ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝ “ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ” የተሰኘው በዮሴፍ ገብሬ እየተዘጋጀ ኢ.ቢ.ኤስ በሚባል የኬብል ቴሌቪዥን (የመስመር ምርዓየ-ኩነት) የሚቀርበው የጥዕይንተ ወግ ዝግጅት ነው፡፡ ወደዚህ ትዕንተ ወግ ጉዳይ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ፡፡
በብዙኃን መገናኛዎች ከሚቀርቡ ዝግጅቶች ውስጥ የትዕይንተ ወጎችን (Talk shows) ያህል የመወያያ፣ የመገናኛ፣ የመቀራረቢያ፣ የመደማመጫ፣ የመተዋወቂያ እንዲሁም አሳታፊ ዐቢይ መድረክ የለም፡፡ እነዚህ መድረኮች ጠቀሜታቸውና ሚናቸው ጎልቶ የመታየት ዕድል የሚያገኙት ግን ካለው ምቹ የአሥተዳደር ሥርዓት የተነሣ በምእራቡ ዓለም ሀገራት ነው፡፡ መቸም ከመወያየት የማይገኝ ጥቅም የማይፈታ ችግር የለምና እነዚህ ዝግጅቶች በእነዚህ ሀገራት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያበረከቱ የማይተካ ሚናቸውንም እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ከጠቀሜታቸው ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ለማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ ይጠቆምባቸዋል ይመነጭባቸዋል፣ ከፈጠራ ሥራ ከሞያ ወይም ከችሎታ ጋር በተያያዘ ዜጎች የመገናኛ ብዙኃን ዕድል የሚያገኙበትና ከሕዝብ ጋር የሚተዋወቁበት ይሆናል፣ እንደ ድልድይ ወይም መሰላል ሆነው ችግር ላይ የወደቁ ዜጎች ሊረዷቸው ከሚችሉ አካላት ጋር ተገናኝተውባቸው ለመረዳት ከመቻላቸው በተጨማሪ ያለባቸውን የተለያዩ ችግሮችን የሚያደምጣቸው ወገን አግኝተው ማውራት መቻላቸው መተንፈሳቸው ማጋራታቸው የሥነ-ልቡና ህክምና ወይም ፈውስ የሚያገኙበት መድረክ ሆነው ያገለግላሉ ወዘተ.
የምዕራቡ ዓለም ሀገራት እነኝህ መድረኮች ያላቸውን ሚና ጠንቅቆ በማወቅና በመጠቀም የሕዝባቸውን አጠቃላይ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ያጠናክራሉ፣ ፖለቲካቸውን (እመነተ-አሥተዳደራቸውን) ያረጋጋሉ፣ ተጠያቂነትንና መልካም አሥተዳደርን ያሰፍናሉ፣ ሥልጣኔያቸውን ያፋጥናሉ፣ ሰላማቸውን ያስተማምናሉ፣ ግንዛቤዎችን ያስጨብጣሉ፣ መንግሥትን ከሕዝብ ሕዝብን ከመንግሥት ያቀራርባሉ ወዘተ.
ወደ ሀገራችን ስንመለስ ካለብን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተነሣ ዝም ብሎ ተራ ወሬ አውርተው የሚያልፉ ውዱን የአየር ሰዓትና የትውልድ ወርቃማ ጊዜን በከንቱ የሚያቃጥሉ ሳይሆን ሐሳብ አፍላቂ፣ ሞጋች፣ ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫ መመልከት የሚችሉ በሳልና የጠነቀቁ የትዕይንተ ወግ ዝግጅት አዘጋጆችና ዝግጅቶች የመኖራቸው ነገር አስፈላጊና ለአጠቃላዩ ሀገራዊ ጉዳይ ቁልፍና አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ ካለው የመናገር ነጻነት ጠላት ከሆነ የአሥተዳደር ሥርዓት የተነሣ የትዕይንተ ወግ (Talk show) መድረኮችን በሚፈለገው ጥራትና