ሰላምና ለአገር ደኅንነት የሚታሰብ ከሆነ ፍርድ ቤቱ ዋስትናቸውን አክብሮላቸው በምርጫው መሳተፍ እንዲችሉ ጠይቀዋል። ያ የማይሆን ከሆነ ግን ምርጫውም ቅቡልነት እንደማይኖረውና የሕዝብ ሰላምም የሆነ የአገር ደኅንነት እንደማይኖር ተናግረዋል።

እነ አቶ እስክንድር የዋስትና መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት ደጋግመው ፍርድ ቤቱን የጠየቁት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊትና በተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ እስከ 25 ዓመታት ሊያስቀጣቸው ስለሚችል የዋስትና መብት ሊፈቀድላቸው እንደማይገባ በመከራከሩ ነው።

ዓቃቤ ሕግ የተከሳሾቹን የዋስትና ጥያቄ በሚመለከት ባቀረበው የመቃወሚያ መከራከሪያ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ዋስትና ሕገ መንግሥታዊና መሠረታዊ መብት ነው። ቢሆንም ግን በሕግ አግባብ ሊከለከል እንደሚችል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) ተደንግጓል። በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 (1) ድንጋጌም ስለሚከለከልባቸው ምክንያቶች በግልጽ ተቀምጧል። ድንጋጌው የተከሰሰ ሰው በፈጸመው የወንጀል ድርጊት ሰው ከሞተ፣ የሚሞት ከሆነ፣ ከፍተኛ የሆነ የሀብት ውድመት መድረሱ ከታወቀ እንደሚል ጠቅሶ፣ ተከሳሾቹም በተሳተፉበት የወንጀል ድርጊት 14 ሰዎች መሞታቸውንና ከ187 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን በክሱ መጥቀሱን አስረድቷል።

በመሆኑም የወንጀሉ ድርጊት እስከ 25 ዓመታት የሚደርስ ፅኑ እስራት ሊያስቀጣቸው እንደሚችልና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 67 (ለ) ድንጋጌም ለዋስትና መከልከያ ምክንያቶችን ካስቀመጠው ድንጋጌ አንፃር፣ የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት ስለማይኖረው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል።

ተከሳሾቹ የሕዝብ ስስ የሆነንና በቀላሉ ስሜት ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሃይማኖትንና ዘርን መሠረት ያደረገ የአመፅና የሽብር እንቅስቃሴ በማድረግ “ሥልጣንን በኃይል እንይዛለን፣ ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት አይኖርም፤” በማለት ሕዝብን ለከፍተኛ ዕልቂት የሚያነሳሳና አገርን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት መፈጸማቸውን አስረድቷል።

በመሆኑም ዋስትና ቢፈቀድላቸው ሕግ አክብረው ይገኛሉ የሚል ግምት ስለሌለው፣ የዋስትና ጥያቄውን በድጋሚ ተቃውሟል። የዋስትና መብት እንዴት መከበር እንዳለበትም የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ እንደሰጠበትም ቅፅና የመዝገብ ቁጥር ጠቅሶም አስረድቷል።

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞትን ምክንያት በማድረግ በትግራይና በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ካስተላለፉት እርስ በርስ የሚያጨራርስ የአመፅ ጥሪና ተልዕኮ አንፃርም ወንጀሉ ከባድ በመሆኑ፣ ከአጠቃላይ የሕግ ድንጋጌና የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ዓላማ አኳያ ሕግ መተርጎም እንዳለበት፣ የሕዝብንና የአገርን ደኅንነት ከመጠበቅ አንፃርም ዋስትና መፈቀድ እንደሌለበት ዓቃቤ ሕግ ደጋግሞ በማውሳት ተከራክራል።

በሁለት ጠበቆች የተወከሉት አቶ እስክንድር፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ሥዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሴ የዓቃቤ ሕግ ክርክርን በመቃወም ተከራክረዋል። ጠበቆቹ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ ዓቃቤ ሕግ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 19(6) ድንጋጌ ጠቅሶ ዋስትና እንደሚከለክል አሳውቋል። ዓቃቤ ሕግ የጠቀሰው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ትክክል ቢሆንም፣ ያ የሚሆነው በልዩ ሁኔታዎች እንጂ ሁሉንም ተከሳሾች የሚያጠቃልል አለመሆኑን ተናግረዋል። የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 63 (1) ድንጋጌ መተርጎም ያለበት፣ ከሕገ መንግሥቱ እንግሊዝኛ ትርጉም (. . . In Exceptional Circumstances Prescribed by Law) የሚለውን አጣምሮ መሆን እንዳለበትም አክለዋል።

