በያዝነው ሳምንት … በአብዛኛው የሀበሻ መገናኛ መንደር፣ በማህበራዊ ድህረ ገጽ ዋንኛ መድረክ በ Facebook መስኮት አንድ መሪር መርዶ ተሰምቷል! የትሁት ፣ አስተዋይና አርቆ አስተዋዩ በጎ ሰው ፣ የጎልማሳው የአቡኬ አሌክስ ህልፈት!!! የአቡኬ አሌክስ በድንገት መለየት ጥልቅ ሀዘናን ሁላችንም አንገብግቦናል! “ከሞቱ አሟሟቱ ” እንዲሉ አቡኬ ባንድ ጀንበር ታይቶ በርቶ ፣ ባንዱ ጀንበር ሳይታሰብ ጠፍቶብናል! እናም በቅርብ ከሚያውቁት ፣ ቤተሰብ ዘመድ አዝማድ ጓደኞች እኩል በስራው በዝና የምናውቀው በሀዘኑ አዝነን ከፍቶናል!
የጎልማሳው በጎ ሰው አቡኬ አሌክስ መረጃዎች የቅርብ ተከታታይ የሆነችው ባለቤቴ በህልፈቱ ጥልቅ ሀዘን የተሰማቸው መካከል አንዷ ናት ፣ ስለአቡኬ ስትገልጽ እንዲህ ብላኛለች ” አቡኬ ብሩህ አዕምሮ የነበረው ፣ ኢትዮጵያውያንን በዘር በሐይማኖታዊ ሳይለየን በህብረት መኖር አለብን ብሎ የሚመክር የሚዘክር ድንቅ ሰው ነበር ፣ አቡኬ !” ብላኛለች … አዎ ! ሁላችንም በፊስ ቡክ የመረጃ መለዋዎጫ መድረክ ሃሳቡን በነጻነት አንሸራሻሪ ፣ መረጃ አቀባይና ተቀባይ ፣ ሩቅ አሳቢ መልካም ሰው አቡኬ አሌክስን አጥተናል … በእርግጥም ተጎድተናል …
እንደኔ እንደኔ አቡኬ ሲለየን ያመመን ፣ አቡኬ እንደ ተመራማሪ ታዋቂ የሀገር አውራ ሰው መለየት ያስቆጠረን ፣ የብዙሃኑ መሪር ሃዘን የመሆኑ የታየን እውነታና ሚስጥር አለው ! ለእኔ የአቡኬ መልካምነት ገኖ መውጣት ውስጠ ምስጥሩ … ጎልማሳው ማህበራዊ መገናኛዎቻችን በመልካም ጎኑ ተጠቃሚ ፣ የሀገርና የህዝብ የሁለትዮሽ እሴቶታችን መሰረት የሆነው የህበረታችን አድማቂ ፣ መረጃዎችን አቅራቢና አስተላላፊ በመሆን ጊዜውን ለቁም ነገርና ለመልካም ስራ ያዋለ አርቆ አሳቢ በመሆኑ ይመስለኛል ! አቡኬ አሌክስ …
የአቡኬ ሳይታሰብ በድንገት የህይዎት ጉዞ ፈጻሚ የብዙዎቻችን ቅስም ሰባሪ አሳዛኝ ሀዘንና መርዶ ነው፣ በህልፈቱ ለተጎዱት ለመላ ቤተሰቡ ፣ ለጓደኞቹና ዘመድ አዝማድ አድናቂዎቹ መጽናናትን እመኛለሁ !
ነፍስ ይማር አቡኬ
ነቢዩ ሲራክ
ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓም
Leave a Reply