ብዛት እንዲገኙ ዕድል በመስጠት በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ (እምነተ-አሥተዳደራዊ)፣ ግላዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ላሉብን ችግሮች ታድመን በመምከር መፍትሔ መፍጠር እንዳንችል ተደርገናል፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል ያሉን ትዕይንተ ወጎች ግላዊ ጉዳይ ላይና የመረዳጃ መድረኮች ብቻ ሊሆኑ የቻሉት፡፡
ጥቂት ቀደም ባሉት ዓመታት ግን ይሄንን መድረክ በተመለከተ አበረታችና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ሕዝብ እቤቱ ሆኖ ሊታደማቸው በጉጉት የሚጠባበቃቸው የትዕይንተ ወግ ዝግጅቶችን ለአጭር ጊዜም ቢሆን ለማየት ችለን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይቀርቡ የነበሩትን “ሻይ ቡና” እና “ሐምሳ ሎሚን” ማለቴ ነው፡፡ በእነዚህ ደረጃ የነበረ ሌላ የረሳሁት ካለ ይቅርታ፡፡ “ሻይ ቡና” በጋዜጠኛና ድምፃዊ ሰሎሞን ሹምዬ ተዘጋጅቶ ይቀርብ የነበረው ዝግጅት ሲሆን “ሐምሳ ሎሚ” ደግሞ የገዥው ፓርቲ (ቡድን) ልሳን ከሆነው ሬዲዮ ፋና አፈ ቀላጤነት ጥለው በመውጣት ትክክለኛ የጋዜጠኝነትን ሞያና ኃላፊነት ለመወጣት ይሞክሩ በነበሩት በማኅደርና ደግ አረገ ተዘጋጅቶ ይቀርብ የነበረ ትዕይንተ ወግ ነበር፡፡
እነዚህ የትዕይንተ ወግ መድረኮች ሥርዓቱ ከሚያደርሰው ጫና የተነሣ በነጻ መድረክነታቸው ላይ የየራሳቸው ችግር ቢኖርባቸውም በአንጻራዊ መልኩ ስናያቸው የተሻሉና ተስፋ የሚታይባቸው መድረኮች ነበሩ፡፡ አገዛዙ በእነዚህ ያውም በብሔራዊ ጣቢያ የሚተላለፉ ይዘጋጁ በነበሩት የመወያያ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚነሡ ጠንካራ ጠንካራ ሐሳቦችና መረጃዎች ጉዳይ ከባድ ሥጋት ላይ ስለጣለው የተፈራረሙበት የኮንትራት ጊዜ ሳይጠናቀቅ ሌላው ቀርቶ የያዙት የመወያያ ርእሰ ጉዳዮች እንኳን ሳይቋጩ እንዲቋረጡ አንባገነናዊ ውሳኔ በማስተላለፍ ታግደው ከአየር እንዲወርዱ ተደረጉ፡፡ ከዚያም በኋላ ተመሳሳይ የትዕይንተ ወግ መድረኮች በዚህ ብሔራዊ ጣቢያ የውኃ ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡
ከእነዚህ ሁለት የትዕይንተ ወጎች ጉዳይ ሳንወጣ አንዴ ምን እንደተደረገ ላጫውታቹህ፡፡ ነፍሱን ይማረውና ከያኔ ኢዮብ መኮንን የዘፈን አልበሙን እንደለቀቀ ከወደድኩለት ዜማዎቹ አንዱ “የወሬ ፈላስፋ” የተሰኘው ዘፈን ነበር፡፡ የዚህ ዘፈን ጸሐፊ የዘፈን አቀናባሪው ኤልያስ መልካ ከዓመታት በፊት በሸገር ነጋሪተወግ (ሬዲዮ) የጠዓም ልኬት የሚባል ዝግጅት እንግዳ ሆኖ ቀርቦ ዘፈኑን ስለ እነማን እንደጻፈው አዘጋጆቹ ጠይቀውት እስኪናገር ድረስ እኔ ዘፈኑ አድሬስ ያደረጋቸው (የተመለከታቸው) ወይም በዘፈኑ ላይ የተገለጹት ገጸ ባሕርያትና እርሰ ጉዳይ ሳስብ ተጣጥሞልኝ ያገኘሁትና ለእነሱ ነው እያልኩ ሳደምጠው የነበረው የዚህ የአገዛዝ ሥርዓት ፓርላማ (የተወካዮች ምክር ቤት) እና አቶ መለስ እንደሆኑ አስቤ በኪናዊ አገላለጽ በደንብ ከመገለጻቸው የተነሣ ለደራሲው ከፍ ያለ አድናቆት ለመስጠት ተገድጀ ነበር፡፡ የጠዓም