በሌላ በኩል የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 63 (1) ድንጋጌን ሕገ መንግሥቱ በዝምታ እንደሻረው ጠቁመው፣ ምክንያታቸው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የፈቀደውን የዋስትና መብት የሥነ ሥርዓት ሕጉ ሊሽረው አለመቻሉ መሆኑን ጠቁመዋል። ዓቃቤ ሕግ እንዳለው፣ ትርጉም ተሰጥቶት ዋስትና መከልከያ ከተደረገ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን መሆኑንም አክለዋል።

ኢትዮጵያ መሠረታዊ መብቶችን በሚመለከት ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ተቀብላ በማፅደቅ የሕጓ አካል ማድረጓን አስታውሰው፣ በደንበኞቻቸው ላይ የተጠቀሰው ዋስትና ማስከልከያ አንቀጽ መተርጎም ያለበት ከስምምነቶቹ ጋር በተጣጣመ መንገድ መሆኑንም ጠበቆቹ ተናግረዋል።

ዋስትና የሚከለክለው ተከሳሹ ከፈጸመው የወንጀል ድርጊት ጋር በተያያዘ ሳይሆን  በዋናነት ከባህሪው ጋር በተገናኘና አደገኛ መሆኑ ሲረጋገጥ እንደሆነ የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ደንበኞቻቸው (እነ አቶ እስክንድር) ቋሚ አድራሻ ያላቸው፣ በመሠረቱት የፖለቲካ ድርጅት አገርና ሕዝብ ለማገልገል እየሠሩና በሕዝብ አመኔታን ያተረፉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር ካልሆነ በስተቀር በደረቅ ወንጀል ተጠርጥረውና  ተሳትፈው የማያውቁ በመሆናቸው፣ የዋስትና  መብታቸው ተከብሮላቸው ከእስር ቢፈቱ ሌላ ወንጀል ሊፈጽሙ ወይም ከአገር ሊወጡ የማይችሉ መሆናቸውንም አክለዋል። ዓቃቤ ሕግ የዋስ መብትን በሚመለከት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ትርጉም እንደሰጠበት የጠቀሳቸው ውሳኔዎች፣ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው፣ የተለያዩ ሌሎች ትርጉሞች የተሰጡባቸውና ደንበኞቻቸው ከተከሰሱበት ክስ ጋር የማይገናኝ የክስ ሒደት ላይ የተሰጡ ውሳኔዎች በመሆናቸው ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል።

ዓቃቤ ሕግ ገና ክስ አቅርቦ ሳለ እስከ 25 ዓመታት ያስቀጣል ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ በቀረበው ክስ ላይ ማስረጃ ቀርቦ፣ ተመዝኖና ከሕጉ ጋር ተገናዝቦ ፍርድ ቤቱ ትርጉም ሳይሰጥበት የደንበኞቻቸውን ነፃ ሆኖ የመገመት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጥስ በመሆኑ፣ ተገቢ አለመሆኑንና ሊታረም የሚገባው መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲገነዘብላቸው ጠይቀዋል። ክሱ ተከሳሾቹን ከፖለቲካ ገለል ለማድረግ የተዘጋጀና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ክስ መሆኑንም አስረድተዋል።

