ህወሐት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል መቀሌ ላይ ከሚገኘዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና በጠገዴ አርማጭሆ በኩል ደግሞ በአማራ ልዩ ኃይል አባላትና ገበሬዎች ላይ የወረራ ሙከራ እንዲሁም በተከዜ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ጥበቃ ላይ በነበሩ የፌደራል ፖሊሰ አባላት ጥቃት መሰንዘሩ ይታወሳል።
ከጥቃቱ የተረፉት 11 የፌደራል ፖሊስ አባላት ዛሬ ህዳር 01/2013 ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ዞን መቀመጫ ደባርቅ ከተማ ገብተዋል።
ጥቃቱ እንዴት እንደተፈጸመ የሰሜን ጎንደር ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አናግሯቸዋል። ካነጋገራቸዉ የፖሊስ አባላት መካከል ዋና ሳጅን ወልደሰንበት ካፊሶ እንዲህ ይላል።
ምንም ይፈጠራል ብለን ባላሰብነዉና ባልጠበቅነዉ ሁኔታ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም 4፡15 ከ250 እስከ 300 የሚሆኑ የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት በብሬንና በዲሽቃ የታገዘ ተኩስ ከፈቱብን። እኛም የመከላከል ሙከራ አድርገናል፤ የተጎዱ አባላቶቻችንም ለማውጣት ብንሞክርም አልቻልንም። ራሳችንን ለማትረፍ ተታኩሰን አምልጠናል ብለዋል።
ኮንስታብል ኪዳነማርያም ጥጋቡ አብረዉን የነበሩት የትግራይ ተወላጅ የፌደራል ፖሊስ አባላትና አመራሮች መቼ ጥቃት መፈጸም እንዳለባቸዉ፣ በየት በኩል መግባት እንደሚችሉ፣ ምሽጋችንና የመሳሪያ ክፍሉን ቀድመዉ መረጃ ስላደረሷቸዉ ባላሰብነዉና ባልጠበቅነዉ ሁኔታ አብረዉን ሲኖሩና አብረዉን ሲበሉ በነበሩ አባላት ክህደት ተፈጽሞብናል ሲሉ ገልፀዋል። (የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን)
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ
Leave a Reply