ልኬት እንግዳ ሆኖ በቀረበበት ዝግጅት ላይ ሲናገር ግን ዘፈኑን የጻፈው “ሐምሳ ሎሚ” ለሚባለው በማኅደርና በደግአረገ ለሚዘጋጀው ቶክ ሾውን (ትዕይንተወግን) በተመለከተ ነው የደረስኩት ብሎ ሲገልጽ ግን በልቤ ከፋታ ቦታ ይዞ የነበረው ይህ አቀናባሪ ከነበረበት ከፍታ ቦታ ተምዘግዝጎ አልተከሰከሰብኝም መሰላቹህ? ለምን መሰላቹህ? ኤልያስ መልካ ከላይ በጥቂቱ የጠቃቀስኳቸውን የትዕይንተ ወግ ጥቅሞችን ጨርሶ አልተረዳም፡፡ ይህ ሰው ሐምሳ ሎሚ ትዕይንተ ወግ ያሉብንን ማኅበራዊ ግላዊና በስሱም ቢሆን በቻሉት መጠን ፖለቲካዊ ሌሎችም ችግሮች እያነሣ የሚያወያይ መድረክ እንደሆነ ያውቃል በስንኞቹም ላይ እንደገለጸው፡፡
አስተማርኩኝ ብሎ ህመሜን ቢነግረኝ፤
አላጨበጭብም መድኃኒት ካልሰጠን፤
ለፈለፈው እንጂ መች አጣሁት እኔ፤
አይራቀቅብኝ እድናለሁ ያኔ፡፡
በማለት ይሄንን ትዕይንተ ወግ በምን ያህል የወረደና አሳፋሪ ግንዛቤ እንደተረዳው ስንኝ ቋጥሮ ገለጸ፡፡ ልጁ መረዳት የተሳነው ነገር ምንድን ነው? ፈረንጆች እንደሚሉት “ችግርን ማወቅ ግማሽ መፍትሔ ነው” የሚለውን ቁምነገር፡፡ ለነገሩ ይህ የዜማ ግጥም ደራሲ አልተረዳውን እንጅ በእነዚያ ውይይቶች የሚነሡት ችግሮች ብቻ ሳይሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦችም የሚሰጡበት መድረኮች ነበሩ፡፡ ሌላው ያለተረዳው ነገር ደግሞ “የሐምሳ ሎሚ” ትዕይንተ ወግ አዘጋጆች ማኅደርና ደግ አረገ የዚያ ዝግጅት አዘጋጅ ጋዜጠኞች እንጅ እንደ ባለሥልጣን የመወሰን ሥልጣን የሌላቸው መሆናቸውን ሊያውቅላቸው አልቻለም፡፡ በጋዜጠኝነታቸው ግን የሚጠበቅባቸውን ጠቃሚ ሚና በመጫወታቸው መደገፍ ማበረታታት ሲገባው ፍጹም ቅንነት በጎደለው መልኩ በአሸማቃቂ ስንኞች ቅስማቸውን ለመስበር ጥረት አደረገ፡፡ እስኪ የዚህን ዘፈን ቀሪ ስንኞች ልጋብዛቹህ፡-
ይገርማል ይገርማል ተርቦ ልብስ ይደርባል፤
ይደንቃል ይደንቃል ተጠምቶ እሳት ይሞቃል፡፡
ተጠራርተው ከየቤቱ፤
ቃልን መርጠው መሻማቱ፤
ለመናገር መጎምጀቱ፤
ለኛስ ነው ወይ መድኃኒቱ፡፡
ሐምሳ ሎሚ ከብዶኝ ይሸከም ጉልበቴ፤
አታግዙኝ በቃ ጌጤ ነው ቅርጫቴ፤
ለምን አደንቃለሁ ጥሩ ቃል መራጩን፤
በምላሱ ስለት የምናብ ቆራቹን፡፡
አዝ.
ሁላችን ከሆንን የቋንቋ ፈላስፋ፤
በተግባር መስካሪ እማኝ እንዳይጠፋ፤
አንዱም ሳይጨበጥ ሳይዳሰስ እንኳን፤
ጀግና ልንባል ነው ቃላት ካሰካካን?
እያለ ነበር የጻፈባቸው፡፡ ከሱ ደግሞ ማን ገረመኝ የጠዓም ልኬትን ከሚያዘጋጁት አዘጋጆች አንዱ ማለትም የዘፈን ስንኞችን በተመለከተ ትንታኔ ይሰጥ የነበረው ስንኞቹ ለሐምሳ ሎሚዎች ነው የደረስኩት እያለው እያለ ቃላት እስኪያጥረው ድረስ አድናቆቱን መቸሩ ነበር፡፡ ብቻ ምን አለፋቹህ በእነዚህ ምክንያቶች ለደራሲው ሰጥቸው የነበረው ያልተገባ ግምት በድንገት እንደ ጉም በኖ እንደ ጢስ ተኖ ጠፋ፡፡ በዚህ ዓይነት ለስንቱ ልሰጠው የማይገባውን ክብርና አድናቆት ሰጥቸ ይሆን? ብየ እራሴን ጠየኩ “አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል” እንዲሉ ጭንቅላታቸው የሚታየው እንደዚህ ዓይነት አጋጣሚ ተገኝቶ አፋቸው ሲከፈት ነበር፡፡ ካልሆነ እንደምን ጭንቅላታቸውን ልናነብ፣ ሊሉ የፈለጉት ምን እንደሆነም እንዴት ልናውቅ እንችላለን?