ዓቃቤ ሕግ የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዲስ አዋጅ ቁጥር 1176 አንቀጽ 6(2) ድንጋጌን ጠቅሶ፣ አቶ እስክንድርንና በክሱ ስማቸው ቢጠቀስም በቁጥጥር ሥር አለመዋላቸው የተገለጸውን አቶ አሸናፊ አወቀና አቶ ፍትዊ ገብረ መድኅን (አቶ እስክንድር ሕዝብ ለማደናገር የተጠቀሰ ተከሳሽ ነው ብለውታል) የተከሰሱበት የወንጀል ድርጊት፣ “የሽብር ወንጀል ለመፈጸም መዘጋጀት” የሚል በመሆኑ፣ የተፈጸመ ወንጀል እንደሌለ ከሚያሳይ በስተቀር ዋስትና የሚያስከለክል ተጨባጭ የተደረገ ነገር ስለሌለ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል። ይኼ ሆን ተብሎ የፍትሕ ሥርዓቱን ለመፈታተንና በፍርድ ቤቱ ላይ ጫና ለመፍጠር የቀረበ ክስ መሆኑንም አክለዋል። “ወንጀል ለመፈጸም ሲዘጋጁ ነበር” ተብሎ መሠረታዊ የሰዎች መብት መገደብ እንደሌለበትም ጠቁመዋል።

የሦስት ልጆች አባት መሆኑን፣ ቋሚ አድራሻ ያለውና የሕዝብ አደራ ተቀብሎ ከዳር ለማድረስ እየሠራ መሆኑን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲያስከብርለት የጠየቀው ተከሳሽ ዳግም ስንታየሁ ቸኮል ነው። ሃይማኖትና ዘርን መሠረት ያደረገ ብጥብጥና ዕልቂት እንዲፈጠር፣ ሕዝብ ሰላም እንዲያጣና የአገር ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በክሱ መጠቀሱን አስታውሶ፣ ዓቃቤ ሕግ ካለው በተቃራኒ የሚሆነው እነሱ በመታሰራቸው መሆኑን ገልጿል። የእነሱ መታሰር ሁከትና ብጥብጥ እንዲቀጥል የሚያደርግ እንጂ የሚያቆም እንዳልሆነም አክሏል። መታሰራቸው አገር ከመበጥበጥ ባለፈ እንዲረጋጋ እንደማያደርግም ጠቁሟል።

ሁሉም ተከሳሾች ቋሚ አድራሻ ያላቸው፣ የቤተሰብ ኃላፊና በሕጋዊ መንገድ ተመዝግቦ በሚሠራ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ የሚሠሩ ሕጋዊ ነዋሪ መሆናቸውን አስረድቶ፣ ዋስትናቸው እንዲከበርላቸው ደጋግሞ ጠይቋል።

ጌትነት በቀለ የተባለው ተከሳሽ የቀረበበት ክስ ለወጣቶች ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ቃል በመግባት፣ ለረብሻና ለአመፅ እንዲወጡ መመልመሉንና ማደራጀቱን የሚገልጽ መሆኑን ጠበቆቹ ገልጸዋል። ቄሮዎች በሌሉበት አብያተ ክርስቲያናትን ሊያቃጥሉ እንደሆነ በመግለጽ ነዋሪው እንዳይረጋጋ፣ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ግጭት እንዲነሳ መቀስቀሱን ዓቃቤ ሕግ በክሱ መጥቀሱንና ይኼንንም ሲያደርግ የፊትና የኋላ ሰሌዳ ቁጥሩ በጭቃ የተሸፈነ ላዳ ታክሲ በመጠቀም መሆኑንም ጠበቆቹ አስታውሰው መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

የዋስትና መብት ጉዳይ የሚመለከተው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ፣ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌና ከቀረበው ክስ ሁኔታ አንፃር መሆኑን ጠቁመው፣ በደንበኛቸው ላይ የቀረበው ክስና የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ እንደማይገናኙ ገልጸዋል። የክሱ ይዘት አይደለም ዋስትና ማስከልከል ተከራክሮ ለማስቀጣት የሚያስችል አለመሆኑንም ጠቁመዋል። የተከሰሰ ሰው በሙሉ ዋስትና ይከለከላል ማለት እንዳልሆነና ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌንም የሚጥስ መሆኑን ተናግረዋል።

ብሔርን ከብሔር ወይም ሃይማኖትን ከሃይማኖት የሚያጋጭ እንቅስቃሴ በማድረግ የተከሰሰ ሰው ዋስትና እንደሚከለክል በግልጽ የተደነገገ ሕግ እንደሌለ ጠቁመው፣ የመኪና መስታወት መስበር የሚያስቀጣው 450 ሺሕ ብር በመሆኑ ዋስትና ሊያስከለክለው ይችላል ማለት ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ጠበቆቹ ተከራክረዋል።