በዚህ አጋጣሚ ዘፈንም ሆነ ሌላ ለሚጽፉ ደራስያን ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር ቢኖር እንዲያው ዝም ተብሎ ቃላትም ማሰካካት ስለተቻለ ብቻ ድርሰት አይጻፍም፡፡ ያ ልትጽፉት የፈለጋቹህት ነገር የሚያንጽ ነው ወይ? እንዳያስገምትም የሐሳቡ መሠረት አዎንታዊ ነው ወይስ አሉታዊ? ማኅበረሰባችን ከደረሰበት የአስተሳሰብ ብስለት ደረጃ አንዳች ነገር ለመጨመር የሚሞክር ነው ወይስ ጭራሹን የሚያደነቁር የሚያወርድ? ከሞራል (ከቅስም ወይም ግብረ-ገብ) ድንጋጌዎች አንጻር ሲለካስ ሚዛን የሚደፋ ነው ወይስ ቀሎ የሚገኝ? ሊያስተላልፈው የሚፈልገው መልእክትስ ከማንነት አንጻር ተቃርኖ ተጣርሶ አለው ወይስ የለውም? ተቀባይነት ያለውንና ማኅበረሰባችንን እንደማኅበረሰብ እንዲቀጥል እንዳይፈርስ አስሮ የያዘውን የተከበረና ሰብአዊ የሆነውን ባሕል ወግና ልማዳችንን የሚቃረን ነው ወይስ የሚጠብቅ? ኢግብረገባዊነትን ዋልጌነትን የሚሰብክ የሚያበረታታ ነው ወይስ የሚቋቋም የሚከላከል? የሚሉ መለኪያዎች እየታዩ ይጻፋል እንጂ በጫት ምርቃናና በስካር መንፈስ እየተጦዘ የሚቃዠው ሁሉ አይጻፍም፡፡ እባካቹህ ገጣሚያን ጻሐፊያን ደራስያን ነን የምትሉ ሁሉ የምትጽፉት ለሕዝብ ከሆነ በእነዚህ መለኪያወች ላይ ጥንቃቄ አድርጉ፡፡
እኔ አሁን እነዚህ እነዚህ ዘፈኖች እነዚህ እነዚህ ድርሰቶች እያልኩ ለመዘርዘር ጊዜና ቦታ አይበቃኝም እንጅ ከላይ በመጠኑ በጠቀስኳቸው መለኪያወች አንጻር ለመለካት ሊበቁ አይደለም ጭራሽ ሊታሰቡ የማይችሉ በርካታ ለሀገርም ለወገንም ለራስም ለማንም የማይጠቅሙ ብላሽ ነውረኛና ኢግብረገባዊ ሥራዎች ሞልተዋል፡፡ እናም ገጣምያን ጸሐፍት ደራስያን ሆይ እባካቹህ???
ችግሩ ከምን ይጀምራል የከያኔነትን ምንነት ጠንቅቆ ቃለማወቅ፡፡ ከያኔነት ማለት ዋልጌነት ማለት አይደለም፣ ከያኔነት ማለት ሰካራምነት ማለት አይደለም፣ ከያኔነት ማለት የጫትም በሉት የምን ሱሰኝነት ማለት አይደለም፡፡ ከያኔነት ከየትኛውም ሞያ ወይም ሥራ በላቀ መልኩ ከባድ ሀገራዊ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ለሌሎች ሞያዎች ወይም ሥራዎች ሁሉ ኃይልን፣ ጉልበትን፣ መነቃቃትን፣ አቅምን የሚሰጥ የሚሞላ የሚቀርጽ፤ ዜጎችን ዜግነት የሚጠይቀውን የዜግነት ግዴታና ኃላፊነት እንዲወጡ የማድረግን ዋነኛ ኃላፊነትና ግዴታ የተሸከመ ከባድ ሞያ ነው፡፡ ይሄንን ሳያውቁና ሳይጠነቅቁ የሚሠሩትን ስላጡ ብቻ ወደ ጥበብ መስክ እየዘለሉ እየገቡ መጠጊያ መሸሸጊያ ያደረጓት በርካታ ወገኖች በጥበብ ዘርፍ ተሰማርተው ጥበብን እንድትጎድፍ እንድትቆሽሽ ያደረጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ግዴታቸውንም ሳይረዱ የእሷ መልእክተኞች ነን የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡
አስቴር አወቀ “አርቲስቶች (ከያኔያን) ፖለቲካ ነገር ውስጥ መግባት አለባቸው ብየ አላምንም” ብላ ለከያኔነት ያላትን የተዛባ አቋም ካስታወቀች ወዲህ የጥበብን ምንነት ጨርሶ አለማወቋን ብቻ ሳይሆን የከያኔ ነፍስ እንደሌላት ተረድተናል፡፡ ነዋይ ደበበ “የሠራኋቸው ሕዝብ ቀስቃሽ የሀገር ዘፈኖች በተደጋጋሚ የተጋፈጥኩትን ሞት ለማምለጫ የተጠቀምኩባቸው ዘዴዎቸ ነበሩ እንጅ ያመንኩባቸው አልነበሩም” ብሎ እንጭጭና አደገኛ አስተሳሰቡን ከገለጠልን ወዲህ እጅግ እየገረመን ነዋይ ደበበ ጥበብን በጨረፍታም እንኳን እንደማያውቃትና የከያኔ ነፍስ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ አረጋግጧል፡፡ ለአብነት ያህል ሁለቱ አይበቁንም?
ጥበብ የሕዝብና የሀገር አገልጋይ ናት፡፡ ጥበብ የእውነት ዘብ ናት፡፡ ሕዝብን የሚጎዳባትን ሁሉ ትታገላለች ትቃወማለች ትፋለማለች፡፡ ከያኔያን ማለት የጥበብ ወታደሮች ናቸው ጥበብ የምታሠማራቸው ተፋላሚዎቹ ታጋዮች እነሱ ናቸው፡፡ ከያኔያን ሕዝብን የሚጎዳ የሚያጎሳቁል የሚያሰቃይን ማንኛውንም አካል ጥበብ ባስታጠቀቻቸው መሣሪያ ይፋለሙታል ይታገሉታል፡፡ ይሄንን ሳይረዱ ከያኔነት ማለት አስመስሎ አጭበርብሮ መብላት የመሰላቸውና እንዲህም የሚያደርጉ ከላይ የተቀስናቸውና ሌሎችም በርካታ ወገኖች አሉን፡፡
“ክደራና ክየና” በሚለው ግጥሜ ላይ እንደገለጽኩት ጥበብ ዓላማ አላት ጥበብ ግብ አላት፡፡ ያ ዓላማዋና ግቧ ገንቢ እንጅ አፍራሽ አይደለም፤ የሚያንጽ እንጅ የሚያማስን አይደለም፡፡ ጥበብ ቅድስት ናት ዝሙትና እርኩሰት አይሰበክባትም፡፡ ከያኔ እንደወታደር በሥነ-ሥርዓት የታነጸ (disciplined) እንደ ካህን ንጹህ ሆኖ ለጥበብ ካልታመነ ጥበብን ሊያገለግላት አይችልም፡፡ የዛር መንፈስ እንጅ የጥበብ መንፈስም አይዋሐደውም፡፡ የዛር መንፈስ የተዋሐደው ከያኔ ነኝ ባይ ሊጠበብና ከጥበብ ልብ ውስጥ ሊገባ ጨርሶ አይችልም፡፡ ያ የዛሩ መንፈስ ለራሱም ለሀገርም ለወገንም በማይጠቅመው ዋዛ ፈዛዛ ፍሬ ፈርስኪ ነገር ሲያስጓራው እንደኖረ ያልፋል፡፡ ረክሶ ያረክሳል እንጅ አይቀድስም አይቀደስምም፡፡ አጥፍቶ ይጠፋል እንጅ አይገነባም አያንጽምም፡፡ የሚከተሉትን ይዞ ገደል ይገባል እንጅ ወደ ተስፋ ምድር አያደርስም፡፡ እናም ማለት ካለብን በርካታ አጥፍቶ ጠፊዎች አሉን እንጅ በርካታ ከያኔያን የሉንም፡፡ ጥቂቶች አንዴ የሚቀደሱ አንዴ የሚረክሱ አሉን፡፡ በጣም ጥቂቶች ደግሞ ከያኔያን አሉን፡፡
ወደ ቀደመው ነገራችን ስንመለስ ይህ የአሥተዳደር ሥርዓት በያዘው አንባገነናዊ አቋም የተነሣ ትዕይንተ ወጎቻችን እንደምዕራቡ ዓለም ትዕይንተ ወጎች ያለ ገደብና ማነቆ ሁሉም ዓይነት ጉዳዮች የሚዳሰሱበትና የሚመከርባቸው፣ ልኂቃኑ በምላት በነጻነትና በንቃት የሚሳተፉበትና መፍትሔዎች የሚመነጩበት የበሰሉና የበቁ ትዕይንተ ወጎችን በመገናኛ ብዙኃኖቻችን ለማየት ሳንታደል ቀርተናል፡፡ እንዲያው ብቻ ግን “ትዕያንተ ወግ” (ቶክ ሾው) የሚለውን ስም ይዘው በጠበበና ግላዊ በሆነ ጉዳይ ተወስነው የሚዘጋጁ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 2ኛውና 3ኛው ቻናል (ክፍል) እንዲሁም ኢ.ቢ.ኤስ በተሰኘው የኬብል ቴሌቪዥን የሚተላለፉ ትዕይንተ ወጎችን ማንሣት ይቻላል፡፡ የኬብል ቴሌቪዥንን ካነሣን በነጻነት በምዕራቡ ዓለም ደረጃ (standard) ትዕይንተ ወግ የሚዘጋጅበት ጣቢያ ኢ.ሳ.ት. ይነሣል፡፡
ነገር ለማሳጠር ያህል ይሄንን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት ስለሆነኝ ኢ.ቢ.ኤስ. በተባለው የኬብል ቴሌቪዥን (የመስመር ምርዓየ-ኩነት) ስለሚተላለፈው “ጆሲ ኢን ዘሀውስ” ስለ ተባለው በድምፃዊ (Artist) ዮሴፍ ገብሬ እየተዘጋጀ ስለሚቀርበው ትዕይንተ ወግ ጥቂት ልበልና ልቋጭ፡፡ እውነት ለመናገር ድምፃዊ ዮሴፍ እውቀቱና አቅሙ በፈቀደለት መጠን እጅግ የሚያስመሰግንና አርዓያነት ያለው ዝግጅቶችን እያቀረበ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም የከያኔ ማንአልሞሽ ዲቦን ልጆች ካለባቸው ችግር ሊረዱ የሚችሉበትን መንገድ በመፍጠር ከችግራቸው እንዲወጡ ማድረግ ችሏል፡፡