የቅጣት ጣሪያን መሠረት አድርጎ ዋስትና እንዲከለከል ክርክር ማቅረብ፣ የሰውን ልጅ መቀጣጫ ማድረግ መሆኑን የገለጹት ጠበቆቹ፣ ክስና አንቀጽ ተዛምዶ በሌለበት ሁኔታ ከአሥር እስከ 25 ዓመታት ያስቀጣል ስለተባለ ብቻ መሠረታዊ የሆነው የዋስትና መብት ሊከለከል እንደማይገባ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። ደንበኛቸው የሚጠየቀው በ450 ሺሕ ብር ቢሆን እንኳን ዋስትና ሊከለከል እንደማይችል፣ ዓቃቤ ሕግ የተረጋገጠ የሒሳብ ግምት ባላቀረበበት “ይኼንን ያህል” በሚል ግምት ለማስከልከል መከራከር ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመው፣ የደንበኛቸው ዋስትና እንዲከበር ፍርድ ቤቱን ደጋግመው ጠይቀዋል። በደንበኛቸው ላይ የተጠቀሰው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 240 መነሻ ቅጣቱ አሥር ዓመታት መሆኑንና መዳረሻው 25 ዓመታት መሆኑን በማስታወስ፣ ዓቃቤ ሕግ ገና ክርክር ሳያደርግና ከ15 ዓመታት በላይ ማስቀጣቱን ሳያረጋግጥ “25 ዓመታት ይፈረድባቸዋል” በማለቱ ያቀረበው ክስ አመክንዮአዊም ሕጋዊም አለመሆኑን ተናግረዋል። በወንጀል ድርጊት ተጠርጥሮ የተከሰሰን ሰው መረጃና ማስረጃ መርምሮና መዝኖ ቅጣት ሊወስን የሚችለው ፍርድ ቤት ሆኖ ሳለ፣ የተከሳሹን ነፃ ሆኖ የመገመት መብት በመተላለፍ ይፈረድበታል ማለት ተገቢ እንዳልሆነም አስረድተዋል።

ዜጋን ማሰርና በእስር ቤት እንዲማቅቅ ማድረግ እውነተኛ ፍትሕ ለማስፈንና የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሳለጥ ከምትንቀሳቀስ አገር የማይጠበቅና ተገቢም እንዳልሆነ የገለጹት ጠበቆቹ፣ የዋስትና መብትን መገደብ ሕገ መንግሥቱን መጣስ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር መንግሥትን የሚያስጨንቅ አጀንዳ ማንሳታቸው፣ ለእስር እንደዳረጋቸው ድጋሚ ዕድል ሲሰጠው የገለጸው አቶ ስንታየሁ፣ የመንግሥትን ሥራ እንዲሠሩ የተመደቡ የከተማዋ ኃላፊዎች ሕገወጥ የመሬት ወረራ ሲደረግ ዝም ማለታቸውን ማጋለጥና በሕገወጥ መንገድ መታወቂያ ሲያድሉ ማጋለጥና መቃወም “በኃይል ሥልጣን ለመያዝ ተንቀሳቅሰዋል” ሊያስብል እንደማያስችል አስረድቷል።  

መንግሥትን የሚያስጨንቅ አጀንዳ ማንሳታቸው “የጦስ ዶሮ” እንዳደረጋቸው ጠቁሞ፣ ማስጨነቅና መታገል ሥራቸው በመሆኑ የሕግ አንቀጽ ባልተጠቀሰበት ሁኔታ ከ15 ዓመታት በላይ ስለሚያስቀጣ በሚል የዋስትና መብት መከልከል ተገቢ ባለመሆኑ እንዲፈቀድላቸው ጠይቋል።