አሁን ደግሞ በ1-1-2007ዓ.ም. አቅርቦት በነበረው ዝግጅቱ አሁን እራሱ ከያኔ ዮሴፍ እያደረገው እንዳለው ሁሉ ያለመታከት ለብዙዎች ችግር መፍትሔ እንዲያገኙ ያደርግ የነበረውን የአለባቸው ተካን ቤተሰቦችና በተለይም ድምፃዊ ዮሴፍ ያለማወቅ በቴሌቪዥን በግልጽ እንዲታዩ በማድረጉ ለሌላ ተጨማሪ ችግር ሊዳረጉ መሆኑ ቢከፋም እነዚያን ሁለት ከኤች.አይ.ቪ. ተሕዋስ ጋር የሚኖሩትን የተቸገሩ ሕፃናት እንዲረዱ በማድረጉ እጅግ አስመስጋኝና የተቀደሰ ምግባር ሠርቷል፡፡ ከእነዚህ ወገኖቻችን የከፋ ጎዳና ላይ ሁሉ የተበተኑ እጅግ ከባባድ ችግሮች የደረሰባቸው አንጀት የሚበሉ ቤተሰቦች እንዳሉ ብናውቅም የእነኝህ ወገኖች በተለይም የሕፃናቱ ታሪክም አስቀድሞም የማናልሞሽ ልጆች ታሪክ አንጀታችንን ስለበላው በተደጋጋሚ ለማንባት ተገደን ነበር፡፡ ድምፃዊ ዮሴፍ በዚህ የተቀደሰ ሥራው ከቀጠለ ከእግዚአብሔር ዘንድ የብፅእናን ክብር ያገኛል ብየ አምናለሁ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተለይም በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ (Social Media) ስለ ድምፃዊ ዮሴፍ ማንነት የተለጠፉና የታተሙ አንዳንድ ነገሮችን ስናይ ጥርጣሬ ላይ የሚጥሉ ነገሮች አሏቸው፡፡ እነኝህ ነገሮች ተጨባጭነት የሌላቸው ተራ ወሬዎች ሆነው እንዲቀሩ ምኞቴ ጽኑ ነው፡፡ ሐሜቱ እውነትነት ቢኖረውና ድምፃዊ ዮሴፍ እንደ ብዙዎቹ ሁሉ አማራጭ አጥቶ ልቡ ሳይፈቅድ ሠርቶ ለማደር ሲል ተገዶ የወያኔ አባል ወይም ደጋፊ እንዲሆን ተደርጎ ቢሆንም እንዲህ በመሆኑ ሰብእናው ቢረክስም ወያኔ መጠቀሚያው እንዳያደርገው እስከተጠነቀቀ ጊዜ ድረስ “ዘርህ ይፍለስ ጨርሶ አንይህ” ለማለት የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡ እኔን ያሳሰበኝ “ድምፃዊ ዮሴፍ ይሄንን የሚያደርገው ከሰብእናው ወይም ካለው ተፈጥሯዊ ደግነት የተነሣ ሳይሆን ወያኔ ለራሱ የሕዝብ ግንኙነት ፍጆታ ሲል ከወያኔ በተሰጠው ስውር ተልእኮ (mission) ነው” መባሉ ነው፡፡
ይሄንን የሚሉ ሰዎች ባለፈው ጊዜ ለማናልሞሽ ዲቦ ልጆች የቀበሌ ቤት እንዲያገኙ የተደረገውና ይሄም በሚገባ ተዘግቦ እንዲታይ የተደረገው በመልካም አሥተዳደር ችግር የተተበተበውን በቢሮክራሲ፣ በኢፍትሐዊነት፣ በዘር መነጽር የታወረውንና በዜጎች ላይ በደል እንግልት የሚያደርሱትን የክፍል ከተማ የወረዳና የቀበሌ አሥተዳደር መሥሪያ ቤቶች ፍጹም ቀናና ፍትሐዊ ያ ሁሉ ጣጣና ችግር የሌለባቸው መልካም አሥተዳደር የሰፈነባቸው መስለው እንዲታዩ የተሠራ አስመሳይ ማስታዎቂያ ነው፡፡ በሂደቱ ባጋጣሚ የድምፃዊዋ ልጆች ተጠቃሚ መሆናቸው መልካም ቢሆንም ለሸፍጠኛው ማስታወቂያ ግን መጠቀሚያ ተደርገዋል” ይላሉ፡፡
አሁንም ደግሞ በዚህኛው ዙር እንዲረዱ የተደረጉት ወገኖች በሂደቱ ተጠቃሚ መሆናቸው ቢጠቅማቸውም “ዝግጅቱ የተቀመረው ግን እንደ ዳሸን ቢራ ላሉ የወያኔ የንግድ ድርጅቶችና ለሌሎች ለተጠቀሱ አንዳንድ አባሪ ድርጅቶች ማስታዎቂያና ለሕዝብ ግንኙነት ትርፍ ሲባል መጠቀሚያ ለማድረግ ነው” ይላሉ፡፡ የዚህ ማረጋገጫው ሌሎች ወገኖችም ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ሥራ ለተቸገሩ ወገኖች ለመሥራት በየክፍለ ከተማው በየወረዳው በየቀበሌው ሲዋትቱ ትብብሩ ቀርቶ ምላሽ እንኳን የሚሰጣቸው አጥተው ፊት ተነስተው አሥተዳደራዊ አገልግሎት መነፈጋቸው ነው ይላሉ፡፡
ስለ ኢ.ቢ.ኤስ ሲናገሩም “ራሱ ኢ.ቢ.ኤስ. የተባለው የኬብል ቴሌቪዥንም ለጭንብል ያህል ለአንዳንድ አካላትና ግለሰቦች የአየር ሰዓት በመፍቀድ ማንነቱን ለመሸፈን ጥረት ቢያደርግም በአንድም በሌላም መንገድ የሥርዓቱና የግለሰቦቹ ኢኮኖሚያዊና (ጥሪታዊና) ፖለቲካዊ (እምነተ-አስተዳደራዊ) ጥቅም አስከባሪ ነው ከጀርባውም ያሉት እነሱ ናቸው፡፡ የጣቢያው ዝግጅቶች አወቃቀርና ይዘትም በሀገሪቱ በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ከሚደርሱ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ባጠቃላይ ይሄንን ሥርዓት ከሚያሳሙ ከሚያሳብቁ ጉዳዮች ሁሉ የራቁ እንዲሆኑ የተደረገውም ሆን ተብሎ ነው፡፡ የጣቢያው ዓላማም ልክ እንደሞላላቸው ሀገራት ሁሉ መዝናኛ ላይ ብቻ በማተኮር የሕዝብን ዐይን በመያዝ እነዚያ የሥርዓቱን አሳሳቢና ከባባድ ችግሮች ሁሉ በሕዝቡ እንዳይታዩ እንዳይተኮርባቸው ማድረግና የሌለ የአገዛዙን ባለሥልጣናት ሀብት እድገትና ብልጽግና የሀገር እያስመሰሉ ማቅረብ ነው፡፡ ይሄንን ሸረኛ ጥረቱንም በግጽ መመልከት ይቻላል” ይላሉ፡፡
ለማንኛውም እንግዲህ ድምፃዊ ዮሴፍ የሚታማው እውነት ከሆነ ረጅም ጊዜ ሳይወስድ በዚሁ በያዝነው ዓመት ልናረጋግጥ እንደምንችል ይሰማኛል፡፡ ያኔ ሐሜቱ እውነት መሆኑን የሚጠቁም የሚገልጥ አንዳች ነገር ያገኘን ጊዜ ድምፃዊ ዮሴፍ ከወያኔ የተሰጠውን ተልእኮ ሰውሮ ይዞ ቆዳውን ሞኝ አስመስሎ እያስለቀሰንና እያለቀሰ በብቃት በተወጣው ትወናው አጃጅሎን ሳናውቀው የወያኔ ሰለባ አድርጎ ሊሸጠን ስለሞከረበት ታላቅ ድፍረቱና ንቀቱ ይቅርታውን መልሶ ላያገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ የሚተፋው ይሆናል፡፡ ሆነም አልሆነ ለልጁ ላሳስበው ላስጠነቅቀው የምሻው ቁም ነገር ቢኖር ከሕዝብ ዐይን ተሠውሮ የሚቀር ምንም ነገር የለምና ሆነህም ከሆነ በጊዜ ተመለስ፡፡ እራስህንም ከአውሬዎች መጠቀሚያነት አውጣ፡፡
ከሕዝብ ጋር ያልቆመ መውደቁ አይቀርም አወዳደቁም የከፋ ነውና ወንድሜ ዮሴፍ ይቅርብህ ለምኑ ብለህ ነው? እስከማውቀው ድረስ ለዚህ ዓይነት ርኩሰት እንድትዳረግ የሚያስገድድህ ሁኔታ የለም የምትበላው አላጣህም ኑሮህ ከእጅ ወደአፍ አይደለም፡፡ በልቶ የማደርና ያለማደር ችግር ተጋርጦብህ ጥያቄው የህልውና ጉዳይ የሆነብህ ሰው አይደለህም፡፡ ይሄ ሁሉ በሆነበት ሁኔታ ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው እንደሆኑት ሁሉ ወያኔ ሆነህ ከሆነ ስሕተትህን እጅግ የከበደ ያደርገዋል፡፡ አንተንም አርቀህና ጠልቀህ ማሰብ የማትችል ብስለት አልባ እንጭጭ አድርጎ ያስቆጥርሀል፡፡
ምክንያቱም የምትደክምላቸው ከወያኔ በተሰጠህ ስውር ተልዕኮ ካልሆነ እነዚህ አንተ ልትረዳቸው የምትደክምላቸው ወገኖችና ሌሎችም የከያኔያን (የአርቲስቶች) ቤተሰቦች ለዚያ ዓይነት ችግር የተዳረጉት ወያኔ በፈጠረው ሸር መሆኑ በግልጽ የሚታይ የሚታወቅ ነገር ሆኖ እያለ ይሄንን በግልጽ በጉልህ የሚታይን ነገር ማየት መገንዘብ ማስተዋል ተስኖህ ይሄንን ግፈኛና ሸረኛ ሥርዓት ለማገልገል በመግባትህ ነው፡፡ ይህ መንግሥት ነኝ የሚለው የወንበዴዎች ቡድን ግዴታውን አውቆ ልክ ደርግ ለቅጅ መብቶች ያደርገው የነበረውን ጠንካራ ጥበቃ ያህል የጥበብ ሥራዎችን የቅጅ መብቶች (ኮፒ ራይት) አክብሮ የሚያስከብር ቢሆን ኖሮ የሥነ-ኪኑ ቤተሰብ ከራሱም አልፎ ለሌላ በተረፈ ነበርና፡፡ ነገር ግን እንደሚታወቀው ይህ ሥርዓት ከአንድ መንግሥት ነኝ ከሚል አካል አይደለም ከተደራጀ የወንበዴ ቡድን እንኳን በማይጠበቅ ሸፍጥ አጠቃላይ የኪነት ሥራዎችንና ሠራተኞቿን (ከያኔያንን) እያዳከመ እንደሚገኝ ለማንም ግልጽ ነው፡፡