ዓቃቤያን ሕግ በቅርቡ የተሾሙ ከመሆናቸው አንፃር ከፍተኛ ጫና ውስጥ መሆናቸውን እንደሚረዱ የገለጸው አቶ ስንታየሁ፣ ፍርድ ቤቱ ግን “ይኼ ታሪካዊ የክስ ሰነድ በመሆኑ ሕግና ሕጉን ብቻ ተከትሎ በአግባቡ እንዲያይልን እንጠይቃን፤” ብሏል። ዓቃቤ ሕግ ዋስትና እንድንከለከል ቢከራከርም ወደፊት ዋጋ እንደሚያወራርድበት አውቆ በትክክል መሥራት እንዳለበት በመጠቆም፣ “የምንደፍረው ሕዝብም ሆነ የምንጣላው ሃይማኖት የለም፤” ሲልም አክሏል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በተጠየቀው የዋስትና መብት ላይ ብይን ለመስጠትና በክሱ ላይ የመጀመርያ መቃወሚያ ለመቀበል፣ ለመስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል።

መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. የዋለው ችሎት ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን ክስ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጠ

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. በእነ አቶ እስክንድር ነጋ፣ በአቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ በወ/ሮ ቀለብ ስዩም፣ በአስካለ ደምሴና በጌትነት በቀለ ላይ የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግሥት ላይ የሚደረግ ወንጀል ክስ ያቀረበባቸው ቢሆንም፣ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤት ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ቀደም ብሎ በነበረ ችሎት በከሳሽ ዓቃቤ ሕግና በተከሳሾች መካከል፣ የዋስትና መብትን አስመልክቶ በተደረገ ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት ነበር።

ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ክሱን ሲመለከተው ብሔርንና ሃይማኖትን ምክንያት በማድረግ በተፈጠረ ግጭት፣ የሰው ሕይወትና ንብረት እንደጠፋና እንደወደመ የገለጸ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ተከሳሽ ምን፣ እንዴትና የት እንደፈጸመ እንዳልተገለጸ ከክሱ መረዳቱን አስታውቋል።

ዓቃቤ ሕግ በክስ ማጠቃለያው ላይ በተለያዩ የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢዎች ብሎ፣ ሰኔ 23 እና 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን የገለጸ ቢሆንም፣ በእያንዳንዱ ቀን ምን ያህል ሰው እንደ ሞተ፣ ምን ያህል ንብረት እንደ ወደመ፣ ማን በየትኛው ቀን ምን እንዳጠፋ እንደማይገልጽም አክሏል።

ዋስትና ሕገ መንግሥታዊ መብት መሆኑን ያስታወሰው ፍርድ ቤቱ፣ ዋስትናን ለመፍቀድ ወይም ለመከልከል ግን የቀረበው ክስ ግልጽና ያንን ትዕዛዝ ሊያሰጥ የሚችል መሆን እንዳለበትም ተናግሯል። በመሆኑም ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ድፍን ያለና በዋስትና መብት ላይ ፍርድ ቤቱ ሊል የሚፈልገውን እንዲል የሚያስችለው ሆኖ ስላላገኘው፣ ዓቃቤ ሕግ ሦስት ነገሮችን ግልጽ በማድረግ ክሱን አሻሽሎ እንዲያመጣ አስታውቋል። ይኸውም ሰኔ 23 እና 24 ቀን በእያንዳንዱ ቀን የተፈጸመውን ድርጊት ለይቶ፣ በየቀኑ እንዲገልጽ፣ ቦታው የትና በየትኛው ክፍለ ከተማና ወረዳ እንደተፈጸመና የትኛው ድርጊት በማን እንደተፈጸመ ለይቶ በማስቀመጥ፣ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 102 እና 112 ድንጋጌ መሠረት ክሱን አሻሽሎ ለመስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን ሰጥቶ እንደጨረሰ አቤቱታ ያቀረበው አቶ እስክንድር፣ በክስ መዝገባቸው የተካተተው ሰባተኛ ተከሳሽ ፍትዊ ገብረ መድኅንን በሚመለከት፣ ቀደም ብሎ ያነሳውን ጥያቄ በድጋሚ አንስቷል። ይህም ግለሰቡ ትክክለኛ ተከሳሽ ሳይሆን ሕዝብን ለማደናገር፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ያቀረበው እንጂ እንደዚህ የሚባል ሰው እንደ ሌለ አንስቶ፣ እንዲጣራለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር። በወቅቱ ዓቃቤ ሕግ ተከሳሹ የተለያየ ስም ይጠቀም እንደነበርና ከማረሚያ ቤትም ያመለጠና የተያዘ መሆኑን ገልጾ ስለነበር፣ አቶ እስክንድር ተከሳሹ ማረሚያ ቤት የነበረ ከመሆኑ አንፃር፣ ዓቃቤ ሕግ አሁን በክስ መዝገቡ የጠቀሰው ስም ትክክል መሆን አለመሆኑን ማጣራቱን ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ ግን ምላሽ ሳይሰጠው ለቀጣይ ቀጠሮ ይጠየቃል በሚል አልፎታል።

ሌላው አቶ እስክንድር ያነሳው ጥያቄ ባለቤቱና ልጁ ከአገር ውጪ ስለሚኖሩ በስልክ እንዲያገኛቸው ማረሚያ ቤቱ እንዲያመቻችለት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል።

ወ/ሮ ቀለብ የተባለችው ተከሳሽ ደግሞ ሕፃን ልጅ እንዳላትና እንደምታጠባ ገልጻ፣ በምርመራ ወቅት ፖሊስ ጣቢያ ቤተሰቦቿ እያመጡላት ታጠባ እንደነር አስታውሳ፣ አሁን ግን ማረሚያ ቤት ማስገባት ስለከለከለ ልጇ እያለቀሰችና ምግብ አልበላ ብላ ቤተሰቦቿን እያስቸገረች በመሆኑ እንዲፈቀድላት ጠይቃለች። ሌላኛው ልጇም ለአንድ ዓመት ታስራ በነበረበት ጊዜ ረስቷት ስትፈታ ከብዙ ችግር  በኋላ ሊቀርባት መቻሉን በማስታወስ፣ አሁን ደግሞ ስትርቀው ስለተቸገረ እሱም አብሮ እየመጣ እንዲጠይቃት እንዲፈቀድላት ፍርድ ቤቱን ጠይቃለች። የጀርባ አጥንት ሕመም እንዳለባት አስረድታ፣ ማረሚያ ቤቱ ወፍራም ልብስ ስለከለከላት በቅዝቃዜ ወቅት እያመማት በመሆኑ እንዲፈቀድላትና እመጫትም በመሆኗ ቤተሰቦቿ ምግብ እንዲያመጡላት እንዲፈቀድላት ጠይቃለች።

አቶ ስንታየሁ ቸኮልም ባቀረበው አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ማረሚያ ቤቱ በሕግ ለታራሚዎች ማቅረብ ያለበት ወይም እንዲያገኙ ማድረግ ያለበትን አገልግሎት መከልከላቸውን ገልጿል። በእነሱ ምክንያትም ሌሎች ተከሳሾችም መከልከላቸውን ገልጿል። ይህንን መከልከልና ማሰር “የሰማዕታቱ እስጢፋኖስ እስር” ማለት እንደሆነና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት የሚያከብሩበትና ሥርዓት የሚያከናውኑበት ቦታ ስለሚያስፈልጋቸው እንዲሠራላቸውም ጠይቋል። ሌሎቹም ተከሳሾች የመብት ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱ አቤቱታዎቹን ካዳመጠ በኋላ ተከሳሾቹ በቤተሰብ የመጎብኘት፣ ሕክምና የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ገልጾ፣ ማረሚያ ቤቱ እንዲፈጽም ትዕዛዝ ሰጥቷል። አቶ እስክንድርም ከቤተሰቡ ጋር በስልክ እንዲገናኝ ማረሚያ ቤቱ እንዲያመቻች ትዕዛዝ በመስጠት፣ ሌላ አቤቱታ ካላቸው በጽሑፍ እንዲያቀርቡና ዓቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ ካቀረበ በኋላ በመብት ጉዳይ ላይ በሚነሱ ጥያቄዎችና አቤቱታዎች ላይ በስፋት መከራከር እንደሚቻል አስታውቋል።

(ታምሩ ጽጌ፤ ሪፖርተር)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Print Friendly, PDF & Email
facebookShare on Facebook
TwitterTweet
FollowFollow us

Filed Under: Law, Middle Column Tagged With: chilot, eskinder, jawar massacre, ችሎት

Reader Interactions

Leave a Reply Cancel reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Primary Sidebar