ይህ ሥርዓት የቅጅ መብትን አክብሮና አስከብሮ ጥበብ በሐገራችን እንድትነቃቃ እንድታድግ የማያደርግበት ምክንያት ሥነ-ኪን (ጥበብ) ለሕዝብ ካላት ጥብቅና የተነሣ ሕዝብን የምታነቃና ብሶትም መተንፈሻ ከመሆኗ አንፃር የሥጋት ምንጭ አድርጎ ስለሚያያት እንድትደክም እንድትከስም እንድትጠፋ በሚያደርገው ሸረኛ ሸፍጡ እነሆ እያየነው እንዳለነው ሁሉ ሥነ-ኪን በሀገራችን ተዳክማ ከሞት አፋፍ ላይ እንድትደርስ አብቅቷታል፡፡ በዚህም ምክንያት በዘርፉ የተሰማሩ ከያኔያንና ቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር በመዳረግ በየመድረኩ ለልመና ለመዋጮ ተዳርገዋል ጨርሶ ሠርቶ ለመብላት አልተቻለም፡፡
የዚህ ሸፍጥ ዋነኛ መገለጫው አገዛዙ ለማስመሰል አንድ ሁለቴ ከወሰዳቸው የዘመቻ እርምጃዎች ውጪ ሕግ በሰጣቸው መብትና ጥበቃ የከያኔያኑን የቅጅ መብቶች ለበጠበቅና ለማስጠበቅ ፈቃደኝነቱና ቁርጠኝነቱ አለመኖሩ ነው፡፡ ከያኔያኑ ማኅበር አቋቁመው በከፍተኛ ንቃት ይከታተሉት የነበረውን በሕግ የተያዘ ጉዳይ ማለትም ሕገ ወጥ ቅጅዎችን በከፍተኛ ብዛት ሲያባዙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ወንጀለኞችን ፍርድ ቤት ተብየው የሥርዓቱ ሸንጎ የከያኔያኑን የፍትሕ ጥማትና ጥያቄ ከመ ጤፍ ባለመቁጠር በአስደናቂ ድፍረት ሀፍረት ያጣ ውሳኔ ወንጀለኞችን በነፃ አሰናብቶ በዘርፉ የተሰማሩትን ባለ ድርሻ አካላት በሙሉ ጨርሶ ባልተጠበቀ መልኩ አስደንግጦ በማሳፈር በዚህች ሀገር ለዜጎች መብት የቆመ መንግሥት የሚባል አካል አለመኖሩን ማርዳቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታና የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ዐይን ያወጣ ኢፍትሐዊ ውሳኔም ይሄንን ሕገ ወጥ ሥራ የሚሠሩትን ወንጀለኞች እጅግ አበረታቷል፡፡ ያለ አንዳች ሥጋት ይሄንን ሕገ ወጥ ሥራ እንዲሠሩ አስችሏል፡፡ እናም የከያኔያኑና ቤተሰቦቻቸው ችግር በማናልሞሽ ዲቦና በአለባቸው ተካ ቤተሰቦች ብቻ የሚቆም አይደለም ገና ገና ተበራክቶ ይቀጥላል፡፡
ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬም ሆነ የሞያ አጋሮቹ ይሄንን ያጡታል ብየ አልገምትም፡፡ እነሱ እራሳቸው በዘርፉ እንደመገኘታቸው ያለውን ሸፍጥና ውስብስብ ችግር ከማንም በላይ ያውቁታል ብየ እገምታለሁ፡፡ ይሄንን እያወቁ ጥበብንና የገዛ እራሳቸውን ለመጉዳት ይሄንን ሸፍጠኛ ነውረኛና ወንበዴ ሥርዓት ለማገልገል ለሱ ተሰማርተው ከተገኙ እኔ ጤነኞች ናቸው ብየ ለመቀበል እጅግ እቸገራለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Engida says
Yegid ante yemat’smamabet hasab s’letsafe lemin lijun endzih t’kesaleh? Wanawu bians yegitmun tinkare bitay minalebet. Mejemeraim lemachberber wededkut alk enji liju Oromona bezia lay Protestant slehone work bianetflh endematwedewu yetaweke newu. You know the reason(s)!
Engida says
1 yeresahunt neger, zim bleh bezih kilil bemayashag’r kuanka at’zeb’z’b. Dehin ymikelewun’na gilts yehonewun Englizegnawn t’teh wede ge’ez atgba. Kechalk endyawum beEnglizegna lemetsaf mokr.