በማኅበራዊ ገጾቻችን ይከታተሉን

Follow by Email
Facebook
fb-share-icon
Twitter
Tweet

Recent Posts

  • ሤራ አክሻፊው ጎንደር ለሦስተኛ ጊዜ ታሪክ ሠራ May 10, 2023 09:25 am
  • ማር በከፍተኛ ደረጃ የኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል May 9, 2023 09:24 am
  • ኦነግ በኦሮሚያ ሪፈረንደም እንዲካሄድ መጠየቁ ለሰላም ንግግሩ ዕንቅፋት ሆነ May 4, 2023 01:12 am
  • መረጃ ቲቪ ያጋራው አሳሳች መረጃ May 2, 2023 12:37 pm
  • “ከፈጣሪ በታች መከላከያ የሁላችን ዋስ ጠበቃ ነው፤ ትልቅ ይቅርታ እንጠይቃለን” April 13, 2023 10:19 am
  • በትግራይ የ”ልጆቻችን የት ናቸው?” ጥያቄ እየተሰማ ነው April 13, 2023 08:56 am
  • በትህነግ የፈረሰው የአክሱም ኤርፖርት ያስከተለው ዘርፈብዙ ኪሣራ April 13, 2023 03:21 am
  • “የከተማው ነዋሪ በመሰላቸቱ ተፈናቃዮች ከፍተኛ የምግብ ችግር” ገጥሟቸዋል April 12, 2023 09:23 am
  • ከዕድሜ ልክ እስከ 20 ዓመት ቅጣት ተበይኖባቸዋል April 11, 2023 02:58 pm
  • የኡጋንዳ የክልሎች ሚኒስትር በቆርቆሮ ሌብነት ተጠርጥረው ታሰሩ April 10, 2023 03:59 pm
  • ታከለ ከተነሳ በኋላ የመዐድን ሌቦች እየተያዙ ነው April 6, 2023 02:53 pm
  • አገር ለማተራመስ ያለመ የምሁራን፣ የሚዲያ ባለቤቶችና አክቲቪስቶች ህቡዕ ቡድን ተያዘ April 4, 2023 10:07 am
  • በ10 ዓመት ውስጥ ከ44 ቢሊየን ዶላር በላይ ሸሽቷል April 4, 2023 09:26 am
  • አየር ጨብጦ አሁን ያለውን መንግሥት ከሥልጣን ልቀቁ አይሆንም March 29, 2023 09:47 am
  • ሦስት ትውልድ የበላ የሐሰት ትርክት! March 23, 2023 11:59 am
  • “ሽብርተኝነቱን ማንሳቱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለማቋቋም ይረዳል” – ዶ/ር ጌዲዮን March 22, 2023 05:05 pm
  • አስነዋሪ ተግባር ሲፈጸምባቸው የነበሩ የምሽት ክለቦች ተዘጉ March 22, 2023 12:57 pm
  • ህወሓትን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ የወሰናችሁ ሁሉ ተጠያቂዎች ናችሁ – ኢዜማ March 22, 2023 12:06 pm
  • የኡጋንዳ ፓርላማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጸደቀ March 22, 2023 12:44 am
  • በጌታቸው ምርጫ ማግስት በትግራይ ሕዝባዊ ዐመፅ ተጀመረ March 21, 2023 11:01 pm
  • በትግራይ ሥልጣንና ንጉሥ ፈጣሪነት ከአድዋ ወደ ራያ ተሻገረ March 19, 2023 03:45 am
  • ኤርሚያስ ከጌታቸው ረዳ ጋር ምሥጢራዊ የስልክ ግንኙነት ነበረው March 19, 2023 02:44 am
  • እየተገባደደ ያለው የምስራቅ አፍሪቃ የትራንስፖርት ኮሪደርና ለውጥ የናፈቃት ኤርትራ March 15, 2023 04:44 pm
  • በባዶ እግር በሮም አበበን ለመድገም March 15, 2023 01:40 pm

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣን በኢሜይል ለማግኘት ይመዝገቡ Subscribe to Golgul via Email

ከዚህ በታች ባለው ሣጥን ውስጥ የኢሜይል አድራሻዎን ያስገቡና “Subscribe” የሚለውን ይጫኑ፡፡
Enter your email address to receive notifications of new posts by email.

Copyright © 2023 · Goolgule